Friday, May 24, 2024

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ታሪካዊ ኃላፊነትና ከትግበራው ጀርባ የሚነሱ ሥጋቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልልና ከተወሰኑ የአማራ አካባቢዎች በስተቀር በአሥር ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች በምክክሩ ሒደት የሚሳተፉ ተሳታፊዎችን የመለየት ሥራ አከናውኖ፣ በ932 ወረዳዎች 17,210 ተሳታፊዎች መለየታቸውን አስታውቋል፡፡

ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጠው መግለጫ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለማምጣት አዲስ የፖለቲካ ባህል የግድ መሆኑን ጠቅሶ፣ ለዚህም ሁሉን አካታች አገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕና የተሐድሶ ተግባራት የዚህ ትልም ዋነኞቹ ማስፈጸሚያ መሣሪያዎች መሆናቸውን አስታውቆ ነበር፡፡

ምክር ቤቱ በመግለጫው አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በጥቂት ሳምንታት አካታች በክልል ደረጃ የሚደረጉ የምክክር መድረኮችን በማካሄድ የምክክር ጉባዔ ይጀምራል ብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል፡፡ ይህ የምክክር አካሄድ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ሕዝብ ማዕከል ያደረገ እንደሆነም ገልጿል፡፡

ከሳምንት በፊት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሒሩት ገብረ ሥላሴ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ የታጠቁ ኃይሎችወደ አገራዊ ምክክር ሒደቱ እንዲመጡ ኮሚሽኑ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ተፋላሚ ወገኖች ወደ አገራዊ ምክክሩ እንዲመጡ፣ በሚሳተፉበት ወቅት ደግሞ ከለላና ጥበቃ እንደሚደረግላቸውና ምንም ዓይነት አደጋ እንደማይደርስባቸው አስታውቀዋል፡፡ ምክትል ኮሚሽነሯ ምን ዓይነት ከለላ እንደሚደረግላቸው ዝርዝር ማብራሪያ አልሰጡም፡፡

 የምክክር ኮሚሽኑ የጀመረው ሒደት በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ያሉ አለመግባባቶችን መፍታት የፖሊሲ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ ምክረ ሐሳብ ማቅረብና በተለይም የፖለቲካ ሥርዓት ማሻሻያ፣ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ለውጦች ማሻሻያ፣ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ የሚደረጉ ማሻሻያዎችና ቀደም ሲል ለተፈጸሙ በደሎች መፍትሔ ማበጀት የሚሉት ይገኙበታል፡፡

በምክክሩ ሒደት የፖሊቲካ ፓርቲዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የነቃ ተሳትፎ በማድረግ፣ በምክክር የማመን የፖለቲካ ባህል ለመገንባትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ማደግ መደላድል በመፍጠር የዴሞክራሲ ልምዳቸውን የሚያዳብሩበት መሆኑንም ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑም ሆነ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ይህን ይበሉ እንጂ አዲስ የፖለቲካ ባህል ለማምጣት መፍትሔ ናቸው ተብለው በተያዙት አገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕና የተሃድሶ ኮሚሸን ተግባራት ላይ ያኮረፉ፣ ትጥቅ አንግተው ጫካ የገቡ፣ ዳር ሆነው የሚመለከቱና የመንግሥት ትልም ያልተዋጠላቸው የተለያዩ አካላት መኖራችው ሒደቱን ስኬታማ እንዳይሆን እንደሚያደርጉ በተለያዩ መንገዶች እየተስተዋለ ነው፡፡ በተመሳሳይ የሕዝብ ተወካዮች አባላትን ጨምሮ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት በእስር ላይ መሆናቸው እንደ ችግር ይነሳል፡፡

ከእነዚህ መካከል በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሰውና በፓርላማው በአሸባሪነት የተሰየመው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ)፣ እንዲሁም በአማራ ክልል ከሚገኙ ታጣቂዎች ጋር በቀጠለው የትጥቅ ትግል ከሚሳተፉ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን ግጭት መንግሥት በሰላማዊ መንገድ መፍታት ካልቻለ እነዚህ ተፋላሚ ኃይሎች ያልተሳተፉበት የአገራዊ ምክክር፣ የሽግግር ፍትሕና የተሃድሶ ኮሚሸን ውጤት ፋይዳው የጎላ ላይሆን እንደሚችል ይወሳል፡፡ የአገሪቱ ልምድ እንደሚያሳየው መሣሪያ ታጥቀው የሚፋለሙ አካላትን በተወካይ ማሳተፍ የተለመደ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ አሁን ባለው ሒደት እስካሁን የተገለጸ ነገር የለም፡፡

በሌላ በኩል እንደገና ባገረሸውና በቅርቡ በትግራይና በአማራ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በሰጠው መግለጫ የማንነት ጥያቄ ያለባቸውን ራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረምና ዛታ አካባቢዎች ወረራ መፈጸሙን ጠቅሶ፣ ‹‹ሕወሓት ከግብረ አበሮቹ ጋር ፖለቲካዊ ግልሙትናና ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማድረግ ከመሞከር እንዲታቀብና የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በማክበር በአጭር ጊዜ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ እንዲወጣ›› መጠየቁ ይታወሳል፡፡

ይህ የማይሆን ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ከሌሎቹ ወንድምና እህት ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ በመሆን፣ ‹‹አገርን ከማፍረስ መታደግና ሕዝባችንንም ከጥቃት ለመከላከል የምንገደድ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን፤›› ሲል በመግለጫው አስታውቆ ነበር፡፡  ክልሉ በመግለጫው አክሎም፣ ‹‹ዛሬም እንደ ትናንቱ በፅናትና በቁርጠኝነት ሕዝቡን በማደራጀት አካባቢያችሁን በመጠበቅ ታሪካዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ፣ ጠላቶቻችን የከፈቱብንን ጥቃት ለመመከት  በሚደረገው ጥረት ከመንግሥት ጎን በመሠለፍ የድርሻህን ጥሪ ተወጣ፤›› የሚል ጥሪም ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡

በተመሳሳይ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በዚሁ ጉዳይ በሰጠው መግለጫ፣ ‹‹የአማራ ተወላጆች ላይ በጠላት በኩል የሚነዙ የፕሮፖጋንዳ ማደናገሪያዎችን እውነተኛ ዓላማ በመረዳት፣ የክልሉ ሕዝብ ዳግም ለጥቃት ላለመጋለጥ አስፈላጊውን ራስ የመከላከል ዝግጅት እንዲያደርግና አንድነቱን እንዲያጠናክር፤›› የሚል ጥሪ አስተላልፎ ነበር፡፡

ከቀናት በፊት ደግሞ የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ሥር ተጠቃለው የተቋቋሙ አስተዳደራዊ መዋቅሮች እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. መፍትሔ እንደሚያገኙ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ሌተና ጄነራል ታደሰ ወረደ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ በዚሁ ሁሉ ሒደት በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ያለው ውጥረት በሰላማዊ መንገድ የማይፈታ ከሆነ በምክክሩ ሒደት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከባድ እንደሚሆን እየተነገረ ነው፡፡

በወሰን አካባቢ መሰል ውዝግቦች በአገር አቀፍ ደረጃ ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ተፈናቅለው በሚገኙበት፣ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዘንድ የተለያዩ የተቃውሞ ድምፆች በዙበት በዚህ ወቅት፣ አገራዊ የምክክር ትልምና ታሪካዊ ኃላፊነት ዕውን የመሆን ጉዳይ አጠያያቂ ይሆናል የሚል ሥጋት አለ፡፡

ኮሚሽኑ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመን የሰፈነበትና አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች እንዲካሄዱ ሥርዓት ለመዘርጋት፣ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ውስጣዊ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችል የፖለቲካ ባህል ለማዳበርና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ምቹ መደላደል መፍጠር የሚሉት ዓለማዎችን ይዟል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕሮፌሰር) በቅርቡ በሰጡት መግለጫ፣ አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አጠቃላይ ሥራ በቀጣይ አሥር ወራት ይጠናቀቃል፡፡ ኮሚሽኑ በቀጣይ ጊዜያት አጀንዳ የመሰብሰብ ሥራው በየዘርፉ ተካሂዶ ወደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንደሚላክ አስታውቀዋል፡፡ የተሰበሰበውና ወደ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተላከው አጀንዳ የኮሚሽኑ ታዛቢዎች ባሉበት በግልጽ መሥፈርት ተመርጦ፣ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡

የምክክር ሒደቱም ኮሚሽኑ በሚሰጠው ቀመር መሠረት እንደሚካሄድና በምክክር ሒደት የሚለዩ ሕገ መንግሥታዊ፣ የባንዲራ፣ የማንነትና የአስተዳደር፣ በአጠቃላይ ማናቸውም ለኩሪፊያ፣ ለቁጣና ለግጭት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው ተወካዮች ባሉበት ምክክሩ ተካሂዶ ወደ ትግበራ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡ በመጨረሻም ምክክሩ ተጠናቆ በትግበራ ምዕራፍ መፈጸም ያለባቸው ጉዳዮች እንደ አስፈላጊነቱ ወደ የሚመለከታችው የመንግሥት፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካ ተቋማትም ሆነ ሌሎች አካላት እንደሚላክ ገልጸዋል፡፡

ኮሚሽኑ ሥራዬን በዚህ ሒደት አጠናቅቄያለሁ ብሎ ዕቅድ የያዘ ቢሆንም የሕግ ባለሙያዎች፣ የፖለቲካ ተንታኞችና ምሁራን፣ እንዲሁም ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. ፀድቆ ወደ ሥራ የገባው የሕገ መንግሥት ዝግጅትና የማርቀቅ ምዕራፍ ኢትዮጵያውያን በእኩል ያላሳተፈና የተወሰኑ ቡድኖችን ጥቅም ያደላ መሆኑን በማውሳት አሁንም ተመሳሳይ ሥጋት እንዳላቸው ይናገራሉ፡፡ በሕገ መንግሥት ይዘት የተነሳ የተፈጠረው አለመግባባት አንዳንዶችን ወደ ግጭት ጋብዟል፡፡ ሌሎች ደግሞ የሕዝቦች የቃል ኪዳን ሰነድ ተደርጎ የሚወሰደውን የሕገ መንግሥት ሰነድ ዋጋ የማሳጣትና በውስጡ ያሉት ድንጋጌዎች እየተጣሱ በርካታ ዜጎች መከራ እየከፈሉበት፣ አገር አሁን ለደረሰችበት ቀውስና ምስቅልቅል አንዱና ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ምከንያት ተደርጎ ይወሰዳል ይላሉ፡፡

በዚህ ረገድ ለዘመናት ያለመግባባት ምንጭ ለሆኑ ታሪካዊ ቁርሾዎች መፍትሔ ያመጣል ተብሎ የተቋቋመው አገራዊ የምክክር ኮሚሽን፣ ከተለያዩ ወገኖች በሚነሱ የተቃውሞ ድምፆችና አስተያየቶች የተነሳ የታለመለትን ግብ የማምጣት ውጥኑ አጠያያቂ ስለመሆኑ ያነሳሉ፡፡

በዚህ ረገድ እንዲህ ዓይነት አገራዊ የመፍትሔ አማራጮች ሲዘጋጁ በመሠረታዊነት የሚከናወኑ ሥራዎች ካለው ችግር ጋር ተመጣጣኝ መሆን እንዳለባቸው የሚናገሩት፣ ፖለቲከኛውና በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህሩ አቶ ደመወዜ ካሴ ናቸው፡፡ እሳቸው እንደሚሉት ይህ የማይሆንና ሥራዎች ሁሉ የይድረስ ይድረስ የሚደረጉ ከሆነ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ዛሬ መፍትሔ ተብሎ የተቀመጠ ጉዳይ ተመልሶ መፈንዳቱና የግጭት መንስዔ መሆኑ አይቀርም ይላሉ፡፡

 ኢትዮጵያ መሠረታዊ የሆነ ስብራት ገጥሟታል የሚሉት አቶ ደመወዜ፣ ለዚህ የሚመጥን ሥራ መከናወን ቢኖርበትም ኮሚሽኑ ከጅምሩ ሲቋቋም የብልፅግና ፓርቲ ፍላጎት ነፀብራቅ ሆኖ የተገነባ ተቋምና ስብስብ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ የተደራጀ ስብስብና ተቋም ለበርካታ ዘመናት የቆዩና የተወሳሰቡ ችግሮችን ሊፈታ አይችልም ብለዋል፡፡

‹‹ብልፅግና የሚባለው ስብስብ በራሱ ችግር ነው፣ ስብስቡ በራሱ ለዚህ አገር ችግር ነው፣ ለአገር አይደለም ለራሱ ችግር መፍትሔ የለውም፣ የመንግሥትነት ባህሪ ከሌለው ስብስብ ውስጥ የሚፈልቁ የመፍትሔ አማራጮች ችግር ይዘው ይመጣሉ፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹የኮሚሽኑ ስብጥር አካታች ያልሆነና ተመራጮችም ገለልተኛ ያልሆኑ፣ በሥራቸውም የብልፅግና ተፅዕኖ የሚጫናቸውና በእርግጠኝነት ከሁለትና ከሦስት ዓመታት በኋላ የሥራቸው ውጤት ሌላ የግጭት መነሻ የሚሆንባቸው ናቸው፤›› ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ጫፍና ጫፍ የረገጠ አስተሳሰብ የተነሳ አይደለም እንዲህ ታሪካዊና አገራዊ ትልቅ አጀንዳ ቀርቶ፣ ትንሽ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር እንኳን የገለልተኛነት ጉዳይ በትልቁ መታየት ያለበት እንደሆነ አክለው ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ኮሚሽን የአገሪቱን ችግር በሚመጥን ደረጃ ውይይትም ምክክርም ሊደረግ አይችልም ይላሉ፡፡

አቶ ደመወዜ በአገራዊ ምክክሩ አማካይነት አንገብጋቢ የሚባሉ የሕዝብ አጀንዳዎች መሰብሰብ ይችላሉ ወይ በሚለው ጉዳይ አስተያየታቸውን ሲሰጡ በርካታ ፖለቲከኞች ታስረው፣ ታጣቂዎች በየጫካው እየተዋጉ፣ እንዲሁም በተወሰኑ አካባቢዎች በአንድም ሆነ በሌላ ውጊያ እየተካሄደ አገራዊ አጀንዳ እንኳን ከፖለቲከኞች ከተራው ሕዝብ ለመሰብሰብ እንኳን በጣም አዳጋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ለታጣቂ ኃይሎች ከለላ እንሰጣለን የሚል አስቂኝ ዜና መስማታቸውን የሚናገሩት አቶ ደመወዜ ይህ ‹‹ቀልድ ነው›› ይላሉ፡፡ ‹‹ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ሰላማዊ ትግል እናደርጋለን የሚሉት ሰዎች እኮ እስር ቤት ነው ያሉት፡፡ አቶ ልደቱ አያሌው እኮ ሁልጊዜ ስለሰላማዊ ትግል እያሉ ሲናገሩ ይሰማል፡፡ ነገር ግን እሳቸው ራሳቸው በሰው አገር ነው ያሉት ተሰደው፡፡ እዚህ መጥተው ሰላማዊ ትግል ማድረግ አልቻሉም፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባሩ አቶ በቴ ኡርጌሳ እኮ በጥይት ተተኩሶባቸው ነው የተገደሉት፡፡ ሰላማዊ ሠልፍ የጠየቁ ሰዎች እኮ አትችሉም ተብለው እስር ቤት ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በዚህ ሒደት ስለምን ሰላማዊ ትግል? ስለምን አራዊ ምክክር ነው የምናወራው? መያዣ መጨበጫ የሌለው ነገር ላይ ነው እኮ ያለነው፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)  ሊቀመንበር መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ በተለያዩ ጊዜ አቋማቸውን ማስታወቃቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል ‹‹ተቋሙ ከመሬት ሳይነሳ የሞተ ነው፡፡ ፈረንጆች እንደሚሉት ‹‹Dead Upon Arrival›› ማለት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የዓለም ተሞክሮን በተመለከተ በተደጋጋሚ በየመድረኩ ስለመናገራቸው የሚያነሱት መረራ (ፕሮፌሰር)፣ ይህ መሰሉ ሥራ በሦስተኛ ወገን ወይም በገለልተኛ አካል መመራት አለበት ብለን ነበር ይላሉ፡፡ አክለውም ይህ ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ባህልም ሽማግሌ ስትቆጥር ግራና ቀኝ አይተህ እንጂ፣ ከአንድ ወገን ብቻ ሽማግሌ ይዘህ መጥተህ ኑ ታረቁ አይባልም ብለዋል፡፡

‹‹እኛም እንዲህ ዓይነት ጨዋታ ተው የትም አያደርስም፣ ላለፉት ዓመታት ከአንድ ቀውስ ወደ ሌላ ቀውስ ስንሸጋገር የኖርነው፡፡ ሕገ መንግሥታችንን ጨምሮ የሚወጡ ፖሊሲዎች በቂ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎ ስለሌላቸው ነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሠረታዊነት የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ከሥልጣን ፍላጎት፣ ጉጉትና ስስት የፀዳ ሕግና ፖሊሲ መውጣት አለበት፡፡ ነገር ግን ሕጎች ከሥልጣን መርዘምና ማጠር ጋር ተቆራኝተው የሚወጡ ከሆነ የትም አይደረስም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

መረራ (ፕሮፌሰር) እንደሚሉት፣ ኮሚሽኑ አወቃቀሩ በአንድ ቡድን ፍላጎት ተመርጦ የተሰየመ፣ ሕጉን ያፀደቀው ብልፅግና በአብላጫ በተቆጣጠረው ፓርላማ ውስጥ ሆኖ የተሾሙት ኮሚሽነሮች የሚገመገሙት በዚሁ ፓርቲ በመሆኑ ሥራውና ውጤቱ ገለልተኛ ነው ብሎ መውሰድ አይቻልም፡፡

ኮሚሽኑ የመጀመሪውን ሥራ ጨረስኩ ብሎ ሪፖርት ሊያቀርብ ቢችልም፣ ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግ ጊዜ እንደነበረው የቅርብ ጊዜ ታሪክ ብልፅግናዎች በሚፈልጉት መንገድ ጉዳዩን መርጠው ይዘውት እንደሚቀርቡ ያስረዳሉ፡፡ በዚህ ሒደት በመጨረሻ ብልፅግናዎች የሚመርጡትን ምክረ ሒሳብ ሥራ ላይ አውላለሁ ብሎ የሚመጣው አካልም ይህ የአንድ ፓርቲ ስብስብ ፓርላማ ይሆናል ብለዋል፡፡

አገራዊ ኮሚሽኑ ከሰላማዊ ትግል ውጪ ያሉ አካላት ወደ ምክክር ቢመጡ ምንም ዓይነት አደጋ እንደማይደርስባቸውና ከለላ ይኖራቸዋል ስለተባለው፣ ‹‹ቀልድ ነው›› ነው ያሉት መረራ (ፕሮፌሰር) እንኳን ጫካ ያሉት አዲስ አበባ ያሉት ሰዎች ቀላል ጊዜ እያሳለፉ አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ይህ ዓይነቱ ንግግር ለቀልድ የተነገረ ነው ይላሉ፡፡ ለአብነት በኦሮሚያ ጫካ ቀርቶ በቅርቡ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ከፍተኛ አመራር የተገደሉት እኮ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሚያደርጉበት ከተማ ውስጥ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

በአጠቃላይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አመሠራረት መሠረታዊ የሆኑ የአገሪቱን ችግሮች ኃላፊነትና ተጠያቂነት ባለው መንገድ ለመፍታት ሳይሆን፣ ሥልጣን ላይ ያለው ‹‹ቡድን›› ወይም ፓርቲ የራሱን ጨዋታ ለማቀላጠፍ፣ ሕዝብንና የዓለም ማኅበረሰብን ለማጭበርበርና ለማደናገር የሚጠቀምበት እንደሆነ መረራ (ፕሮፌሰር) ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር ራሔል ባፌ (ዶ/ር) በዚሁ ጉዳይ ላይ ለሪፖርተር በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹እንደ አገር አሁን ካለንበት ሁኔታ ለመውጣት የሚቻለው ሁሉ መሞከር አለበት፡፡ ነገር ግን አስቻይ ነገር የለም፤›› ይላሉ፡፡ ብሔራዊ ምክክር በሰላማዊ ሒደት የሚከናወን በመሆኑ ማንኛውም ታጣቂ መሣሪያ አስቀምጦ ወደ ውይይት ጠረጴዛ ይምጣ የሚለው አስተሳሰብ ትክክል ነው ብለው፣ ነገር ግን አሁን ባለው የመንግሥት አሠራር የሕዝቡን ሰላምና ደኅንነት ማስከበር አለመቻሉ አገራዊ ሥጋቱ እንዲቀጥል ስለማድረጉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ለአብነት በፕሪቶሪያ ስምምነት መሠረት የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ ይፍቱ ተብሎ ትጥቅ ሳይፈቱ ከአማራው ወገን እንዲፈታ መደረጉ ሌላ ቁስል የሚያመጣ በመሆኑ፣ አሁን ወደ ምክክር ሲገባ ሁለት የተለያዩ አካላት በተለያየ አቅም ይመካከራሉ ወይ የሚለው ጉዳይ ጥያቄ ይፈጥርብኛል፤›› ብለዋል፡፡

የአገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከወራት በፊት በሰጠው መግለጫ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ የፖለቲካ እስረኞችም ሆኑ ሌሎች ታራሚዎች፣ እንደ አንድ የኅብረተሰብ ክፍል በውይይትና በምክክር ሒደቱ እንዲሳተፉ መታየት ያለበት ጉዳይ ካለ በቀጣይ የሚወሰን መሆኑን አስታውቆ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በዚሁ ጉዳይ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

በአካታችነት፣ ታጥቀው የሚታገሉ አካላትንና በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞችና ግለሰቦች በምክክሩ ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎና ኮሚሽኑ ከያዘው ታሪካዊ ኃላፊነት አንፃር ሪፖርተር ተጨማሪ ማብራሪያ የጠየቃቸው የአገራዊ ምክከር ኮሚሽነር ዮናስ አዳየ (ዶ/ር)፣ ዘርዘር ያለ መልስ ከመስጠት ቢቆጠቡም በቅርቡ ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት ለሁሉም አካላት የመጫወቻ ሜዳው የተደላደለ እንዲሆን ለመንግሥት ጥያቄ መቅረቡን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -