Monday, May 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በመጪው ዓመት ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ላይ ምርቶችን በመጠንና በዓይነት በእጥፍ ለማቅረብ ታቀደ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዘንድሮ ኤክስፖ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት ተፈጽሟል

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመጪው ዓመት በሚያካሂደው ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኤክስፖ ከሚሊኒየም አዳራሽ በተጨማሪ በሌሎችም ቦታዎች በማዘጋጀት፣ የምርቶችን መጠንና ዓይነት ከዘንድሮው ኤክስፖ በብዙ እጥፍ ለመጨመር ማቀዱን አስታወቀ፡፡

ከግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለአምስት ቀናት ሲካሄድ በቆየው ‹‹የኢትየጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ኤክስፖ መክፈቻ ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ተገኝተው ስለመርሐ ግብሩ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ግብዓቶችን ቀላቅለው ማምረት ባለመቻላቸው የተነሳ፣ ዘርፉ በከፊልም ቢሆን ተጎድቷል፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው ነበር፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት፣ ጥራት ያላቸው ምርቶች ለውጭ ገበያ በማቅረብ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማሳደግ የተጀመረ መርሐ ግብር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ንቅናቄውን በይፋ ካስጀመሩበት ከሚያዝያ 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተዘግተው የነበሩ በርካታ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ መግባታቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፣ ንቅናቄው ተኪ ምርቶችን ለአገር ውስጥ  ከማቅረብ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ ጭምር  የአምራች ዘርፉ እንዲነቃቃ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ኤክስፖው ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ግለሰቦችና ተቋማት መጎብኘቱን ገልጸው ከ57 አገሮች የመጡ ድርጀቶችና 157 ዲፕሎማቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2017 ዓ.ም. ለማካሄድ ውሳኔ ላይ መደረሱን ጠቁመው፣ በኤክስፖው የሚቀርቡ ምርቶችን መጠንና ዓይነት በብዙ እጥፍ ለማሳደግ ዕቅድ መያዙን አብራርተዋል፡፡

በ2017 ዓ.ም. በሚካሄደው ኤክስፖ የግብርና፣ የቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ የጨርቃ ጨርቅና የማሽነሪ ምርቶች የራሳቸው ይዘት ኖሯቸው እንደሚቀርቡ አክለው ገልጸዋል፡፡

በዘንድሮ ኤክስፖ በአጠቃላይ 210 አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ መሆናቸውን፣ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ግብይት መፈጸሙንም አስታውቀዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› የ2016 ዓ.ም. ኤክስፖ ማጠቃለያ መርሐ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ እንደገለጹት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ታምርት›› ዋና ዓላማ ዘርፉ በሚፈለገው ልክ እንዳያድግ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በመለየት ዕድሎችን መጠቀም ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪውን ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ውስን እንዲሆን አድርገው የቆዩ ችግሮችን በመለየት፣ ደረጃ በደረጃ እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በንቅናቄው አምራች ኢንዱስትሪው ከየት ተነስቶ የት መድረስ አለበት? ለሚለው አሠራር ብቻ ከማስቀመጥ በዘለለ፣ ተኪ ምርቶችን በማምረት በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣት እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መሠረት መንግሥት ለጀመረው ኢኮኖሚያዊ የመዋቅር ሽግግር መሠረት የሚሆኑ ውጤቶችን በአምራች ዘርፉ እየተመዘገቡ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ዘንድ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ኢትዮጵያ ያላትን ዕምቅ ሀብት ለመጠቀም የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አብራርተዋል፡፡

በተለይ ለአምራቾች ዘላቂ የገበያ ትስስር በመፍጠርና በአገር ውስጥ ምርት የመኩራት እሴትን በዘላቂነት መገንባት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቀጣይ የቤት ሥራ መሆን አለበት ብለዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች