Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉየኢትዮጵያ ትንሳዔ ትክክለኛ ቀኑ መቼ  ነው?

የኢትዮጵያ ትንሳዔ ትክክለኛ ቀኑ መቼ  ነው?

ቀን:

በጌታነህ አማረ

ትንሳዔ ማለት ከሞት፣ ከመከራ፣ ከችግር፣ ከሥቃይ፣ ከረሃብ፣ ከድርቅ፣ ከበሽታ፣ ከመፈናቀል፣ ከግጭትና ከጦርነት ወጥቶ ዩቶፒያ  መሆን  ማለት ነው። ‹‹ዩቶፒያ›› ማለት ደግሞ መረዳዳት፣  መፈቃቀር፣ መዋደድ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ፣ ሰላም፣ ዕድገትና ብልፅግና ያለበት ሕይወት መኖር  እንደሆነ  ይነገራል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ ትንሳዔ አንድ ቀን እንደሚፈጸም በብዙዎች ዘንድ እምነት እንዳለ ይታወቃል፡፡ በዚህም መሠረት አንዳንድ ሰዎች የኢትዮጵያ ትንሳዔ እንደተፈጸመ ነገር ግን ትንሳዔው መከወን ብቻ እንደቀረው ሲናገሩ፣  ሌሎች  ደግሞ መፈጸሚያ ቀኑ እየደረሰ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡  ይህንንም ትንሳዔ ከሚጠባበቁት ውስጥ ትንቢተኞች፣ መንግሥትና ሐሳብ አመንጪዎች ይገኙበታል፡፡

- Advertisement -

ትንቢተኞች ኢትዮጵያ በእግዚአብሔር የተባረከችና የተቀደሰች አገር በመሆኗ ከብዙ የሰው ልጅ ፈተናና ሥቃይ  በኋላ ትንሳዔዋ እንደሚፈጸም ትንቢት እንዳለ፣ ይህም ትንቢት በቅርብ እንደሚፈጸም ይናገራሉ፡፡ መንግሥት  የእግዚአብሔር ዕርዳታ ተጨምሮበት ባጠረ ጊዜ ውስጥ በሰው ልጅ ቀን ከሌት ጠንክሮ በመሥራትና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ትንሳዔውን ማምጣት እንደሚቻል ይገልጻል፡፡  

በሌላ በኩል ደግሞ ምሁራን ወይም ሐሳብ አቅራቢዎች  የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በመገንዘብና ያለውን ምቹ ዕድል በመጠቀም ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካውና በማኅበራዊው ዘርፎች ያሉ ዕሳቤዎችን ወደ ዘመናዊ ዕሳቤዎች በመቀየር ቀላልና  ምቹ ሥርዓት ወይም ሲስተም በመፍጠር   ትንሳዔውን መፈጸም እንደሚቻል ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም ይህንን ሁሉ ሐሳብ ወደ አንድ ስንጠቀልለው ትንቢተኞች  ትንሳዔው እንደሚፈጸም የተነገረ ትንቢት መኖሩንና በዚያ መሠረት እንደሚፈጸም፣ መንግሥት ደግሞ   ሌት ተቀን ጠንክሮ  በመሥራትና ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ትንሳዔውን ባጠረ ጊዜ ማምጣት እንደሚቻል፣ ምሁራንን ወይም ሐሳብ አመንጪዎች በሳይንሳዊ መንገድ ብዙ መልፋት ሳይጠበቅብን በቀላሉ እንደሚፈጸም፣ ከሦስት በአንዱ አካል ትንሳዔው እንደሚመጣና እንደሚከናወን የሚጠባበቀው ደግሞ ማኅበረሰቡ ነው፡፡

ከዚህም በመነሳት ስለትንሳዔው የሚያስቡ አካላት በአጠቃላይ አራት ሆኑ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ አካላት አራት ከሆኑ ዘንዳ በመካከላቸው ያለው ግንኙነት፣ ትስስርና ልዩነት ምንድነው የሚለውን ለይተን ለማየት እንሞክር፡፡ 

 ትንቢተኞችን እያሉ ያሉት በተጻፈው ወይም በተነገረው ትንቢት መሠረት በአንድ ሰው ምክንያት ትንሳዔው ይፈጸማል የሚል ነው፡፡ ይህም ሰው  ጎዳና ተዳዳሪ፣ እረኛ፣ ገበሬ፣  ተማሪ፣ አስተማሪ፣ ምሁር፣ ተመራማሪ፣ ሠራተኛ  ወይም ደግሞ የመንግሥት ባለሥልጣን ሊሆን ይችላል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የእነዚህ አካላት ትንሳዔውን መጠባበቅ በሌሎች ማለትም በመንግሥት፣ በምሁራን  ወይም በሐሳብ አቅራቢዎችና በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ይደግፋሉ እምነትም አላቸው ማለት ነው፡፡

የመንግሥት ሐሳብ  ከሌሎች ጋር ያለው ልዩነት ደግሞ ኑ ተደምረን አብረን ሌት ተቀን ጠንክረን በአንድነት ሠርተን የኢትዮጵያን ትንሳዔ አብረን እናብስር፣ በዚህ ሒደት የማትሳተፉ ግን አትረብሹን አርፋችሁ ተቀመጡ፣ ብትችሉ ከእኛ ጋር ተደምራችሁ አብረን እንሥራ ካልሆነ ግን እኛ የምንሠራው እናንተንም የሚጠቅም በመሆኑ በምትችሉት መንገድ  ሁሉ አግዙን የሚል ነው፡፡ ጥሪ የሚደረግላቸው ሰዎች ደግሞ ሒደቱ ረጅም፣ አድካሚና ከፍተኛ ፅናት የሚጠይቅ በመሆኑ ብዙም ተነሳሽነት ሲኖራቸው አይታይም፡፡

ምሁራንን ወይም ሐሳብ አመንጪዎችን በተመለከተ የመንግሥት ሐሳብ በውስጣቸው ጥሩና ለአገር የሚጠቅም ዕው ቀት እንዳለ ያምናል።  በዚህም መሠረት ከመንግሥት ውጪ ያሉ ምሁራንና ሐሳብ አመንጪዎችን በልዩ ሁኔታ መርጦ በማስቀመጥ እንዲያግዙት ሲያደርግ ይታያል።  ለዚህ ደግሞ እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለው  ገለልተኛ የኢኮኖሚ አማካሪዎች ቦርድ ነው፡፡

ነገር ግን ይህ በመሆኑ ምክንያት ከእነዚህ ከተመረጡ ኣካላት ውጪ ያሉ ምሁራንና ሐሳብ አመንጪዎች እንዳይሳተፉ  የሚያደርግ ሕግ እንዳለና ይህም ሕግ ትክክል እንዳልሆነ መንግሥት ውስጥም ከመንግሥት ውጭ የሆነ ሰው ለአገር ጠቃሚ የሆነ ፖሊሲ ወይም የፖሊሲ ሐሳብ   እስካለው ድረስ ለአገር አበርክትዎ እንዲያደርግ ዕድል እንዲሰጠውና እንዲሳተፍ መደረግ እንዳለበት ቢነገርም አሁንም ግን ሐሳብ አመንጪ ሰዎችን ለመጠቀም ያለው ሥርዓት በጣም ደካማ ይመስላል፡፡

መንግሥት ሁለጊዜ ሐሳብ አመንጭዎችንና ምሁራንን ሐሳባችሁንና ዕውቀታችሁን ደብቀችሁ የጋን ውስጥ መብራት አትሁኑ በጋዜጣ፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንም ሆነ በሌላ መንገድ ብትገልጹት እኛ እንሰማችኋለን አውጡትና አገር ትጠቀምበት ዕውቅናና ሽልማቱ ቆይቶ ይደርሳል የሚል ሐሳብ ቢኖረውም ለአገር የሚበጀው ሐሳብ ግን ከምሁራንም ሆነ ከሐሳብ አመንጪዎች አገርን ከድህነት የሚታደግ ሐሰብ በሚባለው መንገድ  እየወጣ አይደለም፡፡

ይህን ጉዳይ ስንመለከተው ሐሳብ ሲባል ለአገር ባለው አበርክቶ ልክ ይመዘናል፡፡ ትናንሽና በማይክሮ ደረጃ ያሉ ሐሳቦችን ልክ መንግሥት ባለው መንገድ ማስተናገድ ይቻል ይሆናል፡፡ ነገር ግን ትልልቅና  በማክሮ ደረጃ ያሉ ሆነው አገርን ከሥር መሠረቱ ሊቀይሩ የሚችሉ  ሐሳቦችን ግን በሚባለው መንገድ  ማውጣት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ሐሳቦች አገርን የመለወጥ  ኃይል እንዳላቸው ሁሉ፣ በሒደታቸው የመጣልም ኃይል ስለሚኖራቸው ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚሹ ናቸው፡፡

ስለዚህ መንግሥት እነዚህን ሐሰቦች የሚያስተናግድበት መንገድ የተለየና ሐሳብ አቅራቢውም ሆነ ምሁሩ በሚፈልገው  መንገድና በምክክር  መሆን እንዳለበት ሊታመንበት ይገባል፡፡    የአገር ባለቤት የሆነው ማኅበረሰብ ትንሳዔው ይፈጸማል ብለው በሚያስቡትና በሚነግሩት አካላት ላይ እምነት በመጣል፣ ትንሳዔው የሚመጣበትን ቀን በከፍተኛ ጉጉትና ፀሎት በመጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ኢትዮጵያ ድህነትና አሰቃቂ ግጭት  ያለባት አገር ስትሆን ይህንን ደግሞ ያባባሱት ከፍተኛ የዋጋ ንረት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ የዕዳ ጫናና ሌሎችም ናቸው፡፡ እነዚህንም ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል፡፡ ከእነዚህም ዕርምጃዎች ውሰጥ በዋናነት የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም ይገኝበታል፡፡

ይህንንም ለማድረግ በዋናነት የተጠቀመበት ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል (Monetary Policy Tightening)፣ የመንግሥት በጀትን መቆጣጠር (Budget Control)፣  የመንግሥት ወጪዎችን መቀነስ  (Cut Spending) የግብር መሠረትን ማስፋት (Expansion of Tax Base) እና መዋቅራዊ ሪፎረም (Structural Reform) አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በሚባለው ፕሮግራም ማካሄድ ነው (በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ዕይታ  አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነባራዊ ሁኔታ  ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መከተል  (Monetary Policy Tightening) የሚደረግበት መንገድና የመንግሥት ወጪዎችን መቀነስ  (Cut Spending) የሚመከሩ አይደሉም)፡፡  

ነገር ግን ይህን  ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያ ፕሮግራም   ለማከናወን አንድ ቁልፍ ነገር እንደቀረ  ይነገራል፡፡ ይህም የገንዘብ ምንጭ መጥፋት ነው፡፡ ይህንን የገንዘብ ምንጭ ለማገኘት ደግሞ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በተለያየ መንገድ  ለማግኘት ብዙ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ገንዘብ ለማግኘት ደግሞ ብዙ ቅድመ ሁኔታዎች ይቀርባሉ፡፡ ከእነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች  ውስጥ ደግሞ አንዱ የብርን ከውጭ ገንዘቦች ጋር ያለውን ዋጋ ማዳከም የሚል እንደሆነ ይነገራል፡፡

ይህ ጉዳይ በነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓት ዕሳቤ ትክክል ነው፡፡ ነገር ግን እስካሁን ድረስ በትመና (Official Exchange Rate) የቆየን የውጭ ገንዘብ ትመና ሥርዓትን ለመቀየር አሁናዊ የአገሪቷን ነባራዊ የኢኮኖሚ ሁኔታ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ማለት አሁን ያለውን ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ ከመጠን በላይ ማጥበቅና እንዲበጠስ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ይህን በጣም የጠበቀ የገንዘብ ፖሊሲ  የአገሪቷ ኢኮኖሚ መሸከም ስለማይችል ተንኮታኩቶ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡

በዚህም መሠረት የውጭ ምንዛሪው ሥርዓት ለገበያው ቢተው ከመጠን በላይ በመውረድ የብር የመግዛት አቅም በመጠንከርና አሁን ካለበት ይፋዊ የምንዛሪ ተመን 57 ብር አካባቢ ምናልባትም በጣም ዝቅ በማለት ብዙ ድርጅቶችን ለኪሳራ፣ እንዲሁም አገርን ለኢኮኖሚ ውድቀት ሊዳርግ  ስለሚችል ጥንቃቄ ሊደረግበት ይገባል እላለሁ፡፡  በዚህም  የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ለመፈጸም እንደ መተግበሪያ  (Application) ይጠቅማል ተብሎ ከሚታሰበውና ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት  ይገኛል ተብሎ ከሚጠበቀው ገንዘብ በላይ፣ የምሁራንና የሐሳብ አመንጪዎች ሐሳባብ የኢኮኖሚውን ማሻሻያ ለማስፈንጠርና የሚፈለገውን ግብ ለመምታት እንደ ዋና መተግበሪያ (Application) ማገልገላቸው ምንም ጥርጥር የለውም፡፡

ይህን ተግባር ላይ ለማዋል ደግሞ ፍፁም ጨዋና ሥርዓት ያለው መሆን፣  ኋላቀርና የማይጠቅሙ ሐሳቦችን መሻር  ብሎም ለተፈጻሚነቱ ቃል ኪዳን  (Hippocratic Oath) መፈጸምና በአንድነት ትንሳዔውን ነገ ሳይሆን፣ ዛሬ በመፈጸምና በመከወን የምትፈለገውን ዪቶፒያ ማምጣት ያስፈልጋል። ዛሬ ማለት ዛሬ የቆምንበት ቀን፣ ነገ ላይ ሆነን የምንጠራው ቀን፣ ከነገ በስቲያ ላይ ሆነን የምንጠራው ቀን፣ ወይም ደግሞ ሌላ ቀን ላይ ሆነን የምንጠራው ቀን ሁሉ ዛሬ ነው።  ስለዚህ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ትክክለኛ ቀኑ ዛሬ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የኢኮኖሚና የባንክ ባለሙያ ሲሆኑ ከ16 ዓመታት በላይ የባንክ ሙያ ልምድ ሲኖራቸው፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው getaneh25@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...