Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊ‹‹የአራስ ቤት›› የገጠመው ፈተና

‹‹የአራስ ቤት›› የገጠመው ፈተና

ቀን:

እናትነት ፀጋ፣ እናትነት ክብር ነው፡፡ እናት መልኳና ልኳ ልጇ ነው፡፡ እናት ለልጇ ስትል የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ወደ ኋላ አትልም፡፡ ተፈጥሮ እናትነትን እጅግ አጉልታዋለች፡፡

እናትነት በፍቅር የተሞላ ሕይወት ሲሆን፣ በፈተና የታጠረ የሚሆንበት አጋጣሚም ይኖራል፡፡ በተለይ አባት በሌለበት የሚወልዱና ያለአባት ልጅ የሚያሳድጉ እናቶች ችግር ያይላል፡፡

‹‹የአራስ ቤት›› የገጠመው ፈተና | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

- Advertisement -

‹‹ጎሽ ለልጇ ስትል ተወጋች›› እንዲሉ፣ በችግርና በፈተና ውስጥም ሆና እናት ልጇን ታሳድጋለች፣ ትንከባከባለች፡፡ ክብሯ፣ ማዕረጓ ጌጦቿ ልጆች ናቸውና ስለ ልጇቿ ስትል የእሷን ውበት አጠውልጋ የልጆቿን ውበት ታፈካለች፡፡

እናት ውዴ ደምሴ፣  የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ከወሎ ወደ አዲስ አበባ ከመጣች አራት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ከሰው ቤት ሠራተኝነት ተነስታ የራሷን አነስተኛ ቁርስ ቤት እስከመክፈት ደርሳለች፡፡ በእነዚህ ሒደቶች የተረዳችው ነገር ቢኖር፣ ዛሬ ከደረሰችበት ደረጃ ከፍ ለማለትና ነገ የተሻለ ለመሆን የሚደግፉትና የሚያግዛት የኑሮ አጋር የምትለው ማግኘት ነው፡፡ ከአንድ ሁለት እንደሚሻል በማመንም ትዳር መሠረተች፡፡ እርግዝናም፡፡

‹‹የኑሮዬ አጋር ነው›› ብላ በትዳር የተጣመረችው ሰው እርጉዝ መሆኗን ሲያውቅ ብቻዋን ትቷት እንደሄደ ትናገራለች፡፡ ‹‹እርግዝናዬ እየታወቀ ሲሄድ፣ ሆዴም እየገፋ ሲመጣ ሥራ መሥራት አቃተኝ፣ እጄ ላይ የነበረውም ገንዘብ አለቀ፣ በዚህም የተነሳ የቤት ኪራይ መክፈል ባለመቻሌ ከተከራየሁበት ቤት ወጥቼ ቤተ ክርስቲያን ለማደር ተገደድኩ›› ትላለች፡፡

‹‹የሰው ቤት ሠራተኛ ሆኜ ለመቀጠር እንኳ እርጉዝ በመሆኔ ወስዶ ሊያሠራኝ ፈቃደኛ የሚሆን ሰው አልተገኘም›› የምትለው ውዴ፣ እንዲት እናት ሠራተኛ ስለተቸገሩና የሚያግዛቸው ስለሌለ እርጉዝም ብትሆንም እንደቀጠሯት፣ የመውለጃ ቀኗ እስኪደርስ ለሁለት ወራት ያህል ከቀጣሪዋ ጋር እንደቆየች ትናገራለች፡፡

ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ካለው ጤና ጣቢያ ሴት ልጅ የወለደቸው ውዴ፣ ከወለደች በኋላ የሚጠይቃት፣ የሚያርሳትና የሚንከባከባት ‹‹የኔነው›› የምትለው ወዳጅ፣ ዘመድ ጎረቤት አልነበራትም፡፡

አራስ ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ የሚመጡ ሰዎች ካመጡት የሚበላና የሚጠጣ እየቀነሱ በሚሰጧት ለ15 ቀናት በጤና ጣቢያው ቆይታለች፡፡

‹‹ሁኔታው ሁሉ ለእኔ ከባድ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ልጄን ይዤ የት ነው የምገባው? ምንድነው? የምሆነው ብዬ ሳስብ ነገሩ ሁሉ ጨለማና ተስፋ የሚያስቆርጥ ሆነብኝ፡፡ ልጄን ለአሳዳጊ ድርጅት እንዳልሰጥ የሚቀበለኝና የማውቀው ድርጅት የለም፡፡ እዚያው ጤና ጣቢያ ሕፃኗን ጥያት እንዳልጠፋ የእናትነት አንጀቴ አልችል አለኝ፤›› ትላለች፡፡

ውዴ፣ በዚህ ፈተና ውስጥ ባለችበት ወቅት ‹‹የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን››   ከእነልጇ ወስዶ ሊያርሳትና ሊንከባከባት ፈቃደኛ ሆኖ በመገኘቱ ወደ ፋውንዴሽኑ ወዳዘጋጀው ማዕከል  መቀላቀሏን ትናገራለች፡፡

ወደ ማዕከሉ ከመጣች ሁለት ወር ከአሥር ቀን የሆናት መሆኑን የምትናገረው ውዴ፣ በማዕከሉ የምግብ፣ የመጠለያና የአልባሳት ድጋፍ ታገኛለች፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የእጅ ሥራ ሙያዎችን እንደ ዳንቴል፣ ስፌት፣ የጥጥ ፈትልና የመሳሰሉ ሥልጠናዎችን በመሠልጠን ላይ ትገኛለች፡፡

ለችግር እጅ የማይሰጡ፣ የማይበገሩ ጠንካራ ሴት እንዲሆኑና ራሳቸውን ችለው በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ በማዕከሉ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እንደሚሰጣቸው ፣የማዕከል ቆይታዋ ሲጠናቀቅ የራሷን ቁርስ ቤት በመክፈት ወደ ቀደመ ሥራዋ ለመመለስና ከቀድሞ በተሻለ መልኩ ሥራዋን ለማከናወን የአዕምሮ ዝግጅት ማድረጓን ትናገራለች፡፡

ዝናሽ ጌታቸው ባሏ እርጉዝ መሆኗን ሲያውቅ ጥሏት የጠፋና በእርግዝናዋ ምክንያት በብዙ ችግር ውስጥ ያለፈች ሌላዋ ሴት ነች፡፡ ዝናሽ ጥሩ ገቢ ያለው ሥራ ለማግኘትና የተሻለ ሕይወት ለመኖር ከወለጋ አዲስ አበባ በመምጣት በተለያዩ ሥራዎች በመሰማራት ኑሮዋን ስትገፋ ቆይታለች፡፡

በሥራ አጋጣሚ ከተዋወቀችው ሰው ጋርም ትዳር መስርታ እየኖረች ነበር፡፡ እርግዝና ሲከሰት ግን ባል ቤቱን ጥሎ ጠፋ፡፡ ከዚህ ክስተት በኋላ ሕይወት ለዝናሽ እጅግ ፈታኝና በመከራ የተሞላች ሆነች፡፡

ክትትል በምታደርግበት ጤና ጣቢያ በሆዷ ‹‹መንታ›› ልጆች እንዳሉ ሲነገራት ያለ አባትና ያለምንም ገቢ ልጆቿን ምን እንደምታደርጋቸው በማሰብ መጪዎቹ ጊዜያት ከወዲሁ ያስፈሯት ጀመር፡፡

ቀን ቀንን እየተካ ሆዷም እየገፋ ሲመጣ ሥራ መሥራት ተሳናት፡፡ የቤት ኪራይ ለመክፈል እጅ ሲያጥር ጓደኞቿ እየተጋገዙ እጠሸፈኑላት የመውለጃዋ ቀን ደረሰ፡፡ በአበበች ጎበና የእናቶችና ሕጻናት ሆስፒታልም ወንድና ሴት መንታ ልጆችን በቀዶ ሕክምና ተገላገለች፡፡

‹‹በእርግዝናዬ ወቅት የምበላውንና የምጠጣውን ቢያንስም ቢበዛም ጓደኞቼ ያመጡልኝ ነበር፣ ከወለድኩ በኋላ ግን ከእርግዝናዬ ወራት በባሰ መልኩ ሰማይ የተደፋብኝ መሰለኝ›› የምትለው ዝናሽ ‹‹ይህ ሁሉ መከራ በእኔ ላይ ስለምን ሆነ›› በማለት ፈጣሪን እስከመጣላት ደረስኩኝ ትላለች፡፡

በቀዶ ሕክምና ከወለደች በኋላ ልጆቹ ማሞቂያ ክፍል ኦክስጅን እየተሰጣቸው ለ15 ቀናት ቆይተዋል፡፡ በእነዚህ ቀናት የሚጠይቃትና የሚንከባከባት ሰው ባለመኖሩ በሆስፒታሉ በቆየችባቸው ሦስት ሳምንታት ሆስፒታሉ አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ሲነከባከባት መቆየቱን ታክላለች፡፡

‹‹ከሆስፒታሉ ከወጣሁ ምንድነው የምሆነው? ዕጣዬ ጎዳና ላይ መውደቅ ነው ብዬ? በተጨነኩበት ወቅት፣ በሆስፒታሉ የምታገለግል ትዕግሥት የተባለች ዶ/ር ችግሬን በመዳት የአምላክ ልጆች ከተባለ ድርጅት ጋር አገናኘችን፡፡ እኔንም ከጭንቀትና ከመከራ አሳረፈችኝ፤ ከጨለማ ወደ ብርሃንም መራችኝ›› ስትል ትናገራለች፡፡

ወደ ድርጅቱ ከመጣች አራት ወራት እንደተቆጠረ የምትናገረው ዝናሽ፣ ድርጅቱ እንደ እናት አባት በመሆን እየተንከባከበ እንዳረሳትና ለእሷና ለመንታ ልጇቿ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ሁሉ እያደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግራለች፡፡

በማዕከሉ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እየወሰደች እንደምትገኝ፣ ‹‹እነዚህን ልጆች በሆዴ የፈጠረ አምላክ ለእኔና ለልጆቼ መሆን አያቅተውም፡፡ የማዕከል ቆይታዬን ሳጠናቅቅ በማዕከሉ ባገኘሁት ሥልጠና በመታገዝ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች በመሰማራት ልጆቼን ተንከባክቤ አሳድጋለሁ፡፡ ለዚህም የሚሆን የሞራል ጥንካሬ አግኝቻለሁ›› ብላለች፡፡

አቶ መልካሙ ዱንፋ የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ድርጅቱ ሐምሌ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. የተመሠረተ ሲሆን፣ የሚሠራውም በወላድ እናቶች ዙሪያ ነው፡፡

ድርጅቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የመንግሥት ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ባለው የሥራ ግንኙነት ያለምንም ቅድመ ዝግጅት ለሚወልዱና አቅምና ረዳት ለሌላቸው እናቶች ‹‹ማማ ሻንጣ›› በማስቀመጥ ወደዚህ ዓለም የሚመጡ ሕፃናትን በክብር ይቀበላል፡፡

አንዲት ደሃ እናት ነፃ የወሊድ ክትትል የምታደርገውና የምትወልደው በመግሥት የጤና ተቋም ነው፡፡ በመሆኑም ድርጅቱ ከእነዚህ ተቋማት ጋር በመቀናጀት ያለምንም ዝግጅት የሚወልዱ እናቶች እንዲስተናገዱ በተቋማቱ ውስጥ ማማ ሻንጣ ያስቀምጣል፡፡

 አንዳንድ ወላድ እናቶች በቤታቸው ሌሎች ተጨማሪ ልጆች ያሏቸውና አቅም የሌላቸው  ከማማ ሻንጣ ጋር በክብር ወደ ቤታቸው የሚሸኙ ይሆናል፡፡ ከዚህ ባለፈ ምንም ዓይነት መጠለያና የሚረዳቸው የሌላቸው እናቶች ወደ ማዕከሉ ይላካሉ፡፡

እነኚህ እናቶች ከወለዱበት ጤና ተቋም ወደ ‹‹የአራስ ቤት›› የሚመጡት በአምቡላንስ ነው፡፡ እናቲቱ መቼ እንደወለች፣ የልጇ ፆታ፣ የልጇ ክብደት፣ የእርሷ የጤና ሁኔታ፣ የወለደችው በቀዶ ሕክምና ነው ወይስ በተፈጥሮ የሚለውንና የመሳሰለውን ሁኔታ የያዘ ደብዳቤ የጤና ተቋሙ አዘጋጅቶ ከእናቷ ጋር ወደ ፋውንዴሽኑ ይልካል፡፡

አንዲት እናት ከወለደችበት ጤና ተቋም ወደ ማዕከሉ ‹‹አራስ ቤት›› ስትመጣ እናቶች በእልልታ እንዲቀበሏት ይደረጋል፡፡ በእርግዝናና በወሊድ ወቅት ከገባችበት ተስፋ መቁረጥ  እንድትወጣ፣  ነገዋ ብሩህ መሆኑን ለማሳየት ድባቡ አመቺ ይደረጋል፡፡

የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ወደ ማዕከሉ የመጡ ወላዶችን ‹‹በአራስ ቤቱ›› በአጥሚት፣ በገንፎና በተለያዩ አቅም በፈቀደ ሁሉ እንዲታረሱ የሚያደርግ ነው፡፡ በማዕከሉ የአራስነት ጊዜያቸውን ላጠናቀቁ እናቶች በምግብ ዝግጅት በሕፃናት እንክብካቤ፣ በእጅ ሥራ ሙያ በንግድ ሥራ በመሳሰሉ የሙያ ዘርፎች የአምስት ወራት ሥልጠና እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡

እንደ አቶ መልካሙ፣ እንዲት እናት በማዕከሉ የምትቆየው ለስድስት ወራት ነው፡፡ ይህም የሚሆነው ሕፃኑ ለስድስት ወር ያህል የእናት ጡት እንዲጠባና እናቲቱ ጤናማ ልጅ እንዲኖራት ለማስቻል ነው፡፡ ከስድስት ወር የማዕከል ቆይታዋ በኋላ አንዲት እናትን የሚቻል ከሆነ ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትቀላል የማስታረቅ ሥራ ይሠራል፡፡

በኢትዮጵያ ባህል ያለ ሕጋዊ ባል የወለች እናትን ባህሉ ስለማያስተናግድ በሽምግልና የማስታረቅ ሥራ ይሞከራል፡፡ ይህ ካልተሳካ የተለያዩ የልጆች ማሰደጊያ ካላቸው ድርጅቶች ጋር የማገናኘት ሥራ ይሠራል፡፡ በዚህም ካልተቻለ በፅዳት፣ በቤት ሠራተኝነትና በልዩ ልዩ ሥራዎች እንዲቀጠሩ ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኙ ይደረጋል፡፡

እነኚሁ ሁሉ አማራጮች ተሞክረው ያልተሳኩ ከሆነ ድርጅቱ የሦስት ወር የቤት ኪራይ፣ የሦስት ወር ቀለብ፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት በተለያዩ የገቢ ምንጮች ተሰማርተው ራሳቸውን እንዲችሉ አምስት ሺሕ ብር በመስጠት እንዲቋቋሙ ያደርጋል፡፡

እንደ አቶ መልካሙ፣ የአምላክ ልጆች ፋውንዴሽን ከምሥረታው ጀምሮ 164 እናቶችንና 167 ጨቅላ ሕፃናትን በማዕከሉ ‹‹የአራስ ቤት›› በእንክብካቤ አስተናግዷል፡፡ ድርጅቱ ራሱን የሚደጉምበት በፕሮጀክት ደረጃ የሚያገኘው ምንም ፈንድ የለውም፡፡ በመንግሥት ደረጃም ድጋፍ የሚደረግላት ተቋም አይደለም፡፡ የድርጅቱ የገቢ ምንጭና የሚንቀሳቀሰው ደጋግ ኢትዮጵያውያን በሚለግሱት ገንዘብ ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ድርጅቱ በከፍተኛ ደረጃ በገንዘብ እጥረት እየተፈተነ ይገኛል፡፡ ለቤት ኪራይ ዋጋ በመናሩ በወር 130 ሺሕ ብር ለመክፈል ተገደዋል፡፡ የአስቤዛ ዋጋውም ቁጥራቸው እየጨመረ ከመጣውና ወደ ማዕከሉ ከሚገቡ እናቶች ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ ችግር የሆነባቸው መሆኑን አቶ መልካሙ ይናገራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...