Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልከ‹እብድ ሐሙስ› እስከ ‹አዳም ሐሙስ›

ከ‹እብድ ሐሙስ› እስከ ‹አዳም ሐሙስ›

ቀን:

ዘንድሮ የፋሲካ በዓል ሚያዝያ 27 ቀን የዋለ ሲሆን፣ በዓሉ እስከዛሬው እሑድ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ ሃይማኖቱን ከባህልና ትውፊቱ ጋር አስተሳስሮ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ‹ሳይጾሙ ፋሲካ ሳያዝኑ ደስታ የለም› እንዲሉ ከፋሲካው የተደረሰው ከ55 ቀኖች ዓቢይ ጾም (ሁዳዴ) በኋላ ነው፡፡ ጾሙ ከመያዙ በፊት ያለው የመጨረሻው ሐሙስ በአገራዊው ትውፊት ‹‹እብድ ሐሙስ›› ይባላል፡፡ የብሎት ድግሱ ቅበላው ጥድፊያ አለበትና፡፡

ከ‹እብድ ሐሙስ› እስከ ‹አዳም ሐሙስ› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የሸውላለ ጨዋታ በትግራይ

ፋሲካው በዋለ በአምስተኛው ቀን የሚመጣው ሐሙስ የተለየ መጠርያ አለው፡፡ ‹‹አዳም ሐሙስ›› ይሰኛል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር አዳምን ከአምስት ቀን ተኩል በኋላ ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ፤›› ብሎ በገባለት ቃል ኪዳን መሠረት 5500 ዘመን ሲፈጸም፣ ታኅሣሥ 29 ቀን 5501 ከእግዚእትነ ማርያም ድንግል ተወልዶ በ5534 ዓመተ ዓለም (መጋቢት 27 ቀን 34 ዓ.ም.) ተሰቅሎ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷል፡፡

ይህንኑ ለማዘከር በየዓመቱ ፋሲካ በዋለ በ5ኛዋ ቀን አዳም ሐሙስ ተብሎ ይከበራል፡፡ ዘንድሮ ከግንቦት 1 ቀን የልደታ ማርያም ጋር በመጋጠሙ ልዩ ድባብ ፈጥሮለታል፡፡

- Advertisement -

‹‹በሰሞነ ፋሲካ የአዳም ዕለት (በአዳም ሐሙስ) ልጆች የሚያዜሙት  ዜማ የት ደረሰ?!›› ብለው የሚጠይቁት አቶ ዘላለም ጌጡ የጎንደር የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት የቤተ መጻሕፍትና መዛግብት ቡድን መሪ ናቸው፡፡

አቶ ዘላለም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕለቱ ከሰሞነ ፋሲካ ዕለታት ጋር ስለሚዘከር አይረሳም። ‹‹ለአባታችን አዳም የተገባው የተስፋ ቃል በዕለተ ዓርብ በስቅለቱ የተፈጸመ ሲሆን በሰሙነ ፋሲካ ዕለታት ከትንሣኤ ዕለት ጀምሮ ሲቆጠር አምስተኛው ቀን ሐሙስ ደግሞ የአዳም ሐሙስ መባሉን አባቶች ያስረዳሉ፤›› ይላሉ።

  በሌላ በኩል እምነቱን መሠረት ያደረገ ባህላዊ ክዋኔ ከድሮ ጀምሮ ይከናወን የነበረው  በብዙ አካባቢ እየተዘነጋ መምጣቱን ያወሳሉ። ከ35 ዓመታት በፊት እሳቸው ተሳታፊ የነበሩበትን ጨዋታውን እንዲህ አስታውሰውታል፡፡

  ‹‹ እናምናለን ትንሣኤውን፣

   በሥልጣኑም መነሣቱን፣

   አርአያ ነው ለሁላችን። 

  ኦኦ ስላዳም ስላዳም 

   ሚስቴ ወልዳብኝ 

    ቋንጣና ቅቤ ብላብኝ።

    የአዳም ሐሙስ ይሄ ዕለት፣

    አይመጣም ካለዓመት፡፡›

ትውስታቸውንም ሲያጋሩ ‹‹ለማስታወስ ሞከርኩ፣ የቃል ግጥሙ ግን እየጠፋኝ ነው። ትዝ የሚለኝ በስቅለት ዕለት ሙሻሙሾ እንደሚባለው ዱላ አይያዝም፣ ዱቄትም አይጠየቅም፣ ግጥሞቹ ቀየር ይሉና በዜማ ከሙሻሙሾ ጋር ተመሳስለው ይዜማሉ። ሙሻሙሾው ሕማማት በመሆኑ በዝግታ ሲባል ስለአዳም ደግሞ ደመቅ ይል ነበር። እንዲያውም ‘ቋጫ መሰልቀጫ’ የሚለው ስንኝ ከስለ አዳም ወደ ሙሻሙሾ የገባ ይመስለኛል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

‹‹በስለ አዳም የተሰበሰበውን ቋንጣና ቅቤ ከመረጥነው ከአንዱ ቤት ታላላቆች ጠባብሰው ያቀርቡልንና  ታላላቆች በሰሞነ ፋሲካ እንደሚጠራሩት፣ እኛም ሌሎች ልጆችን እንጠራራና ተሰባስበን በፍቅር እንበላ ነበር፤›› ያሉት አቶ ዘላለም፣ ይህን ክዋኔ ለብዙ ዓመታት አይቼው አላውቅምና ትኩረት ይሰጠው ይላሉ።

