Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትለዴሞክራሲና ለነፃነት መነጋገርን ማወቅ

ለዴሞክራሲና ለነፃነት መነጋገርን ማወቅ

ቀን:

በገነት ዓለሙ

ዓውደ ዓመት ወይም በዓል እንደየአገሩና በየአገሩ ይለያያል፡፡ በየዓመቱ ያምጣሽ/ያምጣህ ወይም ‹‹Many Happy Returns›› እየተባለ የሚከበረውና የሚነግሠው የበዓል ዓይነት በየአገሩ፣ በአገር ውስጥም የተለያየ ነው፡፡ ከዚህ ለየት ብሎ ግን መላው ዓለም፣ ዓለም በመላው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) አማካይነት የሚጋራቸው የጋራ የወል ያደረጋቸው በዓላት አሉ፡፡ የተመድ ዓለም አቀፋዊ ቀናት ይባላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪና በተጓዳኝም አኅጉራዊ ድርጅቶች (ለምሳሌ አፍሪካ ኅብረት) የሚያከብራቸው፣ የሚያነግሣቸው በዓላት አሉ፡፡ በዓለም ያለው ችግር ሁሉ ከሞላ ጎደል ለክብሩ፣ ለመፍትሔው ሲባል የተሰዋለት የተመደበለት ዓለም አቀፋዊ ቀን አለ፡፡ የሴቶች ቀን፣ የሠራተኞች ቀን፣  የፕሬስ ነፃነት ቀን የመሳሰሉት ለምሳሌ በብዛት የሚታወቁት ናቸው፡፡

አንዳንዶቹ ደግሞ ምናልባትም ጨርሰው የማይታወቁ፣ ‹‹ይህ ደግሞ ምናባቱ ያደርጋል?›› የሚባሉ ዓይነት አሉ፡፡ ለምሳሌ ከሜይ ወር ሳንወጣ ሜይ ሁለት (በዓለም የሠራተኞች ቀንና በዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን መካከል የሚገኘው ሁለት) የዓለም የቱና ቀን ነው፡፡ ተመድን በመሰለ የዓለም ማኅበር ደረጃ የዓሳ ኢንዱስትሪው ቱና የሚባለውን (የዓሳ ዓይነት) ቀን የሚያከብረው ከኢንቫይሮመንት (አካባቢ) ጥበቃ አኳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በአቅሟ በሚደንቅ አቅሟና ሠልፍ ለዕልቂት የተቃረቡ፣ ለዕልቂት አደጋ የተጋለጡ እንደ ዋልያ አይቤክስና እንደ ቆርቄ የመሳሰሉ እንስሳት/አራዊት የሚያስብ፣ የሚጠብቅ አገልግሎት ያለው የፖስታ ቴምብር አሳትማለች፡፡ በተመሳሳይ በማዕከላዊ ባንኳ (በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደንብ አውጭነት ለምሳሌ በመጥፋት ላይ ያሉት የዱር አራዊት ጥበቃ መታሰቢያ ቅንስናሽ ገንዘቦች ደንብ ቁጥር 61/1970 አማካይነት) ተመሳሳይ አንድን ጉዳይ ‹‹ጉዳዬ›› ነው ያገባኛል ባይ ሆና አራምዳለች፣ የሴቶች ቀን የታወቀ ቀን ነው፡፡ የቱና ቀን ብዙም አይገባም፣ አይታወቅም ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያ ለዱር አራዊት ጥበቃ እንዳደረጋቸው በደንብ ቁጥር 86/1976 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሴቶች አሥር ዓመት መታሰቢያ ቀን ቅንስናሽ ገንዘቦች አውጥታ ነገሩን ጉዳዬ ብላለች፡፡

- Advertisement -

ተመድ ከተመሠረተ ከ1945 (እ.ኤ.አ.) ጀምሮ 200 ያህል ቀናት በየዕለታቸው የሚታሰቡ፣ የሚሰለሰሉ፣ የሚንገበገቡባቸው ሆነው እንዲከበሩ ወስኗል፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ የሕዝብ በዓላት ሕግ ማሻሻያ ረቂቅ እየታየ ባለበት ጊዜና ከወራት መካከል በአንፃራዊነት ብዙ የሕዝብ በዓላት በሚገኙበት በዚህ በሚያዝያ ወር ውስጥ ሜይ ደይንና የፕሬስ ነፃነት ቀንን አክብረናል፣ ጉዳያችን አድርገን አስበናል፡፡ አሳሳቢነቱንም ለማሳሰብ ሞካክረናል፡፡ በዚህም መካከል የሚያሳስቡ ጉዳዮችን ዓይተናል፡፡

የምንለውን ነገር ይበልጥ ለማፍታታት ይረዳን ዘንድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በዚህ አጋጣሚ፣ በዚህ አጋጣሚ ከማለት ይልቅ መደበኛ የዕለት ተዕለት፣ የዘወትር ሥራውን ሲያከናውን ካወጣቸው መግለጫዎች፣ ከሰጣቸው አስተያየቶች፣ ወዘተ መካከል አንዳንዶቹን ዋቢ እያደረግሁ ጉዳዩን አስረዳለሁ፡፡ መነሻ/መንደርደሪያ የማደርጋቸው አስተያየቶች ግን የኢሰመኮን ብቻ አይደለም፡፡ የመላው ዓለም ጉዳይ ነውና ዓለም በሙሉ፣ በተለይም እኛን አስመልክቶ በተለይም እዚሁ ከቅርብ የሚሰጣቸውን መግለጫዎች፣ አስተያየቶችንም መነሻችን ይልቁንም ቆስቋሾቻችን ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል አንዱ ‹‹አስተያየት›› አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ የሚገኙ የውጭ አገር፣ በተለይም የምዕራብ አገሮች መንግሥታት (ከኢዩ ጋር አሥራ ሰባት አገሮች) የሰጡት የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን የጋራ መግለጫ ነው፡፡ መነጋገርን፣ ስለመናገር እየተነጋገርንና እያከበርን ሐሳብን የመግለጽ ነፃነትን እያከበርንና እያነገሥን ለምን ተናገሩ አንልም፡፡ የሰብዓዊ የመብቶች ጥበቃ በነዚህ አገሮች የሚገኝበትን የጥበቃ ደረጃ እያየንም፣ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ የእነዚህን አገሮች ደንታ ከጥቅሞቻቸው ጋር እንደሚገነዘቡ አሳምረን እያወቅንም ለምን ይናገራሉ? ለምን ይናገሩናል? ብለን የምናከብረውን ጉዳይ አናናንቅም፡፡ ዋናውን ጭብጥ አንሸሽም፡፡ መጀመሪያ መናገር መብታቸው ጭምር ነው፡፡ ሳይጠየቁ መቅረት መኖር የለበትም ብለን ስለምናምን፣ ማመን ስላለብን እምነት ብቻ ሳይሆን ይህንኑ መተግበር መግለጽና መኗኗሪያችን ማድረግ ስለሚገባን አጉል ተናገሩ፣ ለምን ተናሩን ብለን ተሸፋፍኖ መተኛት›› አንሻም፡፡ ‹‹ገልጦ የሚያይ ጌታ አለ ብለንም እናምናለን››፡፡ እንጂማ አዲስ አበባ ላይ በተለይ በዚህ የፕሬስ ነፃነት ቀን ‹‹ባልተለመደ›› ሁኔታ ‹‹በማኅበር ተደራጅተው ‹‹በሠልፍ ወጥተው›› የፕሬስ ነፃነት የታሰሩ ጋዜጠኞች ጉዳይ ያሳስበናል ያሉ መንግሥታት ኤምባሲዎች ይህን ቢያደርጉ የሚያምርባቸው፣ ቤታቸው ውስጥ ተግባራቸው ከቃላቸው ቢጣጣም ይልቁንም ባይፈነካከር ነበር፡፡

አሜሪካና ታላቋ ብሪታንያ ጁልየን አሳንጅ የሚባል አሳታሚ/ጋዜጠኛ ጉዳዩን የመስለ መደበኛ የማይችሉት ቁስል፣ ቡግንጅና ነቀርሳ ውስጣቸው ይዘውና የዩኒቨርሲቲዎች ግቢ ውስጥ ተቆስቁሶ መላው አሜሪካን ያጥለቀለቀውና የለውጥም ግፊት የሆነው የቬትናም ጦርነት፣ የዘር መድልኦና ተቃውሞ ታሪክ አለኝ ብሎ የሚደነፋው የአገርና የዩኒቨርሲቲዎች አመራር እዚያው ዩኒቨርሲቲ  ውስጥ መመርመርን፣ መጠየቅን፣ መቃወምን በፀረ አይሁድነት (አንቲ ሴመቲዝም) መከላከል ስም ሲደፍቅ እያየን፣ እነ ሲኤንኤን የዚህን ዜና ጉዳይ እንዴት አድርገው እንደሚሠሩት፣ እንዴት አድርጎ እንደሚሠራራቸው እየመሰከርን የእነዚህን አገሮች የመብትና የነፃነት ተቆርቋሪ ነን ባይነት ውሸትነትና አስመሳይነት ከዋናው ጉዳያችን ከዋናው መንገዳችን ውጭ ቢያደርጉን አይደንቅም፡፡ ዋናው ጉዳያችን ግን እነሱም ጋ ጥፋት/ጥሰት አለ ብለን የእኛን ስህተት፣ ጥፋትና ጥሰት ማደባበስና መመረቅ አይደለም፡፡ ዕድሜ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንጂ የእነሱ ነገር ከመንገድ አያወጣንም፡፡

አነሰም በዛም ከፋም ለማም የኢትዮጵያ የራሷ የለውጥ ሒደት ያፈራውና የጎለበተው (ገና ብዙ የሚቀረውም) ኮሚሽኑ የፕሬስ ነፃነትን ቀንም ከፍርድ/ክስ በፊት የእስራትንም ጉዳይ በተለያዩ አጋጣሚዎችና አቅጣጫዎች እያየ አሳይቶናል፡፡ ዝም ብሎ ድፍን መግለጫ ሳይሆን የዘንድሮውን (2024) የፕሬስ ነፃነት ቀን አከባበር/ክብር፣ በተለይም ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(5) አንፃር እንዲታይ ከዚህ አኳያ የሚታይ፣ የሚያቃጥልና የሚያንገበግብ ችግር እንዳለብን አሳስቦናል፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? የተጠቀሰውን የሕገ መንግሥት ድንጋጌ ማየት ነው፡፡ ‹‹በመንግሥት ገንዘብ የሚካሄድ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ መገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያቶችን ለማስተናገድ በሚያስችለው ሁኔታ እንዲመራ ይደረጋል፤›› ይላል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ አማካይነት አገር የተሰጠውን የቤት ሥራ አደራና ግዳጅ ምን ያህል ተወጥቶታል? ወይስ አድበስብሶታል? ወይስ ሸውዶታል? ወይስ የሚያበረታታ ሥራ አለ? የፕሬስ ነፃነትን ቀን ከሌሎች መካከል እነዚህን ጥያቄዎች እያነሳን የምንነጋርበት፣ የምንመራመርበት፣ የምንፈታተሽበት ቀን ነው፡፡ አገራችን ቢያንስ ቢያንስ በቲዮሪ ደረጃ ፐብሊክ ብሮድካስቲንግ የሚባል ተቋም ታውቃለች፡፡

የሕገ መንግሥቱ የአንቀጽ 29/5 ቃልና ድንጋጌ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚካሄድ፣ ወይም በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያለ›› የሚለው/ያለው የመገናኛ ብዙኃን ዓይነት ‹‹ፐብሊክ ብሮድካስተር›› ሆኗል ወይ? ንግግር የማይረግበት ራሱ ንግግርን የሚፈራ ጥያቄ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶና የሚገርመውም፣ ከሕግ በላይ ሆነውና ሕግ ጥሰው ገዥ ፓርቲዎች በባለቤትነት ያቋቋሟቸው የመገናኛ ብዙኃን እንደነበሩ እያወቅን፣ የግል ሚዲያ ብቻ ሳይሆን የመጀመሪያው የግል ሚዲያ እስከመባል ደረሰ መረን የለቀቀ ማናለብኝነት ውስጥ ከነበሩት ከእነዚህ ሚዲያዎች መካከል ውስጥ ብዙዎቹን ሌሎቹም ዛሬ የመንግሥት/የሕዝብ ሚዲያ መባል የበቁበትን ታሪክ/ሒደት ማንም አይናገርም፣ አልነገረውም፡፡ የነፃነት የመብት በዓል ስናከብር ከምንጠያየቃቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህንን ጉዳይ ነው፡፡

ጥያቄው ደግሞ እነዚህ የፓርቲ ሚዲያዎች እንዴት አድርገው ሕጋዊ ሆኑ? (የሚዲያ ሕጉ ያኔም ሲቋቋሙም ሆነ ዛሬም የፓርቲ የሚዲያ ባለቤትነት አይፈቀድም) የሚለው ብቻ ሳይሆን፣ ከመንግሥት ሚዲያነት ወደ ፐብሊክ ሚዲያነት ሽግግር ተደረገ ወይ? ማለትም ስለሆነ ጭምር ነው፡፡ በዚህም ጉዳይ ሆነ በሌሎችም ይህን ጉዳይ የሚገዛ ሕግ አለ ወይ?  የዚህ ጉዳይ/ዘርፍ የዓይን ብርሃንና የእግር  መንገድ ሆኖ የሚያገለግል ሕግና ተቋም አለ ወይ? በቂ ነወ ወይ? መሻሻል የሚገባው አለው?  አዲስ ሕግ ሊወጣለት መሻር ያለበት ሕግ አለን? እነዚህን ሁሉ በዓል ስናከብር ይቆረቁረናል ያንገበግበናል የምንለውን ጉዳይ ስናነግሥ መጠየቅ ያለባቸው ጥያቄዎች ናቸው፡፡ እንዲህ ያለ የተሟላ ሕግ መኖር አንዱ ጉዳይ ነው፡፡ ይህን የመሰለ ከበላዩ ሌላ ጌታ የሌለው ሕግ አለሁላችሁ ይለናል ወይ? የመጀመሪያው ጥያቄና ከዋስትናዎቹ መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህ ብቻ ግን አይደለም፡፡ ሁልጊዜም፣ በዓል ስናከብርም ሆነ በ‹‹አዘቦት›› ቀን ‹‹ሥራ›› ስንሠራም ሌላ መጠየቅ ያለበት ምትክ የሌለው ጉዳይ አለ፡፡ እንደተባለው የሕጉ አለሁላችሁ ባይነት በአፈጻጸምም ሆነ በሌላ ምክንያት ቢፈዝና ቢጓደል ለሕጉ ጥበቃ የሚያደርግለት ዕውናዊ መተማመኛ የሚሰጠውን ዴሞክራሲ አደላድለናል ወይ? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በተለይ በአሁኑ ጊዜ መጠየቅና ቅድሚያ መስጠት ያለብን ነገር ይህንን ነው፡፡ የምንነጋገረው ከሌሎች መካከል ስለፕሬስ ነፃነት ቀን ነውና የዚህ ባለጉዳይ ሁሉ በተለይም የሚዲያዎች ተቀዳሚ ተግባር የፕሬስ ነፃነትን፣ ሐሳብን የመግለጽና የሚዲያ ነፃነታቸውን የሚያጎናፅፋቸው ሰላምና ዴሞክራሲ እንዲደላደል፣ ሥር እንዲይዝና እንዲፀና መታገላቸውን የመጀመሪያው አጀንዳቸውና ጭንቅ ጥባቸው ማድረግ አለባቸው፡፡

ስለነፃነት ስለመብት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ አሁን (አፕሪል 25 ስለተከበረው ከክስ በፊት ያለመታሰር ቀን) በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 17 ስለተደነገገው የነፃነት መብት ስናወራ ዋናው ጥያቄ እንዲህ ያለ ሕግ አለ ወይ ብቻ አይደለም፡፡ ሕጉ ለዚያውም በሕገ መንግሥት ደረጃ በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነፃነቱን/ነፃነቷን አያጣም/አታጣም፣ ማንኛውም ሰው በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም ይላል፡፡ ይህ በ1987 ነሐሴ የወጣ ሕግ ነው፡፡ ከዚያ በፊት ኢትዮጵያ ውስጥ ከ1945 ዓ.ም. ጀምሮ ከ1923ቱ ሕገ መንግሥት ጋር የአገር የበላይ ሕግ አካል በሆነው የፌዴራል አክት በሚባል ሕግ መሠረት፣ ‹‹የቆመውን ሕግ በመጣስ ወንጀል በመሥራት ላይ ካልተገኘ በቀር ደንበኛ ባለሥልጣን ካላዘዘ ማንኛውም ሰው መያዝ ወይም መታሰር የለበትም…›› የሚል የሕግ መተማመኛ ነበረን፡፡ እንዲህ ያለ ሕግ አለን ወይ ተገቢ ጥያቄ ነው፡፡ መብታችንና ነፃነታችን የሕግ መተማመኛ ይሻሉ፡፡ ይህ ሕግ ሺሕ ጊዜ የተሟላ ቢሆንም፣ መጀመሪያ ግን ከበላዩ ሌላ ጌታ የሌለው ሁሉም የሚያከብረው መንግሥት ብቻ ሳይሆን ጉልበተኛም የሚገዙለት/ሕግ ነው ወይ? መመለስ ያለበት የማይናቅ ጥያቄ ነው፡፡

ይህን ጥያቄና መተማመኛ በአዎንታዊ መመለስም ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ ድንገት ወይም ከተቋም ግንባታችን ፍጥርጥር የተነሳ የሕጉ አለሁላችሁ ባይነት ቢፈዝና ቢጓደል ወይም ድንገት ውሸት ቢሆን ለሕጉ ጥበቃ የሚያደርግለት እውነተኛ መተማመኛ የሚሰጥ ዴሞክራሲ አደልድለናል ወይ? ጋዜጠኞች፣ ሚዲያዎች በግንባር ቀደምትነትና መጀመሪያ ገለልተኛ ተቋማት የየትኛውም ቡድን ተቀጽላ ወይም ንብረት ያልሆኑ ተቋማት እንዲገነቡ፣ በሕግ፣ በበላይ ሕግ የተደነገጉ መብቶች ከእርጥባን በዘለለና ከጉልበተኛ ጥቃት ነፃ በሆነ ደረጃ መኖር ደረጃ ላይ መድረሳቸውን የሚያረጋግጥ ሥራ አለን? ወይም ሠርተናል ወይ? ብለው ለዚህ መትጋትና መታገል አለባቸው፡፡ የመናገርና ሐሳብን የመግለጽ ነፃነታችንን የሚያጎናፅፈንን ሰላምና ዴሞክራሲ ሥር እንዲያዝና እንዲፀና የመታገል ሥራ፣ በተለይም ገና ለዚህ ዓይነት ጉዞ አዲስ ለሆነ አገር ከባድ የመሰናዶ ሥራ ይጠይቃል፡፡ የቀደመው አፈናና ጥርነፋ በመቅረቱ ጭንቅ ጥብ ውስጥ የገባው፣ በተለይም በተጠቁ ኃይሎች ከሰላማዊና ከሕጋዊ መንገድ ውጪ የሆነ ትግል የሚገዳደረው የሕግ ማስከበር ተግባር ተቋማትን ከማሻሻል፣ የሰው ኃይሉን ንቃትና ግንዛቤ ከመለወጥ ጋር የሚሠራ በመሆኑ ጭምር የሚታየው የመንግሥት ልዩነት ጭምር ያስከተለው ዴሞክራሲ ገና ሥርዓታዊ አልሆነም፡፡

ዋናው ተግባራችን የሆነውን ይህን ግዳጅና አደራችንን የተገኘውን ዴሞክራሲ የግርግር መደገሻ አድርገን እንማግጥበት ብንል፣ በተለይም በሚኝበት ደረጃ በቀላሉ ይሰበርና መራራ ፅዋ ያስጠጣል፡፡ መብትና ነንነት ኃላፊነት አለበት፣ ኃላፊነቱም የሚጠይቀውን ጨዋነትና ሥነ ምግባር ይፈልጋል የሚባለው ሁልጊዜም እውነት ነው፡፡ በተለይ ወደ ዴሞክራሲ በሚደረግ ጉዞ ወቅት ይህ እጅግ በጣም እውነት ነው፡፡ የአገራችን የዴሞክራሲ ትግል በተለይም ጋዜጠኞችን፣ በተለይም ታጋዮችን ‹‹እታለም (ወይም ወንድም ዓለም) ሥሪው ቤትሽን›› የሚሉት በዚህ ምክያት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ሰላምና ዴሞክራሲ ሥር እንዲይዝና እንዲፀና መታገል በሰላማዊና በሕግ ባልተከለከሉ መንገዶች ሐሳብን ማፋጨትና ሕዝብን መሳብ እንጂ፣ ዴሞክራሲን ‹የኖህ መርከብ› የሚያሰኘው የተለያዩ ፍላጎት ያለበት መሆኑን መነሻ አድርጎ መርከቡን በጥይትም፣ በመጥረቢያም፣ በቆንጨራም፣ በገጀራም መፍለጥና መሸንቆር የማይፈቀድበት፣ የተከለከለበት ሥርዓት የመሆኑ ቋንቋና ወግ አገራችን ገና አዲስ ነው፡፡ ሁልጊዜም አዲስ  ሆኖ መኖር የለበትም፡፡  

‹‹አዲስ››ነታችን ደግሞ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ዴሞክራሲ ይቋቋም ማለት መሰናዶ ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ ይሁን ቢሉት አይሆንም፡፡ በአዋጅ፣ በምርቃት፣ በፀሎት፣ በስለት አይመጣም፡፡ ዴሞክራሲ ማለት ከሌሎች መካከል የቡድኖች መንግሥታዊ ገዥነት ከነፃና ከትክክለኛ ምርጫ የሚመነጭበት፣ አዲስ፣ ከዚህ በፊት ያልነበረ አዲስ ምዕራፍ ይከፈት ማለት ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ገና ሲጀመር የምናማርጣቸውን ቡድኖች (ፓርቲዎች) መኖር ይፈልጋል፡፡ ይህ ራሱ ገና ‹‹ዘንቦ ተባርቆ›› የሚያሰኝ ሥራ አለበት፡፡ የምናማርጣቸው ፓርቲዎች ሁሉ የተወሰነ የዴሞክራሲያዊ አመለካከትና የድርጅት አኗኗር መለኪያን ያለፉ እንዲሆኑ ይፈለጋል፣ ግዴታም ነው፡፡ ፓርቲዎች፣ የፖለቲካ ታጋዮች ከጫካ/ከበረሃ ንቃትና ግንዛቤ ሳይወጡ፣ ወደ ሕጋዊ ሰላማዊ ተፎካካሪዎች ሳይለወጡ፣ እንንዲህ ያለ የሠለጠነና የሰከነ ትግል የሚጠይቀውን ምግባርና ባህሪይ ሳይዙ፣ ጥይት እየተኮሱ፣ ቦምብ እየጣሉ፣ ሰው እያገቱ፣ ከሌሎች መካከል ስለነፃነት መብት ያለ ሕግ፣ ያለ መያዝና ያለ መታሰር መብት መታገል ምን ትርጉም አለው?

ይህ ማለት ይህ ሁሉ እስኪሟላ ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለ ሕግ መያዝ፣ ማሰር በጊዜ ቀጠሮ ‹‹አመሉ መቀጠል›› የፖሊስ የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ጥሶ የያዘውን ሰው ላለመሳቀቅ እንቢ ማለት ይፈቀዳል ማለት አይደለም፡፡ የተረጋጋ የኑሮ ጊዜን ከቀውጢ ወይም የርብርብ ጊዜ ለይተው ሳያዩ ዝም ብለው ‹‹ስለመብትና ነፃነት›› እኝኝ ከሚሉት ጋር ባልስማማም፣ የመንግሥት ሕግ አክባሪነት ግዴታው ግዳጁና ተግባሩ መሆኑን አውቃለሁ፣ የምንታገለውም ለዚሁ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሕግ መከበር እንቅፋት እየሆኑ ይልቁንም ሕገወጥነትን፣ አመፅን፣ ወንጀልን፣ መብት መጣስን፣ አገር ማውደምን የትግል መሣሪያ እያደረጉ፣ የትጥቅ ትግልንና ጉልበትን/ኃይልን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የትግል መሣሪያ አድርጎ ይዞ ስለሰላምና ዴሞክራሲ ግንባታ ማውራት ውሸት ነው፡፡

መልካም ዓላማ፣ ሰናይ ዓላማ፣ የተቀደሰ ግብ ወይም ‹‹ጉድ ኮዝ›› የሚባል ነገር፣ ‹‹የሚሞትለትም›› ነገር አለ፡፡ ሰናይ ጦርነት፣ መልካም ጦርነት፣ የተቀደሰ ጦርነት ብሎ ነገር ግን ዛሬ እየቀረ ብቻ ሳይሆን፣ የድሮዎችም ይህ ስም የተሰጣቸው ትግሎች ለምን? ለምን? ለምን? ለምን? እየተባሉ ናቸው፡፡

በአዘቦት ቀንም ሆነ የትኛውን የተመድ ወይም የአፍሪካ ኅብረት የመብትና የነፃነት ቀን በምናከብርበትና በምናነግስበት፣ ስለእነዚህም ትርጉም ያለው ንግግርና ጭውውት በምናደርግበት ወቅት ሁሉጊዜም መጠያየቅ መነጋገር ያለብን ለመሆኑ ሰላማችንን አደጋ ላይ የጣለው፣ የዴሞክራሲያችንን ጉዞ አበሳ ያበዛበት ምንድነው ብለን ነው፡፡ ዋነኛው ምናልባትም ብቸኛው ምክንያት የተለያዩ ኃይሎች ፓርቲዎች ቡድኖች ግብግብ መሆኑ አይደለም፡፡ ወይም ራሱ ልዩነታችን አይደለም፡፡ ልዩነት ባላቸው፣ እኔ ልክ፣ እኔ እበልጥ በሚባባሉ ቡድኖች መካከል ያለው ግብግብ/ትግል ከሕግና ከሰላማዊ መንገድ ውጪ መውጣቱ ነው፡፡ ዴሞክራሲን የምንናፍቀው መነጋገርን ሳናውቅ ነው፡፡ ይህንን ችግር  ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዋና ኮሚሽነር ራሳቸው ባለፈው ሳምንት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደጉት ቆይታ ገልጸውታል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያውያ ውስጥ የገባንበት ውጥንቅጥ ስተመለከተው ቢያንስ የተወሰኑ ኢትዮጵያውያን እህቶቻችን ወንድሞች የሐሳብና የአስተሳሰብ ልዩነት የሰዎች መብት መሆኑን መቀበል ያቅታቸዋል…›› ብለዋል፡፡ ለዚህም ነው የማያባራ ግጭት፣ የማያባራ የሚመስል ግጭት ውስጥ የገባነው ብለዋል፡፡ ‹‹መንግሥት ኃይሉን ተጠቅሞ የሐሳብ ልዩነት ያላቸውን ሰዎች አለማጥቃት፣ ተቃዋሚ ቡድኖችም ቢሆኑ ከእነሱ የተለየ ቡድን ብለው የሚያስቡትን መንግሥትንም ሆነ ሌሎች አካላትን በሐሳብ ልዩነት የተነሳ ማጥቃታቸው መቆም አለበት፡፡ እነዚህን ነገሮች አክብሮ መኖር የሰብዓዊ መብቶች ባህል ጉዳይ ነው…›› ነው ያሉት እውነት ነው፡፡

በግልም ሆነ በይፋና በፖለቲካ መድረካችን ላይ የተለያዩና ዝርዝር ሐሳቦችን በጤናማነት የማቃረብ፣ የማፍራትና ፈልፍሎ የመረዳት ልምድ ገና አጠገባችን አልደረሰም፡፡ በየትኛውም መስክ በፖለቲካም፣ ከፖለቲካ መለስ ባሉ ጉዳዮችም ከራሳችን የተለየ ሐሳብን ለመስማት ቻይ አይደለንም፡፡ ሐሳባችን ሲተች ኩርፍያን፣ ሐሜትን መሣሪያ አድራጊዎች ነን፡፡ የተለያዩና የማይጥሙንን ሐሳቦች እንኳንስ ጥቅሜ ብሎ ማድመጥና ማቅረብ፣ የሰው መብት ነው ብሎ መስማት አንችልም፡፡ ሳይቀየሙ፣ ቂም ሳይቋጥሩ መለያየት የሚባል ነገር ገና አልገባንም፡፡ የደፈረሱና የተበላሹ ስሜቶቻችን አቃልሎና አረጋግቶ መፈራራትና ኩርፊያን ተሻግሮ፣ በጥያቄዎችና በቅሬታዎች ላይ ለመነጋገር ሳይጻፍና ተቃራኒ ሐሳቦችን ከራስ ሐሳብ እኩል እያከበሩ የሚያቀራረቡ ነገሮችን መፈለጊያ መንገድ፣ አንድም ሳይያዝ በአጠቃላይ መነጋገርን ሳያውቁ ‹‹ድንገት›› የዴሞክራሲ ታጋይ፣ የዴሞክራሲ ቀን፣ የንግግር ነፃነት ቀን፣ ወዘተ አክባሪ/አስከባሪ መሆን ከንቱ ምኞትና የማይጨበጥ ሕልም ነው፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...