Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በሰላም ግንባታ የወጣቶች ሚና እንዴትነት

በገብሬ ይንቲሶ ደኮ (ፕሮፌሰር)

የሰላም ጥረቶች የግጭትን ያህል የሚዲያ ትኩረት ባይስቡም መልካም ሥራዎችን በሚዛኑ ለሕዝብ ማድረስ ተገቢ ይመስለኛል። ከዚህ አንፃር በቅርቡ የገጠመኝን የሚበረታታ የሰላም ጥረት ለአንባቢያን ለማጋራት ወደድሁ።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲ፣ የትግራይ ክልል ወጣቶች ቢሮና ጩራ አቡጊዳ ኪነ ጥበባዊ ማኅበር ከሚያዝያ14 እስከ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የትግራይ ወጣቶች መድረክ በሚል ርዕስ የሰላም ጉባዔ አካሂደዋል። በዚህ የሰላም ጉባዔ ላይ ከመላው ትግራይ የተውጣጡ 500 ወጣቶች፣ ከፍተኛ የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም በርካታ የተጋበዙ እንግዶች ተገኝተዋል። በተዘጋጀው መድረክ ንግግሮች ተደርገዋል፣ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፣ ወጣቱን በሰላም ግንባታ ውስጥ ለማሳተፍ የሚረዱ በርካታ ዝግጅቶች ቀርበዋል።

እኔም በዚህ መድረክ ጥናታዊ ጽሑፍ እንዳቀርብ ተጠይቄ ‘የወጣቶች ሚና በሰላም ግንባታ’ በሚል ርዕስ መልዕክት ያሰተላለፍኩ ሲሆን፣ ትኩረት ያደረግኩት የሰላም ግንባታ ዕድሎች፣ ወጣቶችን በማይመጥኑ የተዛቡ አመለካከቶች፣ በግጭት/ጦርነት ወቅት የወጣቶች ተሳትፎ፣ የወጣቶች ሚና በሰላም ግንባታና የወጣቶችን የሰላም ተሳትፎ የሚገድቡ ተግዳሮቶች ላይ ነበር።

መልዕክቱ ለትግራይ ወጣቶች ብቻ ሳይሆን ግጭት ባለበት አካባቢ ለሚኖር ማንኛውም ሰላም ወዳድ ሕዝብና ወጣት የሚጠቅም ሆኖ ስላገኘሁ የተወሰኑ ሐሳቦችን በዚህ ለማጋራት ወደድሁ።

የሰላም ግንባታ ዕድሎች

የሰላም ግንባታ ዕድሎችን በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል። እነሱም ቅድመ ግጭት መከላከል፣ እርቀ ሰላም ማውረድና ድኅረ ግጭት መልሶ ግንባታ ናቸው። የግጭት/የጦርነት አይቀረነት ሲታወቅ በምክክር ግጭትን መከላከል ማለትም እንዳይከሰት ማድረግ ይቻላል። ነገር ግን ብዙዎች ያለመግባባት ውስጥ የገቡ ወገኖች በግብዝነት፣ በእልህም ይሁን በሌላ ምክንያት ይህንን ዕድል ሳይጠቀሙ ይቀርና ወደ ግጭት ይገባሉ፤ ዋጋም ያስከፍላሉ።

 ግጭቱ/ጦርነቱ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስና የተጋጩ ወገኖች ጨርሶ እንዳይቆራረጡ እርቀ ሰላም ማውረድ ሁለተኛ የሰላም ግንባታ ዕድል ሆኖ ይቀርባል። ይህንን ዕድል ብዙዎች ይጠቀማሉ። ከባድ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት እንዲሁም መፈናቀል ከደረሰ በኋላም ቢሆን ብዙዎች ይታረቃሉ። ይህ በእጅጉ የሚበረታታና የሚደገፍ ተግባር ነው።

ድኅረ ግጭት መልሶ ግንባታ ከደረሰው ጉዳት ለማገገምና ግጭቱ ተመልሶ እንዳያገረሽ ይረዳል። ይህ ዕድል የእርቅ ስምምነት ማክበርና መተግበር፣ የተጎዱ ሰዎችን መደገፍ፣ የተጋጩ ወገኖችን ማቀራረብ፣ የፈራረሰ መሠረተ ልማት መጠገንና ሌሎችም በርካታ የሰላም ግንባታ ሥራዎችን የሚያካትት ቢሆንም በግጭቱ መቆም ተዘናግተውና በደራሽ ጉዳይ ተጠምደው አንዳንዶቹ ይህንን ዕድል ሳይጠቀሙ ይቀርና ሕዝቡ ለከፋ ጉዳትና ለሌላ ዙር ግጭት ይዳረጋል።

ወጣቱ ትውልድ ይህንን አደጋ ተገንዝቦ ባደረ ቂምና ቁርሾ ዳግም ላለመጋጨት በሰላም ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት። በመጀመሪያ የወጣቱን ዓቅምና ሚና የሚያሳንሱና የተዛቡ አመለካከቶች መታረም አለባቸው። በጥቅል ወጣቶች ዓመፀኛና ለኅብረተሰብ አደገኛ እንደሆኑ መግለጽ፣ ያልበሰሉና ምንም የማያውቁ ማስመሰል፣ ኃላፊነት የማይሰማቸው ግድየለሾች ናቸው ማለት፣ ስሜታዊና ግብታዊ እንደሆኑ መግለጽ፣ አክብሮት የሌላቸው /ለባህል፣ ለአዋቂ፣ ወዘተ/ ማስመሰል፣ ትዕግስት የሌላቸው ችኩል አስመስሎ ማቅረብ፣ ራስ ወዳድና ለሌላ የማያስቡ አድርጎ መሣል እንዲሁም ሥራ ፈት፣ ሰነፍና ዕርዳታ ፈላጊ እንደሆኑ መረዳት የተወሰኑ ግለሰቦችን ብቻ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛውን ወጣት የማይወክሉ ናቸው። በቀላል የማይቆጠር ወጣት እነዚህን ባህሪያት ቢያሳይ እንኳ በወጣትነት ዕድሜ የሚገኝን የኅብረተሰብ ክፍል በሙሉ በዚህ መልክ መፈረጅ ስህተት ነው። አዋቂ ናቸው የሚባሉ ግለሰቦች (አባቶች፣ እናቶች፣ አስተማሪዎች፣ ወዘተ) እነዚህን አሉታዊ ባህሪያት የሚንጸባርቁና አንዳንዴም ባላቸው ተጽዕኖ ወጣቱን ወደነዚህ አዝማሚያዎች የሚገፋፉ መሆኑ ሊረሳ አይገባም።

ወጣቶች ለምን በግጭት/በጦርነት ይሳተፋሉ? ማንኛውም ሰው ሰላማዊና የተደላደለ ሕይወት መኖር ይፈልጋል። ሕይወቱን በግጭትና በጦርነት ማሳለፍ የሚወድ ጤናማ ሰው አይኖርም። በመሆኑም ወጣቶች በግጭትና/በጦርነት የሚሳተፉበት ምክንያቶች ይኖራሉ። ለችግር ተጋላጭ ሲሆኑና ከፖለቲካና ኤኮኖሚ ተሳትፎ ሲገለሉ፣ ለቡድን መብቶች ለመታገል የሞራል ግዴታ እንዳለባቸው ሲወስዱና በሌሎች ወገኖች (ፖለቲከኞች፣ ባለሃብቶች፣ አክቲቪስቶች፣ ወዘተ) ተቀስቅሰው የሚገቡ አሉ። ያለዕቅድና ያለምክንያት ሳያውቁ ገብተው ለመውጣት የሚቸገሩም ይኖራሉ። ግርግር ሲፈጠር ዘርፈው/ሰርቀው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት የሚቀላቀሉም አይጠፉም። በውዴታ ይሁን በግዴታ ይጀመር አብሮ ለሚኖር ኅብረተሰብ የግጭትና የጦርነት ውጤት አስከፊ ጉዳትና ኪሳራ ብቻ እንጂ ጥቅም የለውም። ስለዚህም ነው ከግጭት ይልቅ ሰላም ላይ መሥራት የሚገባው።

ወጣቱ ቁጭት፣ ፍላጎት፣ ተነሳሽነት፣ ሐሳብ፣ ራዕይና ጉልበት ያለው ትኩስ ኃይል ስለሆነ በሰላም ግንባታ የላቀ ሚና መጫወት ይችላል። በግልም ይሁን በጋራ፣ በድጋፍም ይሁን ያለድጋፍ ወጣቱ ሊሠራ ከሚችላቸው ሥራዎች የሚከተሉት ይገኙበታል።

 • በውሳኔ አሰጣጥ ሒደት በመሳተፍ ድምፅ ማሰማት
 • ሕዝቡን ለማኅበራዊ ትስስርና መቻቻል ማስተባበር
 • የግጭት መንስኤዎችን በጋራ መፍታት
 • ሕዝቡን ለማኅበረሰብ ልማት ሥራ ማስተባበር
 • የትምህርት/ሥልጠና ዕድሎችን ተጠቅሞ አቅም መገንባት
 • በግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ተሳትፎ መንቃት/ማንቃት
 • በባህላዊና በሃይማኖታዊ የሰላም መድረኮች ላይ መሳተፍ
 • የሰላም ዕይታዎችን ማቅረብ/ማጋራት
 • በፖለቲካ ውስጥ ለመሳተፍ መዘጋጀት
 • በኤኮኖሚ ውስጥ ለመሳተፍ መዘጋጀት
 • የሰላም ኮሚቴዎችን/ክለቦችን መመሥረት/ማጠናከር
 • ማኅበራዊ ሚዲያን ለሰላም/ልማት መልዕክት ብቻ መጠቀም
 • ከታላላቆች፣ አባቶችና እናቶች ጋር በጋራ መሥራት
 • ከመንግሥት አካላት ጋር መተማመን መፍጠርና አብሮ መሥራት
 • የሰላም ግንባታን በባለቤትነትና በተጠያቂነት ማስኬድ

ተፈታታኝ ተግዳሮቶች

የወጣቶችን የሰላም ግንባታ ተሳትፎ ሊፈታተኑ የሚችሉ በርካታ ተዳግዳሮቶች አሉ። ከነዚህ ውስጥ በውሳኔ አሰጣጥ ሒደቶች ውስጥ ለመሳተፍ ከሚመለከታቸው አካላት ዕድል አለማግኘት፣ በወጣቶች ተነሳሽነት ለሚመሩ ሥራዎች ድጋፍ ያለመኖር፣ በግጭት ወቅት ወጣቶች ላይ የደረሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆን፣ በሌሎች ምክንያቶች ወጣቶች ራሳቸው ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆን፣ ወጣቶችን እንደ ችግር ፈጣሪና አደገኛ አድርጎ ማየት፣ ማኅበረሰቡ የወጣቶችን ሚና ለመቀበል ዝግጁ አለመሆን፣ አለመተማመን፣ እና የማኅበረሰብ ትስስር መላላት የተወሰኑት ናቸው።

ስለዚህ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲሁም ኅብረተሰቡ ወጣቱን ያልካተተ የሰላም ግንባታ ጥረት ውጤታማ እንደማይሆን በመገንዘብ በሒደቱ የማሳተፍና እገዛም የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ወጣቱም በበኩሉ ተስፋ ባለመቁጠር እገዛ በማያስፈልጉ ዘርፎች ማንንም ሳይጠብቅ በሰላም ላይ መሥራት ባህሉና ግዴታው ሊያደርገው ይገባል።

ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ወጣቶች ውስጥ የታመቀ ሐሳብ፣ ቁጭትና ፍላጎት ወይም ተነሳሽነት አለ። ይህንን አቅም አስተባብሮና አጠናክሮ መጠቀም ከተቻለ አገር ተረካቢው ባላደራ ወጣት ከሰላም ግንባታ በላይ መሥራት ይችላል። ስለዚህ ወጣቶችን መደገፍ በቸርነት እንደሚሰጥ ልገሳ ሳይሆን በውስጣቸው የታመቀውን ጸጋ በመጠቀም የዛሬውን የአገር ችግር እንዲፈቱና የነገዋን ኢትዮጵያ እንዲረከቡ የሚደረግ አገራዊ ኢንቨስትመንት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል። ወጣቶችም እንደዚሁ ሰላምና ልማት ላይ ማተኮር ጥቅሙ ከማንም በላይ ለራሳቸው የወደፊት ሕይወትና ለልጆቻቸው መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል።

ከአዘጋጁጸሐፊው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ፕሮፌሰርና የጂንካ ዩኒቨርሲቲ መሥራች ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ከምርምር ሥራዎቻቸው መካከል የብሔረሰቦች ግንኙነት፣ የግጭት አፈታት ዘዴዎች፣ የአገር በቀል ዕውቀቶችና ልማዳዊ ሕጎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሚና፣ እንዲሁም ሠፈራና የምግብ ዋስትናን የተመለከቱ ይገኙባቸዋል፡፡ አሁን የግል ተመራማሪና አማካሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው gebred@gmail.com. ማግኘት ይቻላል፡፡   

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles