Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥጋት የመሸከም አቅሙ ከ6.2 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ታወቀ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የኩባንያው ድርሻ በከፊል ለሽያጭ መቅረቡ አቅሙን ያሳድጋል ተብሏል

በዳዊት ታዬ

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ2016 የሒሳብ ዓመት ዘጠኝ ወራት በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የ1.24 ቢሊዮን ትርፍ ማስመዝገቡና የኩባንያው ሥጋት የመሸከም አቅም ደግሞ ከ6.2 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የዘጠኝ ወራት ሥራ አፈጻጸሙን በተመለከተ የተገኘው መረጃ መሠረት፣ በዘጠኝ ወራት የተመዘገበው ትርፍ፣ በኩባንያውም ሆነ በኢንዱስትሪው በሦስተኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ የተገኘ ከፍተኛ የሚባል ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘጠኝ ወራት ከታክስ በፊት የተመዘገበው 1.24 ቢሊዮን ብር ትርፍ እስካሁን ተመዝግቦ የማያውቅ ከመሆኑም በላይ፣ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ35.7 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሙሉ በጀት ዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ትርፍ የተመዘገበው ከሁለት ዓመት ተኩል በፊት ሲሆን፣ በዚህን ያህል መጠን ትርፍ አስመዝግቦ የነበረው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እንደነበር ይታወሳል፡፡

ኩባንያው ያስመዘገበው የትርፍ ምጣኔ ዕድገት አሁን የደረሰበትን አቋም የሚያመላክት ነው ያሉት አቶ ነፃነት፣ በሌሎች አፈጻጸሞቹም ከፍተኛ ውጤት ማግኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በ2016 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም የተለየ ዕድገት የታየበት ለመሆኑ በተለያዩ አኃዛዊ መረጃዎች አስደግፈው ያብራሩት አቶ ነፃነት፣ የኩባንያው ሥጋት የመሸከም አቅም 50 በመቶ ዕድገት ማሳየቱን በምሳሌነት ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በሦስተኛ ሩብ ዓመት መጨረሻ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ሥጋት የመሸከም አቅሙ ከ6.2 ትሪሊዮን ብር በላይ መድረስ ችሏል ብለዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 7.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ32.3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ተገልጿል፡፡

በዚያው ልክ በዘጠኝ ወራት ለካሳ ክፍያ የዋለው የገንዘብ መጠን የ14 በመቶ ዕድገት እንዳሳየም ታውቋል፡፡ በዘጠኝ ወራት ውስጥ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የፈጸመው የካሳ ክፍያ ከ2.2 ቢሊዮን ብር በላይ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለጉዳት ካሳ መጨመር በዋናነት የተጠቀሰው በሒሳብ ዓመቱ እንደ አቪዬሽን ላሉ ትልልቅ የመድን ሽፋኖች ካሳ በመከፈሉ መሆኑን ከተሰጠው ማብራሪያ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ድርሻ በከፊል ሊሸጥ መሆኑ መገለጹ፣ ለኩባንያው ትልቅ ዕድል እንደሆነ አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡ አብላጫውን ድርሻ  ይዞ ከፊል ድርሻውን ለመሸጥ የመንግሥት ፍላጎት መሆኑን የገለጹት አቶ ነፃነት፣ እንዲህ ያለው ውሳኔ ሲተገበር የኢትዮጵያ መድን ድርጅትን አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሳድገዋል ብለዋል፡፡

በተለይ ኩባንያው በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ጠንካራ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመሆን የያዘውን ዕቅድ ከማሳካትም አኳያ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ ወደ 50 ዓመታት የተጠጋ ዕድሜ ያለው ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ የሀብት መጠኑ 13 ቢሊዮ ብር ደርሷል፡፡ ካፒታሉ 3.1 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ የኩባንያው ከፊል የባለቤትነት ድርሻ ለሽያጭ እንዲቀርብ በተሰጠው ውሳኔና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር ከአቶ ነፃነት ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ በገጽ 14 ይመልከቱ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች