Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ለሚታየው የነዳጅ እጥረት ለኮሪደር ልማት የፈረሱ ማደያዎች አስተዋጽኦ እንዳላቸው ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰው አልባ ስማርትነዳጅ ማደያዎች መገንባት አለባቸው ብለዋል

በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚታየው የነዳጅ እጥረት፣ በቅርቡ ለተጀመረው የኮሪደር ልማት የፈረሱ ስምንት ማደያዎች አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንና በሌሎች በሥራ ላይ ባሉ ማደያዎች ላይ ጫና መፍጠራቸው ተነገረ። 

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሔኖስ ወርቁ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ የሚታየው የተወሰነ የነዳጅ እጥረት የፈረሱና ምቹ ባልሆነ  ቦታ የሚገኙ ነዳጅ ማደያዎች የፈጠሯቸው ጫናዎች ናቸው። 

‹‹አሁን እጃችን ላይ ባለን መረጃ መሠረት በጣም ሰፊ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ ከስምንት በላይ ለኮሪደር ልማት የፈረሱ ማደያዎች አሉ። ከዚህም ባሻገር በሥራ ላይ ያሉትም ቢሆኑ ወደ ውስጥ ለመግባት ለተሽከርካሪዎች ምቹ ካለመሆናቸውም በላይ፣ ነዳጅም ለመገልበጥ የማይመቹ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው በተወሰነ ደረጃ አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ የሚሰጡ ማደያዎች ላይ ጫና ፈጥሯል፤›› ብለዋል። 

ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በማብራሪያቸው ከፍትሐዊ የነዳጅ ድልድል የገበያ ድርሻ ጋር በተያያዘም አንዳንዱ ጉዳይ ከፖለቲካ አንፃርም መታየት እንዳለበት፣ ሆን ብለው እጥረት እንዲኖር በሚያደርጉ ላይ በሕጉ መሠረት እየታዩ ዕርምጃዎች እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ከኮሪደር ልማት አስተባባሪዎች ጋር ግምገማ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎችም ኃላፊዎች ለተገኙበት ቡድን ማደያዎችን የተመለከቱ ሐሳቦች አንስተዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተባባሪዎቹን፣ ‹‹ልታስቡበት የሚገባው አንዱ ነገር ማደያ ነው፤›› ብለዋል።  ‹‹ቦሌ መንገድ አራት ማደያዎች ናቸው ያሉት። አራቱም ማደያዎች ረዣዥም ሠልፍ ስላለባቸው መንገድ ይዘጋሉ። ይህ እየሆነ ያለው ዋና መንገድ ላይ ስለሆነ ቢነሱ ተብሎ የሚቀርብ ቅሬታ አለ። ግን ማደያ ከሌለ ደግሞ ከተማው ሕይወት የለውም። ደረጃውን በጠበቀ ርቀት ልዩነት ውስጥ ማደያ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

‹‹ብናስብበትና በኮሪደር ልማት ውስጥ ብናካትተው፤›› ሲሉ አማራጭ ያቀረቡ ሲሆን፣ ያቀረቡት አማራጭ አሁን ካለው የተሻለ ነው ያሉበትን ምክንያት አስረድተዋል።

ይህን በተመለከተም፣ ‹‹አሁን ሰዎች ማደያ ሲሉ እንደ ቦታ መያዣ ነው። እዚያ ውስጥ ካፌና ሌሎችም አገልግሎቶች እያሉ እንደ ቦታ መያዣ ነው የሚያደርጉት፤›› ብለዋል። 

‹‹በዚህ ምትክ ስማርት ማደያዎችን ብንገነባ፤›› ብለዋል። ‹‹ስማርት ማደያ ለምሳሌ ፒያሳ አካባቢ አሥር ልንሠራ እንችላለን። ምንም ነገር የለውም፣ ከታች ማጠራቀሚያ (tanker) ይኖረዋል፣ መጠለያ ትንሽ ሼድ ይኖረዋል፣ ሰው አይኖረውም፣ ተጠቃሚ መኪናውን ያስገባል፣ ነዳጅ ይሞላል፣ በሞባይል ገንዘብ ይከፍላል። ወይም በዛ ከተባለ አንድ አገልግሎት አስተባባሪ ይኖረዋል። ግን አውቶማቲክ በካርድ እንዲከፍል ማድረግ ይቻላል፤›› ብለዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)ስማርት ማደያዎችን መገንባት ብዙ ቦታ እንደማይወስድ፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉት የቦሌ ማደያዎች ከፊት ለፊት ማደያ፣ ከኋላ መዞሪያ፣ በሌላ በኩል የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሰጡ ክፍሎች ስላሏቸው ሰፊ ቦታ ነው የሚይዙት ሲሉ ገልጸዋል። 

‹‹እንደሱ ሳናደርግ በሲኤምሲ መንገድም ወደ አምስት ወይም ስድስት በቀላሉ ሰው ገብቶ ነዳጅ በፍጥነት ሞልቶ የሚሄድበት፣ በፒያሳ አካባቢም በሚያስፈልገው ቦታ እያየን ይህን አድርገን ሰው እንዳይቸገር መሥራት አለብን፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንዴት ይደረግ የሚለውን በጥናት ብታዩት በማለት ለኮሪደር ልማት አስተባባሪዎቹ አሳስበዋል። 

በአነስተኛ ቦታ ብዙ ነገር ሳይወስድ መከናወን ይችላል ባሉት የስማርት ማደያዎችን ግንባታ በተመለከተ፣ ‹‹ከታች የምንቀብረውን ቀብረን ከላይ ግን ማደያውን ብቻ አድርጎ መሥራት የሚቻልበትን መንገድ፣ እዚያው አጠገብ ደግሞ የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረግ የሚቻልበት ሁኔታም መፍጠር ያስፈልጋል፤›› ብለዋል። 

‹‹የኤሌክትሪክ መኪና እያልን ስለሆነ እሱንም ታሳቢ አድርገን ብንሠራ ጥሩ ነው፤›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች