Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየትግራይ ሕዝብ ከደረሰበት ወቅታዊ ፈተና እንዲወጣ የቀረበ ምክረ ሐሳብ

የትግራይ ሕዝብ ከደረሰበት ወቅታዊ ፈተና እንዲወጣ የቀረበ ምክረ ሐሳብ

ቀን:

በበቀለ ፀጋዬ

መግቢያ

የትግራይ ሕዝብ በፖለቲካ ኃይሎቹ መሪነት ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበረውን የደርግ መንግሥት ከሥልጣን ለማስወገድ ብዙ መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ በርካታ የትግራይ ወጣቶችም ተሰውተዋል፡፡ በ1983 ዓ.ም. የደርግን መንግሥት የተካው በሕወሓት የሚመራው ኃይልም በ1992 ዓ.ም. ከኤርትራ መንግሥት ጋር በተደረገው ውጊያ፣ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከተወጣጡ ኃይሎች ጋር በመሆን ከባድ ጦርነትን አስተናግዷል፡፡ እንዲሁም በ2010 ዓ.ም. በተደረገው ለውጥ ሕወሓት የፌዴራል መንግሥቱን ሥልጣን ለቆ ወደ ትግራይ ሲመለስ የለውጥ መንግሥቱን ለመገዳደር የትግራይን ሕዝብ ለጦርነት በማዘጋጀት፣ ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሦስት ጊዜ ከፌዴራል መንግሥቱና ከአጎራባች ክልል መንግሥታት ጋር ጦርነት ማካሄዱ ይታወቃል፡፡ በእነዚህ ጦርነቶች ሕዝቡ በብዙ መቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹን በጦርነቱ ከማጣቱም በላይ የመፈናቀል፣ የንብረት ውድመት፣ በኢኮኖሚና በሥነ ልቦና የመጎዳት በደል ደርሶበታል፡፡

- Advertisement -

የትግራይ ሕዝብ ታታሪ፣ ክብሩን የሚወድ፣ ለክብሩና ለእውነት የሚዋደቅ ሕዝብ ነው፡፡ በሰሜኑ የኢትዮጵያ በር ጠባቂ የጠላት ተከላካይ ነበር፡፡ ሌሎችን ማክበርን  የሚያዘወትር፣ ሌብነትና ማጭበርበርን የማይወድ ሰላማዊ ሕዝብ ነበር፣ አሁንም ነው፡፡ በእኛ ግንዛቤ ሕዝቡ ኑሮውን ለማሸነፍ ተግቶ የሚሠራ፣ ሥራ ወዳድና የሌሎች ክልሎችን ሕዝቦች ወደ ትግራይ ክልል ሲሄዱ በእንግዳ ተቀባይነቱ የኢትዮጵያ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የሚባለውን በይበልጥ የሚያረጋግጥ ሕዝብ ነው፡፡ በሥራ ፈጠራ ድፍረታቸው እንከን የማይወጣላቸው እነዚሁ ብርቱ ዜጎች ኑሮአቸውን የበለጠ ለማሻሻል፣ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎች ተበትነው በሰላም በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ጥቂቶች በኢሕአዴግ መንግሥት ወቅት ከአንዳንድ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥረው በሙስና በመሰማራት፣ ሕዝብን በሚያስቀይሙ ተግባራት ላይ ተሳትፈው ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ይሁን እንጂ የትግራይ ሕዝብ በእነዚህ ጥቂት ሰዎች ዓይን ፈጽሞ መታየት የለበትም፡፡ በእርግጥ በሁሉም ብሔር/ብሔረሰብ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ድርጊት የሚፈጽሙ ዜጎች ቢኖሩም፣ ብሔር/ብሔረሰባቸውን ሊወክሉ ይችላሉ የሚል እምነት በጭራሽ የለንም፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ የገጠመው ችግር ዋና መንስዔ የአስተሳሰብና የአመለካከት ችግር ነው የሚል እምነት አለን፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ችግር በአገራችን ባህላዊ ሆኖ የሐሳብ ልዩነቶችን በመነጋገር ከመፍታት ይልቅ፣ በኃይል በጦርነት ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለሆነም በአስተሳሰብ ላይ በመሥራት ባህሉን በመለወጥ የሠለጠነ ፖለቲካን በዚህ አገር በማካሄድ፣ በሐሳብ ልዩነት ሳቢያ የሚደረግ መገዳደልን ማስቆም በጣም አስፈላጊ ሆኖ ይታያል፡፡ በዚሁ መሠረት ክፍተቱን ለመሸፈን የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ የተወሰን አዎንታዊ ሐሳብ ያለን ኢትዮጵያውያን በመሰባሰብ መስከረም 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ሕጋዊ ዕውቅና ያገኘ፣ “አዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማኅበር” በመባል የሚታወቅ የሲቪል ማኅበር መመሥረት ችለናል፡፡ የማኅበሩ ዓላማዎች በአጭሩ ሲጠቃለሉ አዎንታዊ አስተሳሰብን በኅብረተሰቡ ውስጥ ማስረፅ፣ ሥነ ምግባሩ የተጠበቀ ትውልድን በመቅረፅ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ማገዝ፣ የውይይትና የድርድር መድረኮችን ማመቻቸትና ማስማማት፣ እንዲሁም በአገር ልማት ዙሪያ ገንቢ ምክረ ሐሳቦችን ለሚመለከታቸው ሁሉ ማቅረብን ጨምሮ በመሳሰሉት ታላላቅ ጉዳዮች ላይ የዜግነት ድርሻን መወጣት ናቸው፡፡

 1. የመነሻ ሐሳብ

የዚህ ጽሑፍ የመነሻ ሐሳብ የትግራይ ሕዝብ በጦርነት ከደረሰበት አስከፊ ችግሮች ተላቆ ዳግመኛ ወደዚህ ዓይነት ጦርነት እንዳይመለስና የክልሉም አመራር ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመከባበርና በመተማመን በቅርበት በሚሠሩበት ሁኔታ ላይ ትኩረት እንዲሰጥ፣ ከጎረቤት ክልሎች መንግሥታትና ሕዝቦች ጋር ከልብ የመነጨ ዕርቅ ተደርጎ ዘላቂ ሰላም በሚወርድበት ሁኔታ ላይ እንዲሠራ፣ እንዲሁም በቅርቡ የትግራይና የአማራ ክልል መንግሥታት መግለጫዎችን በማውጣት ሲወቃቀሱ የነበረውና በአማራና በትግራይ ወሰኖች ያለው ችግር ለሌላ ጦርነት የሚጋብዝ ሁኔታ ይፈጠር ይሆን የሚል ሥጋት በመፍጠሩ፣ እነዚህ ትንኮሳዎች እንዲገቱና የሳላም ሁኔታ እንዲቀጥል ጥረት እንዲደረግ ለማሳሰብ ነው፡፡

