Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየሃይማኖት ጉዳዮችን በሚመለከት እየተረቀቀ ባለው አዋጅ ላይ ቅሬታ ቀረበ

የሃይማኖት ጉዳዮችን በሚመለከት እየተረቀቀ ባለው አዋጅ ላይ ቅሬታ ቀረበ

ቀን:

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የወንጌል አማኞች ካውንስል በተናጠል ለሰላም ሚኒስቴር በላኩት ደብዳቤ፣ አዲስ በመረቀቅ ላይ ያለው የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ ላይ ያላቸውን ቅሬታ አሰሙ፡፡

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትና የወንጌል አማኞች ካውንስል ረቂቅ አዋጁ ባይደርሳቸውም፣ ከዚህ ቀደም የአዋጁን መንፈስ በቃል በተረዱት መሠረት ሊካተቱ ይገባቸዋል ያሏቸውን ምክረ ሐሳቦች፣ አስተያየቶችና ቅሬታዎች ለሰላም ሚኒስቴር መላካቸውን ሪፖርተር የደረሰው መረጃ ያመለክታል፡፡   

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሰላም ሚኒስቴር በላከውና ሪፖርተር የተመለከተው ምክረ ሐሳብ፣ ረቂቅ አዋጁ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በዘመናት ትግል ለማረጋገጥ እየሞከሩ ያሉትንና በሕገ መንግሥቱ የተደነገገውን የዜጎች እኩልነትና የሃይማኖት ነፃነት መብቶችን የሚጥስ፣ ሙስሊሞች በዓለም አቀፍ ሕግ የተቀመጠላቸውን የሃይማኖት ነፃነትና ሰብዓዊ መብቶች የሚገረስስ ሆኖ አግኝቼዋለሁ ብሏል፡፡ 

- Advertisement -

‹‹መንግሥት፣ የመንግሥትን ከሃይማኖት የመለያየትና የዜጎችን ሃይማኖታዊ ነፃነትና እኩልነት መብት መርሆዎች ዝርዝር ለመደንገግ የጀመረውን እንቅስቃሴ እናደንቃለን፡፡ ሆኖም ለረቂቁ ግብዓት የሚሆኑ ውይይቶች እንደሚኖሩ በመጠበቅ ላይ ባለንበት ወቅት መጀመሩን ባላወቅነው ረቂቅ ላይ ለመወያየት ሚያዝያ 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰላም ሚኒስቴር መጋበዛችን ቅሬታ ፈጥሮብናል፤›› ብሏል፡፡ 

ምክር ቤቱ የረቂቁን ቅጂ አለማግኘቱን አስታውቆ፣ ይህ ባልሆነበት አስተያየቱን መጠየቁ ለሚያቀርበው ግብዓት ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሰጠና ለይስሙላ መሆኑን የሚያሳይ ሆኖ አግኝቼዋለሁ በማለት ገልጿል፡፡ ምክር ቤቱ አስተያየቱን በጽሑፍ እስኪሰጥ ሳይጠበቅ የፍትሕ ሚኒስቴር ባልደረቦች ከቀናት በኋላ ወደ ክልል ከተሞች ለውይይት ማቅረብ እንደሚጀምሩ መግለጻቸውንም ጠቁሟል፡፡ በተያዘው የግንቦት ወር አጋማሽ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ፍትሕ ሚኒስቴር ረቂቁን ለማቅረብ ማቀዱን ገልጿል፡፡

ረቂቁ የሃይማኖቶችንና የሃይማኖት ተከታዮችን እኩልነት እንዳይረጋገጥ የሚያደርግ፣ የእስልምና መሠረታዊ አስተምህሮዎችን ከግምት ያላስገባ፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከሃይማኖቱና ከዜግነት ተሳትፎው እንዲመርጥ የሚያስገድድ፣ ለመንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ያልተገባ ተቆጣጣሪነት የሚሰጥ መሆኑን በመግለጽ ምክር ቤቱ ቅሬታውን አቅርቧል፡፡

ረቂቁ የያዛቸውን ዝርዝር ጉዳዮች በሚመለከትም ሃይማኖታዊ ምልክቶችን እንደ የቤተ እምነቱ አስገዳጅ ሕግጋቶች ልዩ ሁኔታዎችን መደንገግ ሲገባው ሃይማኖታዊ መገለጫዎችን ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ቤትና ከሥራ ገበታ የሚያስወግዱ ድንጋጌዎችን መያዙ፣ እንዲሁም የሙስሊም ሴቶችን ሰብዓዊ መብት በግልጽና በጥቅሉ የሚጥስ መሆኑን እንደተመለከተ ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በትምህርት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ውስጥ የጋራ አምልኮ ተግባራትን መከልከል፣ ሙስሊሙን ማኅበረሰብ ከእምነቱና ከሥራው ወይም ከእምነቱና ከትምህርቱ እንዲመርጥ የሚያስገድድ መሆኑ፣ እንዲሁም አምልኮን ከተፈቀደለት ቦታ ውጪ ማከናወን መከልከሉ፣ የእምነት ነፃነት መብቶች አተገባበር ላይ ጫና የሚያሳድር መሆኑን ገልጿል፡፡ 

የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን ሐሳብ የሚጋራ ደብዳቤ ዓርብ ግንቦት 2 ቀን 2016 ዓ.ም. ለሰላም ሚኒስቴር የላከው ደግሞ የወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ነው፡፡ ካውንስሉ ረቂቅ አዋጁ አባላቱን በተመለከተ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 1208/2012 የሚቃረን መሆኑን ገልጾ፣ ሕገ መንግሥታዊ የሆኑ የእምነትና የሃይማኖት ነፃነት መብትና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን የሚመለከት በመሆኑ፣ ረቂቁን ለማየት እንዲሰጠው ቢጠይቅም እንዳልተሰጠው አስረድቷል፡፡

ረቂቁ በቤት ውስጥ የሚደረግን አምልኮና የአደባባይ ስብከትን የሚከለክል መሆኑን ካውንስሉ ከሰላም ሚኒስቴርና ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር በነበረው ውይይት ወቅት በተደረገለት ገለጻ መረዳቱን በመግለጽ፣ ይህም በቀጥታ የወንጌል አማኞችን የሚነካና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት የሌለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ መሠረት ዜጎች የአምልኮ ሥርዓት ለመፈጸም በመንግሥት አካል የግድ መመዝገብ የማያስፈልጋቸው ቢሆንም፣ በረቂቁ ውስጥ ግን የነፃነቱ ሰጪና ነሺ የምዝገባው መኖር አድርጎ ማስቀመጡ ትክልል አለመሆኑን፣ እንዲሁም ከመፅደቁ በፊትም ካውንስሉ እንዲስተካከሉ በደብዳቤ የጠየቃቸው ጉዳዮች እንዲስተካከሉ አሳስቧል፡፡

የሁለቱን የእምነት ተቋማት ምክረ ሐሳብ፣ አስተያየትና ቅሬታ አስመልክቶ የሰላም ሚኒስቴር ምላሽና አስተያየት ለማካተት የተደረገው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...