Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የፕላስቲክ አምራቾች የወረቀትና የጨርቅ ከረጢቶችን በአፋጣኝ ማምረት እንዲጀምሩ ማሳሰቢያ ተሰጠ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ0.03 ማይክሮ ሜትር በታች የሆነ ፕላስቲክ ከረጢት የሚያመርቱ እስከ አሥር ዓመታት ይታሰራሉ

አካባቢን ሊበክሉ የሚችሉ ስስ ፕላስቲኮችን የሚያመርቱ ድርጅቶች የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱ የወረቀትና የጨርቅ ከረጢቶች በአፋጣኝ ማምረት እንዲጀምሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡

ፕላስቲክ በማምረት የተሰማሩ ድርጅቶችና ባለቤቶች ከተፈቀደላቸው 0.03 ማይክሮ ሜትር በታች ሲያመርቱ ከተገኙ፣ ከመዝጋታቸው ባሻገር፣ ከሦስት ዓመት እስከ አሥር ዓመት የእስር ቅጣት እንደሚያስከትልባቸው ተገልጿል፡፡

ባለሥልጣኑ በጉዳዩ ላይ በመልሶ ማምረትና መጠቀም ከተሰማሩ የፕላስቲክ ፋብሪካ ባለቤቶችና የፕላስቲክ ምርቶችን በስፋት ከሚጠቀሙ ትልልቅ ሱፐር ማርኬቶች፣ ዳቦ አምራቾችና አከፋፋዮች ጋር መግባባት ለመፍጠር በማለት ማክሰኞ ግንቦት 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት አድርÕል፡፡

ከፕላስቲክ አምራቾች በተጨማሪ ለኅብረተሰቡ ዳቦ የሚያከፋፍሉና ሌሎች ሸቀጦችን በፕላስቲክ ምርቶች ጠቅልለው የሚሸጡ ቸርቻሪዎችም ሆኑ አከፋፋዮች፣ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ይደረጋል ተብሏል፡፡

ሸማቾች ማንኛውንም ዕቃ ለመሸመት በሚሄዱበት ወቅት የፕላስቲክ ውጤቶችን ከመጠቀም ይልቅ፣ ከወረቀትና ከጨርቅ የተሠሩና በድጋሚ ጥቅም ሊሰጡ የሚችሉ ከረጢቶችን እንዲጠቀሙ ማድረግ እንደሚገባ የባለሥልጣኑ የአካባቢ ቁጥጥርና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ለሚሜ ጉደታ አስረድተዋል፡፡

አካባቢን የሚበክሉ የፕላስቲክ ምርቶች ውፍረታቸው ከ0.03 ማይክሮ ሜትር በታች ሆነው እንዳይመረቱና አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ፣ በፕላስቲክ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የሆነ ታክስ መጣል፣ እንዲሁም በካይ ይክፈል የሚለውን ተግባራዊ ማድረግ  የሚሉትና ሌሎች ምርቶቹን ለመቀነስ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ዳይሬክተሩ አብራርተዋል፡፡ 

የፕላስቲክ ምርቶችን በወረቀትና በጨርቅ ከረጢቶች መተካት የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አኳያ ስላለው ሚና ለኅብረተሰቡና ለሚመለከታቸው አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መደረጉን አቶ ለሜሳ ቢናገሩም፣ የፕላስቲክ አምራቾችና አከፋፋዮች ከዚህ ይልቅ በክፍለ ከተማና በወረዳ ያሉ የሥራ ኃላፊዎች የማስፈራራትና የማዋከብ ድርጊት እንደሚፈጽሙባቸው ነው በውይይቱ ወቅት የተናገሩት፡፡

ጉዳዩን ቀደም ብለው ሊያውቁና ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ጊዜ ሊሰጣቸው እንደሚገባም ቅሬታቸውን አሰምተዋል፡፡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ከተለመደ ምርት ወደ አዲስ ምርት በአንድ ጊዜ ሲገባ ቀድመው ሊሠሩ የሚገባቸው በርካታ ተግባራት መኖራቸውን ጠቅሰው፣ መመርያ ስለመውጣቱና በሥራ ላይ ስለመዋሉ ጭምር መረጃ እንደሌላቸው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ የወጣውን መመርያ አንብቦ ለመረዳትና ለማወቅ ቢፈለግ የት እንደሚገኝ ጠይቀዋል፡፡

ቀደም ሲል ኅብረተሰቡ በአነስተኛ ወጪ ሲገለገልባቸው የነበሩ የፕላስቲክ ውጤቶች በከፍተኛ ወጪ ተመርተው ለሽያጭ ከቀረቡ በዳቦና መሰል ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መደረጉ አይቀርም ሲሉ አንድ አስተያየት ሰጪ ተናግረው፣ ይህም ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ ለተጨማሪ ወጪ የሚዳርግ ነው ብለዋል፡፡

‹‹ለምሳሌ አንድ ዳቦ አሥር ብር የገዛ ሰው ለመያዣ የአምስት ብር ከረጢት እንዲገዛ ማድረግ እንዴት ይቻላል? ሲሉ አስተያየት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

ፕላስቲክ የሚያመርቱ ፋብሪካዎችን ለማስቆም ከመሞከር በፊት በተቋሙ ጥናት መደረግ ነበረበት ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ ብክለት ያስከትላሉ የተባሉ ምርቶች እንዳይመረቱ ከመከልከል በፊት መልሰው አገልግሎት የሚሰጡበት አሠራር ቢመቻች የተሻለ ነበር ሲሉ ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

አምራቾችን ከገበያ ከማስወጣት በፊት ከደረጃ በታች ናቸው የተባሉ ፕላስቲኮች መልሰው አገልግሎት የሚሰጡበት ሁኔታ ቢመቻች፣ ለአምራቹም ሆነ ለተገልጋዩ የተሻለ ነበር ብለዋል፡፡

የፕላስቲክ ምርቶችን ከደረጃ በታች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች እንዲዘጉና ዕርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያስገድደው መመርያ ከወጣ ከሦስት ዓመት በላይ እንደሆነው የተናገሩት፣ የከተማ አስተዳደሩ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ ናቸው፡፡

በተያዩ ምክንያቶች ወደ ተግባር ሳይገባ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ዲዳ፣ ከዚህ ውይይት በኋላ ፕላስቲክ አምራቾችና ተጠቃሚዎች ፊታቸውን ወደ ወረቀትና ጨርቅ  ምርቶች እንዲያዞሩ አሳስበዋል፡፡

ከደረጃ በታች ሲያመርቱ የተገኙ ፋብሪካዎች የማያዳግም ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው የተናገሩት ዋና ሥራ አሰኪያጁ፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያና ማሸግ አይኖርም ብለዋል፡፡

‹‹ምርቶቹ ደረጃቸውን ጠብቀው ስለተመረቱ ለተገልጋዮች ዋጋ ጨምራችሁ ሽጡ ወይም በዳቦና በሌሎች ምርቶች ላይ ዋጋ ጨምሩ አላልንም፤›› ያሉት አቶ ዲዳ፣ ‹‹ነገር ግን ለተገልጋዮች ከወረቀት የተሠሩ ከረጢቶችን እንድታዘጋጁ፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች