Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናአገር አቀፍ ሙስናን የሚከታተል ብሔራዊ ካውንስል ማቋቋሚያ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

አገር አቀፍ ሙስናን የሚከታተል ብሔራዊ ካውንስል ማቋቋሚያ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገለጸ

ቀን:

  • ካውንስሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሆናል ተብሏል

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በአገር አቀፍ ደረጃ ያለውን የሙስና ሁኔታ የሚገመግም፣ አቅጣጫ የሚያስቀምጥና አፈጻጸሙን የሚከታተል ብሔራዊ ካውንስል እንዲቋቋም የሚያስችል ‹‹የሥነ ምግባር ግንባታና ሙስና መከላከል›› የተሰኘ ፖሊሲ እያዘጋጀ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ፖሊሲው የሥነ ምግባር ግንባታ፣ የቅድመ ሙስና መከላከልና በሙስና የተመዘበረ ሀብትን ማስመለስ ላይ ትኩረት የሚያደርግ መሆኑን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት አማካሪ አቶ መስፍን በላይነህ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የፀረ ሙስና ትግሉን ለመምራት የሚያስችል ፖሊሲ ባለመኖሩ፣ ተቋማት በባለቤትነት እየሠሩ አለመሆናቸውን፣ ይህም በሙስና መከላከሉ ላይ ጫና ሲያሳድር እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ፖሊሲውን ለማዘጋጀት ሁለት ዓመት ተኩል እንደፈጀ ሪፖርተር በተመለከተው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ የተመለከተ ሲሆን፣ የሕግ ማዕቀፎች ቢኖሩም ሕግ የማስከበር ሥራ አጥጋቢ አለመሆን ለፖሊሲው መረቀቅ አንደኛው መነሻ መሆኑ ታውቋል፡፡

- Advertisement -

በተጨማሪም የጥቆማ ሥርዓቱ የላላ መሆን የወንጀል ምርመራና ክስ ሥራ በመረጃና በማስረጃ ላይ የተደገፈ እንዳይሆን ማድረጉ፣ የተመዘበረና ከአገር የወጣ ሀብት ማስመለስ ላይ አጥጋቢ ሥራ አለመከናወኑ ለፖሊሲው መዘጋጀት ሌላው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡ 

ፖሊሲውን ተፈጻሚ ለማድረግና በአገር አቀፍ ደረጃ ለፀረ ሙስና ትግሉ ተፈጻሚ የሚሆኑ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ፣ በመከታተል፣ የፀረ ሙስና ትግሉ በፌዴራልና በክልሎች በወጥነት ተፈጻሚ እንዲሆን የሚያደርግ የብሔራዊ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ካውንስል እንደሚቋቋም ተመላክቷል፡፡

ካውንስሉ በአገሪቱ ያለውን የሙስና መከላከል ሒደት በኃላፊነት እንደሚመራ ተገልጿል፡፡ ከሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽንና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቋቋመው ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴ፣ የሚቋቋመው ካውንስል ተግባራት በምን ይለያሉ በማለት ሪፖርተር ላነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ መስፍን፣ ‹‹ብሔራዊ የፀረ ሙስና ኮሚቴው በዘላቂነት የተቋቋመ አለመሆኑን አስረድተው፣ ኮሚሽኑም ተቋማት በራሳቸው አቅም ሙስናን እንዲከላከሉ ያግዛል፣ ይከታተላል፣ በተጨማሪም አዲስ ለሚቋቋመው ካውንስል ሪፖርት ያቀርባል፤›› ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበላይነት ካውንስሉን እንደሚመሩትም አቶ መስፍን ጠቁመዋል፡፡ የማኅበራዊ ዘርፍ ተቋማት የትውልድ ሥነ ምግባር የማነፅ ሥራ፣ የሚዲያና የሲቪክ ተቋማት የትውልድ ሥነ ምግባር ግንባታ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችና ሕዝባዊ ተቋማት የአመራሮችንና የሠራተኞችን ሥነ ምግባር ድጋፍ፣ ክትትልና ቁጥጥር፣ እንዲሁም ኮሚሽኑ በባለድርሻ አካላት የሚከናወኑ የሥነ ምግባር ግንባታ፣ ቅድመ መከላከል፣ የሕግ ማስከበር ሥራዎችን ድጋፍና ክትትል፣ በተጨማሪም የፀረ ሙስና ትግል አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያዘጋጅ በረቂቁ ተገልጿል፡፡

ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ የፀረ ሙስና ትግሉ በሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲመራ እንደቆየና ከ2008 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ የሙስና ቅድመ መከላከል ሥራ በራሱ፣ እንዲሁም የሙስና ወንጀል ምርመራና ክስ ሥራ በፍትሕ ሚኒስቴር ሲከናወን መቆየቱ ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...