Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በከፊል ይሸጣል ሲባል ፕራይቬታይዝድ’ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል›› አቶ ነፃነት ለሜሳ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ገበያ ውስጥ ወደ 50 ዓመታት የተጠጋ ዕድሜ አለው፡፡ ብቸኛው የመንግሥት የኢንሹራንስ ኩባንያም ነው፡፡ ከአገሪቱ የኢንሹራንስ ገበያ እስከ 50 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ በመያዝ ሲጠቀስ ቆይቷል፡፡ በየዓመቱ ዕድገት ምጣኔውን እየጨመረ ስለመሆኑ የሚገርለት ይህ ኩባንያ 2016 የሒሳብ ዓመት ሦስተኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የሥጋት የመሸከም አቅሙን 6.2 ትሪሊዮን ብር ማድረስ ችሏል፡፡ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የሰበሰበው የዓረቦን መጠን 7.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በኢትዮጵያ ዓመታዊ ትርፍ ምጣኔውን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ የቻለ ብቸኛው የኢንሹራንስ ኩባንያም በመሆን የሚጠቀስ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በተለይ 2016 የሒሳብ ዓመት ኩባንያው በታሪኩ የመጀመሪያ ሊባሉ የሚችሉ ውጤት ያስመዘገበበት ነው፡፡ በወቅታዊ የኢንሹራንስ ኩባንያው የሥራ አፈጻጸም፣ በተለይም በቅርቡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ ሊሸጥ ስለመሆኑ ከተሰጠው ውሳኔ ጋር በተያያዘ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ይዞ የዘለቀ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡ ኩባንያው አሁን ያለበት ደረጃ እንዴት ይገለጻል? 2016 የሒሳብ ዓመት የዘጠኝ ወር አፈጻጸሙስ ምን ይመስላል?

አቶ ነፃነት፡- የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ በመምራት እየተጓዘ ነው፡፡ በየዓመቱ አፈጻጸሙን እያሳደገ ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በሁሉም ዘርፍ ዕድገት እያሳየ ሲሆን በተለይ በ2016 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙ በከፍተኛነቱ የሚጠቀስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥጋት የመሸከም አቅሙን በ50 በመቶ ማደጉ አንድ ማሳያ ነው፡፡ በ2016 ዓ.ም. የሦስተኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ የድርጅቱ ሥጋት የመሸከም አቅም ከ6.2 ትሪሊዮን ብር በላይ ሆኗል፡፡ ይህንን ሥጋት ለመሸከም የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ደግሞ 7.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ በዘንድሮው ዓመት በዘጠኝ ወራት ማሰባሰብ የቻለው የ7.6 ቢሊዮን ብር ዓረቦን መጠን ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ካስመዘገብነው ጋር ሲነፃፀረ በ32.3 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ የዓረቦን መጠን ዕድገቱ ግን የተሸከምነውን የሥጋት መጠን ያህል አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ በገበያው ላይ ውድድሩ ስላለ በዋጋ ቅናሽና በመሳሰለው ዓረቦኑ ዝቅ የሚልበት ሁኔታ አለ፡፡ በሌሎች አፈጻጸሞችን ካየንም ደግሞ በዘጠኝ ወር ውስጥ የሸጥናቸው ውሎች አሥር በመቶ ዕድገት በማሳየት 136,234 ደርሷል፡፡ ከሌሎች ዓመታት በተለየ ኩባንያው ባለፉት በዘጠኝ ወሮች ውስጥ ፈጽሟል ብለን የምንጠቅሰው 12 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከፍቶ ሥራ ማስጀመሩ ነው፡፡ ይህም የኩባንያውን የቅርንጫፎች ቁጥር 125 ማድረስ አስችሏል፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስ የዓረቦን ገቢያችንም ቢሆን በ29 በመቶ አድጓል፡፡ ሌላው በዚህ በጀት ዓመት ትልቅ ስኬት ተደርጎ የሚወሰደው የዓረቦን አሰባሰባችን ነው፡፡ ዘንድሮ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ከዓምናው 19 በመቶ አድጓል፡፡  

ሪፖርተርየኢንሹራንስ ኩባንያዎች አንዱ ግብ ለሰጡት የመድን ሽፋን ጉዳት ሲደርስ ካሳ መክፈል ነውና በዚህ ዘጠኝ ወር ውስጥ ምን ያህል የጉዳት ካሳ ከፈላችሁ? ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ቢያነጻጽሩልኝ፡፡

አቶ ነፃነት፡- በዚህ ዘጠኝ ወር የከፈልነው የካሳ መጠን ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይኼ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከከፈልነው 14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ 

ሪፖርተርየካሳ ክፍያ መጠኑ በዚህን ያህል መጠን ያደገበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ነፃነት፡- ትልልቅ የሚባሉ በተለይ በአቭየሽን ዋስትና የከልናቸው ትልልቅ ክፍያዎች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የካሳ ክፍያውን ከፍ የሚያደርገው እንዲህ ላሉ ዋስትናዎች በመኖራቸው ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ግን ከፍተኛ የካሳ ክፍያ የተመዘገበበት የተሽከርካሪ መድን ዋስትና ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት የተሽከርካሪ አደጋዎች እየጨመሩ በመምጣታቸው ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመለዋወጫ ዕቃዎች ዋጋ መናርና የመሳሰሉ ሁኔታዎች የካሳ ክፍያ መጠኑን ከፍ ሊያደርገው ችሏል፡፡ ነገር ግን የካሳ ምጣኔያችን ዕድገቱ አንድ በመቶ ነው፡፡ የከፈልነው የካሳ መጠን በ14 በመቶ ቢያድግም የክሌም ሬሾዎችን ግን አንድ በመቶ ብቻ ነው ያደገው፡፡ ይህ ማለት የሰበሰብነው ዓረቦን የከፈልነውን የካሳ መጠን ውጦልናል፡፡ የአንደርራይት ሪዛልታችን ደግሞ በ43 በመቶ ነው ያደገው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የሰበሰብነውን ዓረቦን ኢንቨስት ከማድረግ አንፃር 29 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ ችለናል፡፡ 

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መድን ድርጅት 2016 ለየት ባለ ሁኔታ ከሌላው ጊዜ በተሻለ ውጤት ያገኘበት ከሆነ ለተመዘገበው ውጤት አንድ ማሳያ የሚሆነው የትርፍ ምጣኔ ዕድገቱ ስለሆነ ኩባንያችሁ በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ ምን ያህል ትርፍ አግኝቷል፡፡ አሳየን ካላችሁት የአፈጻጸም ዕድገት ጋር ይመጣጠናል?

አቶ ነፃነት፡- እንደሚታወቀው አንድ ተቋም መጨረሻ ላይ የሚለካበት ውጤት ትርፍ ነው፡፡ የመንግሥትንም ድርሻ በወቅቱ ለመክፈል የሚጠበቀው ትርፍ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በሦስተኛው ሩብ ዓመት መጨረሻ ላይ ያገኘው ትርፍ የሥራ አፈጻጸሙን የሚመጥን ነው፡፡ በዘጠኝ ወር ውስጥ ከታክስ በፊት ለመጀመርያ ጊዜ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተሻግረን 1.24 ቢሊዮን ብር ማትረፍ ችለናል፡፡ ይህ ትርፍ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት አስመዝግበን ከነበረው ትርፍ 36 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ያሳያል፡፡ የተመዘገበው ትርፍ ለድርጅታችንም ሆነ ለኢንዱስትሪው በዘጠኝ ወር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘት የተቻለበት ነው፡፡ የዛሬ ሦስት ዓመት አካባቢ ለመጀመርያ ጊዜ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፋችን የተገለጸ ሲሆን አሁን ደግሞ ይህንን ትርፍ በዘጠኝ ወር ማሳካት ችለናል፡፡ 

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መድን ድርጅት ትልቅ የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡ 2016 የሒሳብ ዓመት እንዲህ ያለ ከፍተኛ ውጤት እያስመገበ መሆኑን ብትገልጹም፣ መንግሥት የዚህን ተቋም ድርሻ ለመሸጥ ውሳኔ ማሳለፉ አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ ይህን የመንግሥት ውሳኔ እንዴት አገኛችሁት? እርስዎስ እንደ መድን ድርጅት ሥራ አስፈጻሚነትዎ ውሳኔውን እንዴት ይገልጹታል? ድርሻው በከፊል የሚሸጠውስ ለማነው?

አቶ ነፃነት፡- እንደሚታወቀው መንግሥት የካፒታል ገበያ እያስተዋወቀ ነው፡፡ ባለሥልጣንም ተቋቁሟል፡፡ የሲኪውሪቲ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ተቋቁሟል፡፡ በነገራችን ላይ ይህንን ኮሚሽን እኛም መነሻ ፋይናንስ ሰጥተን ነው ያቋቋምነው፡፡ በኢትዮ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ያለን አምስት ኩባንያዎች ሆነን በጋራ በመሆን እንዲቋቋም አድርገናል፡፡ ይህንን ተቋም ለመፍጠር የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ግንባር ቀደም አስተዋጽኦ አበርክቷል ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በከፊል ይሸጣል ሲባል ፕራይቬታይዝድ ይሆናል ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ እንደተባለው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ውጤት እያስመገበበት ያለ ወቅት ነው፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አሁን ባለበት ሁኔታ የተወሰነ ድርሻውን በሼር መልክ ቢሸጥ የበለጠ ወደ ተሻለ ዕድገት ደረጃ እንዲወጣ ያደርገዋል፡፡ አሁን በተወሰነው ውሳኔ መሠረት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ባለበት ሁኔታ ወደ ሼር ኩባንያ ይቀየርና የተወሰነ ሼሩን የሚሸጥ ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ብልጫ ያለውን ድርሻ ይዞ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡ በዚህ አግባብ ውሳኔው ሲተገበር ደግሞ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከፍተኛ ካፒታል እንዲኖረው ያስችላል፡፡ የኩባንያዎ አፈጻጸም በግልጽ የሚታወቅ በመሆኑ የዚህን ኩባንያ ሼር የመግዛት ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ የዚህን ኩባንያ ሼር ለመግዛት በጣም ፍላጎት ያላቸው የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች አሉ፡፡ በእርግጥ አሁን ለአገር ውስጥ ይሁን ለውጭ ኩባንያዎች ወይም ለሁለቱም ነው የሚሸጠው የሚለው ነገር ገና ግልጽ አይደለም፡፡ በደፈናው ሼሩ የሚሸጠው ለሕዝብ ነው በሚል የተቀመጠ ነው፡፡ በእኛ በኩል ግን በከፊል መሸጡ ጠቃሚ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ከኩባንያው ሼር የሚገዙ ኩባንያዎችም እንዳሉ እናምናለን፡፡ ለምሳሌ በጠለፋ ዋስትና ድርድሮችና በሌሎች የሥራ ጉዳዮች ወደ ውጭ ስንወጣ ብዙ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ላይ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ በተለይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከጊዜ ወደ ጊዜ ትርፉ እያደገ የሚሄድ ተቋም መሆኑን ስለሚረዱ ብዙ ፍላጎት ያሳያሉ፡፡ የመንግሥት ተቋም መሆኑን ያልተረዱ አንዳንድ ተቋማት ሳይቀሩ ሼር መቼ ነው የምትሸጡት የሚሉ ሁሉ አሉ፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የተወሰነ ድርሻውን እንዲሸጥ መደረጉ ከፍተኛ ጥቅም የሚኖረው ነው፡፡ ሼር ሽያጩን በተመለከተ እኛም የምናውቃቸው ሒደቶችን ያለፈ ነው፡፡ ኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሴኪውሪቲ ኤክስቼንጅ ኮሚሽን ሲያቋቁም አብሮ የሠራውም ሥራ አለ፡፡  በካፒታል ገበያ ላይ ተቋማት ሊስት ይደረጋሉና የተሻለ ፐርፎም የሚያደርጉ፣ ሰዎች በፍላጎት ኢንቨስት ሊያደርጉባቸው የሚችሉ ኩባንያዎች ይፈልጋሉ፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በዚህ ምዘና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ሥር ካሉ 26 ኩባንያዎች ውስጥ ከመጀመርያዎቹ አንዱ ሆኗል፡፡ ይህ ሊሆን የቻለው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አንደኛ በፋይናንስ አቅሙ ጠንካራና ግልጽ የሆነ የሒሳብ አያያዝ ያለው ተቋም በመሆኑ ነው፡፡ የፋይናንሻል ስቴትመንቱ ንፁህ ነው፡፡ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን በ2015 የሒሳብ ዓመት ኦዲት ካስደረጉት የመንግሥት የልማት ተቋማት ውስጥ ግንባር ቀደምም ነው፡፡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ታኅሳስ ላይ ኦዲት አስደርገን ኦዲት ሪፖርታችንን አቅርበናል፡፡ IFRSን በመተግበር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቀጥሎ የመጀመርያው የኢንሹራንስ ኩባንያ ነው፡፡

ከዚያም በላይ ደግሞ በምሥራቅ አፍሪካ ያልተተገበረ IFRS የተባለ የኢንሹራንስ ፕሪሰንል መተግበር የቻለ ነው፡፡ ይህንን እኛ 2020 ላይ ነው ተግባራዊ ያደረግነው፡፡ ይህንን ፕሪንስፕል ለመተግበር ኢንዱስትሪው ገና ድርድር ላይ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ግን 2020 ላይ IFRS-17 እና IFRS-9 የሚባሉትን ፕሪንስፕሎችን መተግበሩ በራሱ በካታል ገበያ ውስጥ ቀድሞ እንዲምረጥ አድርጎታል ማለት ይቻላል፡፡ 

ስለዚህ አጠቃላይ አሠራሩን በማዘመን የመጣ ኩባንያ ስለሆነ በተለይ በካፒታል ገበያ ላይ ሊስት ቢደረግ የመጀመርያ ተፈላጊ ኩባንያ ሆኖ ሊመረጥ ችሏል፡፡ ይህም የሆነው ለዚሁ ሥራ በተመረጠ ኩባንያ ምዘና ጭምር ነው፡፡ ይህንን ጥናት ሲያጠና የቆየውም KPMG ነው፡፡ ጥናቱን ለስድስት ወራት አካሂዷል፡፡ በKPMG ጥናት ሊስት ሊደረጉ የሚችሉት ተቋማት ምንድነው የሚጎላቸው? በካፒታል ገበያ ሊስት ሲደረጉ አትራክት ማድረግ የሚችሉት የትኞቹ ናቸው? በትርፍ ድርሻቸው የተሻሉ የትኞቹ ናቸው በማጥናት በደረሰበት መደምደሚያ የሚለውን ኩባንያችን መሥፈርቱን ከሚያሟሉት አንዱ አድርጓል፡፡ KPMG ይህንኑ ጥናት ጨርሶ ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ ከእነዚህ አምስቱ ተቋማት ሊስት እንደሚደረጉ አረጋግጧል ማለት ነው፡፡ ይኼ ለእኛ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንድንታወቅ ያደርገናል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት አዲስ የአምስት ዓመት ስትራቴጂና የአሥር ዓመት ሮድማፕ እየሠራን ከመሆኑ ጋር ተያይዘ በምዘናው ያገኘነው ውጤት ስትራቴጂዎቻችንን በቀላሉ ለማሳካት ያግዘናል፡፡ ስትራቴጂ ቢያንስ በምሥራቅ አፍሪካ ገበያ ውስጥ መግባት የሚለውን ያካተተ ነው፡፡ ስለዚህ በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ባሉ አገሮች ቅርንጫፎች ለመክፈት ለያዝነው ዕቅድና ተያያዥ ውጥኖቻችን ከፍተኛ ዕገዛ ያደርግልናል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ተቋም ሊስት ሲደረግ መንግሥት ትልቅ ካፒታል ይስባል፡፡ ኢንቨስትመንት ይጠራል፡፡ ይኼ ካፒታል ወደ መድን ድርጅት ሲመጣ መድን ድርጅትን የበለጠ እንዲመነደግ ያደርጋል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ ገበያው ከተከፈሉ ቴክኖሎጂም ዕውቀትም ይዞልን ስለሚመጣ ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ በአገር ውስጥ ገበያ የሚሸጥም ከሆነ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አሁንም ጥሩ እየሄደ ያለ ተቋምም ስለሆነ ገበያውንም እየመራ በመሆኑም በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲኖረው ያግዛል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የኩባንያው የተወሰነ ድርሻ መሸጡ እንደ መልካም ዕድል የሚታይ ነው፡፡ መንግሥታችን ዴቨሎፕመንታል ስቴት ስለሆነ ወሳኝ ድርሻውን ይዞ ግን ይቀጥላል፡፡ ምክንያቱም በተለይ የተረጋጋ ገበያ እንዲኖር ኢኮኖሚው ሊመራ የሚችለው በዴቨሎፕመንታል ስቴት መሆኑን መንግሥት ያምናል፡፡ ስለዚህ አብዛኛውን የሼር ድርሻ ይዞ የሚቀጥለው መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ኢትዮ ቴሌኮምንም በተመሳሳይ ያሰበ እንዳለው በኢትዮጵያ መድን ድርጅትም በተመሳሳይ ሁኔታ የሚሠራ ይሆናል፡፡ ትልቁን ድርሻ ይዞ ካፒታል በማሳደግ ውጤታማ ለመሆን መንግሥት የወሰነው ውሳኔም በበጎ መታየት ይኖርበታል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለምሳሌ አሁን ለሠራተኞች ደመወዝ ለማስፈቀድ በመንግሥት ቻናል ነው መሄድ ይኖርብናል፡፡ ከኢንዱስትሪው ጋር መወዳደር አትችልም፡፡ የግል ዘርፉ ሲገባ ግን ፍሌክሴብል እየሆንክ ትሄዳለህ፡፡ ሼር ሆልደሩ ኩባንያው ከዚህ በላይ አትራፊ እንዲሆን እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ ሌላ ነገር መደረግ አለበት ይላል፡፡ የምወዳደረው በሥራ ብቻ አይደለም ለሠራተኞችም በምትሰጠው ጥቅማ ጥቅም እየተወደድክ መሄድ አለብህና ሼር መሸጡ ለመድን ድርጅት ትልቅ ዕድል ነው፡፡ 

ሪፖርተርይህ ዕርምጃ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አሠራር ላይ ምን ያህል ለውጥ ያመጣል? በምን ያህል ጊዜ ውስጥስ ሼሩን ሸጦ በአዲሱ አደረጃጀት ወደ ተግባር የሚገባው መቼ ይመስልዎታል?

አቶ ነፃነት፡- በነገራችን ላይ ድርጅታችን እየሄደበት ያለው ትራንስፎርሜሽን የአሠራርና የአደረጃጀት ብቻ ሳይሆን በቴክኖሎጂ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ላይ ነው ያለው፡፡ ትልቅ ዳታ ሴንተር ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እየገነባን ነው አሁን የምንጠቀምባቸውን ሁለት የኢንሹራንስ ሶፍትዎሮች እያሳደግን (አብግሬድ) እያደረግን ነው፡፡ ስለዚህ አሁንም ቢሆን መድን ድርጅት በራሱ ለውጥ ውስጥ ነው፡፡ መንግሥትም በቶሎ በካፒታል ገበያው ሰንጠረዥ ውስጥ እንዲገባና እንዲመረጥ ያደረገው እንዲህ ያሉ እንቅስቃሴዎቹና እየሄደበት ያለው ተቋማዊ ሁኔታ ወደ ዲጂታላዜሽን እየገባን በመሆኑ ነው፡፡ ሁለቱን ሶፍትዌሮቻችን አፕግሬድ ካደረግንና ዳታ ሴንተራችንን ከጨረስን በኋላ ከሦስተኛ ወገን ጋር የሚያገናኘን ዲጂታል አገልግሎት እንጀምራለን ማለት ነው፡፡ እዚህ ላይ ሌላ ካፒታል ከውጭ ሲታከልበት ደግሞ በዕቅድ የያዝነውና በምሥራቅ አፍሪካ የበለጠ ተወዳዳሪ ለመሆን የምንችልበት ዕድል ያሰፋልናል፡፡ ገበያው ክፍት በሆነ ቁጥር የእኛም ተወዳዳሪነት ይጨምራል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም የውጭ ተወዳዳሪ መጥቶበት ቻሌንጀ እያደረገ እንዳለው ሁሉ እኛም ቻሌንጅ የምናደርግበት አቅም እናገኛለን ማለት ነው፡፡ 

ሪፖርተርየኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከዚህ ቀደምም ሆነ አሁን በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁን የገበያ ድርሻ ይዞ የመቆየቱን ያህል እስካሁን ገበያውን ከኢትዮጵያ ውጪ ለማስፋት ያልቻለበት ምክንያት ግን ምንድነው? በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው?

አቶ ነፃነት፡- የገቨርናንስ ችግር ስለነበረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል፡፡ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ሲመራ የቆየው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሥር ባለ አንድ ዲፓርትመንት ነው፡፡ ስለዚህ በዚያ አቅም ልክ ነው እየተመራ ያለው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ በኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚሰጡ የመድን ፕሮዳክቶችን ስታያቸው በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጥረት ነው እንጂ የሚሸጡት የፖሊሲ ድጋፍ የላቸውም፡፡ በብዙ አገሮች ኮምፖሰሪ ኢንሹራንሶች በጣም ከፍተኛ ናቸው፡፡ እዚህ አገር ኮንፖሰሪ ኢንሹራንስ የሞተር ኢንሹራንስ ብቻ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ተመሳሳይ አገልግሎቶች ገበያ ውስጥ እየሸጥን የባንኩ በፎርክሎዥር ሕግ ፕሮቴክትድ ሲሆን እኛ ተከራክረን ነው ያንን ክሊር የምናደርገው፡፡ ይኼ የሆነው በአንድ ተቋም ሥር መታጨቃችን ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ያለው ተቀባይነት በጣም አነስተኛ በመሆኑ ኢንዱስትሪው እንዳያድግ ያደረገበት ሁኔታ አለ፡፡ ሌሎች የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ዕድገታቸው በጣም የተመጠነ በመሆኑ በሌሎች ነገሮች ላይ ኢንቨስት ሲያደርጉ አይታዩም፡፡ ለምሳሌ በትምህርት፣ በቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ሲያደርጉ አይታይም፡፡ እንደሚታወቀው ኢንሹራንስ በመደበኛው ትምህርት ስለማይሰጥ ኢንቨስትመንት ይፈልጋል፡፡ የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት ወደ ኅብረተሰቡ አንተ ትሄዳለህ እንጂ ወደ አንተ አይመጣም፡፡ ለዚህ ነው ኢንተርሚዲተር ሁሉ ተጠቅመን የምንሠራው፡፡ ባንክ ኢንተርሚደተር አይጠቀም፡፡ እኛ ግን ያለብሮከርና ያለ ኤጀንት አንሠራም፡፡ ምክንያቱም የግድ ወደ ሕዝቡ መሄድ አለብህ፡፡ ወደ ሕዝብ በወረድክ ቁጥር ደግሞ ወጪውን አትችለውም፡፡ ሁሉም ቦታ ቅርንጫፍ መክፈት አለብህ፡፡ እንዲህ ያሉ ወጪዎችን የሚጨምሩ ጉዳዮች ኢንሹራንሱ እንዳያድግ ያደርገዋል፡፡ ይህ ነገር መለወጥ አለበት፡፡ ብሔራዊ ባንክ እየተከተለ ያለው በአዲሱ አደረጃጀት ግን ሁኔታዎችን ይቀይራል፡፡ ኢንሹራንስን የተመለከተ ትምህርት በትምህርት ፖሊሲ ውስጥም እንዲገባ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ 

ሪፖርተርበነገራችን ላይ የኢንሹራንስ ትምህርት በሌለበት ሁኔታ እስካሁን ባለሙያዎችን እንዴት ነበር የምትገኙት?

አቶ ነፃነት፡- ሠራተኞችን የምንቀጥረው ስለኢንሹራንስ አስተምረናቸው ነው፡፡ ሲቀጠሩ እኛ አንድ ብለን ስለኢንሹራንስ እናስተምራቸዋለን፡፡ ይህ የሆነው ኢንሹራንስ መደበኛው ትምህርት ውስጥ ስለሌለ ነው፡፡ ደህና አካዳሚ እንኳን የለንም፡፡ ብሔራዊ ባንክ የሚመራው አካዳሚ እንኳን አንድ ወቅት ላይ ደህና እንቅስቃሴ ነበረው፡፡ አሁን የለም ማለት ይችላል፡፡ ሠርተፊኬት ነው የሚሰጠው፡፡ እንደ ኮሌጅ ሥልጠና እየሰጠ አይደለም፡፡ ይህ ሁሉ ኢንዱስትሪው እንዳያድግ አድርጎታል፡፡ አሁን ግን የግዴታ መቀየር እንዳለብን በማመን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ በተለይ ኢንሹራንስ ዘርፉን የሚመራው ኮሚሽን ሲቋቋም ብዙ ለውጥ ይታሰባል፡፡

ሌላው ለውጥ ያመጣል ብለን የምናስበው የሚወጡ ፖሊሲዎችንና አዋጆችን በትክክል ቻሌንጅ እያደረግን ለመሄድ የዚህ ኮሚሽን መቋቋምና ሥራ መጀመር አስተዋጽኦ አለው፡፡ ለምሳሌ አሁን የመንገድ ትራንስፖርት መመርያ ሥራችንን የገደበበት ሁኔታ አለ፡፡ እሱን ቻሌንጅ ማድረግ አንችልም፡፡ ታስታውስ እንደሆነ አንድ የጉምሩክ አዋጅ ወጥቶ ሥራ አስፈጻሚዎችን ሁሉ ሲገዳደር መሞገት ያልተቻለበት ሁኔታ ሁሉ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሆነው የኢንሹራንስ ዘርፉ በዲፓርትመንት የሚመራ ስለሆነ ማንም የኢንሹራን ዘርፉ ትዝ ስለማይለው ነው፡፡ አንዳንድ ኢንሹራንስ የተመለከቱ ድንጎጌዎች ሲወጡ ማማከር እንዳለባቸው እንኳን አያስቡም፡፡ ኮሚሽኑ ሲቋቋም ግን  በመንግሥት ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ይሆናል፡፡ ማንኛውም ኢንሹራንስን የሚመለከት አዋጅ ሲወጣ እየተሳተፍን ኢንዱስትሪውን በሚጠቅም ሁኔታ እንዲቀረጽ ለማድረግ ዕድል የሚገኘው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሚመሩት ራሱን የቻለ ኮሚሽን መቋቋም ነው፡፡ የኮሚሽኑ መቋቋም የትምህርት ተቋማት እንዲስፋፋም በማገዝ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፡፡

ሪፖርተርየኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው የበለጠ እንዲያድግ  ራሱን በቻለ ኮሚሽን መመራት እንዳለበት በተደጋጋሚ ስትገልጹ ቆይታችኋል፡፡ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ለመሙላት ሊሻሻሉ ይገባል የምትሏቸው ጉዳዮችም አሉ፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ መልስ ሳያገኙ ገበያውን ለውጭ መክፈት እንዴት ይታያል፡፡ ለምሳሌ እርስዎ የሚመሩት የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ ይሸጥ ብሎ ከመወሰን በፊት የኢንሹራንስ ሕጉ መስተካከል የለበትም? ኮሚሽኑን የማቋቋም ዕቅዱ ምን ደረጃ ላይ ነው?

አቶ ነፃነት፡- እርጥበት ነው፡፡ በነገራችን ላይ አሁንም ቢሆን ኮሚሽኑን የማቋቋሙ ሥራ እየተሄደበት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት ኢንዲፐንደንት ኮሚሽንኑ የማቋቋም ሥራው ሲጀመር በ1963 ዓ.ም. የወጣን የኢንሹራንስ አዋጅ መነሻ በማድረግ ነው፡፡ አዋጁ በዚያን ወቅት ራሱን የቻለ ኢንሹራንስ ኩባንያዎችን የሚመራ ኮሚሽን እንደነበር ነው፡፡ የዛሬ 50 ዓመት አካባቢ የነበረ ኮሚሽን ነው እንደገና ወደኋላ የተመለሰው ማለት ነው፡፡ አሁንም ኮሚሽኑን እንደ አዲስ ለማቋቋም ሲታሰብ መነሻ የተደረገው ይኸው በ1963 ዓ.ም. የወጣው የኢንሹራንስ ኮሚሽን አዋጅ ነው፡፡ እውነት ነው ኮሚሽኑ ከመቋቋሙ በፊት ፖሊሲው በደንብ ተዘጋጅቶ ይወጣል የሚል እምነት አለኝ፡፡ አዲሱ ኮሚሽንም በ2025 ይቋቋማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የካፒታል ገበያውን በተመለከተ የተወሰነ ሼር ነው የምንሸጠው፡፡ ይህም ቢሆን መድን ድርጅት እንደ መድን ድርጅትነቱ ተቋሙም፣ ሠራተኛውም፣ አገልግሎትና ደንበኞቹን ይዞ ነው የሚቀጥለው፡፡ አዲሱ ነገር ኢንቨስተመር ማምጣት ነው፡፡ አቅሙን ነው የምታሳድግለት፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች