Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ጥቅምና ተግዳሮት

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

መንግሥት የኢንዱስትሪ ዘርፍ ችግሮችን ለማቃለል እየተገበራቸው ከሚገኙ የመፍትሔ ዕርምጃዎች መካከል፣ ከአንድ ዓመት በፊት ይፋ የተደረገው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገራዊ ንቅናቄው ዋና ዓላማዎች የአምራች ኢንዱስትሪውን ችግር በጋራ በመፍታት ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ መዋቅር ሽግግር የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲወጣ ማስቻል፣ እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሥራ ባህል ማሻሻል፣ የኢንዱስትሪ ምርቶችን ጥራትና ተወዳዳሪነት በማሻሻል ገቢ ምርቶችን የመተካት ሽፋንን ማሳደግ ናቸው፡፡ ንቅናቄው የአምራች እንዲስትሪዎች ምርትና ምርታማነት ለመጨመር፣ የዘረፉን ልማት ለመደገፍ አምራች ኢንዱስትሪዎችን በጥራትና በቁጥጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ተግባራት የሚከናወንበት መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ከተለመደው አሠራር በማሻገር ምርታማነትን ለመጨመር እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪዎች ለአገር ውስጥ ምርት ዕድገት እያበረከቱ ያለውን አነስተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያሳድግም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ንቅናቄው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኢንዱስትሪ ምርቶችን አምርቶ ለመሸጥ እንዲሁም ከውጭ የሚገቡ የኢንዱስትሪ ግብዓቶችን በአገር ውስጥ ለመተካትና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍ የምታደርገውን ጥረት ወደ ወሳኝ ምዕራፍ የሚያሸጋግር ተግባር ነው፡፡ አገሪቱ ያላትን ትልቅ የዘርፉን ዕምቅ ሀብት በአግባቡ ለመጠቀም ይቻል ዘንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ተሞክሮዎችን በመጠቀም የተጀመረው የ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ንቅናቄ ዋና ዋና ምሰሶዎች ባለድርሻ አካላትን ማሳተፍ፣ ዘርፉን በጥናትና በምርምር መደገፍ እንዲሁም ለዘርፉ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ማድረግና የአገር በቀል ምርቶችን አመራረት ማሳደግ ናቸው፡፡ በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፉ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር የዘርፉን የማምረት አቅም ማሳደግ ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የውጭ ምንዛሪ ግንኘትን ማሳደግና ገቢ ምርቶችን በአገር ውስጥ በመተካት የወጭ ምንዛሪን ማዳን ከመርሐ ግብሩ የሚጠበቁ ውጤቶች ናቸው፡፡

በዚህ መሠረት እነዚህንም ውጤቶች ለማሳደግ ዘንድሮ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› አገራዊ ንቅናቄ የተጀመረበትን ሁለተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከግንቦት 1 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚቆይ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ እያካሄደ ነው፡፡

ሐሙስ ግንቦት 1 ቀን 2016 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአገር ውስጥ አምራቾች በመደገፍና የአገር ውስጥ ምርትን በመጠበቅ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ያገኘናቸውን ውጤቶች ይበልጥ ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን መሠረት በማድረግ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለኢንዱስትሪ የሆነ እምቅ አቅም እንዳላት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች በግብዓት፣ በገበያ እንዲሁም በሰው ኃይል ኢትዮጵያ ያላትን አቅም በተሻለ ሁኔታ በመለወጥ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት የቡና ምርት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ጠቅሰው በዓለም ላይ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አምራች አገሮች ከሚያገኙት ገቢ ይልቅ ቡናና ወተትን ቀላቅለው ሌላ ምርት የሚያመርቱ አገሮች ከኢትዮጵያ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የተለያዩ ግብዓቶችን ቀላቅለው ምርት ማምረት ባለመቻላቸው የተነሳ ዘርፉ በከፊልም ቢሆን መጎዳቱን ገልጸው በቀጣይ በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን ስኬት መሸከም የሚችል የኢንዱስትሪ ልማት መገንባት ይገባል ብለዋል፡፡

ባለፉት በርካታ ዓመታት የሻይ እርሻ ከሦስት ሺሕ ሔክታር ያላለፈ የእርሻ መሬት እንደነበረ፣ በዚህም የእርሻ መሬት ላይ የተመረተው ምርት ከሞላ ጎደል የአገር ውስጥ ፍጆታን ይሸፍን እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ አሻራ ሰላሳ ሺሕ የእርሻ ቦታዎችን መንግሥት እያስፋፋ መሆኑን ገልጸው፣ በፍጥነት ኢንዱስትሪዎች የሻይ ምርትን ማምረት ካልቻሉ ይኼ ሁሉ ኢንቨስትመንት ያለ አግባብ የሚባክን ይሆናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ኢንቨስትመንት ለማሳደግ አንድ ፋብሪካ ብቻ በቂ አለመሆኑንና አሥር ወይም ሃያ ፋብሪካዎች መገንባት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንንም ማድረግ ከተቻለ በአፍሪካ ደረጃ ትልቅ ኤክስፖርት ማድረግ ከሚችሉ አገሮች መካከል አንደኛው መሆን እንችላለን ብለዋል፡፡

ከሻይ፣ ከቡናና ከስንዴ በተጨማሪ የሩዝ ምርት ሲታይ ከባለፈው ዓመት የተሻለ እንደሆነ ጠቅሰው ኢንዱስትሪ ካልተዘጋጀ በስተቀር በግብርና ዘርፍ የመጡ ውጤቶችን በአገር ደረጃ ለምናስበው የብልፅግና ጉዞ በቂ ውጤት ማምጣት እንደማይቻል ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

በተለይ ከሁለት ወይም ከሦስት ወራት በኋላ በግብርናውም ከፍተኛ ምርት እንደሚገኝ ነገር ግን ይኼን ምርት ለመጠቀም የኢንዱስትሪዎች አቅም ዝቅተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል የተመረቱ ምርቶችን ወደ ገበያ ከማውጣት አንፃር እየተሠራ እንደሚገኝና አምስት ወይም ስድስት አገሮች ተደምረው የኢትዮጵያን ገበያ የማይበልጡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በፖሊሲ፣ በአሠራር፣ በፋይናንስ አቅርቦት መንግሥት ሊወስዳቸው የሚገቡ ዕርምጃዎች እንዳሉና ወሳኝ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ከሕግና ከፖሊሱ አንፃር የተደረጉ ዕርምጃዎች በጣም ሰፋፊ እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

እነዚህ ሁሉ ነገሮች ሲፈጠሩ ኢንዱስትሪዎች መዘጋጀት እንደሚኖርባቸው ገልጸው በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ተደምረው የኢትዮጵያን ጂዲፒ እንደማያክሉ፣ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እያደገች ያለች አገር መሆኗን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአዲስ አበባ አሁን እየተደረገ ያለው የኮሪደር ልማትን የትኛውም የአፍሪካ አገር ሊያደርገው የማይችል እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በዘንድሮ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት እኛ እንሸልም›› በሚል መሪ ቃል 83 የምርት ማስታወቂያ ኤክስፖ መካሄዱን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፉን ማነቃቃት እንደተቻለ ገልጸው የዘንድሮ ዓመት ኢትዮጵያ ታምርት ኤክስፖ ከዚህ በፊት ከተከናወነው ኤክስፖ ለየት እንደሚያደርገውና ዓለም አቀፍ ይዘቶችን ይዞ የቀረበ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በኤክስፖው ከ130 በላይ ትልልቅ አምራች ኢንዱስትሪዎች የተሳተፉ ሲሆን ከ80 በላይ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተፕራይዞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

በኤክስፖውም 50 የውጭ ባለሀብቶች የተሳተፉ ሲሆን ከ600 በላይ የንግድና ኢንቨስትመንት ትስስሮችን በመፍጠር ከሦስት ቢሊዮን በላይ ግብይት ይፈጠራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. 25 ምርቶች ለማስታወቅ የተጀመረው የንቅናቄ መርሐ ግብር በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ዕድገትን ማስመዘግቡን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ በ2015 ዓ.ም. 117 ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ማስተዋዋቅ ችለዋል ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የኩባንያዎች ቁጥር ወደ 210 ማደጉን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት መንግሥት ለአምራች ዘርፉ ዕድገት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳዩ ነገሮችን ማከናወን እንደቻለ አስረድተዋል፡፡

በተለይ ከ22 በላይ የሆኑ የጋርመንት ኢንዱስትሪዎች እስትራቴጂ በማሻሻል ዘርፉ ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል የሚሉት ሚኒስትሩ፣ ዘርፉንም ለመደገፍ አዳዲስ ፖሊሲዎችን መዘርጋት እንደተቻለ ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስመጣቸውን ምርቶች በአገር ወስጥ ለመተካት የሚያስችል የተኪ ምርት እስትራቴጂ ፀድቆ ወደ ሥራ እንዲገባ የተደረገ ሲሆን፣ በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራ ብቻ ከ1.9 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጡ ምርቶችን ከመተካት ባለፈ አንዳንድ ምርቶችን ኤክስፖርት ማድረግ እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የገበያ ድርሻ ለማሳደግ የመንግሥት ተቋማት ከአገር ውስጥ አምራቾች እንዲገዙ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እስከ ኢንጂነሪንግ ውጤቶች ለአገር ውስጥ ማቅረብ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶባቸው የገነባቸውና ለውጭ ባለሀብቶች ብቻ ተደርገው የነበሩ ኢንዱስትሪያል ፓርኮች ለአገር ውስጥ ባለሀብቶች ክፍት እንዲሆኑ በመደረጉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ፓርኩ የገቡ ኢትዮጵያውያን ድርጅቶች ድርሻ 53 በመቶ በላይ መሆን ችሏል፡፡

በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚመረቱ ምርቶች ለውጭ ገበያ ብቻ ያቀርቡ የነበሩ ኩባንያዎች እንደየ ምርቱ ዓይነት ከ50 እስከ 100 በመቶ ወደ አገር ውስጥ ገበያ ገብተው እንዲሸጡ በመደረጉ፣ በጥሬ ዕቃ ሲቸገሩ የነበሩ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎች ግብዓት ማቃለል እንደተቻለ አክለው ገልጸዋል፡፡

በተለይ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከዚህ በፊት ይቀርብ ከነበረው አጠቃላይ 12 በመቶ ድርሻ ወደ ሃይ አራት በመቶ እንዲያድግ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ሥራ አቁመው የነበሩ 395 ኢንዱስትሪዎች ውስጥ 217 ወደ ሥራ እንዲመለሱ የተደረገ ሲሆን የአምራች ኢንዱስትሪ የማምረት አቅምና አጠቃቀም በ2013 ዓ.ም. ከነበረው 47 በመቶ፣ በ2016 ዓ.ም. አጋማሽ ወደ 56 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደተቻለ ጠቁመዋል፡፡

የኢንዱስትሪን ምርት በተመለከተ ከ2013 ዓ.ም. ከነበረበት 36 በመቶ ድርሻ የአገር ውስጥ ምርት በዚህ ዓመት አጋማሽ 39 በመቶ ማሳደግ መቻሉን አስረድተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን እዚሁ አገር ውስጥ በማምረት የገበያ ትስስር መፍጠር ቀጥሏል፣ ያሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የዶንግ ፋንግ ቴክስታይል አምራች ድርጅት ማናጀር ናቸው፡፡

ተቋሙ የተለያዩ አልባሳቶችን በማቅረብ የኢንዱስትሪው ዕድገት ከፍ እንዲል ካደረጉ ተቋማት መካከል አንዱ ነው የሚሉት ማናጀሩ የተማሪዎች ዩኒፎርም፣ የፌደራል ፖሊሱ አልባሳትና የመከላከያ ሠራዊት አልባሳትን በማቅረብ የተሻለ አገልግሎት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ አክለው ገልጸዋል፡፡

ከ2015 ዓ.ም. ጀምሮ 300 ሺሕ የመከላከያ ሠራዊት አልባሳትን እንዳቀረበ ገልጸው እንደ አገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት ባይከሰት ኖሮ የተለያዩ ምርቶችን ለመንግሥት ተቋማት ማቅረብ እንደሚቻል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ደረጃውን የጠበቀ ምርት ለመግዛት ፍላጎት እንዳለው የጠቀሱት ማናጀሩ፣ የሰውን ፍላጎት ለማሟላት ከሽመና ጀምሮ ምርቱ ተጠናቆ ለገበያ እስኪቀርብ ድረስ ጥንቃቄ በተሞላ መልኩ እንደሚሠራ አስታውቀዋል፡፡

በተለይ ሁልጊዜ የደንበኛን ፍላጎት ለማሟላት ተቋሙ የተሻለ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸው በቅርቡም ከ100 ሺሕ በላይ የፌዴራል ፖሊስ የሚለብሱትን አልባሳት ለማምረት ከተቋሙ ጋር ውል ማሰራቸውን ተናግረዋል፡፡

መንግሥት ምርቶችን እዚሁ አምርቶ ከማቅረብ ይልቅ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን ማቅረብ እንደ አማራጭ እንደሚጠቀምና ይኼም የውጭ ምንዛሪ እንደሚያሳጣ አብራርተዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች