Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከሥጋና ከተረፈ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 25 በመቶ መቀነሱ ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘንድሮ ከሥጋና ከተረፈ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 25 በመቶ መቀነሱን የሥጋ አምራች ላኪዎች ማኅበር አስታወቀ፡፡

የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት መሠረት፣ ከሥጋና ከተረፈ ምርት የተገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ልዩነት መፈጠሩን የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዘንድሮ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 18,650 ቶን ሥጋና ተረፈ ምርት ለመላክ ታስቦ፣ 8,974 ቶን ብቻ በመላክ 55 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት 12,100 ቶን ሥጋና ተረፈ ምርት ተልኮ 72 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን አስታውሰው በዚህ መሠረት የዘንድሮ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከአምናው 25 በመቶ መቀነሱን አስረድተዋል፡፡

የአገር ውስጥ የእንስሳት መግዣ ዋጋ በከፍተኛ መጠን በመጨመሩ ሥጋ ላኪዎች ከሌሎች ሥጋ ላኪ አገሮች ጋር ተወዳዳሪ መሆን ባለመቻላቸው፣ የውጭ ምንዛሪ ገቢ መቀነሱን አበባው ተናግረዋል፡፡

በድንበር በኩል ሕገወጥ የእንስሳት ዝውውር በመስፋፋቱ ሥጋ ላኪዎች የአቅርቦት ችግር እንደሚገጥማቸው የተናገሩት ዋና ጸሐፊው፣ የኢትዮጵያ ሥጋ ላኪዎችና ለሌሎች አገሮች ሥጋቸውን በሚሸጡበት ወቅት ዋጋቸው ከፍ ስለሚል፣ በርካታ ተቀባዮች ሥጋ የሚገዙት ከሌሎች አገሮች መሆኑ አንዱ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሥጋ ላኪዎች ትራንስፖርትን ጨምሮ አንድ ኪሎ ሥጋ በ7.2 ዶላር እንደሚያስረክቡ ኬንያ፣ ታንዛኒያና ሌሎች አገሮች 6.4 ዶላር ድረስ እንደሚሸጡ ጠቁመዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ከሥጋና ከተረፈ ምርት የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ በከፍተኛ መጠን መቀነሱን ገልጸው፣ የኬንያ ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ጋር በጥቁር ገበያ በመገበያየት በድንበር በኩል የቁም እንስሳት እየገዙ መሆናቸውን አክለዋል፡፡

በርካታ ቄራዎች ችግሩን መሸከም አቅቷቸው ከገበያ እየወጡ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ከሌሎች አገሮች ጋር ያለው ልዩነት ለማጥበብ የግብርና ሚኒስቴር ጉዳዩን የተመለከተ መመርያ ሊያዘጋጅ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮችንም ሆነ ሥጋ ላኪዎችን በማይጎዳ ሁኔታ የእንስሳት አቅርቦት እንዲኖር የሚያስችል መመርያ ነው ያሉት አቶ አበባው፣ መመርያው ፀድቆ ወደ ሥራ ሲገባ ዘርፉን ከተለያዩ ችግሮች መታደግ ይቻላል ብለዋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር መመርያውን ሲያዘጋጅ በተደጋጋሚ ከሥጋ ላኪዎችም ሆነ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ማድረጉን፣ በመመርያው ውስጥ መካተት ያሉባቸው ነገሮች መታየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዋናነት ከሌሎች አገሮች ጋር እንዴት ነው ተወዳዳሪ መሆን የሚቻለው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል ያሉት ዋና ጸሐፊው፣ በቀጣይ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች