Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ከጊዜው ጋር እንዲራመዱ ምን ይደረግ? በሚለው ወሳኝ ጉዳይ ላይ በርካታ የመፍትሔ ሐሳቦች ሲቀርቡበትም ነበር፡፡ ሰሞኑን የተካሄደው ሰባተኛው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት የመጪ ጊዜ መዳረሻቸው ምን ሊሆን እንደሚችል አመላካች የሆኑ ጽሑፎች ቀርበውበታል፡፡ ለሰባት ተከታታይ ዓመታት በዚህ መድረክ የተነሱ ሐሳቦች ምን ውጤት አገኙ ከሚለው ጥያቄ በመነሳት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸው የተወዳዳሪነት አቅም፣ እንዲሁም ሊያጋጥሙት በሚችሉ ተግዳሮቶችና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ ከምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ አዘጋጅና የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው አጭር ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቋማችሁ ለተከታታይ ዓመታት የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔዎችን በማዘጋጀት በርካታ የፋይናንስ ባለሙያዎች ጥናታዊ ጽሑፎች ሲያቀርቡ ይታወቃል፡፡ ወቅታዊ አጀንዳዎችን በመምረጥ የተለየ ዘርፎች ተዋንያን ሙግት ሲያቀርቡ  ይታያል፡፡ እንዲህ ያለው መድረክ በአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ምን ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል? ከዚህ መድረክ የተገኙ ሐሳቦችን የፖሊሲ አውጪዎች ወስደው እንዲለወጥ ያደረጉት ነገር አለ?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- ተቋማችን እንደ መድረክ ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች በተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ተዋንያን ከተለያዩ ማዕዘናት እየተመከረባቸው በጋራ ቅርፅ እንዲይዙ  ይደረጋል፡፡ የኢትዮጵያም ሆነ የአካባቢያችን የፋይናንስ ኢኮ ሲስተም ምን ሊሆን ይችላል? እንዴት ዓይነት ቅርፅ ይኑረው የሚለው፣ በፖሊሲ አውጪዎችና በዘርፉ ቁልፍ ተዋንያን መካከል ምክክርና ንግግር ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ እንዲህ ካለው መድረክም ነው ግብዓት መወሰድ ያለበት፡፡ መድረኩ ለዚህ ሲስተም ግንባታ የራሱን አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በርካታ ዕይታዎች አሉ፡፡ በግጭቶች ላይ መሠረት አድርገው ሊሆን ይችላል፣ በተለያዩ ውድድሮች ላይ ተመሥርተው ሊሆን ይችላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀጥታ በፋይናንስ ዘርፉ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ ክስተቶች እየተፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ ውይይቶች እየተካሄዱ ነው፡፡ ለምሳሌ የብሪክስ ጉዳይ አንዱ ነው፡፡ በዚህም ከዲዶላራይዜሽን፣ ከግጭቶችና ከማዕቀቦች ጋር የተያያዙ በርካታ አጀንዳዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የእኛንም የፋይናንስ ዘርፍ ይመለከታሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ምን ማለት ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ የመረጠችው የብሪክስ አባልነት የሚያስከትለው ምንድነው? በአካባቢው አገሮች እየተካሄዱ ያሉ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ስምምነት፣ የምሥራቅ አፍሪካ ኮሙዩኒቲና የመሳሰሉትን አገሮች አባል እየሆኑ ነው፡፡ ይህ ሒደት ፋይናንስ ዘርፉ በምን ዓይነት መንገድ እንዲዘጋጅ ያደርገዋል ለሚለው ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ይከፈት ሲባል ምንድነው ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው? የእኛስ አገር የፋይናንስ ተቋማት መወዳደር ይችላሉ ወይ? ተዋንያኑ ለውድድር ተዘጋጅተዋል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች እኛ በምናዘጋጀው መድረክ ላይ ሲመከርባቸው ቆይቷል፡፡ ሕግ ይውጣ ወይም ፖሊሲ ይኑር ብቻ ሳይሆን ፖሊሲ ተለዋዋጭ ሲሆን አብሮ መሮጥ የሚችል ተቋም አለ ወይ? ስለዚህ አብሮ መሮጥ እንዲቻል ዘርፉን ማነቃቃት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የሚባሉ ጉዳዮች ላይ እንዲመከር በማድረግ ያደረጋችሁት ጥረት ምን ውጤት አስገኝቷል ማለት ይቻላል? በዚህ መድረክ የሚቀርቡ ግብዓቶችን ፖሊሲ አውጪዎች ምን ያህል ተጠቅመውባቸዋል ማለት ይቻላል? በፖሊሲ ደረጃስ የተለወጠ ነገር አለ?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ እኛ መድረኩን ነው የምናመቻቸው፡፡ ሁሉም ግብዓቱን ከላይ እንዲወስድ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ምን ውጤት መጣ? ወይም ምን አስተዋጽኦ አደረገ? ለማለት አጀንዳው ከመጀመሪያ ጀምሮ መመልከት ያስፈልጋል፡፡ መጀመሪያ ላይ እንዲህ ያለውን መድረክ ስናዘጋጅ መነጋሪያ የነበሩ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ካፒታል ማርኬት ያስፈልጋታል? ወይስ ለካፒታል ገበያ ዝግጁ አይደለችም? የሚሉ ነበሩ፡፡ ከዚያ ላይ ተነስተን ካየነው ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ያስፈልጋታል የሚለው ተቀባይነት አግኝቶ፣ ውይይቱ ምን ዓይነት የካፒታል ገበያ ይኑረን ከሚለው በላይ ተሻግሯል፡፡ ዛሬ ምን ዓይነት ካፒታል ገበያ ይኑረን ብቻ ሳይሆን፣ ተዋንያኑ እነ ማን ይሁኑ የሚለው ላይ ተደርሷል፡፡ እንዴትስ ነው ውጤታማ የሚሆነው ላይ ነው የተደረሰው፡፡ ስለዚህ የመነጋሪያ ጉዳዩ ተቀይሯል ማለት ነው፡፡ መነጋገሪያ የነበረው የፋይናንስ ዘርፉ ጠንካራና ኢኖቬቲቭ መሆን ያልቻለው ተዘግቶ እርስ በራሱ ብቻ ስለሚሸላለም ነው የሚል ነበር፡፡ ዛሬ የምንናገረው ደግሞ እነ ማን ናቸው የሚመጡት? እንዴት እንዘጋጅ? እንዴት ጥሩ ተወዳዳሪ እንሁን? እንዋሀድ ወይ? ወይስ ሌላ የሚል አማራጭ አለ? የሚለው ላይ ነው፡፡ የኢንሹራንስን ከወሰድክ ደግሞ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ማደግ ያልቻለው ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ አካል ወይም ኮሚሽን ስለሌለው ነው የሚል ነበር፡፡

አሁን ደግሞ የኢንሹራንስ ዘርፉ የራሱ ተቆጣጣሪ ይኖረዋል የሚል ደረጃ ተደርሷል፡፡ አሁን የምንመክርበት ጉዳይም እንዴት ውጤታማ የሆነ ተቆጣጣሪ ይኑረን የሚለው ላይ ሊደርስ ችሏል፡፡ እንዲህ ባሉ የምክክርና የንግግር አጀንዳዎች ላይ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮች ተስተናግደዋል፡፡ ለምሳሌ ስለኢኖቬሽንና ቁጥጥር ክርክር ነበር፡፡ የክርክሩ መነሻ ‹‹ኢኖቬሽን›› ነው ወይስ ‹‹ሪጉሌሽን›› ነው የሚቀድመው? የሚል ነው፡፡ ሬጉሌሽን (ቁጥጥር) መቅደም አለበት የሚሉት የማናውቀው ነገር የአደጋ ሥጋት ይዞ ነው የሚመጣውና ዝም ብለን ልንለቀው አንችልም ነው የሚሉት፡፡ ኢኖቬሽን ይቀድማል የሚሉት ደግሞ የማታውቁትን ነገር እንዴት ሬጉሌት ታደርጋላችሁ? ኢኖቬሽን ማለት የማታውቁት ነገር ነው በማለት ተከራክረው ነበር፡፡ ዛሬ ስለመጣ ግን ብዙ ነገር ተለውጧል፡፡ እንዲያውም ሬጉሌሽኑ እየፈጠነ የፋይናንስ ዘርፉ መከተል እስኪሳነው ድረስ የሚመስል ነገር ነው የምናያው፡፡ ለዚህም ነው ለውጦች እየመጡ ያሉት፡፡ ስለዚህ ባካሄድናቸው ውይይቶች በቁጥር ለክተን ባናስቀምጠውም ያ የነበረው ንግግርና ምክክር ይህንን ተከትሎ ለዚህ ለውጥ አስተዋጽኦ አድርጎልናል ብለነው የምናምነው፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ዘርፉ ለደረሰበት ሥነ ምኅዳር ምክክሮቹ ወሳኝ ሚና ነበራቸው ብለን በእኛ በኩል እናምናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለተከታታይ ዓመታት ባዘጋጃችኋቸው የምክክርና የውይይት መድረኮች ከተሰበሰቡ መረጃዎች አንፃር ወይም ባደረጋችሁት ግምገማ፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ከአካባቢው አገሮች ጋር ሲነፃፀር አቅሙ የቱ ጋ ነው ያለው? ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት ደረጃ ላይ ነው ወይ?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- ይህንን ለማየት የአፍሪካ ምርጥ አንድ መቶ (ቶፕ ሃንድረድ) ባንኮች ተብለው የተዘረዘሩን በመመልከት፣ በዚህ ሰንጠረዥ ውስጥ ያሉ እነ ማን ናቸው ብሎ መጠየቅ ነው፡፡ ከእነዚህ አንድ መቶ የአፍሪካ ባንኮች ስንት የአገራችን ባንኮች አሉ? በስንተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ናቸው? የሚለውን ማየት ነው፡፡ ሁለተኛ የእኛ የፋይናንስ ተቋማት ያላቸውን የካፒታል አቅም በዶላር ስንመነዝረውና በአካባቢያችን ካሉ አገሮች ጋር ስናነፃፅረው የቱ ጋ ናቸው የሚለውን ምላሽ ሊሰጥ ይችላል፡፡ አንዱ መለኪያ የካፒታል አቅም ነው፡፡ ሌላው የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ነው፡፡ ለምሳሌ በሌላ አገር የምናገኛቸው ፋይናንሻል ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ፈጣን የፋይናንስ አገልግሎቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እያገኘን ነው ወይ የሚለውም ሌላው መወዳደሪያ ነው፡፡ ይህ ማለት የሌሎች አገሮች የፋይናንስ ተቋማት ኢትዮጵያ ቢገቡ በቀላሉ የሚተገብሯቸው ፕሮጀክቶችና አገልግሎቶች አሉዋቸው፡፡ ይዘው የሚመጡት የኮርፖሬት ገቨርናንስ፣ የአሠራር ሒደት፣ የቴክኖሎጂ አቅምና የመሳሰሉት ጉዳዮች አሉ፡፡ እነዚህን ስናይ ብዙ መሥራት አለብን፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያለውን ልዩነት ስናይ ተወዳዳሪ ለመሆን ብዙ የሚቀሩን ነገሮች አሉ፡፡ ተወዳዳሪነት ሲባል አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉንም እኩል ጨፍልቆ መወዳዳር አይችሉም ማለት አስቸጋሪ ነው፡፡ ግን በአብዛኛው እንዲህ ዓይነት ተወዳዳሪነትን የምትገልጸው በደረጃ አሰጣጥ ነው፡፡ በካፒታል አቅም፣ በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የአገልግሎት ዓይነቶች ታይተው ነው ደረጃ የምትሰጠው፡፡ እውነቱን ለመናገር ግን ከዚህ አንፃር የእኛ የፋይናንስ ዘርፍ ጥሩ ደረጃ ላይ አይደለም ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመድፈንና ጥሩ ተወዳዳሪ ለመሆን የፋይናንስ ተቋማትም ሆኑ መንግሥት ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል? እየመጣ ላለው ጠንካራ ውድድር እንዴት ይዘጋጁ? የፋይናንስ ተቋማት ሊጫወቱ ስለሚችሉት ሚና ምን ዝግጅት ተደርጓል ተብሎ ይታመናል?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- የመጀመሪያው ነገር ኢትዮጵያ ብሪክስን ስለተቀላቀለች ምን ዓይነት ምልካም ዕድሎችን ይዞላት ነው የመጣው? ይህ ወደ ፋይናንስ ዘርፉ ሲተረጎም ምን ማለት ነው? የሚለውን ቁጭ ብሎ መነጋገር ይጠይቃል፡፡ ስለጉዳዩ ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ዘርፉን ማንቃት ያስፈልጋል፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ተዋንያን እንደ ማንኛውም ሰው ኢትዮጵያ ብሪክስን ተቀላቅላለች የሚል መረጃ እንጂ፣ ብሪክስን መቀላቀል ወይም ይህ ውሳኔ ለእኔ ባንክ ወይም ለእኔ ኢንሹራንስ ኩባንያ ምን ማለት ነው? ለሚሉትና ለመሳሰሉት ጥያቄዎች መልስ ማግኘት አለባቸው፡፡ ብሪክስ ሊሰጣቸው የሚችላቸው ዕድሎችን ስትራቴጂያቸው ውስጥ ተካተው መታየትና መተርጎም አለባቸው፡፡ ይህንን ለማድረግ ከመንግሥት ጋር ብሪክስ ምን ዕድል ይዞ ይመጣል በማለት ሰፊ ውይይት ማድረግ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን እኔ የሚታየኝ የሬጉላቶሪ ችግሮች ብቻ አይደሉም ያሉብን፡፡ የፖሊሲ ችግርም የለም፡፡ ስለዚህ መወዳደር የሚችል የነቃ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ ከተለመደውና ባህላዊ ከሆነው አሠራር መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ጠንካራና በተለዋዋጭ ሁኔታ ውስጥ መሥራት የሚችሉ የፋይናንስ ዘርፍና ተዋንያን ያስፈልጋሉ፡፡ አገር ከአገር ጋር ሲወዳደር እኮ መንግሥት ለመንግሥት አይደለም የሚወዳደረው፡፡ ብሪክስ ተቋማት ናቸው፡፡ አገሮቹ አይደሉም የሚወዳደሩት፡፡ ስለዚህ ውድድሩ የሚሆነው በተቋማት መካከል ነው፡፡ ደረጃችን ዝቅተኛ ከሆነ ተቋሞቻችን ዝቅተኛ ናቸው ማለት ነው፡፡ ተወዳዳሪነታችንም ዝቅተኛ ነው ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ቁጭ ብለን ከሰሃራ በታች ያለ ትልቅ ኢኮኖሚ ይዘን ሁልጊዜ የምናወራው ሌሎች ወደ ኢትዮጵያ ይመጡብናል እንጂ፣ የእኛ ኩባንያዎች ወደ ውጭ ሄደው ተወዳድረን እናሸንፋለን የሚል አይደለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ሌሎቹ አይፈሩንም፡፡ እኛ ነን የምንፈራው፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ሌሎች አገሮች በመሄድ ለመወዳደር ፈሪ የተሆነበት ምክንያት ምንድነው? በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ተቋማት እስካሁን ወደ ውጭ ሄደው ሊወዳደሩ ያልቻሉበት ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀሰው ምክንያት ምንድነው? ቢያንስ በምሥራቅ አፍሪካ ጠንካራ ተወዳዳሪ የሚሆን ተቋም ለምን አልኖረም?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- ለዓመታት የመጣንበት ታሪክ ነው፡፡ ገበያ መር ኢኮኖሚ በምንለው ወይም ደግሞ የግል ዘርፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ከተጀመረበት ዕድሜ ምክንያት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግል ባንኮች ከተፈጠሩ 29 ዓመት አካባቢ ነው፡፡ ግን 28 እና 29 ዓመትም ቢሆን ቀላል ጊዜ አይደለም፡፡ ስለዚህ ባንኮቻችን ተደላድለው ነው የቆዩት፡፡ ሲቋቋሙም ለአገር ውስጥ ውድድር እንጂ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርጋቸው የሚችለውን አቅም አደራጅተው አይደለም፡፡ ልምዳቸው በአገር ውስጥ ውድድር ላይ የተገደበ ነው፡፡ የውጭ ተወዳዳሪ ባንክ እንዲገባ በሩ አለመከፈቱ በራሱ የተደላደለ የቢዝነስ ድባብ ፈጥሯል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ስለዚህ ውጭውን ላለማየት እንዲህ ያለው ሁኔታ አስተዋጽኦ አድርጓል ሊባል ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በውጭ ባንኮች መግባት አስፈላጊነት ላይ ብዙዎች የሚስማሙ ቢሆንም፣ አሁንም አንዳንድ ወገኖች ለውጭ ባንኮች ገበያውን መክፈት ጉዳት ያመጣል ይላሉ፡፡ የእርስዎስ ምልከታ ምንድነው?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- እኔ የሚታየኝ እንግዲህ ኢትዮ ቴለኮምን ተመልከቱ ነው፡፡ ሌላ ነገር ማለት ሳያስፈልግ ይህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በአሥር ዓመት ያልታየ ሥራ ነው በሦስት ዓመት እያሳየን ያለው፣ ይኸው ነው፡፡ ድሮ አገልግሎት እናገኝበት የነበረው መንገድና አሁን አገልግሎት የምናገኝበት መንገድ ተቀይሯል፡፡ ብዙ አማራጭ መንገዶች ተከፍተውልናል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከውድድሩ ጋር ተያይዞ በለውጡም ምክንያት ያመጣቸው ለውጦች ብዙ ውጤት አስገኝተዋል፡፡ ጠንካራ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል አሳይቷል፡፡ አዳዲስ ሐሳቦች እያመጣ ነው፡፡ አዳዲስ ፈጠራዎችን እያከለ በየጊዜው አገልግሎቱን የበለጠ እያሰፋ ነው፡፡ ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት ዘርፉ ለውጮቹም እንዲከፈት በመፈቀዱ ነው፡፡ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያ ባይፈቀድ ኖሮ ኢትዮ ቴሌኮም ምን ሊሆን እንደሚችል ማሰቡም ጥሩ ነው፡፡ በበፊቱ አሠራር ነበር የሚቀጥለው፡፡ እውነት ለመነጋገር የትኛው ዘርፍ ምን ለውጥ ሲያመጣ አየን በማለት፣ ለውጥ ሲመጣ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም መሆን እንደሚቻል ልምድ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በቴሌ ብር አማካይነት ፋይናንስ ዘርፉ ውስጥ አለበት፡፡ ስለዚህ የፋይናንስ ዘርፉ እንደ ቴሌ ያለ ትልቅ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ገብቶብናል ብሎ የሚያምንበት ምክንያት ከውድድሩ ጋር ተያይዞ ለውጡ ያመጣቸው መነሳሳቶች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ባንኮች እንዲገቡ ቢፈቀድም በኢንሹራንስ ዘርፉ ግን ይህ ዕድል እስካሁን አልተሰጠም፡፡ መንግሥት የውጭ ባንኮች እንዲገቡ እንደፈቀደው ሁሉ የኢንሹራንሱንም መክፈት አለበት እየተባለ ነው፡፡ ቀድሞ መፈቀድ ያለበት የኢንሹራንሱ እንደነበር የሚሞግቱ አሉ፡፡ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ዘርፍ ለኢኮኖሚው ያለው አስተዋጽኦ አንድ በመቶ እንኳን የማይሞላ ከመሆኑ አንፃር፣ ይህንን አስተዋጽኦ ከፍ ለማድረግ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች አለመፈቀዱ ብዙ ነገር አሳጥቷል ማለት ይቻላል?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- አንደኛ ትንንሽ መሆን ማቆም አለብን ብዬ ነው የማስበው፡፡ ትንንሽ ሆኖ የትም አይደረስም፡፡ ሁለተኛ የኢንሹራንስ ዘርፉ ከብሔራዊ ባንክ ወጥቶ ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ ወይም ኮሚሽን ይኑረው በሚለው ጉዳይ ላይ እኛ ባዘጋጀናቸው መድረኮች ውይይት ተደርጎበት፣ አሁን ባለው ደረጃ ራሱን የቻለ ተቆጣጣሪ እንዲኖረው ስምምነት ተደርሶ ይህ እየተሠራበት ነው፡፡ ቀጥሎ ግን ምን ዓይነት ሪጉሌተር  (ተቆጠጣሪ) ይኑር? ጠንካራ ፋይናንስ ዘርፍ እንዲፈጠር እንዴት ያግዝ የሚለው ውይይት ይቀጥላል፡፡ ይህንን ካልን ቀጥሎ የሚመጣው ነጥብ የኢንሹራንስ ዘርፉ ለውጭ ኩባንያዎች ይከፈት አይከፈት የሚለው ነው፡፡ አንዳንዴ ይከፈት አይከፈት የሚለው ውይይት ግን፣ የውጮቹ ቢገቡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ይቀጥላሉ ወይስ ይጠፋሉ ከሚለው አንፃር ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ኢኮኖሚው ማደግ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተሻለ የኢንሹራንስ ዘርፍ ይገባዋል፡፡ አዳዲስና ኢኖሼቲቭ የሆኑ አሠራሮች ያስፈልጉታል፡፡ የአደጋ ሥጋት ኃይለኛ የሆነበት ጊዜ ነው፡፡ ከዚያም በላይ ፈጣን የሆነ ምላሽ የሚፈልግ ነው፡፡ ይህንን የሚመጥኑ የኢንሹራንስ ተቋማት ሊፈጠሩ ይገባል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡

ስለዚህ ገበያው ተከፍቶ ሌሎችም መጥተውና ተወዳዳሪነታቸው አጠናክረው አንድ ላይም ቢሆን ሰብሰብ ብለው ለተወዳዳሪነት መዘጋጀት ነው እንጂ፣ ልምዶች የሚነግሩን ዝግ ሆኖ መቀጠል አያዋጣም፡፡ አሁን የትርፍ ድርሻ ምን ያህል እንዲከፋፈሉና ከዚያ ከመወዳደር ውጪ በኢኖሼሽን፣ በቴክኖሎጂ፣ በሰው ኃይል ብቃት፣ በደንበኛ ብዛትና በካፒታል አቅም የሚወዳደር ተቋም መፍጠር የተቻለ አልመሰለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ከዚህ ገለጻም የተገነዘብኩት በኢንሹራንስ ዘርፉም ሆነ በሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ጠንካራ ተወዳዳሪ ለመሆን ሰብሰብ በማለት ወይም ተዋህደው መሥራት የሚገባ መሆኑን ነው፡፡ ጠንካራ ተቋም ለመፍጠር ውህደት ቀዳሚ አማራጭ ነው?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- ሌላ ምን አማራጭ አለን? ለምሳሌ የፋይናንስ ተቋማቱ ካፒታል ከፍ ማለት አለበት፣ መጨመር አለበት፡፡ ትልቅ አደጋ ለመሸከም ትልቅ አቅም ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ኢኮኖሚው እያደገ ከመጣ ትልልቅ ሥጋቶችን የመሸቀም አቅም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ አንዱ አቅማቸውን ማሳደግ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር መወዳደር ካልቻሉ ግን ያላቸውን አማራጭ ማጥናት ግድ ይላል፡፡ አሁን በቀዳሚነት እየታየ ያለው መፍትሔ ግን መዋሀድና ጠንከር ብሎ ለውድድር መዘጋጀት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ኩባንያዎች በማንኛውም ዘርፍ መግባታቸውና ከአገር ውስጥ ተቋማት ጋር እንዲወዳደሩ በማድረግ የሚፈጠረው አሠራር፣ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ምን ዓይነት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- እኔ የሚያሳስበኝ አንድ ነገር ነው፡፡ የመጀመሪያው ነገር ጠንካራ ኢኮኖሚ ያስፈልገናል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሊያደርገን የሚችልና ለተጠቃሚዎች ብዙ አማራጮችን የሚሸጥ ኢኮኖሚ ያስፈልገናል፡፡ ምክያቱም ይህንን ካላደረግን የምንፈልገውን ነገር ማድረግ አንችልም፡፡ ትንንሽ ነገር ይዘን እንዲህ ያለውን ኢኮኖሚ ለመገንባትና በፍጥነት ለመሄድ ትልልቅ ተቋማት እንዲኖሩን ማድረግ የግድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ያስፈልጋሉ የሚላቸው ትልልቅ ተቋማት በፋይናንስ ዘርፍ ብቻ ነው ወይስ በሌሎችም ዘርፎች?

ገመቹ (ዶ/ር)፡- እውነት ነው በሁሉም ዘርፍ ነው፡፡ የፋይናንስ ዘርፉ ብቻ ሳይሆን ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩልህ ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ ስንሆን ሌላ መወዳደሪያ ነጥብ የለንም፡፡ ተቋሞቻችን ተወዳዳሪ መሆን አለባቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት የሚያስፈልጉት ደግሞ ለመወዳደር አቅም ሲፈጥሩ ነው፡፡ ሁለተኛ ለውድድር ሲዘጋጁ ነው፡፡ የምንወዳደረውም ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የበለጠ እየተከፈቱ በሄዱ ቁጥር፣ ቀጣናዊ ትብብሩ ተቋማት ከተቋማት ጋር፣ አገልግሎት ከአገልግሎት ሰጪው ጋር ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ወደ ሌሎች አገሮች ግንኙነት በጨመሩ ቁጥር ገበያዬ ኢትዮጵያ ብቻ ነው፣ ወይም አዲስ አበባ ብቻ ነው ብሎ የሚቀመጥ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ኬንያም ገበያዬ ነው፣ ጂቡቲም፣ ሩዋንዳም፣ ገበያዬ ነው ብለው የሚያስቡ ተቋማት ያስፈልጉል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይወዳደሩናል የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ መቼ ነው ኬንያና ሩዋንዳ ሄጄ የምወዳደረው? እዚያ ገበያ ስላለ ወደ እዚያም መሄድ አለብኝ የሚሉ ተቋማት ያስፈልጉናል፡፡ ለዚያ ደግሞ አሁን የሚደረጉ ለውጦች የግድ ናቸው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...

‹‹ብሪክስ ኢትዮጵያ የበለጠ ጠንካራ ሆና የትኛውንም ዓይነት ጫና መቋቋም ያስችላታል›› ቪክቶሪያ ፓኖቫ፣ የሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና የባለሙያዎች ምክር ቤት ዋና ኃላፊ

ቪክቶሪያ ፓኖቫ (ዶ/ር) በሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና የባለሙያዎች ምክር ቤት ዋና ኃላፊና በሩሲያ ኤችኤስኢ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚተዳደረው የአገር አቀፍ የኢኮኖሚክስ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዲን ሲሆኑ፣...