‹‹አዳም ሐሙስስ የዘመኑ ልጆች ይከውኑት ይሆን?›› የሚሉትም ጠቀሜታውን በመግለጽ ጭምር ነው፡፡ ‹‹ክዋኔው ለሕፃናት ከማዜም እና ከመብላት ያለፈ ጥቅም አለው። አብሮነትን፣ ትንሣኤ ማሰብ፣ ስለፍጥረትና ፈጣሪ ለመጠየቅ ለማወቅም ቀስቃሽ ነበር።›› 

በላሊበላ ከተማም የፋሲካ በዓል ሳምንቱን ሲከበር ከሚከወኑ ድርጊቶች አንዱ፣ የአካባቢው ልጃገረዶች የሚጫወቱት ሹላሌ የተሰኘ ጨዋታ ነው፡፡ እንደ መምህር ዓለሙ ኃይሌ አገላለጽ፣ ሹላሌ ከትልቅ ዛፍ ላይ ጠፍር ታስሮ ልጃገረዷ በጠፍሩ ላይ ተቀምጣ የምትጫወተው ነው፡፡ ሌሎች እየገፏት እየዘፈኑ ዥዋዥዌውን ይጫወታሉ፡፡

 ሹላሌ የተሰኘው ጨዋታ ከፋሲካ (ትንሣኤ) እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ልጃገረዶቹ በጠፍር ላይ ሆነው መወዛወዛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዶች የክስ አደባባይ ከሔሮድስ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ እንደገና ወደ ሔሮድስ መመለሳቸውን ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ በሚኖረው ጨዋታ ዝማሬም ያለ ነው፡፡

‹‹አብ እየበደለኝ እያዘነ ሆዴ

ለወልድ እነግራለሁ ለሥጋ ዘመዴ

አብን ተዉትና ንገሩት ለወልድ

ተሰቅሏል ተገርፏል እርሱ ያውቃል ፍርድ፡፡››

የፋሲካ በዓል በተለይ ለወጣት ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች የተለየ ጊዜ በመሆኑ በምንጃሮች አጠራር ‹‹ሸንጎ›› ላይ በመውጣትና በመጫወት የሚተጫጩበት፣ ወጣት ወንዶችም የትግል ጨዋታ የሚጫወቱበትና አሸናፊና ተሸናፊ የሚባባሉበት፣ ‹‹እሽኬ›› የተባለውን ጨዋታ ይጫወቱበታል፡፡

በዓሉ የምቾት፣ የድሎትና የደስታ ጊዜ መሆኑን ለማመልከት ልጃገረዶች እንዲህ እያሉ ያዜማሉ ይላል፤ በሰሜን ሸዋ ላይ የተሠራው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ሰነድ፡፡

 ‹‹አወይ ፋሲካ ኮበለለ

 የሽሮ ቅሉን እያንከባለለ

 አወይ ፋሲካ ጀግናው

       ሥጋ እንደጎመን የሚበላው

       አወይ ፋሲካ የተውሶ

       ይሄዳል ተመልሶ

የፋሲካ ዕለት እነማዬ ቤት እነአባዬ ቤት

ያለ ደስታ ያለ ድሎት

የስንዴ ቆሎ በገበታ

       አወይ ፋሲካ የኛ ጌታ››

እያሉ በዘፈኖቻቸው ይገልጻሉ፡፡

ቀሲስ ሰሎሞን ወንድሙ መታፈሪያ ‹‹ሰሙን ቅድስት›› በሚባለው መጽሐፋቸው በሰሜናዊው የኢትዮጵያ አካባቢ ከዓርብ ስቅለት ጋር የተያያዙ ጨዋታዎችን ገልጸዋል፡፡ 

በትግራይ በዕለተ ዓርብ ልጃገረዶች ስቅለቱን በማሰብ ሁለት ድንጋዮችን እርስ በርስ እያጋጩ ይዘምራሉ፡፡ በቤተ ክርስቲያን ወይም በአካባቢያቸው በሚገኝ ዛፍ ላይ የመጫኛ ገመድ በማሰርም እንዲህ ይጫወታሉ፡-

‹‹ሸው ሸውላለ

ሓሙስ ጽጎ

ኢፍ እኳ ትጸግቦ

ዓርቢ ስቕለት

ልበይ ተሰቕለት

ቐዳም ስዑር

ኢፍ እኳ ትስዕር››

(በጸሎተ ሐሙስ ወፍ እንኳ ትጠግባለች፣ በዓርብ ስቅለት ልቤ ተሰቀለች፣ በቅዳሜ ስዑር ወፍ እንኳ ትሽራለች)፡፡

ይኸው የልጃገረዶች ጨዋታ በሰቆጣ አካባቢ እሸውላሌ ተብሎ ይጠራል፡፡ ልጃገረዶቹ ዥዋዥዌ የሚጫወቱት እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የደረሰበትን የመከራ ዓይነት መውደቅ መነሣቱትን፣ ወደ ፊት ወደኋላ መጎተቱን በመሳብ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...