Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች ውይይት የተደረገበት የገጠር መሬት አስተዳዳርና አጠቃቀም አዋጅ ፀደቀ

ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች ውይይት የተደረገበት የገጠር መሬት አስተዳዳርና አጠቃቀም አዋጅ ፀደቀ

ቀን:

ከስድስት ወራት በፊት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ከትግራይ በክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎች ውይይት ሲደረግበት የነበረው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ ፀደቀ፡፡

ምክር ቤቱ ትናንት ማክሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው 26ኛ መደበኛ ስብሰባ ያፀደቀው የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም አዋጅ፣ የመሬት ይዞታን በማስያዝ ብድር ማግኘት ያስችላል፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብርና ጉዳዮችና የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች መሪነት ከታኅሳስ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከትግራይ ክልል በስተቀር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ውይይት መካሄዱን፣ የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን ላሌ ባቀረቡት የመጨረሻ የውሳኔ ሐሳብ አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

በውይይትና በግብዓት መሰብሰቢያ መድረኮች ሁለቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ከክልሎች ጋር ዋነኛ የመገናኛ መስመራቸው የክልል ምክር ቤቶች ቢሆኑም፣ በትግራይ ክልል ሕጋዊና በሕዝብ የተመረጠ ምክር ቤት ባለመኖሩ ተነጋግሮ ውይይት ማድረግ አለመቻሉን አቶ ሰለሞን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የገጠር መሬት ጉዳይ እስከ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ድረስ ወርዶ ውይይት ሊካሄድበት የሚገባ ትልቅ ጉዳይ በመሆኑ፣ በአፈ ጉባዔው አማካይነት በትግራይ ክልል ውይይት እንዲመቻች ቢጠየቅም፣ ለውይይት የሚሆን መድረክ አለመገኘቱን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡

ከሕግ አውጪው በተጨማሪ በአስፈጻሚው በኩል ጥረት ሲደረግ የነበረ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰለሞን፣ እንደታሰበው መድረክ ሊፈጠር አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ አዋጁ ቢፀድቅም ወደፊት ከትግራይ ክልል የሚገኙ ግብዓቶች ካሉ ለአዋጁ ማስፈጸሚያ የሚሆኑ ደንብና መመርያዎቹ ሲወጡ ሊካተቱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡

የምክር ቤት አባላት በአዋጁ አንቀጽ 17 በገጠር መሬት ይዞታ ላይ የተገኘ ንብረት በሽያጭ ማስተላለፍ ተብሎ የተቀመጠውን ድንጋጌ ቅሬታ አቅርበውበታል፡፡

በዚህ አንቀጽ ባለይዞታዎች በመሬት ይዞታቸው ላይ በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸው ወይም በመፍጠር ችሎታቸው ያፈሯቸውን የማይንቀሳቀሱ ቋሚ ንብረቶች ባሉበት ሁኔታ የመሸጥ፣ የመለወጥ ወይም በሌላ በማንኛውም ሕጋዊ መንገድ የማስተላፍ መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡

አቶ ዓለሙ ጎንፋ የተባሉ የምክር ቤት አባል፣ አንቀጹ አንድን ሰው ቋሚ ተክሉንና መሬቱን ሸጦ እንዲፈናቀል ያደርገዋል የሚል ሥጋት ይፈጥራል ብለዋል፡፡ በተመሳሳይ ሌላ የምክር ቤት አባል በዚህ መሠረት የመሸጥና የማስተላለፍ ፈቃድ መስጠት፣ አርሶና አርብቶ አደሩ እንዲፈናቀል የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሕግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ አባል አቶ ለማ ተሰማ ለቀረቡት ሐሳቦች በሰጡት ማብራሪያ፣ አንድ አርሶ አደር መሬቱ ላይ ያለውን ቋሚ ንብረት ሲሸጥ መፈናቀል እንዳይፈጠር ክልሎች አርሶ አደር፣ አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደሮች ካላቸው መሬት ላይ ምን ያህሉን ማስተላለፍ እንደሚችሉ ሕግ እንዲያወጡ አዋጁ ይፈቅዳል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ በበኩላቸው የመሬት ሀብት በአግባቡ እንዲመራ ታስቦ የተዘጋጀ አዋጅ መሆኑን ጠቅሰው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 3 መሬት መሸጥ መለወጥ እንደማይቻል መደንገጉን አስታውሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዚሁ አንቀጽ 40 ንዑስ አንቀጽ 7 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በላቡና በወዙ ያፈራውን ሀብትና ንብረት የመሸጥ፣ የመለወጥና የማስተላለፍ መብት እንዳለው መደንገጉን አስረድተዋል፡፡

የድንጋጌው ዓላማ የገጠሩ ማኅበረሰብ የፋይናንስ ችግሩን ለመቅረፍ፣ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አንደኛ በኪራይ መልክ በባንክ አስይዘው ብድር እንዲያገኝ፣ እንዲሁም ቋሚ ንብረት አፍርቶ በመሸጥ ወይም በማስተላለፍ እንዲጠቀም ለማድረግ ታስቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ነገር ግን መሬት ላይ ያለው እውነትና አሁን እየወጣ ያለው ሕግ ባይኖርም እየተሸጠ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ በተለያዩ ሰበቦች በሚሸጠው ምክንያት የገጠር መሬት አርሶ አደሩ እንዳይፈናቀልና መሬቱን እንዳያጣ በሕግ መገደብ ስለሚያስፈልግ ነው ብለዋል፡፡

በፀደቀው አዋጅ ውስጥ እንደተገለጸው ማንኛውም ሰው የግል፣ የወል ወይም የመንግሥት ይዞታን በሕገወጥ መንገድ የወረረ ከሆነ ከ30,000 እስከ 100,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል፡፡

በተመሳሳይ ማንኛውም ሰው በግል፣ በወል ወይም በመንግሥት ይዞታ ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከ50,000 እስከ 150,000 ብር ወይም ከሦስት ወይም እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

ባልተፈቀደ ቦታ ላይ ማንኛውንም ግንባታ የሠራ ወይም እንዲሠራ የፈቀደ ማንኛውም ሰው ከ25,000 እስከ 50,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም የሚቀጣ ሲሆን፣ ከመሬት አጠቃቀም ዕቅድ ውጪ ይዞታውን ጥቅም ላይ ካዋለ ደግሞ ከ20,000 እስከ 50,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡

ሐሰተኛ የመሬት ይዞታ ማስረጃ ያቀረበ ባለይዞታ፣ ማስረጃ የሰወረ ወይም የተሳሳተ ማስረጃ የሰጠ ባለሙያ ከ10,000 እስከ 25,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም የሚቀጣ ሲሆን፣ መሬት የሸጠ   ወይም የገዛ እንደሆነ ከ100,000 እስከ 200,000 ብር ወይም ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ወይም በሁለቱም እንደሚቀጣ የአዋጁ ድንጋጌ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...