Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋት

ቀን:

የኢኮኖሚ አቅምንና የጤና ሁኔታን ያላገናዘበ የልጆች ቁጥር መብዛት በቤተሰብም ሆነ ማኅበረሰቡ ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ ይታመናል።

በመሆኑም የልጆችን ቁጥር ለመመጠንና አራርቆ መውለድን ልማድ ለማድረግ፣ የጤና ባለሙያዎችና የኅብረተሰብ ጤና ሳይንስ ተመራማሪዎች አፅንኦት ሰጥተው ይሠሩበታል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ  ያለውን የሕዝብ ቁጥር ከኢኮኖሚው ጋር ተመጣጣኝ ለማድረግ ከሚሠሩ ሥራዎች  መካከል የወሊድ መቆጣጠሪያ ወይም ፅንስ መከላከያና እርግዝናን ለማዘግየት ወይም ለማስቀረት  የሚያስችሉ  ዘዴዎች  ተጠቃሽ  ናቸው፡፡ ልማዳዊ  የወሊድ መቆጣጠሪያ  ዘዴዎችንም ብዙዎች እንደሚጠቀሙባቸው ይነገራል፡፡

- Advertisement -

ከዚህ ባሻገር  የቤተሰብ ምጣኔን  ለመቆጣጠር፣ አራርቆ ለመውለድና ወሊድን ሙሉ በሙሉ ለማቋረጥ እንዲሁም የተለያዩ ተላላፊ የሆኑ በሽታዎችን ለመቆጣጠር  የሚያስችሉ ሰው ሠራሽ የወሊድ መቆጣጠሪያዎች ይቀርባሉ፡፡

በዓለም ከ15 የሚበልጡ ሰው ሠራሽ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴዎች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል ገሚሶቹ በእንክብል መልክ ተዘጋጅተው በአፍ የሚወሰዱ ናቸው። በመርፌ የሚሰጡና በክንድ ወይም በማህፀን የሚቀበሩ፣ የወንድ ዘር ፈሳሽ ወደ ማህፀን እንዳይገባ የሚከላከሉና የመሳሰሉ ዘዴዎችም አሉ፡፡

 እነዚህ የወሊድ መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች በሚወሰዱበት ወቅት  ለተለያዩ የጎንዮሽ ጉዳቶች ከማጋለጣቸው ባሻገር  አወሳሰዱን በአግባቡ  ካለማወቅ በተነሳ  ለተፈለገለት ዓላማ ላይውል  የሚችልበት አጋጣሚ የሚኖር መሆኑንም የጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም መንግሥት፣ መድኃኒቱን ወደ አገር ውስጥ የሚያስገቡ አካላትና የሚያከፋፍሉ  እንዲሁም  ለተጠቃሚዎች በቀጥታ የሚሸጡ  መድኃኒት ቤቶችና የጤና ተቋማት  ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ስለአጠቃቀማቸው ግንዛቤ ካለመኖሩም ባሻገር በሚፈለገው ልክ በቂ  አቅርቦት አለመኖሩ ሌላኛው ተግዳሮት ስለመሆኑ ይነሳል፡፡

እነዚህን ችግሮች  ለማቃለል ያስችላሉ የተባሉና  ጥራት ያለው የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተደራሸነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ሁለት የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን  ለተጠቃሚዎች ማቅረቡን ፒ ኤስ አይ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሶሻል ኢንተርፕራይዝ  አስታውቋል፡፡

ድርጅቱ ‹‹ምዩሪ ኢትዮጵያና ፕሮንታ 1›› የተሰኙ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን ይፋ አድርጓል፡፡

በአገሪቱ  የሥነ ተዋልዶ ጤና ተደራሽነት አሁንም ፈተናዎች እንዳሉበት ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ችግሮቹን  ለማቃለል  ጥራት ያለው የቤተሰብ ምጣኔና  የሥነ ተዋልዶ ጤና   አገልግሎትን  ለማሳደግ  የሚያግዙ ምዩሪና ፕሮንታ አንድ የተሰኙ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን  ለገበያ ማቅረቡን አስታውቋል።

እንክብሎቹ አሁንም ድረስ የተደራሽነት እጥረት ያለበትን የወሊድ መቆጣጠሪያ ፍላጎት ለማሟላትና ያልታቀዱ እርግዝናዎችን  እንዲሁም የሚያስከትሏቸውን የጤና ጫናዎች ለመከላከል  የጎላ ሚና እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

ምርቶቹ ዘላቂ በሆነ አቅርቦትና ማከፋፈል በመላው አገሪቱ ላሉ ሴቶች በእኩል ደረጃ ተደራሽ    መሆናቸውን የተናገሩት የድርጅቱ የገቢ ማስገኛ ክፍል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን ካሳ፣ ምዩሪ  ዘመኑ የደረሰበትን  የሳይንስ ደረጃ  የጠበቀ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብል መሆኑን ተናግረው፣ በውስጡ ፕሮጀስቱንና ኢስትሮጅን የተጣመሩበት በመሆኑ በወሊድ መቆጣጠሪያ ሕክምና ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃን የያዘ ነው ሲሉ አብራርተዋል።

በተጨማሪ እንክብሉ የጎንዮሽ ተፅዕኖን የሚቀንስና ቀደም ሲል ከነበሩት እንክብሎች ለየት የሚልበት ዲሶጀስትሪል የተሰኘ የሦስተኛው ትውልድ ፕሮጀስቱን የተባሉ ቅመሞችን በውስጡ የያዘ መሆኑ ከሁሉም የተሻለና ምቹ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንደሚያደርገው አክለዋል።

በአሁኑ ወቅት ምርቶቹ  በአዲስ አበባና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በስፋት እየተሠራጩ እንደሆነ የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ በወሊድ መቆጣጠሪያና በሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

የእንክብሎቹ ጥራት በዓለም ጤና ድርጅት የተረጋገጠ ነው ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት  ባለሥልጣን  ስለአስተማማኝነታቸው ማረጋገጫ መስጠቱንም አክለዋል።

“ፕሮንታ አንድ”  የተሰኘው  እንክብል  የተለየ ነገር  እንደሌለው ተናግረው፣ ነገር ግን እየታየ ያለውን የተደራሽነት ችግር ለመፍታት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያግዝ አብራርተዋል።

ፒ ኤስ አይ ኢትዮጵያ በ2ዐዐ3 ዓ.ም. የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን፣ ሥራውን የጀመረው በወባ መከላከል ላይ ነው፡፡

ድርጅቱ  በአራት ዋና ዋና የጤና መስክ ላይ  አተኩሮ እየሠራ ይገኛል ያሉት አቶ ወንድወሰን፣  የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር፣ የሥነ ተዋልዶ ጤናና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከል ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየሠራ እንደሚገኝ አክለዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...