Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹መዝገበ አእምሮ›› የተወጠነው የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ

‹‹መዝገበ አእምሮ›› የተወጠነው የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ

ቀን:

በኢትዮጵያ በብራና ተጽፈው በድንጋይና በልዩ ልዩ ጥንታዊ መክተቢያዎች ላይ ሰፍረው ለትውልድ እየተላለፉ ከሚገኙት ታሪክ፣ የሕክምና ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ሃይማኖታዊ አስተምህሮዎችና ቀመሮች ይልቅ በየዘመኑ በነበሩ ጠቢባን ውስጥ ተቀብረው ‹በቃል ያለ ይረሳል› እንደሚባለው፣ በመረሳት ከትውልድ ሳይደርሱ ተዳፍነው የቀሩ እልፍ ጥበባት ስለመኖራቸው ይነገራል።

ለዘመናዊ ሕክምና፣ ሥነ ጽሑፍ ፍልስፍናና ዕውቀት መነሻ የሚሆኑ መሠረታዊ የዕውቀት ምንጮች ሊሆኑ የሚችሉ አስተምህሮዎች በአግባቡ ተሰንደው ባለመቀመጣቸው ዛሬም ድረስ ቁልፋቸው ሳይገኝ የጋን መብራት ሁነው ስለመቅረታቸው የሚመሰክሩ ምሁራን አሉ፡፡

ኢትዮጵያ ሺሕ ዓመታትን የተሻገረ የደለበና የተነባበረ ጥንታዊ ዕውቀት እንደነበራት ቢነገርም በአግባቡና በሥርዓቱ ከዘመናዊ ዕውቀት ጋር አጣጥሞ ለመሻገር ግን አዳጋች እንደሆነባት ይታያል።

- Advertisement -

በየገዳማቱና አድባራቱ በየዋሻውና በየጢሻው ሸረሪት አድርቶባቸው የሚገኙ መጻሕፍት ያልተገለጡና ያልታዩ ያልተመረመሩ የሊቃውንት ዕውቀቶች ስለመኖራቸውም ይወሳል።

እነዚህን ጥንታዊና አገራዊ ዕውቀቶችን ‹‹የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ›› እንዲሉ በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎችን በማበረታታት ከዘመናዊ ትምህርትና ፍልስፍና ጋር አዋዶና አጣጥሞ መሻገር ቢቻል ኑሮ ምንኛ ጥሩ ነበር።

ዳሩ ግን ይህ አልሆነም፡፡ ይልቁንስ እንደ አገር ችላ ተብለው ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትና ሌሎች ጠቃሚ ሰነዶች ከያሉበት እየተፈለጉ ወደ ውጭ እየተላኩ ነው።

‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ…›› እንደሚባለው በአግባቡ ተሰንዶ ባለቤትነት ተሰጥቶት ጥናትና ምርምር ተደርጎበት ከዘመናዊ ዓለም ጋር አብሮ ዘምኖ ያልተቀመጠ ዕውቀትን ማንም ተነስቶ እንዳሻው ከመጠቀም አልፎ በግሉ ለማድረግ ቢሞክር ምን ይባላል? ይላሉ ባለሙያዎቹ፡፡

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተዘቆ የማያልቅ የሊቃውንትን ጥበብ የጥንታዊና ታሪካዊ ገዳማትን ሥራ የብራና ላይ ጽሑፎችን ሰንዳና አደራጅታ ለቀሪው ዓለም በምልዓት አላሳየችም የሚል ትችት ይቀርብባታል፡፡

እነዚህንና መሰል ችግሮችን ለመቅረፍና ከጥንት እስከ አሁን ያሉ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶችን በአጭሩ አሰናድቶና ሰንዶ ለማስቀመጥ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡

እነዚህ መንፈሳዊና ቁሳዊ ሀብቶች እንዲሁም አስተምህሮዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለቤትና እውቅና ይኖራቸው ዘንድ  ‹‹መዝገበ አእምሮ›› (ኢንሳይክሎፔዲያ) ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆኑን አሳቀውቋል፡፡

የሚዘጋጀው መዝገበ አእምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ጥንታዊና ሐዋርያዊ አስተምህሮ፣ ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት እንዲሁም የጳጳሳትን፣ የሊቃውንትን፣ የትልልቅ ገዳማትንና አድባራትን ታሪክ ወዘተ. አካቶ እንደሚይዝ ተጠቁሟል።

የመዝገበ አእምሮ የምዝገባ ሒደት ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለማዘጋጀት እንዲቻል በተለያዩ የሙያ መስኮች የተሰማሩ ምሁራን ዕውቀታቸውንና ልምዳቸውንም እያጋሩ ይገኛሉ፡፡ ጥናቱ የተጀመረው በማኅበረ ቅዱሳን ጥናትና ምርምር ክፍል በ2005 ዓ.ም. ሲሆን ለስምንት ዓመታት አንዳንድ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተው በተለያዩ ምክንያቶች በ2013 ዓ.ም. ተቋርጦ ነበር፡፡

አስተባባሪ ባለሙያዎችን በመቅጠር፣ የመዝገበ አእምሮ ፍኖተ ካርታ ክለሳ በማድረግና ከባለሙያዎች ጋር በመወያየት እንዲሁም ማስገንዘቢያን በመስጠት በ2016 ዓ.ም. እንደገና ወደ ሥራ መመለሱን ኮሚቴው አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያም ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. ከባለሙያዎች ጋር ውይይትና ምክክር አድርጓል። በወቅቱ በቀረበ ሪፖርት ላይ 12 ሺሕ ስረይ ቃላት ተሰብስበው 4865 ሊጻፍባቸው የሚችሉ ተብለው በአርትኦት ኮሚቴው መመረጣቸው፣ 279 ሥረይ ቃላት ለጸሐፍት ተሰጥተው 227ቱ ተጽፎባቸው ተመልሰዋል ተብሏል።

ኢንሳይክሎፔዲያ ላይ የሚሰፍሩ ቃላት በጣም የተመረጡ አጭርና ግልፅ ይሆኑ ዘንድ በርካታ የየዘርፉ ሙሁራን ሊሳተፉበት እንደሚገባም ተነግሯል።

ሥራው የሙያተኞችን ርብርብ በብዛት የሚጠይቅ ሲሆን ወጭውን ቤተ ክርስቲያኗ ብቻዋን መሸፈን ባለመቻሏ እህት አብያተ ክርስቲያናት ባለ ሀብቶች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ተቋማት እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል፡፡

ሌሎች የሃይማኖት ተቋማትም በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሙያዊ እገዛ እያደረጉ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡

ምንም እንኳን መዝገበ አእምሮው በአግባቡ ተሰንዶ ሲቀመጥ ጠቀሜታው ለሁሉም ሃይማኖቶች ቢሆንም ቤተ ክርስቲያኒቱ ስለነበራት የታሪክ የባህልና የጥበብ አስተዋጽዖ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ እይታ እንዴት እንደሚገለጽ ማሳየቱም የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።

ይህ መዝገበ አእምሮ ከኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሚጻፍ ከመሆኑ የተነሳ የሌሎችን የእምነት ተቋማት በተመለከተ መካተት ያለበት ይዘት በደንብ ሊታይ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

አዲሱ የኦርቶዶክስ ኢንሳይክሎፔዲያ ዝግጅት አወዛጋቢ የኾኑ፣ የታሪክና ሌሎች እምነቶችን በተመለከተ የሚያካትተው ይዘት ከጅምሩ በጥንቃቄ መታየት እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡

የቋንቋና የፊደል አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የተለያዩ ምሁራን አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፣ ተገቢውን የአማርኛ ሥርዓተ ጽሕፈት ተከትሎ ማዘጋጀት፣ በሒደት ወደ ሌሎች የአገር ውስጥ ቋንቋዎችና ወደ እንግሊዝኛ መቀየር እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ስለመዝገበ አእምሮ ስያሜ ተለያዩ አስተያየቶች የቀረቡ ሲሆን ‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝገበ አእምሮ›› (Ethiopia Church Encyclopedia) ቢባል የበለጠ ለዓለም ተደራሽ መሆን እንደሚያስችለው ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...