Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የግንባታ ኢንዱስትሪዎች የሚገናኙበት መድረክ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በኢንቨስትመንት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ ልማትና በኤክስፖርት የሚመራ ዕድገትን እንዲያስመዘግብ ታልሞ የተነደፈና በአብዛኛው በማደግ ላይ ባለው የግንባታው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህ ዘርፍም ወደ 41 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ዋጋ እንዳለው ይገመታል፡፡ እነዚህ ዘርፎች የሚፈጥሯቸውን ምቹ የሥራ ዕድሎች ለመጠቀም መንገድ የሚያመቻቸው፣ ሁለተኛው የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ የግንባታው ዘርፍ ንግድ ትርዒት ከግንቦት 22 እስከ 24 ቀን 2016 ዓ.ም.  በአዲስ አበባ ሚሌኒየም አዳራሽ ይካሄዳል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ የሰጠውን መግለጫ ሪፖርተር እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለግንባታው ዘርፍ ምን ያህል ተመራጭ ናት?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- በኢትዮጵያ ለግንባታው ኢንዱስትሪ ተመራጭ መሆኗን የሚያመላክቱ ትልልቅና ግዙፍ የግንባታና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች አሉ፡፡ በኢንዱስትሪው ውስጥ ያለውን ለውጥና ዕድገት ለመደገፍ ብሎም በርካታ የሥራ ግንኙነቶችን ለመፍጠር ቢግ 5 ኮንትራክት ኢትዮጵያ፣ አገር በቀልና ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ዕውቀታቸውን እንዲሁም ምርቶቻቸውን የሚያሳዩበትና በአገሪቱ ውስጥ ያሉ ሰፊ የዘርፉ የሥራ ዕድሎች የሚስተናገዱበትን የንግድ ትርዒት አመቻችቷል፡፡ የንግድ ትርዒቱ ከአገሪቱ ታላቅ ግብ ማለትም ራዕይ 2025 ግቦች ጋር በሚጣጣም መልኩ የዘርፉን የንግድ ሥራ በማመቻቸትና ኢንዱስትሪውን በመደገፍ ግንባር ቀደም ተዋናዮችን በአንድ መድረክ የሚያገናኝ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በዝግጅቱ ተሳታፊ የሚሆኑት እነማን ናቸው?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ዕውቅና ያለው ይህ የንግድ ትርዒት፣ በዋነኝነት ለሕንፃ ተቋራጮች፣ ለአልሚዎች፣ ለአማካሪዎች፣ ለንድፍ ሥራ ባለሙያዎች፣ ለፕሮጀክት ኃላፊዎች፣ ለሲቪል መሐንዲሶች፣ ለዲዛይነሮች፣ ለከተማ ንግድ ባለሙያዎች፣ ለግዥ ሥራ አስኪያጆች የተዘጋጀ ነው፡፡ ዘንድሮ ዝግጅቱን ከ9,000 በላይ ጎብኚዎች እንደሚያዩት ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ግዙፍ የግንባታና የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነች ነው፡፡ ከነዚህም መካከል በአራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ በመከናወን ላይ ያለው የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ማስፋፊያ ፕሮጀክት፣ 1.9 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በመገንባት ላይ ያለው መልከ ብዙ ልማት፣ የለገሀር ግንባታ እንዲሁም በ681 ሚሊዮን ዶላር ሊገነባ የታቀደው ባለ 70 ፎቅ መሶብ ታወር ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ቢግ 5 ኮንስትራክሽን ኢትዮጵያ ተሳትፎው ምን ይሆናል?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፣ በእነዚህ ትልልቅ ፕሮጀክቶች እየተመራ በማደግ ላይ ያለውን የግንባታ ዘርፍ ይበልጥ ማገዝ የሚያስችሉ የተለያዩ የግንባታው ዘርፍ ምርትና አገልግሎት ዓይነቶችን በንግድ ትርዒቱ ላይ ያቀርባል፡፡ እነዚህም የግንባታ ዕቃዎችን፣ የሕንፃ የውስጥ የውበት ሥራና አጨራረስ ሥራዎችን፣ የግንባታ መሣሪያዎችና የግል ደኅንነት መጠበቂያዎችን፣ ዲጂታል የግንባታ ምርቶችና አገልግሎቶችን፣ ከባድ የግንባታ መሣሪያዎችን፣ ማሽኖችና ተሽከርካሪዎችን፣ የኤችቪኤሲአር ምርቶችን፣ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን፣ የከተማ ዲዛይንና የኤምኢፒ አገልግሎቶችን፣ የፀሐይ ብርሃንን የሚጠቀሙ የግንባታ መሣሪያዎችን፣ የከተማ ዲዛይንና የመልክዓ ምድር ምርቶችን፣ የመስኮት፣ የበርና የፊት ለፊት ገጽታዎችን እንዲሁም ልዩ ግንባታዎችን ያካተቱ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በንግድ ትርዒቱ ምን ያህል አገሮች ይሳተፋሉ?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- ዘንድሮ በሚካሄደው የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ንግድ ትርዒት፣ ከ19 አገሮች ከተወጣጡት 150 ምርትና አገልግሎት አቅራቢዎች ይሳተፋሉ፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓውደ ርዕዩ የሚሳተፉ ድርጀቶችም አሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ‹‹ጆቱን ፔይንትስ›› የቀለምና ኮንግ ስፔሻሊስቶች፣ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ አስፈላጊ ማጣበቂያዎችን የሚያመርተው የጀርመኑ ‹‹ኢጄኦት››፣ ‹‹ቦስቲክ›› የተሰኘውና በፈረንሣይ ሲላንትና ፕላስቲክ አምራችና አከፋፋይ፣ የፕላስቲኮች አምራች፣ የሳዑዲ ዓረቢያውና መካከለኛው ምሥራቅ የጣሪያ ምርቶች አምራችና አከፋፋይ ‹‹አራይብ›› ፋብሪካና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ በቅድመ ምሕንድስና የተሠሩ የብረት ሕንፃዎችና የክላዲንግ ምርቶችን በዋነኛነት የሚያቀርቡ አምራቾች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በምሕንድስና፣ ንድፍ፣ በፕላንና በፕሮጀክት አስተዳደር ዙሪያ የሚሠራ አማካሪ ድርጅትና የቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ዓውደ ርዕይ የወርቅ ደረጃ ስፖንሰር የሆነው ‹‹ዳር አል – ሀንዳሽ›› ድርጅት ተሳታፊ ነው፡፡ ዳር አል ሪንዳሸ በየትኛውም ሥፍራ ላይ ያለ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ ቀልጣፋ፣ የበለጠ ዘላቂና ሀብት ቆጣቢ ለመሆን በሚፈለግበት ጊዜ ድርጅታችን በዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ በፈጠራ ዲዛይንና በግንባታው ዘርፍ ላይ ያለውን የካበተ ልምድ የማካፈልና ተግባራዊ ልምድ የመስጠት ሥራ ያከናውናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከኮንስትራክሽን ባለፈ የውጭ አገር ተሳትፎ ምን ይመስላል?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- ዘንድሮ በሚደረገው የንግድ ትርዒት ለዕይታ ከሚቀርቡት የግንባታው ዘርፍ የቴክኖሎጂ፣ የምርትና አገልግሎት ውጤቶች ባሻገር የጣሊያን፣ የቱርክ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶችና የቻይና ባህልና አኗኗር ዘይቤዎችንም   ለዕይታ የሚቀርቡ ይሆናል፡፡ እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም በቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ የንግድ ትርዒት 22 በሲፒዲ ዕውቅና የተሰጣቸው ቢግ 5 ንግግሮች (ቢግ 5 ቶክስ) ከ28 በላይ በሆኑ ተናጋሪዎች የሚቀርቡ ሲሆን፣ ይህም ጎብኚዎች በኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ ያሉ ወቅታዊ ሁነቶችና መረጃዎችን እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ ይህም የላቀ አቅም ያለውንና በባለሙያ የሚገነባ ኢንዱስትሪን ለመፍጠር ዕድሉን ያመቻቻል፡፡

ሪፖርተር፡- ድጋፍ የሚያደርግላችሁ ማን ነው?

ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ፡- ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ድጋፍ ያለውና በአጋርነትም አብሮ የሚሠራ ነው፡፡ ዝግጅቱን ከሚደግፉ ማኅበራት መካከል የኢትዮጵያ ሲቪል መሐንዲሶች ማኅበር፣ ቻርተርድ የግንባታ ተቋምና የኢትዮጵያ ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ይገኙበታል፡፡ እንደ ቢግ 5 ኮንስትራክት ኢትዮጵያ ያሉ ዝግጅቶች ዓለም አቀፍ ኢንተርፕራይዞችን ወደ መዳረሻችን በመሳብ ምርትና አገልግሎት ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ የንግድ ዕድገት ለመቅረፅ ያስችላሉ፡፡ ከ18 ዓመት በላይ የሆኑ የኢንዱስትሪው ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ባለሙያዎች ዝግጅቱ ላይ በነፃ መሳተፍ የሚችሉ ሲሆን፣ የተሳትፎ ምዝገባም ተጀምሯል፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

ኤስ ኦ ኤስ እና ወርቅ ኢዮቤልዩ

ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ ከ1949 ዓ.ም. ጀምሮ የቤተሰብ እንክብካቤ ላጡ ሕፃናት ቤተሰባዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የዓለም አቀፉ ኤስኦኤስ የሕፃናት መንደሮች ፌደሬሽን አካል ነው፡፡...

ከጎዳና ከማንሳት ራስን እስከማስቻል የሚዘልቀው ድጋፍ

ጎዳና ተዳዳሪነትን ለማስቀረት መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ለዓመታት ሠርተዋል፡፡ ከችግሩ ስፋት አንፃር ሙሉ ለሙሉ መፍትሔ ባያገኝለትም፣ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ለመለወጥ በሚሠሩ ሥራዎች ዕድሉን አግኝተው ራሳቸውን...

አሠርታትን በስኬት የዘለቀው የካንሰር ተቋም

ሕፃን ልጅን በሞት እንደመነጠቅ መሪር ሐዘን የለም። ክፉና ደጉን ያለየ፣ ከእናትና ከአባቱ ውጭ ሰው ያለ ለማይመስለው ሕፃን፣ በዕድሜ የገፉ እንኳን ፈጽመው በሚጠሉት ሞት ከእናት...