 1. የችግሩ ዝርዝር ጉዳዮች

በትግራይ ለተፈጠሩ ችግሮች ዋና መንስኤው የሕወሓትና የፌዴራል መንግሥት ግጭት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም. በተካሄደው ሕዝባዊ አመፅ ግፊት በለውጡ ዋዜማ ላይ ለረዥም ጊዜ (17 ቀናት) በተካሄደ የኢሕአዴግ የእርስ በርስ ግምገማና ስብሰባ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና በኋላም በጠቅላይ ሚኒስትርነት በመመረጥ የሕወሐት የበላይነት ሥልጣን አበቃ፡፡ ይሁን እንጂ የሕወሐት መሪዎች ይህንን ተቀብለው ለፌዴራል መንግሥት ሥልጣናቸውን አስረክበው ሌሎች ተፅዕኖ ፈጣሪ በሚሆኑበት መንግሥት መተዳደርን መቀበል አልቻሉም ተብሎ በወቅቱ በሰፊው ይነገር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የሕወሐት መሪዎች የለውጥ ኃይሉን አካሄድ ባለመቀበል የተቃውሞ ዝግጅቱን ማጧጧፍ ቀጠሉ፡፡ ስለሆነም ሕወሓት በትግራይ ራሱን በማዘጋጀት፣ እንዲሁም የአንዳንድ የብሔርተኛ ፖለቲከኞችን በማደራጀትና አጋር በማድረግ ሥልጣን የያዘውን የለውጥ መንግሥት በኃይል ከሥልጣን የማውረድ፣ መረጋጋትና ሰላም እንዳይኖር መሥራት ጀመረ፡፡ ይህ አንዳንድ የብሔር/ብሔረሰብ ድርጅቶችን የማደራጀት ሥራ የበለጠ ተጠናክሮ የቀጠለው በብልፅግና ፓርቲ ምሥረታ ሒደት ላይ በተፈጠረ ልዩነት ነበር፡፡ ከኦሮሞ የተወሰኑ ልሂቃንም በኋላ ላይ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ተብሎ የነበረውን ኦሕዴድን አፍርሶ፣ አገር አቀፍ ብልፅግና የሚባል ፓርቲ እንዲቋቋም ያለመፈለግ ተቃውሞ ነበር፡፡ ሕወሓትም ተመሳሳይ አቋም ስለነበረው በዚህ ሳቢያ ሌሎችም ተመሳሳይ አቋም ያላቸውን ማሰባሰብ ቀጠለ፡፡ ይህ እያንዳንዱ ከክልል የራሱን ፓርቲና የክልል መንግሥታት ኖሮት በእነዚህ ስምምነት ማዕከላዊ መንግሥት ያቋቁሙ የሚለው አቋም የብሔርተኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አቋም የነበረ ቢሆንም፣ ይህ በተለይ የዓብይን (ዶ/ር) አካሄድ በመጠራጠርና የቀድሞ ዓይነት ብሔር/ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን የሚጨቁን አሀዳዊ መንግሥት እንዳይመሠረት ለመከላከል ሲሉ ነው የሚሉም አሉ፡፡ በሁለቱ መካከል የነበረውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የአፍሪካ ኅብረትና የፌዴራል መንግሥት ብዙ ጥረት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ የሴቶች ተወካይ እናቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ በአዲስ አበባ የሚኖሩ ታዋቂ የትግራይ ባለሀብቶችና የውጭ አገር አምባሳደሮች ሳይቀሩ ወደ መቀሌ ተልከው ውጤት ሳይገኝ ቀርቶ ሦስት ጊዜ ጦርነት ተካሂዶ በኋላ በፕሮቶሪያ ስምምነት መቋጨቱ አይዘነጋም፡፡ በዚሁ መሠረት የማንነትና የወሰን ጥያቄ ከተነሱባቸው ጉዳዮች ሁለቱም ኃይሎች ማለትም የትግራይና የአማራው በሚጠቅማቸው መንገድ የፌዴራል መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ ፍላጎት ግን ሁለቱም ሰጥቶ በመቀበል መርህ ዓይነት በመጀመሪያ የተፈናቀሉት ዜጎች ወደ የቤታቸው እንዲመለሱና ከመሀላቸው በሚመርጡት አካል እንዲተዳደሩ፣ የፌዴራል የፀጥታ ኃይል ጥበቃውን እንዲያካሄድና ከተወሰኑ ጊዜያቶች በኋላ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግና የሕዝቡን ውሳኔ ሁለቱም እንዲቀበሉ ይፈልጋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ የትግራይ ፖለቲከኞች የአካባቢዎቹ  ፀጥታ ቁጥጥር በትግራይ ክልል ሥር እንዲሆን ይሻሉ፡፡ በዚህ ሳቢያ ከትግራይ አካባቢ የተወሰኑ ኃይሎች ለጦርነት እየተዘጋጁ እንደሆነ ይገለጻል፡፡

የጦርነቱ ዓላማ ወልቃይት፣ ጠገዴንና የማንነት ጥያቄ የተነሳባቸውን የራያ አካባቢ በኃይል ለማስመለስ ከሆነ ባለፉት ወቅቶች ጦርነት ተሞክሮ ውድመት እንጂ፣ ውጤት ያላስገኘ አሁንስ አሸናፊና ተጠቃሚ የሚያደርግ ምን የተለየ ሁኔታ ተፈጠረ? ሌላ ጦርነት የሚታቀድ ከሆነ ፈጽሞ ለትግራይ ሕዝብ ማሰብና መቆርቆር  ሊሆን አይችልም፡፡ ቂምና እልህ ውጤታማ አያደርግም፡፡ ቂም በቀል የበለጠውን የሚጎዳው ይህን ሐሳብ የሚያራምደውን ነው፡፡ የእዚህ ዓይነት ጦርነት አሸናፊ ስለማያደርግ ዳግመኛ ይህ መሞከር የለበትም ነው የምንለው፡፡

በኢትዮጵያ ችግሮችን በጦርነት ለመፍታት መጣር ከአሁን በኋላ መታሰብ የለበትም፡፡ ግን ይህ በትግራይ ሕወሓት፣ በኦሮሚያ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መንግሥት ሸኔ የሚለውና በአማራ ራሳቸውን ፋኖ የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያካሄዱት ጦርነት አሸናፊ የማያደርገው ጦርነቱ እውነታን ወይም በቂ ምክንያት ይዞ ባለመነሳት የሕዝብ ድጋፍም ማግኘት ያለመቻል ነው፡፡ በአገሪቱ ለውጥ በተጀመረበት ጊዜና የሕዝብ ድጋፍ ለለውጥ ኃይሉ በሚኖርበት የዚህ ዓይነት ውጊያ የሕዝቦችን  ጥቅም የተፃረረ በመሆኑ ነው አሸናፊ የማያደርገው፡፡ ስለዚህ ለእነዚህ ኃይሎች የዚህ ዓይነት ጦርነትን ለማሸነፍ አይቻላቸውም፡፡ ይህ የጀግንነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላው የዚህ ዓይነት እርስ በርስ መጋጨት ለውጭ በተለይ የኢትዮጵያ ጠላቶች ለሚባሉት አገሮችና ለአንዳንድ የምዕራባዊያን አገሮችም የሚጠቅምና ለአገር መከፋፈልም የሚዳርግ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጦርነቱን በመቃወም ከመንግሥት ጎን እንዲሠለፍ ሆኗል፡፡ ስለሆነም በዚህ የለውጥ ጊዜ በተለይ የትግራይን ሕዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር በማዋጋት በጦርነት አሸናፊ እንሆናለን ብሎ መነሳት ከባድ ስህተት ነበር፡፡ ከዚህ በፊት ሕወሓት ደርግን ያሸነፈበት ጊዜና አሁን የተለያዩ ናቸው፡፡ በፊት የነበረው የደርግ ሥርዓት ያረጀበትና ለውጥ የሚፈለግበት ጊዜ ሲሆን፣ ለደርግ መሸነፍ የኢትዮጵያ ሕዝብና የሌሎችም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች አስተዋጽኦ ነበራቸው፡፡

በትግራይ የሚስተዋሉ ችግሮች በአራት ዋና ዋና ጉዳዮቶች ላይ የተመሠረቱ ሆነው ይታያሉ፡፡ እነዚህም ስህተቶችን አምኖና ተቀብሎ ያለማረምና የሰጥቶ መቀበልን መርህ መተግበር ያለመቻል፣ የትግራይን ሁለንተናዊ ቁመና ከቁጥር ባስገባ መጠን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ ለመወሰን መቸገር፣ የትግራይ ሕዝብ ክብር ተደፈረ፣ ሕዝቡ የህልውና ሥጋት አለበት የሚል ዕሳቤ መያዝ፣ የወልቃይትና የሌሎች የማንነት ጉዳዮችን እንደ የትግራይ ብቸኛ ህልውና ማድረግና ለዚህ አስፈላጊ ያልሆነ መስዋዕትነትን መክፈል የመሳሰሉት ናቸው፡፡

3.1 ስህተቶችን አምኖ አለማረምና የሰጥቶ መቀበልን መርህ መተግበር አለመቻል

በትግራይ በሐሳብ መሸነፍን መቀበል፣ በሐሳብ ብልጫነት መሸነፍን ማስተናገድ አለመቻል ይስተዋላል ይባላል፡፡ በሐሳብ መሸነፍ እንደ ውርደትም ይቆጠራል፡፡ በሌላ በኩል የትግራይን ሰው በመፎከርና በማስፈራራት ሐሳብን እንዲለውጥ ማድረግም አይሞከርም፡፡ ዜጎቹ ለክብራቸው የሚዋደቁ በመሆናቸውና ‘አባቶቻችን ሽንፈትን አላስተማሩንም’ የሚልም ባህል በውስጣቸው የገነቡ በመሆኑ፣ ሞትን በመፍራት ከዓላማቸው ወደኋላ መመለስ የለም፡፡ በትግራይ ተወላጆች ምናልባት የእነዚህ ሁሉ ዕሳቤዎች ድምር በተደረገው የፖለቲካ ልሂቃኑ አነሳሽነት ቀላል ግምት የማይሰጠው ኅብረተሰብ ለዚህ አልሸነፍም ባይነት ጦርነት ዳርጓል ተብሎ ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል አልሠለጠነም የሚባለው አንዱ መገለጫ ልዩነቶችን በውይይት፣ በመደማመጥና በመተማመን ስህተት የሠራው ስህተቱን አምኖ ተቀብሎ በስምምነት ጉዳዮችን መቋጨት አለመቻል ነው፡፡ ስህተት ዕውቀት የሚገበይበት ትልቅ የትምህርት ምንጭ ነው፡፡

ከዚህ በፊት ከነበሩት ጦርነቶች ከደረሱት ብዙ ጉዳቶች መማር ሲገባ ባለፈው በየካቲት ወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) ከትግራይ ከተወከሉ የሕዝብ ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት፣ ሕወሓት አመራር ውስጥ አሁንም ለሌላ ጦርነት የሚያስቡ እንዳሉ የነገሩን መረጃ አስደንጋጭ ነበር፡፡ ሦስት ጊዜ ጦርነት ተካሂዶ ከደረሰው ፍጅትና ውድመት ባለመማር ለአራተኛ ጊዜ ለመዋጋት ማሰብ ጤናማ ሊሆን አይችልም፡፡ ከዚህ በፊት በደረሱት ስህተቶች አለመፀፀትም ይሆናል፡፡ ሌላው ለግጭቱ የበለጠ መባባስ በሰላማዊ መንገድ በድርድርና በውይይት እንዳይፈታ ምክንያት የሆኑት የሕወሓት መሪዎች፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ሽምግልናን መቀበል አለመቻል ነው፡፡ የሕወሓት መሪዎች ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ላነጋገሯቸው የአገር ሽማግሌዎችና የሃይማኖት መሪዎች እኛ ብቻችንን አይደለም የምንነጋገረው ሌሎችም ሊሳተፉ ይገባል ሲሉ፣ አሁኑኑ የሽግግር መንግሥት ካልተቋቋመ ከሚሉ ኃይሎች ጋር ነን ማለታቸው እንደነበር የሚገመት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከለውጥ መሪዎቹ ፍላጎት በተፃረረ ልዩነቶቹ እንዲፈቱ መፈለግ በመሆኑ ወደ ስምምነት ሊወስዱ አልቻሉም፡፡

ሌላው ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላም ቢሆን ሕወሓት ስህተቶቹን አምኖ ተቀብሎ ከልብ በመሥራት ላይ፣ እንዲሁም መንግሥት በስምምነቱ መሠረት የሚጠበቅበትን ግዴታ በመወጣት ላይ አዝጋሚነት ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ የክልሉን ሕዝብ በተረጋጋ መንፈስና በተስፋ በሙሉ ኃይሉ ወደ ልማት ሥራ እንዳይገባ አድርጎታል፡፡ ሌሎች ኢንቨስተሮች በተለይ በመቀሌ ኢንዱስትሪ ፓርክ ኢንቨስት አድርገው ያቋረጡ፣ እንዲሁም አዳዲሶቹ ተማምነው እንዳይገቡ ይህ ሁኔታ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ ወጣቶችም ተስፋ በመቁረጥ ከክልሉ ውጪና ሌሎች አካባቢዎች እየፈለሱ ነው የሚሉ መረጃዎች ይደመጣሉ፡፡ በዚህም ሕዝቡና አገር እንዲጎዳ ተደርጓል፡፡

በእርግጥ በዚሁ ረገድ ተስፋ የሚሰጠው የትግራይ ሕዝብ አሁን ሌላ ጦርነት እንዲካሄድ እንደማይፈልግ ነው፡፡ ሕዝቡ ጦርነት ጉዳት እንጂ ጠቀሜታ እንደሌለው ከዚህ በፊት ከተካሄዱ ጦርነቶች በቂ ትምህርት አግኝቷል፡፡ በየካቲት ወር 2016 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ በዩቲዩብ በተላለፈው አንድ ቪዲዮ ኮሎኔል ቢኒያም ተወልደ ያስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹የትግራይ ሕዝብ እንደገና ወደ ጦርነት መግባት የለበትም፡፡ ከዚህ በፊት ስህተት ነው የተፈጸመው፤›› በሚል በግልጽ ያንፀባረቁት ሐሳብ የትግራይን ሕዝብ ይወክላል ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ነው፡፡ ብዙዎች ይህንን ሐሳብ የሚያንፀባርቁ ቢሆኑም፣ የኮሎኔሉ ትኩረት ሊያገኝ የሚገባው ባለፈው ጦርነት አምነው በረሃ ድረስ የዘመቱ ስለሆኑና ለዚያው ጭምር በመፀፀት በድፍረት በዚህ መልክ  ስሜታቸውን መግለጻቸውም ነው፡፡ ከአሁን በኋላ በማስታረቅ ሥራ ነው የምሳተፈው ማለታቸውም የሚያስመሠግናቸው ነው፡፡ ስለሆነም ይህንኑ አስተሳሰብ ሌሎች ፖለቲከኞችና ምሁራንም ቢጋሩትና ቢተገብሩት መልካም ይሆናል፡፡

3.2 የትግራይን ሁለንተናዊ ቁመና ከቁጥር ውስጥ ባስገባ መጠን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ የመወሰን ችግር 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ ግንባር ቀደም ሚና ካላቸው ብሔር/ብሔረሰቦች የትግራይ ሕዝብ ፖለቲከኞች ይገኙበታል፡፡ ከአፄ ምኒልክ በፊት የትግራይ ተወላጅ የሆኑት አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያ መሪ መሆንና በኢትዮጵያ ታሪክ ከሰሜን የድንበር መከላከል ጋር ተያይዞ፣ የትግራይ ተወላጆች በኢትዮጵያ ፖለቲካ የላቀ ተሳትፎ እንደነበራቸው ታሪክ ያረጋግጣል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመንም መንግሥታዊ የሥልጣን ድርሻን በፓርቲ የሥልጣን ክፍፍል በተረጋገጠው በሩብ እጅ በመያዝና የመሪነት ሚና በመውሰድ ሕወሓት የበላይነት ስለነበረው፣ ሥልጣኑ ከሁሉ የሚልቅ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሁኔታ በለውጡ መንግሥት ሊቀጥል የማይችል መሆኑ የግድ ሲሆን ነው ሕወሓት እውነታውን መቀበል ባለመቻል፣ በአዲሱ መንግሥት ላይ ማመፅ የጀመረው ተብሎ ይታመናል፡፡ የእኩልነትና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት በኢትዮጵያ እንዲመሠረት ካስፈለገና የብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ መንግሥት እስካለ ድረስ፣ የሥልጣን ምንጩ በብሔር/ብሔረሰብ የሕዝብ ቁጥር ላይ የተመሠርተ መሆኑ የታወቀ በመሆኑ ይህን ሁኔታ የትግራይ ፖለቲካኞች መቀበልና መተግባር የግድ ይሆናል ማለት ነው፡፡

3.3  የትግራይ ሕዝብ የህልውና ሥጋት አለበት የሚለው ትርክት 

በአንዳንድ የትግራይ ፖለቲከኞች ዘንድ በሕዝባችን ላይ የተደቀነውን የህልውና አደጋ ለመከላከል ነው ጦር የምናዘጋጀው የሚባል ነገር አለ፡፡ የትኛው የኢትዮጵያን አካል ነው የትግራይን ሕዝብ የሚያጠቃው? ለምንድነው ሕዝቡስ የሚጠቃው? ከፌዴራል መንግሥትና ከሕወሓት መነታረክ ካልሆነ በስተቀር እንደ ሕዝብ የትግራይን ሕዝብ የሚያጠቃ ምንም ነገር አልታየም፡፡ በእርግጥ በጦርነት ወቅት በአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና የፌዴራል መንግሥት በሕዝቡ ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ ደግሞ የጦርነት አስከፊው ገጽታ ስለሆነ ማስወገድ አይቻልም፡፡ በእርግጥ ከኤርትራ መንግሥት የዚያ ዓይነት ሥጋት ይኖራል እንኳ ቢባል የኢትዮጵያን ድንበር የሚጠብቀውና የሚከላከለው የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል ሥራው ይህስ አይደለም እንዴ? በዚህ ጉዳይ ሕዝቡን በማስፈራራት አስፈላጊ ላልሆነ ሥጋት መዳረግ ተገቢ አይሆንም፡፡ ተደጋግሞ እንደተገለጸው ይህ ጦርነት ሕዝብ ለሕዝብ የተደረገ አይደለም፡፡ ለዚህ ማረጋገጫው የሕወሓት ታዋጊዎች በአማራ አዋሳኝ ክልሎች ጦርነት ካደረጉ በኋላ፣ በ2014 ዓ.ም. የካቲት/መጋቢት ላይ በረሃብ የተጎዳው የትግራይ ወገኖች የሸሹት ወደ ጎረቤቶቻቸና ታሪካዊና ባህላዊ ትስስር ወደ አላቸው የአማራ ሕዝብ ነበር፡፡ የአማራ ሕዝብም በትግራይ ተዋጊዎች እንደዚያ ያለ በደል ደርሶበት እያለ የጋራ ባህልና ታሪክ ያለው ሕዝብ በመሆኑ፣ ረሃብን ሸሽተው የተጠጉትን የትግራይ ወንድሞችና እህቶች ወገኖች ከቂምና በቀል ነፃ በሆነ መንገድ በሰላም ተቀብሎ ማስተናገዱ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በድንበር ላይ ያለው የአማራ ሕዝብ ጦርነቱ ባደረሰበት ጉዳት ራሱ በችግር ላይ ሆኖ እያለ ተጎጂዎችን የትግራይ ኅብረተሰብ ቂም ሳይዝ በጨዋነት ማስተናገድ፣ ሕዝብ ለሕዝብ የነበረው ትስስርና መተሳሰብ ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህም በሕዝቦች መካከል የጠላትነት መንፈስ በጭራሽ የሌለ መሆኑን ያሳያል፡፡ በትግራይም ውስጥ በሌሎች ብሔር/ብሔረሰብ አባላት ላይ የደረሰ ምንም ዓይነት የመጠቃት ሁኔታ አልነበረም፡፡

በመጀመሪያው የመንግሥት ለውጥ ወቅት ከጎንደር እንዲፈናቀሉ የተደረጉትን የትግራይ ተወላጆችን በተመለከተ ጦርነቱ ሳይካሄድ በፊት አንዳንድ የጎንደር ነዋሪዎች በቁጭት ሲናገሩ የነበረው፣ ‹‹ጥቂት ስሜታዊ የሆኑ ወጣቶች ለብዙ ዓመታት በጥሩ ጉርብትና አብረን የኖርነውን የትግራይ ተወላጆችን አፈናቅለው አለያዩን፤›› የሚል ነበር፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ የማፈናቀል አድራጎት በአማራ ሕዝብ እንደተከናወነ መውሰድ አይገባም፡፡ ሕዝቡ እንደዚያ እንዲደረግ ውክልና ለእነዚህ ወጣቶች አልሰጠም፡፡ ግን ጊዜው የሽግግርና ሥርዓተ አልበኝነት የሰፈነበት በመሆኑ ሕዝቡ ይህን ድርጊት መከላከል አለመቻሉ ነበር ፀፀቱ፡፡ ወጣቶችን ለዚህ የሚዳርገው ቀደም ሲል በሕወሓት የበላይነት የሚመራው መንግሥት በአማራው ሕዝብ ላይ አንዳንድ ዜጎች ባለሥልጣናትን መከታ በማድረግ ያደረሱት በደልን የተበቀሉ መስሏቸው ይሆናል፡፡ ይህ በፍፁም ስህተት በመሆኑና የወቅቱ የክልሉ መንግሥትም መከላከል ባለመቻሉ ጥፋተኛነቱን አምኖ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል በትግራይ አንዳንዶች መንግሥት ለውጭ ኃይል አጋልጦን ሰጠን በማለት መንግሥትን ሲተቹ ይሰማል፡፡ በእርግጥ የኤርትራ ጦር የሚሰቀጥጡ በደሎችን በትግራይ ሕዝባችን ላይ ማድረሱ ይታወቃል፡፡ ይህ ወታደሮች ያደረሱት ግፍ የጦር ወንጀል በመሆኑ የሚወገዝ ተግባር ነው፡፡ በሌላ በኩል በመቀሌ ከተማ እንደ ሌሎቹ አካባቢዎች ጉዳት እንዳይደርስ ሕዝቡ ነቅሎ በመውጣት የመከላከያ ኃይሉም ዕገዛ በማድረግ፣ በመከላከል ከተማው ከዘረፋና ከውድመት መትረፉ ይነገራል፡፡ የትግራይን ሕዝብ የሚከላከልን ኃይል የመታውና ሕዝቡን ለዚህ የዳረገው የሕወሓት የተሳሳተ ዕርምጃ መሆኑ ግን ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል በወቅቱ ከትግራይ ተዋጊ ኃይሎች ጋር በውጊያ ላይ የሚገኝ የመከላከያ ኃይል የትግራይን ሕዝብ ለመከላከል ከኤርትራ ጦር ጋር ለመዋጋት ሁኔታዎች የሚፈቅዱ አልነበሩም፣ ሊሆንም አይችልም፡፡

ሌላው በአንድ አገር ሁለት የተለያዩ ታጣቂ ኃይሎች መኖር ለአገር አንድነትና ሰላም ጠንቅ ነው፡፡ በ1983 እና 1984 ዓ.ም. ከኦነግ ጦር ጋር የነበረው ግጭት፣ እንዲሁም በጎረቤታችን ሱዳን የገጠመው ሁኔታ ይህንን እውነታ ያረጋግጣል፡፡ ስለሆነም አሁንም 270 ሺሕ የትግራይ ኃይል ስለመኖሩ የሚሰማው ድምፅ የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ጦር በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት ትጥቁን ፈትቶ ወደ ሌሎች የሥራ መስኮች መሰማራት ያለበት ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች በተለያዩ ሥራዎች ተሰማርተው ትግራይን ቢያለሙ ነው ለሕዝቡ የሚጠቅመው፡፡ ጥርጣሬው ትክክል ከሆነ የትግራይ ሕዝብ ይህን ይታሰባል የሚባለውን ጦርነት አጥብቆ በመኮነን መቃወም ይኖርበታል የሚል እምነት አለን፡፡ የትግራይን ሕዝብ የሚያጠቃ ኃይል ካለም እንዲሁ የፌዴራል መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትግራይ ሕዝብ ጎን መሰለፍ ግዴታቸው በመሆኑ፣ የትግራይ ሕዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለየ ሁኔታ ሊሰጋ አይገባም፡፡ ይልቅስ የበለጠ ለመተማመን የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ከተለያዩ የኅብረተሰብ አካላት ጋር የግንኙነትና የውይይት መድረኮችን በመፍጠር አጠንክሮ መቀጠሉ የበለጠ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

3.4  የወልቃይትና የሌሎች የማንነት ጉዳዮችን እንደ የትግራይ ብቸኛ ህልውና መውሰድ

የማንነትና የወሰን ጥያቄ የተነሳባቸው ጉዳዮች በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዋና የፖለቲካ ስበት እንደሆኑ ይታያል፡፡ እነዚህ አካባቢዎች ቀደም ባሉት ጊዜያት በቅደም ተከተል በጎንደርና በወሎ ጠቅላይ ግዛቶች/ክፍለ ሀገሮች ሥር ይተዳደሩ ነበር የሚለው ክርክር ከአማራው ክልል ፖለቲከኞች ይነሳል፡፡ በትግራይ ወገን ደግሞ ጥንትም በትግራይ ሥር የነበሩ ሲሆን፣ በኋላ በቋንቋ ላይ በተመሠረተው አከላለል የትግራይ ክልል አካል ሆነዋል የሚል ሐሳብ ይደመጣል፡፡ ይሁን እንጂ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ በሁለቱ ወገኖች መግባባት ላይ አልተደረሰም፡፡ ከ2010 ዓ.ም. ለውጥ በፊት ጀምሮ የወልቃይት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ተመሥርቶ አቤቱታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር ሲያቀርብ ነበር፡፡ ከለውጡም በኋላ ይኼው ጥያቄ ምላሽ ባለማግኘቱ እንደገና ሲነሳ ነበር፡፡ ይህ በዚህ እያለ በ2013 ዓ.ም. በተካሄዳው የሰሜኑ ጦርነት እነዚህ አካባቢዎች ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ተነጠቁ፡፡ ቀደም ሲል በጦርነት የተያዙብንን በጦርነት አስመለስነው የሚሉት የአማራ ፖለቲከኞች ይዞታውን አጠናከሩ፡፡ ይህ ሁኔታ ለትግራይ ፖለቲከኞች የማይዋጥ ስለነበር አካባቢውን መልሶ ለመያዝ ብዙ የውጊያ መከራ ተደረገ፡፡ ይህም ባለመሳካቱ ጉዳዩ ለፖለቲከኞቹና በትግራይ ሕዝብም ቁጭትን የጫረ ትልቅ ርዕስ ሆኖ ይገኛል፡፡

 1. የመፍትሔ ሐሳቦች

2.1. የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከሕወሓትና ከትግራይ ሕዝብ ምን ይጠበቃል?

በትግራይ የተፈጠረው ጥፋት ዳግመኛ እንዳይከሰት እዚህ ላይ ቆሞ የአስተሳሰብ ማስተካከያ ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሁልጊዜ በእልህ ላይ የተመሠረቱ ዕርምጃዎች ጉዳትን ያስከትላሉ፡፡ በማስተዋልና በተረጋጋ ሁኔታ ጥቅምና ጉዳትን አመዛዝኖ መወሰን ጠቃሚ ነው፡፡ ስለሆነም ያሉትን ዓለም አቀፋዊ፣ አገራዊና የትግራይ ክልል ሕዝብን ሁኔታን ባገናዘበ መልኩ ክስተቶችን በመተንተን ካለፈው ስህተት በመማር ወደ ሰላማዊ ሁኔታ የሚያመጣ ውሳኔ ላይ መድረስ ያስፈልጋል፡፡ ሕዝቡ የመሸነፍ ስሜት ፈጽሞ ሊሰማው አይገባውም፡፡ በጦርነት የተሸነፈውና የሚሸነፈው የትግራይ ሕዝብ አይደለም፡፡ የሚሸነፈውና የተሸነፈው የጥቂት የሕወሓት መሪዎች የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡ ይህ ከትግራይ ሕዝብ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ አይደለም፡፡ በእኛ ግምትና እምነት በተወሰኑ የፖለቲካ ልሂቃን የተፈጠሩና የተመሩ በጥርጣሬ ላይ የተመሠረቱ አሉታዊ አስተሳሰቦች ናቸው፣ ከላይ የተገለጸውን የትግራይ ሕዝብ ዕሴት እንዲሸረሸር ያደረጉት፡፡ በሌላ በኩል እነዚህ ድርጊቶች የፖለቲከኞች አሉታዊ የጥላቻ ቅስቀሳዎች ሕዝብን ከማሳሳትም ባሻገር፣ ሌሎች በፍርኃትና በይሉኝታ የአሉታዊ አስተሳሰቡ ተጋሪ ተደርገዋል ማለትም ይቻላል፡፡

ማንኛውም ወገን ከጦርነትና ከጠላትነት የሚያተርፈው ጥቅም የለም፡፡ ስለዚህ ለዚህ ሲባል ልጆቻችን የጦር መሣሪያ ተሸካሚ ሳይሆኑ የደብተርና የእርሳስ ተሸካሚ እንዲሆኑ ነው መሠራት ያለበት፡፡ ስለዚህ በሁሉም ወገን በአማራ ክልል የሚገኙት የፖለቲካ ልሂቃንም ካለፈው ስህተት በመማርና በመፀፀት ለሕዝቦቻችን፣ ለአገራችንና በተለይ ለታዳጊ ወጣቶቻችን ስንል ከልብ የመነጨ፣ ከቂምና በቀል የፀዳ፣  ዕርቀ ሰላም ለማውረድ ከልብ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከአሁን በኋላ ከጦርነት አዙሪት ውስጥ በመውጣት ወደ ልማት በመዞር የባከነውን ጊዜ ለማካካስ ነው መሠራት ያለበት፡፡ የትግራይ ሕዝብ ይህን ጉዳይ እንደ የትምህርት የፈተና ጊዜ ከባድ ጥያቄን አልፎ በመሄድ ቀላል ጥያቄዎች ከተሠሩ በኋላ፣ ተመልሶ እንደገና መሞከር ዓይነት ዋና መከራከሪያ የሆኑትን የማንነትና የወሰን ጉዳዮችን ለጊዜው ይህ ለወደፊት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ፍፃሜ ያግኝ በሚል ቢያልፈው ይሻላል፡፡ ይልቅስ ወደ መደበኛ የልማት ሥራና አዋራጅ የሆነውን ድህነትን በመግታት ሥራ ላይ መጠመዱ ነው ለትግራይ ሕዝብ የሚጠቅመው፡፡ በሌላ በኩል ይህንን ትቶ መልካሙን በማሰብ ሕዝቡ በአንድነት ከተነሳ በሌላው የኢትዮጵያ ክልል የሚኖረውና በውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች በግንባር ቀደምነት፣ እንዲሁም መንግሥትና ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተረባርበው በቅንጅት ከተሠራ ትግራይን በአጭር ጊዜ ማልማት ይቻላል፡፡

ትግራይ በማዕድን ሀብትና በታታሪ ሠራተኛ የሰው ሀብት የታደለች፣ ብዙ የተማሩ ተወላጆች በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ በመሆናቸው እነዚህን ፀጋዎች በአዎንታዊነትና በይቻላል ሙሉ መንፈስ በማንቀሳቀስ መሥራት ነው የሚያስፈልገው፡፡ በአክሰዮን መልክ፣ በግለሰብና በሽርክና ኢንቨስትመንቶች በርካታ ትልልቅ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ይቻላል፡፡ አገልግሎት የመስጫ ሥራዎችንም ማስፋፋት ሌላው መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በተለይ በቂ ጥሬ ዕቃ በመኖሩ የሲሚንቶ ፋብሪካዎችን በአክሲዮን መልክ በማቋቋም ለኤክስፖርት ገበያ ጭምር ሲሚንቶ በብዛት ለማቅረብ ሰፊ ዕድል አለ፡፡ ከዚህ በፊት የተጀመረው በጨው ላይ የተመሠረተው ኮስቲክ ሶዳ፣ ክሎሪን፣ በረኪና፣ እንዲሁም የፕላስክ ጥሬ ዕቃዎች ከሆኑት አንዱ የሆነውን ፒቪሲ ለማምረት የታሰበውን ፕሮጀክትንም ከፍፃሜ በማድረስ በርካታ የሥራ ዕድሎችን በተለይ የኋልዮሸና የወደፊት ትስስሮችን ለመፍጠርና የውጭ ምንዛሪን በማደን ጭምር ለክልሉ ሕዝብና ለአገር ትልቅ አስተዋጽኦ ያላቸውን ሥራዎች ወደ መሥራቱ መግባቱ የበለጠ ይጠቅማል፡፡ ስለሆነም የዚህ ጠንካራና የሥራ ወዳድ የሆነው የትግራይ ሕዝብ፣ እንዲሁም ፖለቲከኞች የህሊና ጉዳት የሚታደገው በዚህ ዓይነት የልማት ሥራ በመሳተፍ አገርንና ሕዝብን በመካስ መሆን አለበት፡፡

2.2. የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትስ ምን ይጠበቃል?

ከመጀመሪያው ጦርነት በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ብዙ ገንዘብ መድቦ የምግብ ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ ሲያቀርብና የወደሙትን የመሠረተ ልማት ሥራዎችን ሲሠራ ነበር፡፡ የተለያዩ ማኅበረሰቦችና የክልል መንግሥታት ከሕዝባቸው ቀንሰው ዕርዳታ ለትግራይ ሕዝብ እያቀረቡ የሕዝብን ሕይወት ለመታደግ ሞክረዋል፡፡ በቅርቡም ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላም በሕዝብም ሆነ በክልል መንግሥታት፣ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት በርካታ ድጋፎች ለትግራይ ሕዝብ ሲደረግ መቆየቱን መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡፡ አሁንም ይኼ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም የትግራይ ሕዝብን ማበራታታትና ከጎኑ መሆኑን የበለጠ ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በትግራይ በጦርነቱ ምክንያት የተፈጸሙት ጉዳቶች በርካታ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጦርነቱ ያስከተላቸውን ችግሮች አጉልቶ በማውጣት በውጤት ላይ ብቻ በመመሥረት የጎረቤት አገር ንብረት ወሰደ፣ ሰው ገደለ፣ ወዘተ. የሚባሉትን በማራገብ ደጋግመን ሕወሓትን መርገምና መተቸት አብሮ የተሠለፈውን የትግራይ ሕዝብ የሥነ ልቦና ስብራትን ከማባባስ የዘለለ ጠቀሜታ የለውም፡፡ ጥፋቱ ከሚታሰበው በላይ በሆነ ሁኔታ ተፈጽሟል፡፡ ስህተቶች ይፈጠራሉ፣ ተፈጥረዋልም፡፡ ሆኖም ይህንን ከእነ ቆሻሻው ቀብሮ ለወደፊት በሚደረጉት ላይ ነው ጊዜ ማጥፋት የሚያሻው፡፡ ከሦስቱም ክልሎች የተጎዱ ወገኖችን በሥነ ልቦና ማከም፣ ማቋቋም፣ ኢኮኖሚያዊ ድጋፍ ማድረግ፣ ወዘተ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው፡፡

 1. ጊዜ ሳይወስዱ መደረግ የሚገባቸው ተግባራት

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት በአፍሪካ ኅብረትና በአሸማጋይ ወገኖች መፈጸም ያለባቸው ተግባራት እንደተጠበቁ ሆነው የሚከተሉት ተጨማሪ ዕርምጃዎች እንዲወሰዱ ምክረ ሐሳብ እናቀርባለን፡፡

 1. ጉዳዩን ለሰላም ሚኒስቴር በማቅረብ በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ አማካይነት የሚመለከታቸው አካላት የአፈጻጸም ፕሮግራሞችን በጋራ በመንደፍና በጀት ከሚመለከታቸው አካላት በማስፈቀድ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመር፣
 2. አሸማጋይ የሚሆኑትን ገለልተኛና ዕውቅና ያተረፉ ኢትዮጵያውያንን መምረጥና መመደብ፣
 3. መቀሌ በመጓዝ በጉዳዮቹ ዙሪያ ከክልሉ መሪዎችና ከሕዝብ ተወካዮች ጋር መመካከር፣
 4. ከአማራና ከአፋር የመንግሥት መሪዎችና የሕዝብ ተወካዮች ጋር በየክልሎቹ ዋና ከተማዎች እንዲሁ መነጋገርና መመካከር፣
 5. ሕዝብ ለሕዝብ ያለውን ቁርሾ ለማስወገድና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የየክልሉ የሕዝብ ተወካዮች በመቀሌ፣ በባሕርዳርና በሰመራ የሚገናኙበትን መድረክ መፍጠር፣
 6. በመጨረሻም ሁሉንም ወገኖች ያካተተ የሰላምና ዕርቅ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሚገኙበት በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ማድረግና የመሳሰሉት ናቸው፡፡
 7. ማጠቃለያ

የትግራይ ምሁራን፣ የንግድ ማኅበረሰብ፣ የፖለቲካ ኃይሎች፣ እንዲሁም ሌላው የኅብረተሰብ አካል ከእልህና ቂም በቀል በፀዳ መንገድ፣ በአዎንታዊነት የበጎ መንፈስ በትግራይ የገጠመውን ችግር ለመፍታት ከልብ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ ቀደም ሲልም የትግራይ ምሁራን ለምን የዚህ ጦርነት አካል ሆኑ የሚለው ብዙ ያነጋግራል፡፡ ምሁርነት ጠቀሜታው ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመር ጥቅምና ጉዳቱን አሥልቶ ለወገንና ለአገር የሚጠቅመውን መንገድ ማሳየትስ መሆን አልነበረበትም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ያጭራል፡፡ በአሁኑ በ21ኛ ከፍለ ዘመን ልዩነቶች በዘላቂነት በጦርነት ይፈታሉ ብሎ ማሰብ ራሱ የምሁርነትን ማንንነት ከጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ በእርግጥ ይህ ጉዳይ የትግራይን ብቻ ሳይሆን የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ምሁራን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ የትግራይ ሕዝብ አሁን ጦርነት ይበቃዋል፡፡ በንፁህ ልቦና ሁኔታዎችን በማስተዋል ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ የሚወስዱትን ፖለቲከኞችን መስመር ማስያዝ አለበት፡፡ የማንነትና የወሰን ጥያቄ የሚነሱባቸው አካባቢዎችም በሰላማዊ መንገድ ማስመለስ፣ ሕጉና ሌሎች ሁኔታዎች ካልፈቀዱ ውሳኔውን ተቀብሎ ሌላውን ትግራይ በማልማት ከድህነት በመውጣት ላይ ነው ማተኮር  የሚያስፈልገው የሚል እምነት አለን፡፡

ይህ ጉዳይ የአገራችንን የመጠፋፋት ፖለቲካ ባህል የመቀየሪያ አዲስ ቁልፍ ሆኖ ከዚህ በኋላ በዚህ አገር ሥልጣን ላይ የሚገኝን መንግሥት በሴራና በተንኮል፣ እንዲሁም በኃይልና በትጥቅ ከሥልጣን የማውረድ አስተሳሰብ መቅረት ነው ያለበት፡፡ ሰላማዊ በሆነና በሐሳብ ብልጫነት በአብሮ አሸናፊነት የሥልጣን ርክብክብ የሚደረግበትና የመከባበር፣ የመቻቻል፣ የመተሳሰብና የመተጋገዝ ባህል ነው መለምለም የሚኖርበት፡፡ ይህን አጋጣሚ አገራችን ወደ ሥልጣኔና ወደዚህ የፖለቲካ ባህል ለውጥ አስተሳሰብ የምትቀየርበት ሥርዓት ማክበሪያ ገጸ በረከት በማድረግ ይህን የእልህኝነትና የቂም በቀል አጀንዳ እንቅበረው፡፡ ለዚህ ጦርነት መንስዔ የሆኑ ኃይሎች ከስህተታቸው በቂ ትምህርት ያገኙ ስለሆኑ በድርጊታቸው እየተፀፀቱ እንዲኖሩ ቀጣይ ትውልድ እነሱን በመበቀል ሳይሆን፣ በቅርቡ በታዘጋጀው የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ስህተቶቹ ዕውቅና አግኝተው ጥፋተኛው ጥፋቱን አምኖ ምሕረት በመደራረግ ከሚገኘው የህሊና ቅጣት እንዲማር ማድረጉና የተጎዱ ዜጎች የሚካሱበት ሥርዓት ቢፈጠር ለአገራችን የበለጠ ይጠቅማል ብለን  እናምናለን፡፡

የሕወሓት መሪዎች በአምስት አሮጌ ጠመንጃ የደርግን መንግሥት ለመጣል በ1967 ዓ.ም. በረሃ የገቡበትና ያሳኩበትን የፅናት ሚስጥር፣ የአሁኑ ትውልድ ድህነትን በማሸነፍ ተመሳሳይ ስኬት እንዲያስመዘግብ አዎንታዊ ልምድ ቢያካፍሉ ለሕዝብ ውለታ እንደ ዋሉ ይቆጠራል፡፡ በድህነት ላይ ድል እንዲቀዳጅና እነሱ ተመኝተው ያላሳኩትን የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ይህ ትውልድ እንዲተገብር በመደገፍ ለህሊናቸው ዕረፍት ቢያገኙ ነው የሚሻለው፡፡ ያለፈውን ሁሉ በመተው  በይቅርታና በምሕረት አጀንዳው ተዘግቶ በአዲሰ መንፈስ በአዎንታዊነት አስተሳሰብ ለአገርና ለወገን የሚጠቅም፣ በአምላክም የሚወደድ ተግባር ሠርተን ለልጆቻችን የተመቻቸ አገር ብናስረክብ ለቀሪ ሕይወታችን ጤና፣ ዕርካታና ደስታን ያጎናፅፋል የሚለው ቀና ዕይታ የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማኅበር ምክረ ሐሳብ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የአዎንታዊ አስተሳሰብ ለኢትዮጵያ ማኅበር ቦርድ ሰብሳቢ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...