Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹ምድር ፋሲካን አደረገች…››

‹‹ምድር ፋሲካን አደረገች…››

ቀን:

ሁለት ምዕመናን በዕለተ ሆሳዕና ዘንባባቸውን ይዘው በደጀ ሰላሙ እያወጉ ነው፡፡ ፋሲካ በየዓመቱ ለምን እንደ ልደት፣ ጥምቀት በቋሚ ቀን አይከበርም? እያሉ ይጠያየቃሉ፡፡

‹‹ምድር ፋሲካን አደረገች…›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ34 ዓ.ም. መጋቢት 29 ቀን በዕለተ እሑድ ከሙታን ተለይቶ መነሳቱን በመጽሐፍ መጻፉን፣ መምህራኑም ሲያስተምሩ ማዳመጡን አንደኛው ይገልጻል፡፡ ሌላኛውም እሑድ የክርስቲያኖች ሰንበት የሆነው ጌታ የተነሳባት ስለሆነ እሑድን እንዳይለቅ በማሰብ እንደሆነ መነገሩንም ያወሳል፡፡

- Advertisement -

ከመነሻው ወጋቸውን ያዳምጡ የነበሩ ካጠገባቸው የቆሙ አንድ አባትም (ካነጋገራቸው የቤተክርስቲያን መምህር መሆናቸው ያስታውቃል) ስለ በዓሉ ጥንተ ነገር ያወጉ ጀመር፡፡

‹‹የቤተክርስቲያን በዓላትም ሆኑ አጽዋማት ቋሚና ተንቀሳቃሽ ናቸው፡፡ ልደትን፣ ጥምቀትን፣ የገና ጾም የመሳሰሉት ቋሚዎቹ በፀሓያዊ አቆጣጠር ላይ ሲመሠረቱ፤ ትንሣኤን፣ ዕርገትን፣ ዓቢይ ጾምን የመሳሰሉት ተንቀሳቃሾቹ የሚገኙት ግን በፀሓይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር  የተመሠረቱ ናቸው፡፡

‹‹ምድር ፋሲካን አደረገች…›› | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የፋሲከ በዓል  በኒቅያ ጉባዔ እንደተወሰነው፡- አንደኛ ሁልጊዜ እሑድ መዋል ይኖርበታል፤ ሁለተኛ ፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) ከሚውልበት የጨረቃ ሚያዝያ (ኒሳን) 14 ቀን ቀጥሎ በሚመጣው እሑድ ይውላል፤ ሦስተኛ ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12፣12 ሰዓት ከሚሆንበት ከመጋቢት 25 ቀጥሎ ይውላል፡፡ በዚህኛው ድንጋጌ መሠረት ትንሣኤ ከመጋቢት 26 እስከ ሚያዝያ 30 ባሉት መነሻና መድረሻዎቹን ጨምሮ በ35 ቀኖች ውስጥ ይመላለሳል፡፡

በዚህ ድንጋጌ መሠረት የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ የጁሊያን ቀመር በሚከተሉ የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ዘንድ እየተከበረ ይገኛል፡፡ ይህም በዓል ባለፈው ሳምንት አይሁዶች ፋሲካቸውን ካከበሩ በኋላ የመጣ ነው፡፡

ጥንታዊ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ፣ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹… የትንሣኤውን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታድርጉ፣ በመንፈቀ ሌሊት ብሉ፣ ያም ባይሆን በነግህ ብሉ. . . ከዚህም በኋላ ፈጽሞ ደስ እያላቸሁ ጾማችሁን በመብል በመጠጥ አሰናብቱ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡››

የግሪጎሪያን ቀመር በሚከተሉት የምዕራብ ክርስቲያኖች ፋሲካውን ያከበሩት ከወር በፊት መጋቢት 22 ቀን እንደነበረ ይታወሳል፡፡

እሑድ የክርስቲያን ሰንበት

ሊቀ ጉባዔ ጌታሁን በጻፉት ኖኅተ ስብከት ዘቅዱስ ያሬድ ቅጽ  መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ‹‹ትንሣኤ›› የሚለው ቃል  ‹‹መነሣት፣ አነሣስ›› ማለት ነው፡፡  እንዲሁም የፋሲካን ምንነት እንደሚከተለው አብራርተውታል፡፡ ‹‹ፋሲካ በዕብራስጥ ቋንቋ ‹ፓሳሕ›› ማለት ሲሆን፣ ማለፍ መሻገር ማለት ነው፡፡ ይኼውም እስራኤል ዘሥጋ ያከብሩት የነበረው የፋሲካ በዓል ከግብፅ ባርነት ወደ ነፃነት ምድር ወደ ከነአን ከኀዘን ወደ ደስታ የተሻገሩበት በዓል ነበር፡፡

በሐዲስ ኪዳን የሚከበረው የፋሲካ በዓል የክርስቶስ ትንሣኤ የታወጀበት፣ እስራኤል ዘነፍስ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ፣ ከሐሳር ወደ ክብር፣ ከሰይጣን ባርነት ወደ ዘለዓለማዊ ነፃነት፣ ከአሮጌው ኪዳን ወደ አዲሱ ኪዳን፣ ከጎሰቆለ አሮጌ ሕይወት ወደ ሐዲስ ሕይወት የተሸጋገርንበት መንፈሳዊ የነፃነት በዓላችን ነው፡፡›› 

የስድስተኛው ምታመት ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ለዕለተ እሑድ (ሰንበት ክርስቲያንን) ሲቀኝላት እንዲህ ብሏታል፡፡ ‹‹የቀደምት በዓላት ራስ የሆንሽ ሰንበተ ክርስቲያን ሆይ! በሰላም ነዪ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ዕለት እሑድ በሰላም ነዪ፣ ዓለም ሁሉ በአንቺ የተጌጠብሽ የተሸለመብሽ የበዓላት ሁሉ በኩር የሆንሽ ዕለተ እሑድ ሆይ! በሰላም ነዪ፡፡››

የኢትዮጵያ አከባበር

በኢትዮጵያ ምዕመናን ክብረ በዓሉን ‹‹ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ ተሐጺባ በደመ ክርስቶስ›› – በክርስቶስ ደም የታጠበችው ምድር ፋሲካን አደረገች- እያሉ እያሸበሸቡ፣ እየወረቡ ያከበሩት ልዩ ልዩ ባህላዊ መገለጫዎችና ማዕዶችን በማዘጋጀት ነው፡፡

በሁሉም ክፍላተ ሀገር በሚገኙ ታላላቅ ገዳማትና አድባራትን ጨምሮ በየአጥቢያው ሰሙነ ሕማማትን በተለይ ዓርብ ስቅለትን በስግደት፣ ለምለም ቅዳሜ/ ቀዳም ሥዑርን፣ የፋሲካ ሌሊትን በልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ምዕመናኑ አክብረዋል፡፡

የፋሲካው ሌሊት

በፋሲካ ሌሊት የምሥራቹን ጧፍና ሻማ በመለኮስ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚደረገው ዑደት ‹‹ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ›› – ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን ወደኛ- በሚለው ዝማሬ የታጀበ ነው፡፡ ‹‹አማን በአማን ተንሥአ እሙታን›› – እውነት በእውነት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ- በማለት ትንሣኤውን ያበስራሉ፡፡

እንደየኅብረተሰቡ ባህል የፋሲካ ድፎ ዳቦ፣ ዶሮ ዳቦ፣ ኅብስት፣ የዶሮ ወጥ እንቁላል፣ የዕርድ ከብቶችን ማዘጋጀት ጠጅና ጠላ መጠጥ ማዘጋጀት የክብረ በዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ከመልካም ምኞቱ እንኳን አደረሳችሁ፣ ጾመ ልጓሙን እንኳን ፈታልዎ በአነጋገር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት ያሉ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ስጦታ ሙክት፣ ድፎ ዳቦና መጠጦች የሚለዋወጡበትም ነው፡፡

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በግጭትና በጦርነት ምክንያት ከየቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖችም በዓሉን በየመጠለያዎቻቸው ሆነው ማሰባቸውም አልቀረም፡፡ በችግር ላይ የሚገኘው ኅብረተሰብ ሰብዓዊ ዕርዳታ እየጠየቀ፣ እየከፋ የመጣው  የኑሮ ውድነት ተጭኖት በዓሉን እያሳለፈው ነው፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው ሳይጠይቁ ያለፉበትም ጊዜ የለም፡፡

የኢየሩሳሌሙ ክብረ በዓል

የፋሲካ በዓል በተለይ ቅዱሱ እውነት በተፈጸመበት በኢየሩሳሌም በመንፈሳዊና ትውፊታዊ ሥርዓት እየተከበረ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ምዕመናንም ከአገር ቤትና ከተለያዩ አገሮች በመጓዝ በቀራንዮ በሚገኘው የኢትዮጵያ ይዞታ በሆነው ከትንሣኤው ቤተ ክርስቲያን ጋር ከተያያዘው የዴር ሡልጣን ገዳም እያከበሩት ይገኛሉ፡፡

ይህ የትንሣኤ ቤተ ክርስቲያን ‹‹የቤተ ክርስቲያን ሁሉ እናት›› ተብሎ ይጠራል፡፡ ስለምን ቢባል የመጀመሪያው ቤተ ክርስቲያን ይህ ብቸቻ ነውና፡፡

ምዕራባውያን ክርስቲያኖች (ካቶሊክ) ‹‹የቅዱስ መቃብር ቤተ ክርስቲያን›› ብለው በሚጠሩት፣ ኦርቶዶክሳውያኑ ምሥራቃውያን ክርስቲያኖች ‹‹የትንሣኤ ቤተ ክርስቲያን›› ብለው በሚጠሩት ነው ፋሲካው የሚከበረው፡፡

በፋሲካ ዋዜማ፣ ምዕመናኑ በቅዱስ መቃብር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሰብሰብ፣ እግዚእ ኢየሱስ የተቀበረበትና ከዚያም ከሞት በተነሣበት ቦታ ላይ ካለው ድንጋይ ላይ የቅዱስ ብርሃን (እሳት) ማብራት ይጀመራል፣ ብርሃኑ እየተንቦገበገ ሲሄድ ምዕመናኑም በቅብብሎሽ ብርሃኑን በያዟቸው ጧፎችና ሻማዎች ላይ በመለኮስ እየዘመሩ ‹ክርስቶስ በእውነት ተነሳ› እያሉ ደስታቸውን ይገልጻሉ፡፡

የእግረ መስቀል ጉዞ

ሊቀ ካህናት መርዓዊ ተበጀ (ዶ/ር) በጻፉት ‹‹ቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም›› መጽሐፋቸው በዕለተ ስቅለት መታሰቢያ ምዕመናኑ መስቀል ተሸክመው ወደ ጎልጎታ ስለሚያደርጉት ጉዞ እንደሚከተለው ጽፈዋል፡፡

‹‹ኢየሩሳሌም የምድር ማዕከል እንደመሆኗ መጠን ወደ እርሷ የመጣ ሁሉ የተለያየ ስም ሰጥቷታል፡፡ ከመንገዶቿ አብዛኛው ሕዝብ የሚያውቀውን ‹‹ቪያ ዶሎሮዛ››ን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል፡፡ የዚህ ቃል መሠረቱ ላቲን ሆኖ ‹‹ቪያ›› መንገድ ‹‹ዶሎሮዛ›› የመከራ፣ የስቃይ፣ የሕመም፣ የጻዕር፣ የጋዕር፣ የጭንቅ መንገድ እንደማለት ሲሆን፣ ወደ ግእዝ ሲለወጥ ደግሞ ደግሞ እግረ መስቀል፣ ፍኖተ መስቀል፣ ሕማማተ መስቀል ማለት ነው፡፡

‹‹በእግረ መስቀሉ ጉዞ በመንገዱ ላይ 14 ድርጊቶች ስለተፈጸሙበት 14ቱ የመስቀል መንገዶች በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከእነርሱም ጋር ተያይዘው በጌታ ላይ የደረሱት ስቃዮችና እንግልቶች 14ቱ ሕማማተ መስቀል ይባላሉ፡፡

የቪያ ዶሎሮዛ መንገድ የሚጀምረው በምሥራቅ ኢየሩሳሌም ከጌቴሴማኒ ፊት ለፊት የበጎች፣ የአንበሶች የማርያም፣ ወይም የእስጢፋኖስ በር ተብሎ በሚጠራው በኩል ነው፡፡ የሊቀ ካህናቱ ወታደሮች ጌታን ይዘውት በሄዱበት መንገድ በቀኝ በኩል የእመቤታችን የትውልድ ቦታ የቅዱስ ሐና ቤተ ክርስቲያንና ጌታችን የ38 ዓመት በሽተኛውን የፈወሰበት የቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ይገኛሉ፡፡

ጸሐፊው ካተቱባቸው ምዕራፎች አንዱ በ8ተኛው ምዕራፍ በቅዱስ ካራላምቦሶ ስም የተሰየመ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ይገኛል፡፡ ከዚያም ወደ ምሥራቅ በኩል ትንሽ ደረጃ እንደወጡ እ.ኤ.አ. በ1812 የጀርመን ንጉሥ ነገሥት ፈረደሪች ቪልሄም 3ተኛ በገዛው ቦታ ላይ የተቋቋመውና በዮሐንስ መጥምቅ ስም የተሰየመው የእንግዶች ማረፊያ መገኘቱን፣ በስተቀኝ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ንጉሠ ጽዮን ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ አራተኛ፣ በገንዘባቸው ገዝተው ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያበረከቱት መንበረ ጵጵስና የገዳሙ ጽሕፈት ቤት እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

‹‹የራስ ቅል››

የምድር እምብርት እንደሆነች በምትታሰበው ኢየሩሳሌም እግዚእ ኢየሱስ በዕፀ መስቀል መጋቢት 27 ቀን 34 ዓ.ም. ተስቅሎ መሞቱ በሦስተኛ ቀን መነሳቱ ተመዝግቧል፡፡

እግዚእ ኢየሱስ የተሰቀለበት ቦታ በተለያዩ ቋንቋዎች የተለያዩ ስሞች መሰጠቱን በዕብራይስጥና በአረማይስጥ ጎልጎታ፣ በግሪክ ቀራንዮ፣ በሮማስጥክ ወይም በላቲን ካሊቫሪዮ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ የሁሉም ትርጉም ‹‹የራስ ቅል›› ለማለት ነው፡፡

እንደ ሊቀ ካህናት መርዓዊ ማብራሪያ፣ በአሁኑ ጊዜ ሥፍራወ ቤተ ክርስቲያን ስለተሠራበት ማየትና ለይቶ ማወቅ ባይቻልም፣ ቤተ ክርስቲያኑ ከመሠራቱ በፊት ቦታውን ራቅ ብሎ ለተመለከተው የራስ ቅል መስሎ ይታይ ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ቦታው የመቃብር ቦታ ስለሆነ የሰውነት አካል ሁሉም ፈርሶና በስብሶ ወደ አፈርነት ሲለወጥ የማይፈርሰው የራስ ቅል በመሆኑ፣ ይህ የመቃብር ቦታ ጎልጎታ፣ ቀራንዮ፣ ካሊባሪዮ፣ የራስ ቅል ተባለ፡፡ በየትኛውም የጌታ ሥዕለ ስቅለት ሥር የሰው ጭንቅላት ተሥዕሎ የሚታየው በዚህ ምክንያት ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...