Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ሕይወትም እንዲህ ናት!

ከዊንጌት ወደ አየር ጤና ነው የዛሬው የጉዞ መስመራችን፡፡ አንዳንዴ በአድካሚው ውጣ ውረድ በበዛበት ሕይወት ውስጥ፣ ለራስ ፋታ ሰጥቶ ውጣ ውረዱን መገምገም የግድ ይሆናል፡፡ በሥራም ሆነ በትምህርት ምክንያት በቀን ቢያንስ አንድ ጊዜ ታክሲ ውስጥ ገባ ብሎ መውረድ አይቀርም፡፡ ይህ ጉዳይ የሚመለከተው መኪና የሌላቸውን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ በታክሲ ሲሄዱ አፌ ቁርጥ ይበልላችሁ የሚባሉ፣ ወይም ደግሞ አፋችሁ ይቆረጥ መባል የሚገባቸው ወያላና ሾፌር ሊያጋጥሙን ይችላሉ፡፡ በአንዳንድ ሥርዓተ አልባ ወያላዎች የተማረሩ ሰዎች፣ ‹እግዜር ይይላችሁ› ብለው ተራግመው ሲወርዱ፣ ሌሎች ደግሞ ለመብቴ መንግሥትንም ሆነ እግዜርን መጥራት አይጠበቅብኝም በሚመስል ስሜት የአፍ ጦርነት ይማዘዛሉ፣ ይጨቃጨቃሉ፣ የሚቧቀሱም አይጠፉም፡፡ እነሱ እንደሚሉት መብታቸውን ያስከብራሉ ማለት ነው፡፡ መብት ለማስከበር የምንሄድበት ርቀት እንደ ቁርጠኝነታችን የሚለያይ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ መብት ለማስከበር የዓላማ ሰው መሆኑን መገንዘብም እንዲሁ!

ብዙ ጊዜ ወያላዎች፣ ‹‹መብቴ ነው…›› የሚላቸው ሰው ጠላታቸው ነው ሊባል ይችላል፡፡ ‹‹መብታችሁ ታክሲ ውስጥ ትዝ አይበላችሁ…›› በማለት ታክሲያቸው ውስጥ በሰቀሉት ጥቅስ ይከራከራሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ተርፈው ካሳፈሩት ሰው ጋር ይጨቃጨቃሉ፣ ይወዛገባሉ፡፡ በአንድ በትንሽዬ አጋጣሚ ሳይሆን በርስት ወይም በሌላ ንብረት የሚከራከሩ ነው የሚመስሉት፡፡ አንድ ሰው፣ ‹‹ወገኖቼ ኧረ በደህና ነገር እንጨቃጨቅ፣ ማን ይሙት አሁን ደህና ውይይት የሚሻ አገራዊ ጉዳይ ጠፍቶ ነው እንደዚህ በረባ ባልረባው የምንነታረከው?›› አለ፡፡ ሌላኛው ሰው ደግሞ፣ ‹‹አየህ ሰው በርካታ ብሶቶች ሳይኖሩበት አይቀርም፡፡ ስለዚህ ትንሽ ነካ ስታደርገው በሆዱ ውስጥ አፍኖ ያቆየውን ሁሉ ይዘረግፈዋል፡፡ ወዶ አይደለም በሰው አትፍረድ፤›› አለው፡፡ ነገሩ ይፈረድብሃልና ነው፡፡ ከህሊና በላይ ፈራጅ ማን ይሆን!

የሁለቱ ሰዎች ክርክር ታክሲዋን በከፊል ተቆጣጠራት፡፡ የመጀመሪያው ወጣት፣ ‹‹ቢሆንም ለአገርም ለሕዝብም በሚጠቅሙ ጉዳዮች ላይ መከራከር ያዋጣል፡፡ በማይረቡ ጉዳዮች ጊዜያችንን እያጠፋን አዕምሮአችንን ከምናደንዘው ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ መነጋገሩ ይበጀናል…›› ሲል አንዲት ወጣት ደግሞ፣ ‹‹እውነት ነው፣ ለምን ስለዓባይ ጉዳይ አናወራም? ለምን ሕገ መንግሥቱን በተለመለከት እኛም ሐሳብ አንለዋወጥም? ኧረ እንዲያውም ወሳኝ ስለሆነው ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ላይ ለምን አንነጋገርም? የኑሮ ውድነት ሊያደርስ የሚችለውን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት እንዴት ማስወገድ እንደምንችል አንመክርም?›› በማለት አስተያየቷን ሰነዘረች፡፡ ወሬውም እየጦፈ ሄደ፡፡ ወጣቱና ወጣቷ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ወግ ቀጠሉ፡፡ ሌሎች ተሳፋሪዎች አፌን በዳቦ ያሉ ይመስል ጭጭ አሉ፡፡ አንድ ጎልማሳ በታፈነ ድምፅ፣ ‹‹አሁን ፖለቲካ ምን ያደርጋል? ክፉ እያናገሩ ለክፉ ይዳርጉናል…›› አለ፡፡ የማይለቀንን ነገር እየሸሸን የት እንደበቅ ያሰኛል እኮ!

ወያላው በተጀመረው ውይይት ብዙ የተመሰጠ አይመስልም፡፡ ለሾፌሩ የድሮ ታሪኩን ይተርክለት ጀመረ፤ ‹‹ድሮ ልጅ እያለሁ ጫማ የሚባል ነገር ጠላቴ ነበር…›› አለ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹እግር ኳስ እንኳን ታኬታ ካደረጉ ልጆች ጋር በባዶ እግሬ ነበር የምጫወተው፡፡ የመጫወቻ ሥፍራዬ ተከላካይ ነበር…›› አለ፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹እሺ እባክህ እስቲ በደንብ አጫውተኝ…›› በማለት ለታክሲዋ ነዳጅ እየሰጠ ወያላውም እንዲያወራ ቆሰቆሰው፡፡ ወያላው ቀጠለ፣ ‹‹ቅፅል ስሜ ‹ቀልጥመው› ነበር፡፡ እያቆላመጡ ‹ከቀልጥም ኳስ ቢያልፍ እግር አያልፍም› ሲሉኝ በቃ ማንም ይሁን እንኳን በታኬታ በታንክ ቢመጣ ማንንም አላሳልፍም ነበር፡፡ ኳሱን አታሎኝ ቢያሳልፍ ልጁን ግን ተዓምር ቢፈጠር አላሳልፈውም…›› እያለ ተረከለት፡፡ አያችሁ ጎበዝ እንዲህ ዓይነቶቹ እኮ ናቸው ሊቀለጥሙን ያሰፈሰፉት!

ወያላው በዚያ እንደ ብረት በሚከተክተው እግሩ የስንቱን ቅልጥም እንደሰበረ ሲናገር የጦር ሜዳ ውሎ የሚተርክ ይመስል ነበር፡፡ ሾፌሩ ብስጭት እያለ፣ ‹‹በፈጠረህ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አንተን አሠልፈውህ ቢሆን ኖሮ በሰላሳ አምስተኛ ሰከንድ ፈጣን ጐል እየገባብን ሪከርድ ላያችን ላይ አይሰበርም ነበር…›› አለው፡፡ ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹እባክህ እነሱን ተዋቸው እንኳን የአፍሪካ ዋንጫን ይቅርና የበረኪና ዋንጫ አያነሱም፡፡ አታስታውስም እንዴ ከምድብ ማጣሪያ ማለፍ አቅቶን በጊዜ ስንሸኝ?›› አለ፡፡ ወያላው ቀጥሎ፣ ‹‹እኔን ግን ሠፈር ውስጥ በጣም የሚያማርሩኝ ልጆች ነበሩ…›› በማለት የድሮውን እያስታወሰ ይስቅ ጀመር፡፡ ሾፌሩም፣ ‹‹ለምንድን ነው የሚያማርሩህ? አታነክታቸውም እንዴ?›› አለው፡፡ እሱም፣ ‹‹ያላነከትኩት የለም፣ ግን ትችታቸውን አያቆሙም፡፡ አንዴ ምን እንዳሉኝ ታውቃለህ?›› አለው፡፡  ሾፌሩም፣ ምን ብለው እንደ ተቹት ለመስማት እየጓጓ፣ ‹‹ደግሞ ምን አሉህ?›› አለው፡፡ ወያላው ከመናገሩ በፊት ሒሳብ መሰብሰብ ጀመረ፡፡ ይኼኔ ቅድም የተጀመረውን ወሬ ለመስማት ፋታ ተገኘ፡፡ የመጀመሪያው ወጣት አንድ ነገር ሲናገር ጆሮአችንን ውስጥ ጥልቅ አለ፡፡ ጆሮአችን ያልቻለው ጉድ የለም!

የመጨረሻው ወንበር ላይ በጥግ በኩል የተቀመጠው ወጣት፣ ‹‹በአንድ አገር ውስጥ የሕዝብ ንዴት በየትኛው ቅጽበት እንደሚነሳ ማወቅ አይቻልም…›› ብሎ የተወሰኑ ሰዎችን ጆሮዎች ሰበሰበ፡፡ ቀጥሎም፣ ‹‹ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ለዓረብ አገሮች የፀደይ አብዮት መነሻ በሆነችው ቱኒዚያ በተነሳው አመፅ፣ ራሱን አቃጥሎ በመግደል ለቱኒዝያውያን መነሳሳት ምክንያት የሆነው ሰው ይህን ያህል ቀውስ እንደሚያስከትል መንግሥት ቢያውቅ ኖሮ፣ እንኳን መንገድ ላይ አትክልት አትሽጥ ሊለው ይቅርና እባክህ ቤተ መንግሥት ውስጥ ገብተህ የፈለግከውን ሽጥ ብለው ሁኔታዎችን ያመቻችለት ነበር…›› ሲል መሀል ወንበር ላይ ለብቻው የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹እኔ እንዲያውም የፕሬዚዳንቱ ገበታ ላይ በየቀኑ እንዲሳተፍ የሚያደርጉት ይመስለኛል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እያባበሉና እያጎረሱት ያሞላቅቁት ነበር…›› ሲል፣ የባሰ አታምጣ አልን በሆዳችን፡፡ የመጀመሪያው ወጣት ከሰውዬው አፍ ተቀብሎ፣ ‹‹ስለዚህ አመፅ የቱ ጋ በምን ቅጽበት እንደሚነሳ ማወቅ አይቻልም፡፡ የኑሮ ውድነት በፈጠረው ጭንቀት የአዕምሮ ሁከት የሚያጋጥማቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ስለሚሄድ፣ መንግሥትም ሆነ ፀጥታ አስከባሪዎች የሚወስዱት ዕርምጃ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል…›› አለ፡፡ ወጣቱን ምን እንዳስጨነቀው በቅጡ ባይታወቅም ከመናገር የሚገታው ጠፋ፡፡ ‹‹ውኃ ቀጠነ ብለን በመንግሥት ላይ መማረር አንፈልግም፡፡ ነገር ግን እንጀራችን ሲቀጥን፣ ዳቦአችን ሲያርና የሚያሰማራቸው ሹሞች የዘፈቀደ ዕርምጃ ሲወስዱ ዝም ብለን መቀመጥ አንችልም፡፡ ስለዚህ ተገቢው ድጋፍና ማበረታቻ ሊደረግልን ይገባል…›› አለ፡፡ ብዙዎች አይናገሩም እንጂ ከተናገሩ ይዘረግፉታል!

የወጣቱ እንደዚያ መማረር ያስገረማቸው አንድ አባት ምክራቸውን ለገሱት፣ ‹‹ተው ልጄ አንተ ገና አንድ ፍሬ ልጅ ነህ፤…› ብለው ወሬያቸውን ሲጀምሩ ልጁ ተቆጣ፡፡ ‹‹ምኔ ነው አንድ ፍሬ? ተማርኩኝ፣ ተመረቅኩኝ፣ አሁን ሰላሳ ዓመት ሊሞላኝ ነው፡፡ ታዲያ ምኑ ነው አንድ ፍሬ ያሰኘኝ?›› ሲላቸው አዛውንቱ አሁንም በሰከነ አንደበት፣ ‹‹ድሮ ወጣቱ በሰላም መኖር አይችልም ነበር፡፡ ልማት ቢባልም ለሕዝቡ ጠብ የሚል ነገር አልነበረም፡፡ ዴሞክራሲም ቢሆን አልነበረም፡፡ ያ ጨቋኝ ሥርዓት በማለፉ ፈጣሪን ማመሥገን ነው የሚገባህ…›› ሲሉት የባሰ ተበሳጨ፡፡ ‹‹ለምንድነው ዕድሜ ልካችንን ያለውን መንግሥት ካለፈው መንግሥት ጋር ብቻ የምናወዳድረው? ለምን ከአሜሪካ ወይም ከአውሮፓ ወይም ደግሞ ከእነ ደቡብ አፍሪካ ጋር አናወዳድረውም? ድሮም የወደቀ ዛፍ ምን ይበዛበታል አሉ…›› በማለት መቶ ሜትር የሮጠ ይመስል ቁና ቁና ተነፈሰ፡፡ የወጣቱ ነገር ያላማራቸው አዛውንት ዝም አሉ፡፡ ሌሎቹ ተሳፋሪዎች በሥጋት እያዩት አሁንም ዝም ብለዋል፡፡ የቅድሙ ጎልማሳ ወጣቱን በጥርጣሬ እያየው፣ ‹‹አንተ አስመሳይ ሳትሆን አትቀርም፡፡ እኛ ዝም ብለን አንተን የማያስለፈልፍህ ምንድነው?›› ሲለው ጥቂት ሰዎች ሳቁ፡፡ ወጣቱ ግን በንዴት እያየው ዝም አለ፡፡ ካልተዋወቅን እኮ የፍላጎታችን ምንጭ አይታወቅም!

የተነሳውን ወግ አይሉት ንትርክ እያሰብኩ፣ ‹‹እንዲህ ዓይነቱን ነገር እንኳን ማውራት መስማትም አንዳንዴ ሊያስጠይቅ ይችላል…›› የሚሉ ጎረቤቴን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ከጀመርኩ ጥቂት ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ጎረቤቴ፣ ‹‹አንዳንዱ ባልሆነ መንገድ ወሬ ይጀምርና ወይ ያስከስስሃል ወይ ያስጠይቅሃል…›› ይላሉ፡፡ የጎረቤቴ ጥንቃቄ እኔ ዘንድ ተጋብቶ እኔም እንደ እሳቸው የጥርጣሬ ማርሼን ቀይሬአለሁ፡፡ ሾፌሩ ወያላውን፣ ‹‹በፈጠረህ ታሪክህን ቀጥልልኝ፣ ምን እያሉ ነበር የሚተቹህ?›› አለው፡፡ ወያላውም ሳያቅማማ ማውራት ጀመረ፡፡ ‹‹እንዳልኩህ ጫማ የሚባል ነገር አልወድም፡፡ እናም ሁልጊዜ በባዶ እግሬ ስሄድ ነበር ሰላም የሚሰማኝ፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ቤተሰቦቼና እኔ የተጋበዝንበት አንድ የቅርብ ዘመድ ሠርግ ነበር፡፡ እዚያ ሠርግ ላይ ታዲያ ባዶ እግሬን መገኘት ለእኔም ሆነ ለቤተሰቦቼ ውርደት ነበር፡፡ ስለዚህ ቤተሰቦቼም እንደ ምንም ተጣጥረው አሮጌ አዲዳስ ጫማ ገዙልኝ፡፡ ያንን ጫማ አድርጌ ትንሽ ‹ወክ› ለማድረግ ከቤት ወጣ ስል እነዚህ እርጉም የሆኑ የሠፈራችን ልጆች አጋጠሙኝ…›› ብሎ ወሬውን አቋርጦ ‹‹መጨረሻ!›› በማለት አየር ጤና መድረሳችንን አወጀ፡፡ ወያላው የጀመረው ወሬ መጨረሻው ሳይታወቅ ፒያሳ ላይ ተሰነባብተን ተለያየን፡፡ ሕይወትም እንዲህ ናት! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት