Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም ዓይነት ጥረት ተደርጎ አገራቸው ከገባችበት ቀውስ ውስጥ ትወጣ ዘንድ፣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችና መድረኮች ግጭት ወይም ጦርነት ይብቃ እያሉ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው ሕዝብም በአገኘው አጋጣሚ ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን እየተማፀነ ነው፡፡ ባለፈው ሰሞን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው የመወያየት ዕድል የገጠማቸው የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የወከሉ ወገኖችም፣ አገራቸው ከግጭት ማዕበል ውስጥ ወጥታ ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን ሲያሳስቡ ተደምጠዋል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከነገሠው ፅኑ ድህነት በተጨማሪ የሰላም ዕጦት ሕዝባችንን ከማሰቃየት አልፎ፣ ነገን በተስፋ ለመቀበል ከመዘጋጀት ይልቅ ምን ይመጣ ይሆን የሚል ሥጋት ፈጥሮበታል፡፡

አሁን ዋነኛ ጥያቄ መሆን ያለበት ኢትዮጵያ ከገባችበት አደገኛ አረንቋ ውስጥ ወጥታ ሕዝቧ ዕፎይ እንዲል ምን መደረግ አለበት የሚለው ነው፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ አትፈርስም›› እየተባለ መፈክር ማሰማትም ሆነ ቀና ቀናውን ብቻ በማሰብ ባለህበት እርገጥ የትም አያደርስም፡፡ በየቀኑ በተለያዩ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶች፣ ጦርነቶችና ጭካኔ የተሞላባቸው ጥቃቶች የንፁኃን ደም እንደ ጎርፍ እየፈሰሰ ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን አደገኛ ሒደት ማስቆም ካልተቻለ የኢትዮጵያ ትንሳዔ ሳይሆን መፍረስ ነው የሚታወጀው፡፡ ይህንን ዘግናኝና ሲሰሙት የሚያስደነግጥ እውነታ ከልብ ተቀብሎ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ብሔራዊ አጀንዳ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ በአገር በቀል የግጭት አፈታትና የሽምግልና ባህሎች የታደለች ስለሆነች፣ ለአገር እናስባለን የምትሉ በሙሉ ግጭት ከማጋጋልና የዳር ተመልካች ከመሆን ተላቃችሁ የሚፈለግባችሁን ኃላፊነት ተወጡ፡፡ አገር አንዴ ካመለጠች እንደማትገኝ ተገንዘቡ፡፡

የጥንቶቹ ኢትዮጵያውያን በጨቋኝ ገዥዎች መዳፍ ውስጥ ሆነው ሳይቀር አገራቸውን ከውጭ ወራሪዎችና ተስፋፊዎች መከላከል የቻሉት፣ ለአገራቸው በነበራቸው ጥልቅ ፍቅርና የአርበኝነት ስሜት እንደነበረ ብዙ የተባለበት ነው፡፡ ታላቁን ፀረ ኮሎኒያሊስት የዓድዋ ድል የተጎናፀፉት ከምንም ነገር በላይ አገራቸውን በማስቀደማቸው ነበር፡፡ ለዓለም ጥቁር ሕዝቦችና ለተገፉ ጭምር ተምሳሌት የሆኑት ከአገራቸው በፊት ራሳቸውን መስዋዕት ለማድረግ የቆረጡ ስለነበሩ ነው፡፡ ከገዥዎች ጭቆና ይልቅ የእርስ በርስ ፍቅር፣ መከባበር፣ መተሳሰብና አርቆ አሳቢነት ነው ታላቁን የዓድዋ ድል ያስገኘው፡፡ በዚህ ዘመን ግን ከአገር በፊት ሥልጣን፣ ጥቅም፣ ብሔር፣ እምነትና የመሳሰሉት ተቀጥላዎች በመብዛታቸው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የመከራ አዝመራ እያጨዱ ነው፡፡ ገለልተኛ የሃይማኖት መሪዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሰከኑ ዜጎች የሚያቀርቧቸው ሰላማዊ ጥሪዎች እየተናቁ ጦርነት ይቀነቀናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ግን የትም መድረስ አይቻልም፡፡

በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በእምነት፣ በፖለቲካ አቋምና በመሳሰሉት ቢለያዩም በአገር ጉዳይ ግን አንድ መሆን ነው ያለባቸው፡፡ አገርን ከሥልጣንና ከተለያዩ ፍላጎቶች በታች ማድረግ የሚያስከትለው መዘዝ ከባድ ነው፡፡ ለዚህም ነው በሥልጣን ላይ ያለው ብልፅግና ፓርቲ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት፣ ቤተ እምነቶችና የአገር ጉዳይ የሚመለከታቸው በሙሉ ግጭቶችን የሚያስቆሙ አማራጮች ላይ ማተኮር ያለባቸው፡፡ አገርን በመምራት ላይ ያለው መንግሥት ከፍተኛ አደራ ስላለበት በተቻለ መጠን ለዘለቄታዊ ሰላም መስፈን በግንባር ቀደምነት መሠለፍ ይጠበቅበታል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች አኩርፈው ትጥቅ ያነገቡ ወገኖችም ለሰላም መስፈን የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ ከአንድ ጦርነት ወደ ሌላው ጦርነት እንደ ዘበት የሚገባበት ደም ፍላት፣ ከዕልቂትና ከውድመት የዘለለ ምንም ፋይዳ እንዳልነበረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ህያው ምስክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ልማትና ዕድገት የሚገኘው ከሰላም እንጂ ከጦርነት እንዳልሆነ ማንም በቀላሉ የሚገነዘበው ጉዳይ ነው፡፡ ጦርነት ንፁኃንን ሲፈጅ፣ ንብረታቸውን ሲያወድም፣ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ሲያስከትልባቸው፣ የአገርን ኢኮኖሚ ሲያደቅና መቅኖ ቢስ ሲያደርግ ነው የሚታወቀው፡፡ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላና በተለያዩ ሥፍራዎች በርካቶች አልቀዋል፣ ከፍተኛ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልል በሚካሄዱ ውጊያዎች አገር ሰላም አጥታለች፡፡ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው መሥራት ካለመቻላቸውም በላይ፣ ምርቶችን ወደ ገበያ ማውጣት በማቃቱ ከፍተኛ የኑሮ ውድነት ተከስቷል፡፡ ሰላም ጠፍቶና ድህነት ተንሰራፍቶ መኖር አልበቃ ብሎ የአገር ህልውና ዋናው ሥጋት ሲሆን፣ ሰከን ብሎ ተነጋግሮ የጋራ አገራዊ መድረክ ለመፍጠር ዳተኛ መሆን መዘዙ ከሚታበው በላይ ነው የሚሆነው፡፡

ማንም ሆኑ ማን የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል የሚሉ በሙሉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም፣ ሰላም፣ ልማት፣ ዕድገትና የወደፊት ብሩህ ተስፋ የሚጠቅም ሐሳብ ካላቸው ይደመጡ፡፡ በኢትዮጵያ ምድር በእኩልነት ለመነጋገር የሚያስችል የጋራ መድረክ ተፈጥሮ፣ ሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በነፃነት እንዲመከርባቸው ዕድሉ ይመቻች፡፡ ለኩርፊያ የማያበቁ የሐሳብ ልዩነቶች እየተለጠጡ እርስ በርስ መጋደልና አገር ማውደም ይቁም፡፡ ከማንኛውም ሥልጣን፣ ጥቅምና ፍላጎት በላይ ለአገር ህልውና ቅድሚያ ተሰጥቶ ለንግግርና ለድርድር በሩ ወለል ብሎ ይከፈት፡፡ ልዩነትን በሕጋዊና በሰላማዊ መንገድ አለማስተናገድ ያተረፈው ነገር ቢኖር ዕልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ የሐሳብ ልዩነት ለንግግርና ለድርድር መተው ሲገባው፣ እንደ ዘመነ መሣፍንት እርስ በርስ መፋጀት ለዚህ ዘመን የሚመጥን ተግባር አይደለም፡፡ ይልቁንም የተለያዩ ሐሳቦች ተፋጭተው ለአገር የሚጠቅሙ ተግባራት ይከናወኑ፡፡ ለዚህ ደግሞ አገርን ከቀውስ ውስጥ የሚያወጣ ብሔራዊ አጀንዳ ላይ ይተኮር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ቅንጦት አይደለም!

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት በየዓመቱ እ.ኤ.አ. ሜይ 3 የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ነው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን የሚዘከርበት ምክንያትም የፕሬስ ነፃነትን...