Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከራያ አላማጣ የተፈናቀሉ ከ39 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተሰማ

ከራያ አላማጣ የተፈናቀሉ ከ39 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተሰማ

ቀን:

በሚያዝያ ወር 2016 ዓ.ም. መጀመሪያ ሳምንት በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች፣ በራያ፣ አላማጣ፣ በኮረምና በኦፍላ ወረዳዎች እንዲሁም በአላማጣ ከተማ ዙሪያ ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት  ተፈናቅለው በቆቦ ከተማ የሚገኙ 39 ሺሕ 632  ተፈናቃዮች  በከፋ ችግር ውስጥ መሆናቸው ተነገረ፡፡

የሕወሓት ታጣቂዎች ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም. ወደ አካባቢው ዘልቀው መግባታቸውን ተከትሎ  ነዋሪዎቹ ቤት ንብረታቸውን ትተው ወደ ቆቦ ከተማ  የተፈናቀሉ   ሰዎች በመጠለያና በምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን  የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና አስታወቀ፡፡.

ተፈናቃዮቹ አካባቢያቸውን ለቀው ሲወጡ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን፣ ወደ ቆቦ ከተማ ከገቡ ከ20 ቀናት በላይ ማስቆጠራቸውን  የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ  ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ከተፈናቀሉት ውስጥ 7,100 ለሚሆኑት ብቻ  በብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በኩል የዕለት ደራሽ ምግብ እንደቀረበላቸው ኃላፊው  ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ከ32 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተፈናቃዮች ምንም ዓይነት ዕርዳታ እንዳልደረሰላቸው የተናገሩት አቶ ዓለሙ፣ በአካባቢው ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ባለመሆኑ ወደ አካባቢያቸው ሊመለሱ እንዳልቻሉ  አስረድተዋል፡፡

‹‹በካምፕ ውስጥ ከተሰበሰቡ ሌላ አደጋ ሊደርስባቸው ይችላል የሚል ሥጋት ስላደረብን ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው እንዲኖሩ አድርገናል፤›› ያሉት ኃላፊው ምንም ዓይነት የመጠለያ ካምፕ አለመኖሩን አስታውቀዋል፡፡

‹‹ወጣቶቹ የደፈጣ ውጊያ ሊደረግብን ይችላል በሚል ሥጋት አካባቢውን ለቀው ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌሎች ከተሞች ተበትነዋል›› ያሉት አቶ ዓለሙ፣ ሕፃናትና ሽማግሌዎች እንዲሁም ነፍሰ ጡር እናቶች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው በማለት አስረድተዋል፡፡

አላማጣ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት ቢኖርም በከተማዋ በቅርብ ርቀትና በሌሎች የራያ አላማጣ  አካባቢዎች የሕወሓት ታጣቂዎች በመኖራቸው ተፈናቃዮች መመለስ አልፈለጉም ሲሉ ኃላፊው አክለዋል፡፡

የክልሉ መንግሥት በቅርበት ካሉ ፋብሪካዎች 90 ኩንታል የሚሆን ዱቄት  ለእናቶችና ለሕፃናት ማቅረቡን የተናገሩት አቶ ዓለሙ፣ ከሌሎች የክልሉ ከተሞች ዕርዳታዎችን ለማስገባት  መንገዶች ዝግ በመሆናቸው አልተቻለም ሲሉ  አብራርተዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ ዕርዳታ ማስተባበሪያ ቀደም ሲል ባወጣው መግለጫ በግጭቱ ከ50 ሺሕ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል። ተፈናቃዮች አስቸኳይ የሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በተለይ ሴቶችና ሕፃናት የሚገኙበት ሁኔታም አሳሳቢ እንደነበር በወቅቱ አሳውቆ ነበር ።

በአማራ ክልል በድርቅና በተለያዩ የፀጥታ ችግሮች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 2 ሚሊዮን 500 ሺሕ ማደጉን  ክልሉ  ያስታወቀ ሲሆን፣ መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች በየወሩ ሁለት ቢሊዮን ሁለት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ  አሳውቋል፡፡

በራያ አላማጣ አካባቢ  ተፈናቅለው  በችግር ላይ  ስለሚገኙ ሰዎች ከክልሉ መንግሥት መረጃ ለማግኝት ሪፖርተር ያደረገው ጥረት ባለመሳካቱ  ምላሹን ማካተት አልተቻለም፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...