Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የቤተሰባቸውን እንክብካቤ ላጡ ሕፃናትና ወጣቶች ባቋቋማቸው ማዕከላት የቤተሰብ ተኮር ክብካቤ፣ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶችን  ይሰጣል። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ ቤተሰቦችና ማኅበረሰቦች የተጋረጡባቸውን ችግሮች አሸንፈው የተሻለ ሕይወት መገንባት እንዲችሉ እየሠራ የሚገኘው የኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት (ኢዮቤልዩ) ማክበር ጀምሯል፡፡ የተመሠረተበትን 50ኛ ዓመት  አስመልክቶ የድርጀቱ ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለጋዜጠኞች ገለጻ አድርገዋል፡፡ ምሕረት ሞገስ እንደሚከተለው አጠናቅራዋለች፡፡

ጥያቄ፡-  ኤስኦኤስ ሕፃናት መንደሮች እንዴት ተቋቋመ?

አቶ ሳህለማርያም፡- ኤስኦኤስ ሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት በተለያዩ ክልሎች ውስጥ ሕፃናት ላይ ትኩረት ያደረጉ መርሐ ግብሮችን ዘርግቶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በርካታ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ ቤተሰቦችንና ማኅበረሰብን ከተለያዩ ችግሮች ታድጓል፡፡ ከነበሩባቸው አሰቃቂና አስቸጋሪ የሕይወት ገጠመኞች አውጥቶ ስኬታማ ወደሆኑ የሕይወት መስመሮች ማሻገር ችሏል፡፡ ድርጅቱ የዓለም አቀፉ የኤስኦኤስ ሕፃናት መንደሮች አባል ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ድርጅት የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1949 በኦስትሪያ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማግሥት ነው፡፡ በወቅቱ በተለያየ ምክንያት የተጎዱ ሕፃናትንና ወጣቶችን ሰብስቦ ልጆቹ ያጡትን ቤተሰብ፣ ማኅበረሰብ የመገንባት ሥራን ዓላማ አድርጎ የተነሳ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ 75ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ 50ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘው ድርጅት፣ አሁን ላይ 137 አገሮች ውስጥ ይሠራል፡፡

ጥያቄ፡- በዋናነት ትኩረቱ ምን ላይ ነው?

አቶ ሳህለማርያም፡- የቤተሰቦቻቸውን ጥበቃና እንክብካቤ ያጡና ለተመሳሳይ ችግር የተጋለጡ ሕፃናት ላይ መሥራት ዋና ትኩረቱ ነው፡፡ ተጋላጭነት ያላቸውን ወጣቶችና ሕፃናት ስናስብ፣ ያለቤተሰብ ማሰብ ከባድ ነው፡፡ ስለሆነም በሕፃናትና በቤተሰብ ልማት ላይ ይሠራል፡፡ ቤተሰብ የማኅበረሰብ አካል ስለሆነ ጠንካራ ቤተሰብ በመፍጠር ረገድ ማኅበረሰብ ጠንካራ አስተዋጽኦ ስላለው ለማኅበረሰብ ልማትም ትኩረት እንሰጣለን፡፡ ሁሉም ልጆች በቤተሰብ ታቅፈው በፍቅር፣ በሰላምና በሙሉ ዋስትና ሲያድጉ ማየትም ራዕያችን ነው፡፡ ሁሉም ልጆች ዕድገታቸውን በሚደግፍ፣ ፍቅርንና ሰላምን በሚለግስ ስብዕናቸውን፣ ልዩነታቸውንና ማንነታቸውን በሚያከብር ቤተሰብ ውስጥ እንዲታቀፉ እናደርጋለን፡፡ በቤተሰብ ታቅፈው ሲያድጉ የነገ ዕድላቸውን እንዲያስተካክሉ የሚያስችላቸውን ድጋፍ እንዲያገኙ እናደርጋለን፡፡ ማኅበረሰብ ልማት ላይ መሳተፍና የልጆች መብቶች እንዲከበሩም እንሠራለን፡፡

ጥያቄ፡- በኢትዮጵያ በምን ያህል ክልሎች ትሠራላችሁ?

አቶ ሳህለማርያም፡- ድርጅቱ በ1966 ዓ.ም. ተከስቶ የነበረውን ድርቅ ተከትሎ የመንግሥትን ጥሪ ተከትሎ ነው ወደ ኢትዮጵያ የገባው፡፡ ደርቁ በርካታ ሕፃናት፣ ወጣቶችንና ማኅበረሰቡን በእጅጉ ጎድቶ ስለነበር፣ ድርቅ አደጋ በተከሰተበት በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ሥራውን የጀመረው ድርጅቱ፣ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ለመስጠት ቢገባም፣ ይህንን ካጠናቀቀ በኋላ ቤተሰቦቻቸውን ላጡ መሥራት አስፈላጊ ስለነበር የመጀመርያው የኤስኦኤስ የሕፃናት መንደር በመቀሌ ከተማ ተደራጅቷል፡፡ በርካታ ሕፃናትና ወጣቶች በፕሮግራሙ እንዲታገዙ ተደርጓል፡፡ በጊዜ ሒደት ችግሮችንና አደጋዎችን እየተከተልን በአሁኑ ሰዓት በዘጠኝ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ ፕሮግራሞችን እየተገበርን እንገኛለን፡፡

ጥያቄ፡- ከሕፃናት መንደርነት በተጨማሪ ምን ፕሮግራሞች አሏችሁ?

አቶ ሳህለማርያም፡- ከሕፃናት መንደር በተጨማሪ ሌሎች አዳዲስ ፕሮግራሞችን እየጨመርንና እያደግን መጥተናል፡፡ ብዙ ጊዜ የምንታወቀው በሕፃናት መንደር ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ሥራችን ያለው ማኅብረሰብ ውስጥ ነው፡፡ ከፍተኛ ሀብት የሚፈስበት ሥራችን ማኅበረሰብ ውስጥ ነው፡፡ በአንድ የአስችኳይ ጊዜ ምላሽ ፕሮግራም የጀመረው ድርጅታችን፣ በአሁኑ ጊዜ 41 ፕሮጀክቶችን እየተገበረ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሰባቱ ብቻ ናቸው የሕፃናት መንደሮች፡፡ 34ቱ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚሠሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ ከፕሮጀክቱ አንዱ ቤተሰብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ነው፡፡ ለተለያዩ ችግሮች ተጋላጭነት ያላቸውን ቤተሰቦች ከመንግሥትና ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለይተን፣ በፕሮግራሞቻችን ታቅፈው የሚጠናከሩባቸውን ሥራዎች እንሠራለን፡፡ ተጠናክረው ለልጆቻቸው ሁለንተናዊ ዕድገት የሚያስፈልገውን ድጋፍ የሚያደርጉበት አቅም ላይ እናደርሳቸዋለን፡፡ ቤተሰብ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት እንዳይፈርስና ልጆቻቸው ወደ ውጭ እንዳይወጡ የምናደርግበት ሥራ ነው፡፡ የማኅበረሰብ ልማት ሥራም ጎን ለጎን የምንሠራው ሌላው ፕሮግራማችን ነው፡፡ በምንገባባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ አገር በቀል፣ ማኅብረሰብ በቀል ከሆኑ ድርጅቶች ጋር በጋራ እንሠራለን፡፡ ከዕድር፣ ከወጣት ማኅበራት፣ ከሴቶች ማኅበራትና ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር እንሠራለን፡፡ የእነሱን አቅም እንገነባለን፡፡ ከገነባን በኋላ ለተቸገሩ ልጆች፣ ቤተሰቦች የመድረስ ሥራን እንዲከውኑ እናደርጋለን፡፡ ልጆችን ወደ ቤተሰብ የመቀላቀል ሥራም እንሠራለን፡፡ ከጎዳናና አማራጭ እንክብካቤና ጥበቃ ከሚሰጡ ድርጅቶች ልጆችን ወስደን እንንከባከባለን፡፡ ይህንን የምናደርገው ልጆች ትክክለኛው፣ ሊያድጉበት የሚገባው ቤተሰብ ውስጥ ነው ብለን ስለምናምን ነው፡፡

ጥያቄ፡- በወጣቶች ላይ ምን ትሠራላችሁ?

አቶ ሳህለማርያም፡- የወጣቶች ልማት ሥራ አንዱ ፕሮግራማችን ነው፡፡ የሥራ ፈጠራ ሥራ እንሠራለን፡፡ ወጣት ማጎልበት ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞችን አሉን፡፡ ይህ ለወጣቶች ራሳቸውን የሚችሉበትን ዕድል የምንፈጥርበት ነው፡፡ የተለያዩ ትምህርቶችንና ሥልጠናዎችን ይወስዳሉ፡፡ የራሳቸውን ሥራ የሚጀምሩበት ፈጠራ ውስጥ የሚገቡ ከሆነ ተያያዥ ሥልጠናና የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙባቸው አግባብ ይፈጠራል፡፡ የንግድ ትስስር ሥራ እንሠራለን፡፡ በዚህ አግባብ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲችሉ እናደርጋለን፡፡

ጥያቄ፡- የአደጋ ጊዜ ፕሮግራማችሁ ምን ይመስላል?

አቶ ሳህለማርያም፡- በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች በተለያዩ ምክንያቶች ማኅበረሰብ ለችግሮች ሲጋለጥ እንረዳለን፡፡ ጦርነት፣ ድርቅ፣ ጎርፍና በተለያዩ ምክንያቶች ለተለያዩ ችግሮች የሚጋለጡ ቤተቦች አስቸኳይ ዕርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ከመንግሥትና ከሌሎች አጋር ድርጀቶች ጋር በመሆንና በመተባበር የአጭርና የመካከለኛ ጊዜ የድጋፍ መስጫ ፕሮግራሞችን እንተገብራለን፡፡   

ጥያቄ፡- በትምሕርት ዙሪያ ያላችሁን ተሳትፎ ቢያብራሩልን ?

አቶ ሳህለማርያም፡- በትምህርት ሥራዎች ሰፊ ተሳትፎ አለን፡፡ በትምህርት ተቋማታችን ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆነው፣ ከመንግሥት ትምህርት ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች እንተገብራለን፡፡ የትምህርት ቤት አቅም ግንባታ፣ ትምህርት ቤቶችን መገንባት፣ የመምህራንንና የትምህርት አስተዳደር አካላትን አቅም እንገነባለን፡፡ የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን እንሰጣለን፡፡ ከትምህርት ገበታ ውጭ የሆኑ ልጆችና ወጣቶች እንዲመለሱ የማድረግ ሥራዎች እንሠራለን፡፡ በጤና በኩል በጤና ተቋማት ከምንሠራው ባለፈ የጤና ፕሮግራሞችን ቀርፀን እንተገብራለን፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች የአካል ጉዳት የገጠማቸውን የሚያሳትፉ ፕሮግራሞችን እንተገብራለን፡፡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት የሚያገኙበትና በልማት የሚሳተፉበትን የምናጠናክርበት ፕሮጀክቶች አሉን፡፡ በእነኚህና በሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶቻችን አማካይነት በርካታ ወጣቶችን፣ ልጆችንና ቤተሰቦችን መድረስ ችለናል፡፡ ዘንድሮ ብቻ 700 ሺሕ የሚጠጉ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ቤተሰቦችን እያገዝን እንገኛለን፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት 8.1 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጆች፣ ወጣቶችና ቤተሰቦች የፕሮግራም ተጠቃሚ ማድረግ ችለናል፡፡

ጥያቄ፡- በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ለተጎዱት ምን ዓይነት ምላሽ መስጫ ፕሮጀክቶችን ተግብራችኋል?

አቶ ሳህለማርያም፡- የገንዘብ አቅርቦቱና ተደራሽነቱ በፈቀደልን መሠረት ለመሥራት ሞክረናል፡፡ ከሠራናቸው የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጫ ፕሮግራሞች አንዱ ሰሜን ሸዋ ላይ የሠራነው ነው፡፡ ሰሜን ወሎ፣ መቀሌና ሳምሪ ላይ ሠርተናል፡፡ እየተተገበሩ ያሉ ፕሮጀክቶችም አሉ፡፡ ሰሜን ወሎ ላይ የተሠራው ሰፊ ሥራ በብዙ አቅጣጫ ለችግር ተጋላጭ ለሆኑ ቤተሰቦችና ማኅበረሰብ ምላሽ የሰጠንበት፣ የዕለት ተዕለት ድጋፍ ያደረግንበት፣ መልሶ የማቋቋም ሥራ የሠራንበት ነው፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ ከአሥር ሚሊዮን በላይ ዩሮ ኢንቨስት አድርገናል፡፡ በተጨማሪም በምሥራቅ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በኦሮሚያ የአደጋ ጊዜ ምላሽ መስጫ ፕሮጀክቶችን እየተገበርን እንገኛለን፡፡ በአሁኑ ሰዓት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቀውስ ያለ መሆኑ እኛም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ አውሮፓና አሜሪካ አካባቢ ያለውን ሀብት የሚቀራመት ብዙ ችግር አለ፡፡ ዩክሬን ላይ ያለው ችግር ከፍተኛ ገንዘብ እየወሰደ ነው፡፡ ጋዛ አካባቢና አፍሪካ በየቦታው ያሉ ችግሮች ብዙ ገንዘብ ስለሚፈልጉ ያለውን ሀብት ይቀራመቱታል፡፡ ስለዚህ ወደ አገራችን የሚመጣው ሀብት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው፡፡ ሆኖም አቅማችን በፈቀደ የረጂዎችን ልብ ሊገዙ የሚችሉ ፕሮፖዛልና ኮንሰፕት ኖት እያዘጋጀን ለአጋሮች እየላክን ነው፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ ይመጣል ብለንም ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ጥያቄ፡- ወደፊት ምን ለመሥራት አቅዳችኋል?

አቶ ሳህለማርያም፡- እ.ኤ.አ. ከ2023 እስከ 2027 ድረስ የሚዘልቅ የድርጊት መርሐ ግብር ቀርፀን ወደ ሥራ ገብተናል፡፡ በቀጣይ ሦስት ዓመታት ያሉንን የማስተባበሪያ ጣቢያዎች ከሰባት ወደ 11 የማሳደግ ዕቅድ አለን፡፡ በዚህ መሠረት አራት የክልል ከተሞች ውስጥ ተጨማሪ የማስተባበሪያ ጣቢያዎችን እንገነባለን ብለን አቅደናል፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ አክሱም ከተማ አንድ፣ በአማራ ክልል ከባህር ዳር በተጨማሪ ደሴ ውስጥ አንድ የማስተባበሪያ ጣቢያ እንገነባለን፡፡ አፋር ሰመራ ተጨማሪ የማስተባበሪያ ጣቢያ ይኖረናል፡፡ አርባ ምንጭ ውስጥ ሁለት ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ሲሆን፣ የማስተባበሪያ ጣቢያ ግንባታም ተጀምሯል፡፡ እስከ 2027 ባለው ያሉንን ተደራሾች ቁጥር ከ700 ሺሕ ወደ 4.5 ሚሊዮን ለማሳደግ ዕቅድ አለን፡፡ ይህንን ለማድረግ 210 ሚሊዮን ዶላር ያስፈልገናል፡፡ ይህ ማለት አሁን ያለንን ዓመታዊ ገቢ በ30 በመቶ ማሳደግ ይጠበቅብናል፡፡ ዓመታዊ ገቢያችንን በ30 በመቶ ለማሳደግ የተጠናከረ ሥራ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ለዚህም ከውጭ ዕርዳታ ለማግኘት ከምንሠራው በተጨማሪ አገር ውስጥ ሥራዎች እየሠራን ገቢ የምናገኝባቸውን አመቻችተናል፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ የአገር ውስጥ ስፖንሰርሺፕ ነው፡፡ ብዙዎቹ ልጆቻችን የሚታገዙት በውጭ ዜጎች ነው፡፡ ዘር ቀለም ሳይሉ ምንም የማያውቋቸውን የውጪዎቹ ከረዱ፣ እኛ ይህ ያቅተናል ብለን አናምንም፡፡ በራሳችን ሀብት ለችግር ተጋላጭ የሆኑ ሕፃናትን ማገዝ እንችላለን ብለን ስለምናምን የስፖንሰርሺፕ ፕሮግራም ዘርግተናል፡፡ ለአንድ ልጅ ስፖንሰርሺፕ የሚያስፈልገውን በወር 500 ብር ነው፡፡ በርካታ ይህንን ማድረግ የሚፈልጉ ኢትዮጵያውያንም አሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የድርጅታችንን ዓላማ ለመደገፍ በንግድ ሚኒስቴር የተመዘገበ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት የሚያደርግ ተቋም አቋቁመናል፡፡ በስድስት ክልሎች ውስጥ የትምህርት ተቋማት አሉን፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ የትምህርት ተቋም ይኖረናል፡፡ ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች እየሰጠን በሚገኘው ትርፍ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ያሉ ቤተሰቦችና ልጆችን እንደግፋለን፡፡ የፈርኒቸር ምርት ሥራ ውስጥ ለመግባትም ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ የወተት ሀብት ልማት ውስጥ ለመግባት ጥናት እያስጠናን ነው፡፡

ጥያቄ፡- ፕሮግራሞቻችሁን ስትተገብሩ የተባበሯችሁ አካላት ማን ናቸው?

አቶ ሳህለማርያም፡- ከተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ ሠርተናል፡፡ ከኛ ሥራ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅርበት እንሠራለን፡፡ ከትምህርት፣ ከጤና፣ ከገንዘብ ሚኒስቴሮች ጋር አብረን እንሠራለን፡፡ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በፈለግናቸው ጊዜ ሁሉ አብረውን ናቸው፣ ሥራችንንም ይከታተላሉ፣ ቴክኒካዊ ድጋፍ ያደርጋሉ እንዲሁም ግብረ መልስ ይሰጣሉ፡፡ በእነኚህ እየታገዝን ፕሮግራሞቻችንን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያጠናከርን ለዜጎቻችን እየደረስን ነው፡፡ ለመንግሥትም ጠንካራ የልማት አጋር የመሆን ዕድል አግኝተናል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪ በገንዘብና በቴክኒክ እያገዙን ያሉ ረጂ ድርጅቶች አሉ፡፡ አብዛኛዎቹ አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከአሜሪካ የገንዘብ አጋር አግኝተናል፡፡ እነዚህ ናቸው እስካሁን እንድንሠራ ያደረጉን፡፡ የኤስኦኤስ ሕፃናት መንደሮች ኢትዮጵያ ሠራተኞች የዚህ ሁሉ ውጤት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ከዚህ ድርጅት ወጥተው ራሳቸውን ችለው መልሰው የሚያገለግሉንና የሚያግዙንም ውለታቸው ከፍተኛ ነው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...

አሠርታትን በስኬት የዘለቀው የካንሰር ተቋም

ሕፃን ልጅን በሞት እንደመነጠቅ መሪር ሐዘን የለም። ክፉና ደጉን ያለየ፣ ከእናትና ከአባቱ ውጭ ሰው ያለ ለማይመስለው ሕፃን፣ በዕድሜ የገፉ እንኳን ፈጽመው በሚጠሉት ሞት ከእናት...