Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከጽዋ ወደ በጎ አድራጎት ያደገው ማኅበር

ከጽዋ ወደ በጎ አድራጎት ያደገው ማኅበር

ቀን:

ብርሃነ ኪብሮን የአረጋውያን መርጃ በጎ አድራጎት ማኅበር፣ የተቸገሩ ወገኖችንና  አረጋውያንን ለመጦር ከስምንት ዓመታት በፊት ቀጨኔ ማዞርያ አካባቢ በወጣቶች የተቋቋመ ማኅበር ነው፡፡

ማኅበሩ አምስት መሠረታዊ ዓላማዎችን አስቀምጦ እየሠራ መሆኑን የማኅበሩ  የቋሚ ተረጂዎች ክፍል ኃላፊ ወጣት ሚሊዮን መኰንን ይናገራል፡፡ አቅም አጥተው በየ ጎዳናው የወደቁ የአገር ባለውለታዎችን በተቻለው ሁሉ መደገፍ የማኅበሩ ዋና ዓላማ ነው ያለው ወጣቱ፣ አቅሙና ጉልበቱ ኖሯቸው በተለይ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ጎዳና ለሚወጡ ሴቶች ድጋፍ በማድረግ አነስተኛና ጥቃቅን ሥራዎች እንደሚያስጀምሩም አክሏል፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች ከክልል ተፈናቅለውና ከወላጆቻቸው ተለይተው የመጡ ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ ደብተርና እስክሪብቶ በማሟላት ሌሎች ወጭዎችን በመሸፈንም ይሠራል፡፡

- Advertisement -

በልዩ ልዩ ችግሮች ምክንያት በቤተ ክርስቲያን እና በመስጊድ አካባቢ ተጠልለው በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚገኙ አረጋውያንና ሕፃናት በቋሚነትና በጊዜያዊነት በመደገፍም ይሳተፋል፡፡

ማኅበሩ በየጎዳናው እየተዟዟረ ከሚደግፋቸው በተጨማሪ ወደ ጎዳና ከመውጣታቸው በፊት በየቤታቸው በመሄድ የቤት ኪራይ በመክፈል ወደ ጎዳና እንዳይወጡ ያግዛል፡፡

ማኅበሩ በበዓል ወቅት ለበዓል የሚያስፈልጋቸውን ወጭ በመሸፈን 51 ሰዎችን በቋሚነት ከመንከባከቡም ባሻገር፣ ከአዲስ አበባ ውጭ በገዳማትና በፀበል ሥፍራ ሆነው ችግር ላይ የወደቁ አረጋውያንን ቦታው ድረስ በመሄድ ይጎበኛል፡፡

ከክርስትና እምነት ሦስት በዓላትን እንዲሁም ከእስልምና ሁለት በዓላትን በመምረጥ በቋሚነት እንደ ዶሮ፣ ዘይት፣ ሽንኩርትና የመሳሰሉትን ሙሉ ወጭ በማሟላት በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ በማገዝ ላይ እንደሚገኝ ወጣቱ አስረድቷል፡፡

እሑድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በሚከበረው የፋሲካ በዓል ለ60 አቅመ ደካሞች ዶሮ፣ ዕንቁላል፣ ሽንኩርትና ዘይት እንዲሁም የተለያዩ ለበዓል አስፈላጊ ግብአቶችን ያቀርባል፡፡

ማኅበሩ ድንገተኛ አደጋ ሲደርስ በሰማበትና ባየበት ፈጥኖ በመድረስ የጉልበትም ሆነ የገንዘብ ዕገዛ ማድረግ የሚያስችል ‹‹ፈጥኖ ደራሽ››. የተሰኘ ቡድን እንዳለው፣ ወጣት ሚሊዮን አስረድቷል፡፡

በተለይ በአቅራቢያው የመኪና አደጋ፣ የቤት ቃጠሎና ሌሎች ድንገተኛ ክስተቶች ሲፈጠሩ ለዕለቱ የሚሆን ነገር ለመርዳት ይንቀሳቀሳል፡፡

ስለ ማኅበሩ አመሠራረት ወጣቱ ሲናገር፣ የሠፈር ልጆች ተሰባስበው የጽዋ ማኅበር በመመሥረት በየወሩ ሲሰባሰቡ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ወጣቶቹ የአሁኑን ሥራ የጀመሩት የጽዋ ማኅበራቸውን በቁጥርም በአቅምም ከፍ በማድረግ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳት፣ የወደቁትን በማንሳትና ባሉበት በዙርና በቋሚነት በመንከባከብ ነው፡፡

ወጣቶቹ ይህንን በጎ ሥራ ሲሠሩ ምንም ዓይነት የገቢ ምንጭ አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ሰውን ለመርዳት በጎ አስተሳሰብና ፍቅር ካለ ሌላው በመሥራትና በሒደት የሚመጣ ነው፣ የተቸገሩ ወገኖችን ለመርዳት ገንዘብ ካለ በገንዘብ፣ ከሌለ ደግሞ በጉልበት መርዳት አስፈላጊ ነው፤›› ሲል ያክላል፡፡

በጉልበት ከሚደረጉ ድጋፎች በዘለለ ገንዘብ ለሚያስፈልጋቸው ደግሞ ከወር ገቢያቸው በማዋጣትና ከሰዎች በመጠየቅ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግሯል፡፡

በሌላ በኩል ወጣቶች ለየት ያለ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ እንዳላቸው ያስረዳው ሚሊዮን፣ ‹‹እርስዎ ዛሬ ባስቀመጡት ገንዘብ አረጋውያንን ይጦሩበታል፣ የታመሙትን ይጠይቁበታል፤›› የምትል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ከረጢት ለግለሰቦች እንደሚሰጡ ከረጢቷ በየግለሰብ ቤት ተቀምጣ የያዘችውን ይዛ በዓመት እንደምትሰበሰብ፣ ይህም አንዱ የገቢ ማሰባሰቢያቸው መሆኑን ተናግሯል፡፡

 ‹‹በጉብዝናህ ወራት ፈጣሪህን አስብ›› ይላል የሚለው ወጣቱ፣ ‹‹እኛ በዚህ በጉብዝና ዘመናችን ተንቀሳቅሰን  ሠርተን ወገኖቻችንን ካልጦርንና ካልቀበርን የነገ የእኛ ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አናውቀውም፤›› ሲል ያስረዳል፡፡

በቀጣይ የገንዘብ ምንጫቸውን ከፍ በማድረግ ለአቅመ ደካሞችና ለተቸገሩ ሰዎች ለመድረስ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግሯል፡፡

አረጋውያንን በአንድ ቦታ አሰባስቦ ለመንከባከብ ቋሚ ማዕከላትን መገንባትና መሥራት የሚችሉትን ከሥራ ጋር ማገናኘት አንዱና ዋነኛው ዕቅዳቸው ነው፡፡ ማኅበሩ የዳቦ ማሽን በመግዛት ዳቦ በመጋገርና በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ እንዲሁም ለመግዛት እጅ ላጠራቸው ሰዎች በመርዳት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ወጣት ሚሊዮን  ይገልጻል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...