Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉአዲስ አበባ ይብስ ጠወለገች - ከተሜነት እንደ አገርና ዓለም አቀፍ የነፃነት ጥያቄ

አዲስ አበባ ይብስ ጠወለገች – ከተሜነት እንደ አገርና ዓለም አቀፍ የነፃነት ጥያቄ

ቀን:

(ክፍል ሁለት)

በሱራፌል ወንድሙ

  1. ግቢያ

“አሁን እነትዬ ብርቄና እትዬ አስካለ ኒዮሊብራሊዝም ቢሸሽ ወይም ቢያፈገፍግ አይደለም ፈርጥጦ ቢጠፋ ምን አገባቸው?” የሚለውን ተረብ አዘል አስተያየት የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር አንድ የጋዜጣ ፖለቲካዊ ምፀት አምደኛ የጻፈው። ሐሳቡን ያጫረው ደግሞ በወቅቱ “ኒዮ ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” በሚለው ርዕስ ዙሪያ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ተወያዩ የሚለው የመንግሥት ዜና ነበር። በእርግጥም በኅዳር-ታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. “ኒዮሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” የሚል ሰፊ ውይይትን የሚያጭር (ምንም እንኳን የኢሕአዴግን የትርክትና የተግባር መምታታት ባንዘነጋውም) ትንተና አዲስ ራዕይ በተሰኘው የኢሕአዴግ ልሳን መፅሔት ላይ ከታተመ በኋላ ነበር ካድሬዎች መሰል ውይይት ሲያደርጉ የነበረው። የብልፅግና ፓርቲ “ኒዮ ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” የሚለውን የ2010 ዓ.ም. መጽሔት ሽፋን ዛሬም በድረ ገፁ ላይ ለጥፎት ይታያል (ከዚህ በኋላ ያጠፋው ይሆን?)። በጣም የሚገርመው ነገር፣ በአሁኑ ሰዓት በፖለቲካና ኢኮኖሚ ውሳኔዎች እየሆኑ ያሉትን ነገሮች “ኒዮ ሊበራሊዝም ሸሸ ወይስ አፈገፈገ?” ከሚለው ከዚያ ጽሑፍ ጋር ስናስተያይ፣ ተለያይተናል ባሉት በኢሕአዴግና በብልፅግና መካከል ያለውን እንቆቅልሻዊ ግንኙነት (Uncanny Relationship) እንድንመረምር ይገፋናል። ዛሬ ያንን ግንኙነት ከመዳሰስ ይልቅ፣ እንደ ውይይቴ መነሻ ላደርገው ነው የፈለግኩት። በመግቢያዬ ላይ እንዳነሳሁት የዚያ ጋዜጣ አምድ አስተያየት እንደጠቆመው፣ የየዕለት ኑሮ ለፍቶ አዳሪዎችም ሆኑ ሁላችንም ኒዮ ሊበራሊዝም ቢሸሽ ባይሸሽ፣ ልማታዊ መንግሥት ምን ማለት እንደሆነ ብናውቅ ባናውቅ  ምንም አያገባንም ማለት እንችል ይሆን? ፓርቲዎች በውስጣቸውም ሆነ ከሕዝብ ጋር ጥልቅ ውይይቶችን ቢያካሂዱም ባያካሂዱም፣ እንደ ሕዝብ ችግሮቻችንን በስፋት መተንተኑ የሚጠቅመን፣ በንድፈ ሐሳቦች ላይ ለመራቀቅና ሕዝብን ለማደናገር ሳይሆን፣ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ውስብስብ ሁኔታዎቻችንን በማፍታታት፣ ሕዝባዊ መፍትሔዎችን ከሕዝብ ጋር ለሕዝብ ስንል ለማምጣት ነው።    

- Advertisement -

አገራችን ቢያንስ ላለፉት ስምንት ዓመታት፣ የምርት ሥርዓቷ በሕዝባዊ አመፆችና ፖለቲካዊ ነውጦች ምክንያት እንደተዛባባት አለች። ሌላው ቀርቶ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተቀጣጠለውን ተቃውሞና እስከ ዛሬ ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች የተነሱትን ግጭቶች፣ ጦርነቶ፣ ሞቶች፣ የመቁሰል አደጋዎች፣ መፈናቀሎች፣ ስደቶች፣ ረሃቦች ልብ እንበል። እነዚህ ችግሮች ደግሞ የምርት ሥርዓቱን ማዛባት ብቻ ሳይሆን የሕዝቡን ሰውነት፣ አዕምሮ፣ ሀብትና ንብረት በእጅጉ ጎድተውታል። የወደመው የአገሪቱ ሀብት የትየለሌ ነው። እነዚህ የአሥር ዓመታት ሕይወታችን ማሳያ ብቻ ናቸው። ከዚያ ቀድሞ ለዘመናት ተከማችተውብን የነበረውን አገራዊ የድህነት ችግሮች አዳብለን ስናየው፣ አገራችን ምን ያህል የችግርና የፈተና አረንቋ ውስጥ እንደተዘፈቀች በደንብ መረዳት እንችላለን። ምንም እንኳን ‘ደህና ነን፣ መርዶ ነጋሪዎች ከሚሉት በተቃራኒው እየተመነደግን ነው’ የሚል አለባብሶ የማረስ ሁኔታ በመንግሥት ዘንድ በተደጋጋሚ ቢስተዋልም፣ አገሪቱ ደጋግማ በአረም እየተመላለሰች ወይም ሰብዓዊነትን እየፈተኑ ባሉ ችግሮች እየታመሰች ነው። ያንን ደግሞ ከማንም በላይ ደሃው ሕዝብ በዕለት ኑሮው ያውቀዋል።

የሚያሳዝነው ነገር ተቃዋሚዎችን ጨምሮ በኢኮኖሚ ላይ በተለይ ደግሞ በድሃ ተኮር ኢኮኖሚ ለውጥ ላይ ትንታኔ እየሰጠን አለመሆናችን ነው። በማንነት ጥያቄዎች የሚያጋድሉን መሪዎች፣ በአብዛኛው ወይ የኢኮኖሚ ጉዳይን በቅጡ አይተነትኑም ወይም ደግሞ በተመሳሳይ ሁኔታ የኒዮሊበራሊዝምን አዳኝነት ነው የሚሰብኩት። የሊበራሊዝም ኢኮኖሚ መንግሥትን ነፃውን ገበያ እንዳትደርስበት፣ የነጋዴውንና የሸማቹን የፍላጎትና አቅርቦት ድርድር በርቀት እያየህ ዳር ይዘህ ኑር ማለቱ ይታወቃል። ገበያን እንደ መልካም ዳኛ በመቁጠሩ። ጭቆና በተጫወተባትና ጥቂቶች ከባርነት፣ ከቅኝ ግዛትና ከተለያዩ አምባገነንነቶች ሀብት ዘርፈው ባሉባት ዓለም “ነፃ” የሚባል ገበያ አለ ማለት፣ ያው መልሶ በነፃ ገበያ ስም እነዚያኑ ሃብታሞች የበለጠ እናጠናክራቸው ማለት እንደሆነ እናውቃለን። ኒዮሊበራሊዝም ደግሞ እኔ የሊበራል ኢኮኖሚን ላፀና እንጂ ልሽር አልመጣሁም አለ። እንዲያውም መንግሥት ለግል ባለሃብቶች ጥቅም ሲባል ሕጉን በማደላደል ቀጣይነት ያለው ጥበቃ መስጠት አለበት የሚል አስተሳሰቡን አመጣ። ገበያ የፍላጎትና አቅርቦትን ድርድር የሚያሳካ መልካም ዳኛ ብቻ ሳይሆን የሕይወታችንም ዋነኛ መሪ ነው አለ። በዚህ ብቻ ሳይወሰን የሸማችነት ፍላጎትን በምናባችን ውስጥ በረቀቀ ዘዴ በመክተት፣ መንፈሳችንንና ህልማችንን ለመቆጣጠር አበክሮ ይሠራ ጀመር። እናም የዜጎች የሕይወት ግብ በትርፍና ኪሳራ የሚለካ የግልና የግል ቁሳዊ ስኬትና ሸቀጥ ሸማችነት ነው የሚለውን አስተሳሰቡን ማንሰራፋቱን ተያያዘው። ከትላልቅ የዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚ ቲዎሪዎች በከፍተኛ ባለገንዘቦች እስከሚደገፉ የጥናትና ምርምር ተቋማት እንዲሁም ከመንግሥታት ፖሊሲዎች እስከ ዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነቶች ድረስ ኒዮሊበራሊዝም ራሱን በሐሳብም በእጅ ጥምዘዛም ዓለምን ካላስገበርኩ እንዳለ አለ። ምንም እንኳን የመንግሥት የተቀየጡ ኢኮኖሚያዊ ተግባራት ቢስተዋሉም፣ በእኛም አገር ሆን ተብሎም ይሁን በየዋህነት ኒዮሊበራሊዝም እንደ ሃይማኖት እየተሰበከ ነው። በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከፖለቲካ መሪዎች እስከ መጻሕፍት መሸጫ ሱቆችና የመንገድ መደብሮች እንዲሁም የአገሪቱ ሬዲዮኖችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ድረስ፣ የስኬት ቁልፍ ማግኛ ዕውቀቶችን እንሰጣለን የሚሉ “አዳኞች” እየፈሉ ነው። ዕድገትም ውድቀትም የግለሰቡ ኃላፊነቶችና የግል አዕምሯዊ ጠባዮች ናቸው እያሉ የሕዝባዊ ጥቅሞችን (Public Good) ሐሳብ በመናድ ትምህርትን ሳይቀር ጥቂት ባለገንዘቦች የሚደርሱባት ሸቀጥ ሊያደርጓት እየተጣደፉ ነው። አነቃቂ የሚባሉ ንግግሮችና ከፖለቲካ የተነጠሉ “ግብረገባዊ” ስብከቶች ከመድረክ እስከ ሚዲያ ይህንኑ ድግምት ያነበንባሉ። ግብር ከፋዮች ከመንግሥት መብቶቻቸውን እንዳይጠይቁ፣ ወጣቶች ለማኅበራዊ ችግሮች ማኅበራዊ መልስ እንዳያፈላልጉ፣ የማኅበራዊ ፍትሕን አንድ ላይ ማስተጋባት ከተሳነው የኢትዮጵያዊነትም ሆነ የብሔር ፅንፈኝነት እንዳይላቀቁ፣ የሚያጫርሷቸውን ጥቅመኛ ብሔረተኞች እንዳይፋለሙ፣ መሪዎችን ሳይሆን እነሱን የሚበላቸውን ጦርነት እንዳይቃወሙ፣ ፖለቲካዊ መልስ እንዳይሹ ያደነዝዟቸዋል። ታዲያ ይሄኔ ኒዮ ሊበራሊዝም (በኢትዮጵያ) የራሱን መልክና ባህሪ ይዞ ያለ ሃይ ባይ ይገማሸራል። በዚህ መሀል ዋናው ጥያቄ ድሃን የሚወግኑ ፖሊሲዎችን እየቀረፅን፣ የግድ ዘለን ልናመልጠው የማንችለውን ኒዮ ሊበራሊዝምን በረቀቀ አካሄድና መላ እየተደራደርን እንቀጥላለን ወይስ ገበያውን ለባለገንዘቦች በሕግ እያደላደልን (በቅርቡ እየወጡ እንዳሉት አዳዲስ ሕጎች) መንግሥትን ድሃ ረጋጭ፣ የሃብታም አሻሻጭና በሥልጣንና ሀብት ማማ ላይ ተፈናጣጭ አድርገን እናስቀጥለዋለን? ያ ነው ጥያቄው።

የኒዮሊበራሊዝምን ሐሳብ እየተንሰራፋ መምጣት ከዛሬው ርዕሴ ጋር አያይዤ ለማውራት ስንደረደር፣ እሴትን የሚጨምሩና በዓለም ገበያ ተፎካካሪ የሚያደርጉ አዳዲስ ምርቶች ላይ በማተኮር የውጭ ምንዛሪን ማበልፀግ ላይ አለማተኮራችን ያለውን ጉዳት ማስገንዘብ እወዳለሁ። በተለይ አሁን ትርፍ እናገኝበታለን ብለን የምንሄድበት መንገድ ኪራይ ተኮር የገንዘብ ኒዮሊበራሊዝምን ወይም የጨበጣ ቁማር መሰል ውርርድን (Financial Neoliberalism) የተንተራሰ እንደመሆኑ፣ አገራችንን ለጊዜው እንኳን ያዳናት ቢመስል በሒደት የበለጠ ያመነምናታል። የኒዮሊበራሊዝም ነገር ሲነሳ “የኮሪደር ልማት” እየተባለ የሚጠራው፤ ነገር ግን መላውን የከተማውን ገፅታ፣ ኑሮና አኗኗር ከመሠረቱ ሊለውጥ የተነሳው ፕሮጀክት የኒዮሊበራሊዝም ቋንቋን ተገን አድርጎ ነው፣ ድሃ ጠረጋና ሀብታም ተከላውን እየተያያዘው ያለው። በዚህ በኩል የመንግሥት ኃላፊዎችም ሆኑ በከተማ ቅየሳ የካበተ ትምህርትና ልምድ አለን የሚሉት ሰዎች እየተጠቀሙ ያሉትን ቋንቋ መመልከቱም ይጠቅማል።

‹‹ማፍረስ ማልማት ነው›› የሚል ቅልጥ ያለ የኒዮሊበራሊዝም መፈክር እየተስተጋባ ነው አዲስ አበባ እየፈረሰች ያለችው። ለሥራ አጦች የሥራ ዕድል ፈጥረናል በሚል፣ የቤት ፍርስራሾችን ጭምር “ድሆች” ከተባሉት የከተማው ነዋሪዎች ላይ እየተነጠቁ ሲሸጡ የምናየው ለዚያ ነው። ይህ የኒዮ ሊበራሊዝም ሎጂክ ባይንሰራፋ እንኳን አቆጥቁጦ እያበበ መሆኑን ያሳያል። ማፍረስ ልማት ነው ወይም ፈጠራዊ ፈረሳ [creative destruction] ይሉት የካፒታሊስት ቴክኒክ ከአሮጌ ወደ አዲስ ሕይወት እወስዳችኋለው ቢልም፣ ፀጋን በምትለግሰው ተፈጥሮና በሰው ልጅ ላይ በመጨከኑ [Cannibal Capitalism] ብቻ ሳይሆን፣ የገደለውን ሬሳ ጭምር በትርፍ አስልቶ በመሸጡም፣ ጥንብ አንሳው የከበርቴው ሥርዓት [Vulture Capitalism] በተሰኘው አስተሳሰቡ እናውቀዋለን። ከዚያም አልፎ በዓለማችን ሞት ራሱ ትርፍ ማግኛ መሣሪያ (Necro-economy) እየሆነ እንደመጣና፣ ጦርነቶችም በሒደታቸውም ሆነ በውጤታቸው የዚህ አስተሳሰብ እንደሚዘውራቸው እያየን ያለንበት አሳዛኝ ዘመን ነው። እነዚህን ጉዳዮች መተንተኑ የሚጠቅመን በድህነት ተሰቅዛ የተያዘችን አገር፣ ወደ ተሻለ ሕይወት ለመውሰድ በምንጣጣርበት ወቅት፣ ሰፊውን ሕዝብ ለጥቂቶች ሲባል ላለመሰዋት ጥንቃቄ ለማድረግ ነው።

ፓሪስና ፈረንሣይ፡ ከዓለም ከተሜነት ታሪክ ምን እንማራለን? 

ስለ ማኅበራዊ ፍትሕ በመሟገትና ስለ ከተማ ጉዳይ በጥልቅ በማሰብ የሚታወቀው ዴቪድ ሃርቪ የተባለ ፈላስፋና የግፉአን ተሟጋች፣ የነበረውን በስፋት ንዶ አዳዲስ ሕንፃዎችን የመገንባቱ ሁኔታ የሚከሰተው ከበርቴዎች ከሌሎች ቦታዎች (ጭቆናዎች፣ ዘረፋዎችና ንግዶች ብለን ማሰብ እንችላለን) ያገኟቸውን የተትረፈረፉ ወረቶች የሚያደርጉበት ቦታ አጥተው ሲቅበዘበዙ ቆይተው፣ አንዳች “ገንዘብ ማፍሰሻ” ቦታ (Capital Surplus Absorption) በሚሹበት ሰዓት ነው ይላል። በመጨረሻ ከበርቴዎቹ ወይም ለነሱ የሚሠሩት መንግሥታት ያንን የተትረፈረፈ ሀብት አንዳች ቦታ ላይ በማፍሰስ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ሥራ አጥ ለመቀነስና ጉልበታቸውን ተጠቅሞ ትርፋቸውን ለማባዛት ያውሉታል። በዚህ ረገድ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ በመላው አውሮፓ በተለይም በፈረንሣዩዋ ፓሪስ ላይ የተካሄደውን ሰፊ የከተማ ጠረጋና ግንባታ በምሳሌነት ይጠቅሳል። የንጉሥ ናፖሊዮን ፈረንሣይ የት ላድርገው ብላ እጇ ላይ የምታንቀዋልለውን የተትረፈረፈ ወረት፣ በአንድ በኩል በየአቅጣጫው በዓለም ዙሪያ በተለያዩ ቦታዎች በመዋዕለ ነዋይነት እያፈሰሰች፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከተማ ለመናድ ምንም የማይሳሳውን የጥፋት መሪ – ሃውስማን የተባለውን ሰው በፓሪስ ላይ በፊት አውራሪነት ሾመችባት። ሃውስማን የፈረንሣይን ዓላማ ተረድቶታል። ንጉሡ ናፖሊዮን ቦናፓርት የፈለገው በከተማ ማስፋፋት አማካይነት ፈረንሣይ የተትረፈረው ወረቷን ቦታ እንድታስይዝ ማድረግ ነው። የሥራ አጥ ችግሯን እንድትቀርፍ ማስቻልም ሌላኛው ዓላማዋ እንደሆነ ገብቶታል። ሂቶርፍ የተባለው የኪነ ሕንፃ ባለሙያ ፓሪስን በስፋት የመናዱ ዘመቻ በደንብ ገብቶኛል ብሎ ሃውስማንን ለማስደሰት አንዱን የከተማ አውራ ጎዳና ብቻ 40 ሜትር ስፋት እንዲኖረው አደረገው። ሃውስማን ግን እጅግ ተበሳጨ። በንዴት ፕላኑን ወዲያ አሽቀነጠረው። 40 ሜትር አነሰችብኝ ብሎ ነበር በንዴት የጦፈው። የኪነ ሕንፃውን ባለሙያ የአውራ መንገዱን ስፋት 120 ሜትር እንዲያደርገው አዘዘው። ከተማን መናድ ከክብርና ከማዕረግ ተቆጠረ። ይህንን የአንድ አውራ ጎዳና ስፋት በዓይነ ህሊናችሁ ተመልከቱና ፓሪስ የደረሰባትን ከፍተኛ ጠረጋ አስቡት። የቀድሞዋ ፓሪስ ተደረማመሰች። ሕንፃዎች ተገጠገጡባት። ከንቲባ አከል ሰዎችና የኪነ ሕንፃ ባለሙያዎች፣ መሐንዲሶች ሕዝቡ ተው አይሆንም እያላቸው ንጉሥ ናፖሊዮንን ለማስደሰት የፓሪስን ባለ ዝቅተኛ ገቢና ቅርሶቻቸውን ጠራርገው ሰፊ ባዶ መሬት ለመንግሥት አስረከቡ። ‹‹ሌላ!›› የምትሰኝ ከተማ ተገነባች። ፓሪስ ብርሃናማዋ ከተማ ተሰኘች። ገንዘብ መበተኛ፣ የቱሪዝም መዳረሻ፣ የሐሴት እርካብ መርገጫ ሆነች። ካፌዎች፣ ገበያ ማዕከላት፣ የፋሽን ኢንዱስትሪ መናኸሪያ፣ የትላልቅ ኤግዚቢሽኖች መታያ ሆነችና የት ላድርገው ስትለው የነበረውን የትረፈረፈ ሀብቷን በሸቀጥ አቅርቦትና ግዥ ያለ ቁምነገር እንዲሁ እንዲረጭ አደረገችው። ንጉሡ የአንጀታቸው ደረሰ። ፊት አውራሪዎቻቸው እነ ሀውስማን ደረታቸውን ገለበጡ። ጮቤ ረገጡ።

ነገር ግን በኪራይ ግንባታ ላይ የተመሠረተው ገንዘብ ተኮር የጨበጣ ንግድ በ1868 ዓ.ም. ግድም ተንኮታኮተ። ሳልሳዊ ናፖሊዮን በተስፋ መቁረጥ ቢስማርክ ከሚመራት ጀርመን ጋር ጦርነት ገጠመ። የከተማው የጥፋት ቀያሽ ፊታውራሪ ሃውስማን ከሥልጣኑ ተባረረ። በዚህ መሀል ነው ቀውስ በናጣት ፈረንሣይ ውስጥ የፓሪስ ኮሚዩን በመባል የሚታወቀው (ከመጋቢት እስከ ግንቦት 1863 ሥልጣን ላይ የቆየው መንግሥት) እና በካፒታሊስቶች የከተማ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቀው አብዮታዊ የፖለቲካ ኃይል ብቅ ያለው። ሃውስማን ነጥቆናል ያሉትን የድሮ ትዝታ መልሰው በእጃቸው ለማስገባት የተደራጁት በአንድ በኩል  ‘ቅርሶቻችንን ያወደሙት ይውደሙ’ ሲሉ አገሪቷን ናጧት። ‘ፓሪስ እኛን ያገለለች ከተማ ነች ፍትሕ ልትሰጠን ይገባል’ ያሉትም ያችን ንጉሡ የብርሃን ከተማ ያላትን ፓሪስን ‘ድሆችን አግልላና ገልላ ነው እዚህ የደረሰችው’ በሚል ኅብረተሰባዊ (ሶሺያሊስት) የሆነ ንቅናቄን ፈጠሩ። የሴቶችን መብቶች እንዲከበሩ ታገሉ። የሠራተኛውን መደብ ከፊት አስቀድመን ትግላችንን እናራምድ የሚሉ አብዮተኞች ከፊት ተሠለፉ። በሳልሳዊ ንጉሥ ናፖሊዮን ዓይነት ትልም የሚሠሩ፣ ጥቂት ካፒታሊስቶችን አምነውና ማዕከል አድርገው የሚቀየሱ፣ የከተማ አዲስ ፕላኖችና የሕዝብ ጠረጋዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የተደመደሙትና የእስከዛሬ ታሪካቸውም የቀጠለው።

በዚህ ረገድ ዴቪድ ሃርቪ በምሳሌነት በረዥሙ የጠቀሰውንና ፍሬደሪክ ኤንግልስ ከ152 ዓመታት በፊት ንጉስ ናፖሊዮንና ሃውስማን ከአርክቴክቶቹ ከነሂቶርፍ ጋር በመሆን አውድመው በመገንባት ‘ብርሃናማ አድርገናታል’ ያሏትን ፓሪስን ተንተርሶ የተናገረውን ለእኛም ጥሩ ማስገንዘቢያ ነውና እንዲሀ ተርጉሜ አቀርበዋለሁ፡

ያ መፍትሔ ተብሎ የሚመጣው ነገር ጥያቄውን የሚያስወግድ ሳይሆን ችግሩን እየደጋገመብን ዘወትር እንደ አዲስ ጥያቄ እንድናነሳ የሚያደርግ ነው። ይህ መንገድ የ‘ሃውስማን’ መንገድ ይባላል። ምን ማለቴ ነው? በትላልቅ ከተማዎቻችን ውስጥ አሁን አሁን የተለመደውን ለፍቶ አዳሪዎች የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች በተለይም እምብርት የሚባሉትን ሰፈሮች የማሸበር ተግባር፣ ‘የማኅበረሰቡን ጤና ለመጠበቅ ነው፣ ወይም ከተማዋን ለማስዋብ ነው፣ አሊያም በከተማው እምብርት ላይ ሊቋቋሙ የሚገባቸው የንግድ ማዕከሎች ፍላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ነው፣ ትራፊኩን ለማሳለጥ ነው፣ የባቡር ሃዲዶችን፣ መንገዶችን […] ለመዘርጋት ነው’  የሚሉት ነገሮች ከእውነት የራቁ ናቸው። ምክንያቶቹ ምንም የተለያዩ ቢሆኑም እንኳን፣ ውጤቱ ሁሌም አንድ ነው። ‘በምግባር የላሸቁ ናቸው’ እየተባሉ የሚፈርሱት ቀጫጭን መንገዶች ባለሃብቱ “ውብ ስኬቶቼ ናቸው” እያለ በሚያመፃድቃቸው ነገሮች ይተካሉ። ነገር ግን እነዚያ ምግባረ ብልሹ የሚባሉት ቦታዎች እዚህ ቢፈርሱም ወዲያውኑ ሌላ ቦታ ብቅ ይላሉ። የበሽታ መራቢያ፣ የጋጠ ወጥ ተግባር መፈጸሚያ ቦታዎች የሚባሉትና [ሥርዓታዊ በሆነ ችግር] ሠራተኛውን ክፍል መሽቶ በነጋ አንቀው እዚያው እንዲዳክር የሚያደርጉት ሥፍራዎች [ድህነትን በማጥፋት] መሠረታዊ መፍትሔ እንዲያገኙ አልተደረጉም። ቦታ እንዲቀይሩ ነው የተደረገው። ችግሮቹን ትናንት እንዲከሰቱ ያደረጋቸው የኢኮኖሚ ጥያቄ [በመሠረታዊነት ባለመመለሱ]፣ ዛሬም ሌላ ቦታ [ድሆችንና ድህነትን] እንዲራቡ ያደርጋቸዋል። (ፍሬደሪክ ኤንግልስ)

ልክ የዛሬ 152 ዓመት እንደተደረገው ሁሉ በአገራችንም ድሆች ካሉበት ቦታ የተሻለ መኖሪያ ይሰጣችኋል፣ ልማቱ ለናንተ ነው እየተባሉ ነው እየተጠረጉ ያሉት። ኤንግልስ እንዳለው በአገሪቱ የተንሰራፋውን ችግር በመሠረታዊነት፣ ለመቅረፍ የሚደረጉ መፍትሔዎች ሳይኖሩ፣ እነዚህን ለፍቶ አዳሪዎች ወደ ሌላ ቦታ መውሰዱ ድህነትንና ኢፍትሐዊነትን ያባብሳል፣ እንደ አዲስም ይወልዳል።

  1. ከተማና አገር፡ አዲስ አበባና ኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ “የተትረፈረፈ ካፒታል” ከተለያዩ ምንጮች ሊቀዳ ይችላል። በዕዳ ለተያዘችና ገንዘቧ ጥንቡን እየጣለባት ላለች አገር “የተትረፈረፈ ካፒታል” የሚለውን ሐረግ ስንጠቀም አስቂኝ ቢመስልም፣ ብዙ ነገሮች በተደበቁበት ሁኔታ ውስጥ እንደመሆናችን ነገሩን በደምሳሳው ለመረዳት እንድንሞክር ነው የምጋብዘው (ድሃ ተኮር ኢኮኖሚን የሚያጠኑ የዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎችም የየመስኩ ተመራማሪዎች ሁሉን አቀፍ የተንሰላሰለ ውይይት እንዲያደርጉ ግብዣዬም ምኞቴም ነው)። የሀብቱ ምንጭ አንዱ በገፍ ወይም በትንሽ በትንሹ የሚገኝ “ስጦታ” ሊሆን ይችላል (አገር የምትቀበለው ስጦታ በምን ውለታ እንደሚመለስ ማሰቡ ፖለቲካዊም ኢኮኖሚያዊም መዘዞች እንዳሉት ሳንዘነጋ)። ያንን ዓይነት ስጦታ ኢትዮጵያ ባለፉት ስድስት ዓመታት ስታገኝ እንደኖረች ይታወቃል። ዝርዝሩ ለሕዝቡ በግልፅነት ባይነገርም። በነገራችን ላይ በከተማ የመኖር መብትን የሚያቀነቅኑ አሳቢዎችና የመብት ተሟጋቾች ሕዝብ እንዲህ ያሉ ሀብቶችን የማወቅ ብቻ ሳይሆን፣ በዝርዝሮቻቸውና በምን በምን ላይ እንደሚውሉ የመወስን
ዴሞክራሲያዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል ይላሉ። እኛ ደግሞ እንኳንስ ልንሳተፍበት፣ ዝርዝሩን ልናውቅም አልተፈቀደልንም። በተጨማሪም የካፒታሊስቶች የተትረፈረፈ ወረት አዲስ ትርፍ ለማግኘት ዘወትር ስለሚቅበዘበዝ፣ አዳዲስ የንግድ ቦታዎችን ይፈልጋል። በዚያም መሠረት ወደ አገራችን በመዋዕለ ንዋይነት የሚመጣ የውጭ ገንዘብ ይኖራል። የዚህ የውጭ ኢንቨስትመንት ክፋቱ ፋብሪካዎች ላጠሯት አገራችን የሚገነባውን ገንብቶ ምርቶቻችንን በማብዛት፣ በውጭ ንግድ ምንዛሪያችንን በዚያውም አብታችንን ከፍ የሚያደርግ ሳይሆን፣ ቀደም ሲል በጠቆምኩት የገንዘብ ውርርድ ወይም ቁማር ላይ ያተኮረ የገንዘብ ኒዮሊበራልኪዝም ለምሳሌም የሪል ኢስቴት (የኪራይ ግንባታ) ውስጥ የሚሳተፍ በመሆኑ፣ አገራችንን ካላት ላይ ያሟጥጥባታል። ለጊዜው ማስተንፈሻ ብለን የምናገኘው ገንዘብ፣ በጎን በኩል ለሚደማው ኢኮኖሚ ዘላቂ ሕክምናን የሚሰጥ ነው ወይ ብሎ ማሰብ ያሻል። 

ከዚህም ሌላ በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ጦርነቶች እየተካሄዱ በመሆኑና የክልሎቹ የግብርናም ሆነ የግንባታ እንቅስቃሴዎች በመስተጓጎላቸው፣ ለእነዚያ አካባቢዎች ይሆኑ የነበሩት ገንዘቦች አዲስ አበባ ላይ እየፈሰሱም ሊሆን ይችላል የሚሉ ሰዎችም አሉ። ለዚህም ነው ያደጉ ከሚባሉት አገሮች በተለየ ሁኔታ እንደ ኢትዮጵያ ባሉት አገሮች የከተሜነት ጉዳይን ከዓለም አቀፍና ከአገራችን ገጠሩ ክፍል ጋር አስተሳስረን መመልከት ያለብን። በአገር ውስጥ የገንዘብ ኖትን ቋጥሮ በመያዝ ሌላ ቦታ መልሶ ለማዋል የመፈለግ አዝማሚያ፣ በመንግሥትና በግል ድርጅቶችም ዘንድ እንደሚስተዋል ልብ ልንልም ይገባል። ዛሬ የልማታዊ መንግሥትነት መገለጫ የግልና የመንግሥት ዘርፎች ጥምረት ሆኖ እያደር የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ሊመራው የሚገባው አካሄድ ነው (Public-Private Partnership -PPP) የሚለውን አስተሳሰብ ብቸኛ እውነት አስመስለው ለኢትዮጵያ የሚመክሩ የኒዮሊበራል አቀንቃኞች እንዳሉ ይታወቃል (በፖለቲካ ሽግግሩ መጀመሪያ ላይ የታተመውን ‹‹Ethiopia in the Wake of Political Reforms›› የተሰኘውን መጽሐፍ በተለይ በኢኮኖሚ ላይ የተጻፉትን ምዕራፎችና ፉኩያማ ኢትዮጵያ መጥቶ የተናገረውን በምሳሌነት መመልከት ይቻላል)። ኢትዮጵያም በሕግ ድጋፍ አቋቁማው ወደ ሥራ ገብታበታለች። መንግሥትም “ትርፍ ለማካበት የማይሽቀዳደሙ” እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸውን፣ ነገር ግን ወገን በችግር እያለቀ “ሠርግ ላይ ለሙሉ ሠርገኞች ከረሜላ ሳይሆን ሰዓት የሚበትኑ” ደልቃቆችን ፍትሐዊ ባልሆነ መልኩ እያስጠጋ እንደሆነም ይታወቃል። ይህ አካሄድ በኢሕአዴግ ዘመን እንዳስተዋልነው ሁሉ፣ በየብሔር “ተጠሪነት” እና “አቤት ባይነት” የሚመሠረቱ አዳዲስ የናጠጡና አድራጊ ፈጣሪ የሆኑ ቁልፍ ቡድኖችን ወልዶ ሊያሳድግ ይችላል።  

ከዚህም ሌላ ከውጭ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል “እስከ ዛሬ ተቆልፎባት የነበረቸውን ኢትዮጵያን፣ እነሆ ከፈትንላችሁ” በሚል፣ ለውጭ ባለሀብቶች በተለያዩ ንግዶች ላይ መዋዕለ ነዋይ እንዲያፈሱ አዋጆች እየወጡም፣ ጥሪዎችም እየቀረቡ ነው። አፅንኦት መስጠት ያለብን ነገር፣ የኢትዮጵያ “የተትረፈረፈ ካፒታል” እርስ በእርሱ በሚቃረን ሁኔታ የመጣና እየመጣ ያለ መሆኑን ነው። ለዚህም ብዙ ምክንያቶችን መጥቀስ ይቻላል። ለምሳሌ አገሪቱ በከፍተኛ ዕዳ መያዟ ብቻ ሳይሆን፣ ዕዳዋን በጊዜ መክፈል ሳትችል ቀርታ የበለጠ አጣብቂኝ ውስጥ መሆኗን ማየት ነው (ራሷን በከፋ ሁኔታ በማጋለጥ)። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ደግሞ የሚገነቡት ነገሮች ከቤተ መንግሥት ግንባታ፣ ከከተማ ማስዋብ፣ ከገበያ ማዕከላት ግንባታና ከሪል ስቴት ጋር የተያያዙ መሆናቸው፣ በኖረ ድህነትና በሽታ እንዲሁም በረሃብና በጦርነት መዘዞች የሚሰቃዩትን ሕዝቦች ቅድሚያ አለመስጠቱን ብቻ ሳይሆን፣ ሰላም በሌለበት አገር ውስጥ ፕሮጀክቶቹ እንዴት ዕውን ሊሆኑ ይችላሉ? ብለን እንድናስብም ያስገድዱናል። በረዥሙ ደግሞ ለጊዜው አገሪቱ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ (ገንዘብ) ፍላጎት ያሟሉ ቢመስሉም፣ ፕሮጀክቶቹ እሴቶችን እየጨመሩና ምርቶችን እያመረቱ ሕዝቡ ሀብትን በማፍራት እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲሳተፍና ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ከበርቴዎች መጫወቻነት በሒደት እንዴት ሊጠበቅ ይችላል? የሚሉት ጥያቄዎች ፈተናዎቻችን ብዙ መሆናቸውን ያሳዩናል። ይሄን ሁሉ ለሚያጤኑ ሰዎች፣ ኢትዮጵያ ወይ በወል የማትጠቀምበት፣ ወይም ደግሞ በአንዴ ዞር በልልኝ ብላ የማትገላገለውን አውሬ (ፈረንጆች ነጩ ዝሆን) የሚሉትን እያዋለደች ስለሆነ፣ ከወዲሁ ሁኔታውን በቀና ልብ አስቦ መማከሩ ከብዙ ጥፋት ያድነናል።     

ፍሬደሪክ ኤንግልስ እንደሚለን አዳዲሶቹ ቦታዎች ውብነታቸው ነገ ለሚወርሷቸው ከበርቴዎች እንጂ፣ ዛሬ ለተፈናቀሉት ድሆች አይደለም። ምክንያቱም ላብ አደሮች ኑሯቸውን ለማሸነፍ ሲጋጋጡ ከመዋል ባሻገር፣ መጥተው የእነዚህን የከተማ ክፍሎች ውበት ማድነቅ የሚችሉበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም የሚሆኑት። ‘ዛሬ በአገራችን ከተሞች ሲፈርሱ የሚንጫጩት ራሳቸውን በትላልቅ ግንቦች አጥረው በተቀመጡ የቅንጦት ዝግ ጊቢዎች ውስጥ ያሉ፣ ድሃ የተሻለ ኮንዶሚኒየምና የተሻለ ሽንት ቤት እንዲያገኝ የማይፈልጉ፣ የሃብታም ምቀኞች ናቸው’ የሚል መከራከሪያ በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ሲነገር ሰምተናል። ቃላቶቹ ለድሃ ተቆርቋሪ ይመስላሉ። የዛሬውም ሆነ የወደፊቱ እውነት እንደነዚህ ቃላት ለድሆች ያማረ ሕይወትን የሚያስገኙላቸው ቢሆን ኖሮ ምንኛ ደስተኞች እንሆን ነበር?! ሊገነቡ እየታሰቡ ያሉት ከተሞች እኮ ዴቪድ ሃርቪ እንደሚለው ከዝግ የሃብታም ቅጽር ግቢ (Gated Community) ወደ ዝግ የናጠጡ ሰዎች ከተማዎች (Gated City) እየተሸጋገርን ነው። ያ ማለት ደግሞ ድሆች ወደነዚህ ከተሞች በዋናነት ከገቡ የሚገቡት በተወሰኑ ንግዶችና ቴክኖሎጂ ተኮር በሆኑ ሙያዎች፣ በላብ አደርነት፣ እንዲሁም የወሲብ ንግድን በመሳሰሉ ሰፊ መረቦች እየተጠመዱ ነው የሚሆነው። እናም ሰፊው ሕዝብ እነዚህ ሰፈሮች ሰፈሮቹ እንዳልሆኑ በመደብ ደረጃው ይረዳል። የውጭ አገር ዜጎች የሚኖሩበትም ስለሚሆን፣ ቀድሞ ጣልያን ፒያሳ ለነጮች ብቻ ነች ብሎ በዘረኛ አፓርታይድ ሥርዓት ኢትዮጵያውያንን እንዳገደው ባይሆንም፣ በኋላ ላይ በነ ኪንግ ጆርጅ ነጭ ባለቤቶች እንደተስተዋለው፣ ኢትዮጵያውያንን አንቀጥርም፣ አናስተናግድም የሚሉ ዘረኞችም ሊከሰቱበት እንደሚችል ማሰብ አለብን። በእነዚህ ሁሉ ምክንያቶች ነው ጥያቄው የሰውነትና የነፃነት ጉዳይ የሚሆነው። 

ሌላው ኤንግልስ ያለውና አሁን በአዲስ አበባ (በኢትዮጵያ) ከተማ ለማፍረስ መንግሥት እየተጠቀመበት ያለው ዲስኩር የሚፈርሱት ቦታዎች ጭርንቁስ (Shanty Town)፣ ቁሻሻ፣ የወንጀልና የወሲብ ንግድ ማካሄጃ ናቸው የሚል ነው። ኤንግልስ የሚለውን እንደ ታሪክ ንፅፅር ሳይሆን እንደ ማሰቢያ መንገድ ብናየው “ማፅዳት” (Sanitization) እንደ ዘመናዊነት ዘዴ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው። በኢትዮጵያ ከተማን ለማፍረስ እየተፈበረከና እየተዘዋወረ ያለው ትርክት የከተማ ነዋሪዎችንና ሰፈሮችን የፅዳት ጉድለት ያለባቸው፣ ኋላቀር ወይም ያልሠለጠኑ፣ ማኅበራዊ “ጠንቆች” በማድረግ የማፍረሱን ሥነ ሥርዓት አስፈላጊ፣ ጠቃሚና አስቸኳይ አድርጎ የማቅረብ ነገር ነው። ታዲያ ይሄ የመንግሥታት ትርክት አዲስ አይደለም። ከአውሮፓ የዘመናዊነት መጽሐፍ ገፆች ላይ የተወሰደ ነው። የእኛዎቹም መንግሥታት ከአፄ ምኒልክ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ፣ ከደርግ እስከ ኢሕአዴግ እነዚህኑ ትርክቶች በአዲስ አበባ፣ ሲያመቻቸውም በሌሎችም ከተማዎች ላይ እየተጠቀሙ ከተማን “እናፀዳለን” በሚል ድሃን በአንድ አካባቢ ሲያጅሉና መድረሻ ሲያሳጡ ነው የኖሩት። እነዚህን የከተማ ታሪኮች ብዙ ጊዜ የማይነገረውን የውስጥ የማፈናቀል ተግባርን በመያዝ ብቻ ሳይሆን፣ በከተማ ዙሪያና ከዚያም ውጭ ባሉ የገጠር አካባቢዎች አያሌዎችን ሲጠርጉና ሀብት ሲነጥቁ፣ ሜዳ ሲጥሉ እንደነበር ከሚያሳዩት አስከፊ ሁኔታዎች ጋር አያይዞ ማሰብ ያስፈልገናል። ይኼንን ስንል በእነዚህ አካባቢ ያሉና የነበሩ ሕይወቶችን እንዳሉ ይቀጥሉ የምንል ለማስመሰል የሚሞክሩ ሰዎች፣ ነገሩን ቅልል አድርገው፣ የሚጠየቁትን ጥያቄዎች ለማድበስበስና ለሕዝብ ሳይገልጡ ውስጥ ለውስጥ ያሰቡትን ያለ ሃይ ባይ ለማስፈጸም  የሚሞክሩ ናቸው።

እየተባለ ያለው መንግሥት እነዚህን የኅብረተሰብ ክፍሎች ያሉባቸውን ሥርዓታዊ ችግሮች፣ ማለትም የኢፍትሐዊነት፣ የዴሞክራሲ ዕጦት (በሀብት ፈጠራና ክፍፍል ላይ የመወሰን ነፃነትን ጨምሮ) እና የአስተዳደር በደሎች የፈጠሯቸው ችግሮች መሆናቸውን አምኖ፣ መሠረታዊ ችግራቸውን ሊፈታላቸው እንጂ፣ ‘ቁሻሻና ወንጀለኛ’ እያለ ሰብዓዊ ክብራቸውን በማዋረድ እነሱን ጠርጎ ጥሎ፣ ሥፍራዎችን ለአዳዲስ ሃብታሞች ሊሰጥባቸው አይገባም ነው። በደርግ ዘመን በሕዝብ ትግል “የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ቁጥር 47/1967” ሲታወጅ “የአንዱ ብልፅግና በሌላው መቆርቆዝ ላይ እንዳይመሠረት” እና “የአብዛኛውን ሕዝብ በጥቂቶች መበዝበዝ ለማስወገድ” የሚል ነበር። ያ የሕዝብ ትግል በአምባ ገነን ሥርዓቶች እየተቆራረጠና እየተረሳ ሄደ እንጂ፣ ደርግ መሬትን የሕዝብ (Public) ሳይሆን የመንግሥት (State-owned) ያደረገበት አካሄድ፣ በኋላም ኢሕአዴግ.  ነገሩን ጭራሽ ገለባብጦ መሬትን በጊዜ ተመን ኪራይ ወደሚሸጥ ሸቀጥነት ለውጦ እንደፈለገ የራሱን ቡርዣ የፈጠረበት ታሪክ ከዛሬ ሁኔታዎች ጋር ተሳስሮ መተንተን አለበት። ብልፅግና ፓርቲ እነዚህ ሕዝባዊ ታሪካዊ ጥያቄዎች ዕልባት ሳያገኙና ‘የመሬት ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ ውሳኔ ይፈልጋል’ በሚል በይደር አቆይቼዋለሁ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ሆነን ነው፣ ይኼ ሁሉ ነገር እየተካሄድ ያለው። እንደ ደሳለኝ ራህመቶ ዓይነት በጉዳዩ ላይ የብዙ አሥርታት ጥናቶችን ሲያካሂዱ የኖሩ ተመራማሪዎች የጉዳዩን አሳሳቢነትና ከፍተኛ ትኩረት ፈላጊነት ቢያስገነዝቡም፣ የዘመናት የሕዝብ ጥያቄ ተደብቆ ነው ድሃውን ኅብረተሰብ ከኖረበት ቤቱ የማፈናቀሉ፣ ሀብቱን የመንጠቁና በወንጀለኝነት፣ መንገድ ላይ በመፀዳዳት (መሠረተ ልማቱ እንኳን በውጭ በቤትና በመሥሪያ ቤቶች ሳይሟላለት የኖረን ሕዝብ) ልክ እንደ ውጭ ዘረኛ ቅኝ ገዢ ኃይል ሕዝብን ያልሠለጠነ ወይም ኋላቀርና ቆሻሻ በማለት ከሰውነት ዓውድ የማውጣቱ (Dehumanization) እና ሞራላዊ-ፖለቲካዊ (Ethico-political) ስህተት መፈጸሙ የቀጠለው።

አብዛኛው የከተማ ነዋሪዎች እኮ ፊትም አፄያዊ ግዛቱ፣ ኋላም አብዮቶች በተለያዩ ታሪካዊ ሁኔታዎች ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አንዱን እያፈናቀሉ፣ ሌላውንም እየሳቡ አንድ ቦታ ያከማቿቸው የኢትዮጵያ የግፍ መታያዎች ናቸው። ቢሆንም አዲስ አበባ ላይ በላባቸው እየደከሙ ልጆች አስተምረዋል፣ ለወግ ለማዕረግ አብቅተዋል፣ ድረዋል፣ ኩለዋል፣ ለአገርና ለአኅጉር እንዲሁም ለዓለም ታላቅ አበርክትዎ መስጠት የቻሉ ዕንቁ ሰዎችን አፍርተዋል። ብዙዎች በተደራራቡና በተቆላለፉ ችግሮች ውስጥ ተብትበው ቢኖሩም፣ እነዚያ ችግሮችና ችግሮቹን ለመቅረፍ የሠሯቸውም ሥራዎች፣ የማኅበረሰባዊ ችግሮች የወለዷቸው መሆናቸውን የሚያውቁም ነበሩ። ባገኙትም አጋጣሚ ያንን ሁኔታ ለመለወጥ ትግል ያደረጉ ማኅበረሰቦችን ያቀፉ ቦታዎችም ናቸው (እነሱን ከከተማ ማስወጣትና መበታተኑም መፃዒ ተቃውሞን የማጥፋት ዘመቻም ሊሆን ይችላል። ግፍ ባለበት ተቃውሞ ሊጠፋ ባይችልም)። እንደ ገጠሩ ሕዝብ ሁሉ፣ ከተሜዎች በኢትዮጵያ ለማኅበራዊና ፖለቲካዊ ፍትሕ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ አመፆች ላይ በስፋት ተሳትፈዋል። ለምሳሌ የወሲብ ንግድ ማካሄጃ ነበር እያሉ አካባቢውን የሚያበሻቅጡ ባለሥልጣናትና የባለ ሥልጣናቱ አፎች፣ የወሲብ ንግድ ተዳዳሪ ሰዎች በ1966ቱ አብዮት አደባባይ ወጥተው የማኅበራዊ ችግሮቻቸው ይፈቱላቸው ዘንድ ሕዝባዊ ንቅናቄውን የተቀላቀሉ እንደነበሩ ልናስታውሳቸው እንገደዳለን።  የተለያዩ የኅብረተሰብ አካላትን በመደብ፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በዘርና በአካል ጉዳተኝነት ሰበብ ከሰውነት ተርታ የማውጣት ሁኔታዎች መኖራቸው ቢታወቅም፣ የሥርዓተ ፆታን ጉዳይ እንደ አንድ አንጓ በምሳሌነት ወስጄ ጥቂት ልበል።

  1. አራዳና ሴትነት፡ እነ አስናቀች ወርቁ

ልማት አሁን በምናውቀው ሁኔታ የወንደኛ ሥርዓትን መነፅር ለብሶ ፍረጃ የሚያካሂድ፣ ጡንቸኛ (Masculinist) ፕሮጀክት ነው። የሴቶችን በሥርዓታዊ ችግሮች መጎዳት ተመልክቶ ሕይወታቸውን በዚያው ልክ ለማሻሻል ከመሥራት ይልቅ፣ እነዚያኑ ሴቶች “ማኅበራዊ ጠንቅ” የሚለው ትርክቱ መሪ ተዋንያን አድርጓቸው፣ ከከተማው ቆርጦ ሊያወጣቸው ይታገላል። አራት ኪሎ ስትፈርስ አያሌ አረጋውያንና ወጣት ሴቶች መውደቂያ ስለተነፈጋቸው በየአቅጣጫው ተበትነዋል። እነዚያ ከተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ተሰደው የከተማውን የደከሙ ሥፍራዎች ተጠግተው የተለያዩ ሰብዓዊነትን የሚፈትኑ ሥራዎችን እየሠሩ ኖረው፣ ደሞ በልማት ስም ያሉባቸው ሥፍራዎች ሲፈርሱ ወደተለያዩ ቦታዎች ተሰደው ነበር።  የተወሰኑት የፈለሱት ወደ ፒያሳ ነበር። እዚያም ቤት ቁጥር ሳይሰጣቸው በደባልነት ሳይሆን በተለጣፊነት ለመኖርና አስከፊ የወሲብ ንግድን ለማካሄድ ተገደው ነበር። አሁን ፒያሳን መንግሥት ሲያፈርሳት፣ እነዚህ ተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያሉ የዝቅተኛ ኑሮ ገፊዎች ሜዳ ላይ ወደቁ። በመሀል በግድ ሰብረው ወረዳ 5 በሚባለው አዳራሽ ውስጥ ገብተው ማደር የጀመሩም ነበሩ። መንግሥት ከዚያም አስወጣቸው። ምክንያቱም በተለጠፉባቸው ስሞች የተነሳ፣ ከዜግነትም ከመኖሪያ ሥፍራም ተፍቀዋል። ማንም ከሕይወት አውጥቶ የሚወረውራቸው (Disposable) ተደርገዋል። እንደዚህ ዓይነት ስሞች እየተለጠፈባቸው እንዲያልፉ መደረጋቸው ቢቀጥልም፣ እነሱ ግን ገፀ ብዙ ተፋላሚ የሕይወት ሴቶች መሆናቸውን ለማሳየት አራዳ ካፈራቻቸው ወይም ሕይወት ራሳቸውን አራዳ መሀል እንዲያገኙ ካደረገቻቸው አያሌ ሴቶች መካከል ጥቂቶቹን በምሳሌነት እጠራለሁ።

ሜሪ አርምዴ ገና በአሥራ ሦስት ዓመቷ ነበር ጣልያንን ለመዋጋት ከዘመተ አንድ ጦር ጋር በሽሬ ግንባር ተሠልፋ፣ በድምጿ ወኔ ስታነቃቃ የነበረው። ኢትዮጵያ ድል አልሆን ብሏት ሠራዊቱ ተበታትኖ በዱር በገድል ሲሰደድ፣ ሌላውም ወደ ስደትም ሆነ ጣልያን ወደያዛቸው ከተሞች ገብቶ ሲኖር፣ ሜሪ አርምዴ የኮረዳነት ዕድሜዋን ጣልያን በያዘው የከተማው እምብርት ላይ ለማድረግ ተገደደች። ጣልያን ፒያሳን ተወላጆች አይረግጧትም ብሎ ከለከለ። ኢትዮጵያውያን የእናንተ የጥቁሮች ሰፈር መርካቶ ነው ተብለው፣ ፒያሳን ነጭ ሀብታም በዝግ ቅፅርነት ያዛት። ሰዎች ቢገፉም ከተገፉበት ቦታ ሆነው በፈጠራ ተሞልተው ሕይወትን የሙጥኝ ማለታቸው አይቀርምና፣ የአገሬው ተወላጆች እንደ መርካቶ ያሉትን ሰፈሮቻቸውን በራሳቸው መንገድ ሞቅ ሞቅ ያደርጓቸው ጀመር። በክራር ጨዋታ፣ በጠላ ሽያጭ፣ በትናንሽ ንግዶች። የጣልያን አገዛዝ ለወታደሮቹ ሀብት ታፍሳላችሁ ብሎ ሲያመጣቸው፣ አንዱ ቃል የገባላቸውና ቤት ገንብቶ ያው ዝረፏቸው ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ነበር። ለዚያም ነው ሥሩ ከጣልያን በፊትም ቢመዘዝም፣ የወሲብ ንግድ የመሀል ከተማዋ ዕጣ ፈንታ ተደርጎ በኢትዮጵያውያት ላይ እንዲያ ያለ ፍርጃ የተፈረደባቸው። ፒያሳ ነፃ ወጥታ የተወላጆች ስትሆንም፣ ኢኮኖሚዋ አዲስ ሕይወትን የሚተልም አልነበረምና ብዙ ሴቶች ሌላው ቀርቶ የታላላቅ ባላባቶች፣ የደጅ አዝማች፣ የፊታውራሪ ልጆች ሳይቀሩ በመጠጥና በወሲብ ንግድ መተዳደር ግዴታ ሆነባቸው። ከገጠር ወደ ከተማ የነበረው ስደት በብዙ ቁጥሮች ሴቶችን በእነዚህ ቦታዎች እንዲፈሱ አደረጋቸው። በአገራችን ከነበሩት ፋብሪካዎችና የተለያዩ ሥራዎች የበለጠ ሴቶችን ማሳተፍ የቻለው የወሲብ ንግድ መሆኑን ተመራማሪዎች በስፋት ጽፈውበታል።  እናም የውቤ በረሃ ማዳሞችን፣ የእነ አሰገደች አላምረውን፣ የነ ጋዴሴን፣ የነ ላቀችን፣ የነ ሜሪ አርምዴንና የነ አስናቀች ወርቁን ሕይወት ከዚህ ውስብስብና አስከፊ የከተማ-ገጠር ታሪክ ውጪ አድርጎ መተንተን የአገሪቱን ውስጠ ሚስጢር አለማየት፣ ካዩም ደግሞ በወንደኛ መነፅር ብቻ መመልከት የሚሆነው።

“አማረች አዲስ አማረች” እያለች በአፍሪካ አንድነት ምሥረታ ወቅት የአገሩን ቀልብ የጨበጠውን ዜማ ያንቆረቆረችው፣ ፍቅርን በአደባባይ በዚያ መልኩ መግለጥ ነውር በነበረባት ወግ አጥባቂ አገርና ከተማ “አብዮተኛ ሴት” በመሆን፣ ከራሷ ትውልድ አልፋ እስከዛሬ ተወዳጅነትን ያፈራችው አስናቀች ወርቁ ውቤ በረሃ ነበር ቤቷ። ኪዮስክ ከፍታ በመጠጥ ንግድ፣ ክራርዋን እየደረደረች፣ ሸክላዋን እያጫወተች ነበር የምትተዳደረው። ተገዳ እዚያ ሕይወት ውስጥ ብትገኝም፣ የእሷና የባልንጀሮቿ ገፀ ብዙ መልክ በዜሮ ሊባዛ አይችልም። ፍቅርን በአደባባይ መግለጥ ሃፍረት በነበረበት ዘመን፣ ውቤ በረሃ የወሲብ ንግድ ብቻ ሳትሆን የፍቅርም መናኸሪያ በመሆኗ ነበር ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር በልብ ወለድ ሥራው ኢትዮጵያ አይታው የማታውቀውን ልዩ ማኅበራዊ የከተሜነት ክስተት ያስተናገደች ሥፍራ ነች ያላት። የውቤ በረሃንና የአካባቢውን ጥልቅ የሰውነት መስተጋብርና ዘመኑ ይዞ የመጣውን ማኅበራዊ ችግር ከፆታና ወሲባዊ ጥያቄ አንፃር በማያያዝ በኢትዮጵያ አንድ እፁብ ድንቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራ (Masterpiece) ነው ታላቁ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር የሰጠን። እሱና እንደ ሰሎሞን ዴሬሳና ተስፋዬ ገሰሰን የመሳሰሉ ፈላስፎችና የጥበብ ሰዎች ራሷ አራዳ አማምጣ የወለደቻቸው ስጦታዎቻችን ናቸው።            

አስናቀች ውቤ በረሃን “ዴዘርት” እያለች በማንቆለጳጰስ ነበር የምትጠራው። ሥፍራው ችግር እንደነበረበት ጠፍቷት አይደለም። አያሌ ውብ የሕይወት ሰበዞች እየተሰፉ በብዙ ጌጦችም እንድትዋብ ስላደረጋት እንጂ። በኋላ ወደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀጥሎም ወደ ብሔራዊ) ቴአትርነት ያደገው፣ የድሮው ማዘጋጃ ቤት ቴአትርና ሙዚቃ ማስፋፊያ ለአንድ ለአገሪቱ አዲስ የሆነን የወጣቶች የፍቅር ታሪክ በመሪ ገፀ ባህሪነት የምትጫወት ምርጥ ተዋናይት ሲፈልግ በቀጥታ የሄደው ውቤ በረሃ ነበር። አስናቀች ወርቁ የመጠጥ ንግድ ቤት። አስናቀች ለመንግሥት ቴአትር ከኪሷ ገንዘብ እያወጣች አልባሳት እየገዛች፣ በመድረኩ ነግሳ ኖረች። የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ልክ እንደዛሬዎቹ እዚያ አካባቢ ያሉትን ነዋሪዎች “እናንተ ጽዳታችንን ትበክላላችሁ” እያለ ከከተማ ሊያባርራቸው ሲጣጣር፤ ያንን በሚቃወም ቴአትር መሪ ገፀ ባህሪን ወክላ፣ ‘እኛ ኮ እዚህ ሕይወት ውስጥ እንድንገባ ያደረገን ጉቦ የማይጠየቅበት፣ የዘመድ አማላጅነት የማያስፈልግበት የመጨረሻ አማራጫችን ስለሆነ ነው  … የተማራችሁትና መፍትሔ እናመጣላችኋለን ያላችሁት፣ እኛን ከከተማ ማስወጣትን እንደ መሠረታዊ መፍትሔ ነው የምታዩት?’ እያለች በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ቆማ መዋቅራዊ መፍትሔ እንዲመጣ ሞገተች።  ከውቤ በረሃ እስከ ሰንጋ ተራ ያሉ በወሲብ ንግድ ሥራ የሚተዳደሩ ሴቶች ብሔራዊ ቴአትር በተመልካችነት እየታደሙ አስናቀች ለወከለቻት ገፀ ባህሪ – ለአየለች – ድጋፋቸውን በጭብጨባ ሰጡ። በዘመናዊነት ስም እነሱን ወደ ዳር የሚገፋውን መንግሥት በአደባባይ ተቹ ማለትም አይደል?! አስናቀች ኢትዮጵያን ወክላ ከባልንጀሮቿ ጋር በአፍሪካ አገሮች የነፃነት በአሎች፣ በፓን አፍሪካ ፌስቲቫሎችና በሌሎች ዓለም አቀፍ መድረኮች እየተውረገረገች፣ እያዜመች የባህል አምባሳደር ሆና ኖረች። የጥበብ ገንዘብ ሕይወት ለዋጭ ስላልነበር፣ አስናቀች ከነዚያ ዓለም አቀፍ መደረኮች ስትመለስም ውቤ በረሃ መግባት ግዴታዋ ነበር። ለዚያ ነበር በ1966 አብዮት ወቅት የኪነ ጥበብ ሰዎች ሕይወታችን ሊለወጥልን ይገባል ሲሉ ሰፊውን ሕዝባዊ ትግል የተቀላቀሉት። አስናቀች አራት ኪሎ አደባባይ ለተቃውሞ ሠልፍ ወጥታ፣ በጥይት እሩምታ መሀል (አንድ አርቲስት ተገድሏል) ከሥራ ባልደረቦቿ ጋር በመሆን ከደርግ ወታደሮች ጋር ፊት ለፊት የተጋተረች ጀግናም ነበረች። ከተሜነትንና ቅርስን በስፋት ብናስብ ኖሮ እነዚህን ሁሉ ታሪኮችን አቅፈው ያቆዩትን ሥፍራዎች፣ ብድግ ብለን አንንዳቸውም ነበር። በእነዚህ ሥፍራዎች ውስጥ የተኖሩትንም ሕይወቶች ከመንግሥታት የዘመናዊነት ፕሮጀክቶች አንፃር መፈተሽና በዘመናት ለተደራረበባቸው ሥርዓታዊ ችግሮች መፍትሔ ፈላጊዎች ሆነን በመጣን ነበር።

  1. በከተማ የመኖር መብት እንደ አገርና ዓለም አቀፋዊ የነፃነት ጥያቄ

“በከተማ የመኖር መብት” (The Right to the City) የሚለውን ሐሳብ ቀድሞ የተነተነው ሄንሪ ለፌቭር የተባለ ፈረንሣዊ ፈላስፋ ነው። ሐሳቡ እንደ መፈክርም እንደ ንድፈ ሐሳባዊ ማዕቀፍም የተሰተጋባው ከተሞች ፍትሕንና ዴሞክራሲን እንዲሁም የነዋሪዎችን መብት ያረጋገጡ እንዲሆኑ በተደረጉ ውይይቶችና ትግሎች ነበር (የ1960ዎቹን የፈረንሣይን ሕዝባዊ ትግሎች ልብ ይሏል)። በዚያም አስተሳሰቡ በከተሞች ውስጥ ከሰው ልጅ ይልቅ እንዴት ሸቀጥ የበለጠ ሊከበር ቻለ? ያም ሥርዓት የብዙኃኑን ሕይወት በዋጋ ተመን እየለካ፣ ድሆችን ከተወሰኑ ተፈላጊ ከሚባሉ ቦታዎች፣ ያላቸውን ነጥቆና ጠርጎ በማስወጣት የሥፍራ ወይም የማኅበራዊ መበላለጦችን (Spatial Inequalities) ለምን ፈጠረ (ለምሳሌ መሀል ላይ ሀብታም ዳር ዳሩን ድሃ ማድረግ)? የሚሉ ጥያቄዎችን አነሳ። ከዚያም ተነስቶ ነው በከተማ ውስጥ የመኖር መብት ሊከበር ይገባል ብሎ መተንተንና መከራከርም የጀመረው። ታዲያ ለፌቭር መብት ሲል በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ውስጥ የተለመደውን የግለሰብ መብትን ሳይሆን የማኅበራዊ መብትን (Collective Right) ነበር የሚያነሳው። ይሄ ማለት ለፌቭር የግለሰብ መብትን ይክዳል ማለት ሳይሆን፣ ድሃና ሃብታም በሰፈር የሚለያዩባቸው ኢፍትሐዊነቶች (Spatial Inequalities) የሚከሰቱት፣ የምርት ማምረቻ መሣሪያዎችን የያዙ ሰዎች ከጉልበታቸው በቀር ሀብት የሌላቸውን ላብ አደሮችን በመጨቆን የሚፈጠር ሥርዓታዊ ችግር ስላለ ነው አለ። መፍትሔ ብለን የምናመጣውም ሐሳብ ያንን ሥርዓት እንዳይቀጥል ወይም እንዳይራባ ማድረግ የሚችለው፣ ማኅበረሰባዊ መብትን ማቀፍ ስንችል ነው ሲል አብራራ። ለዚህ ነው እንደ ዴቪድ ሃርቪ ዓይነት ፈላስፎችም “መብት” የሚለውን ጉዳይ በጥንቃቄ ፈትሸን፣ ከብዙኃን ተገፊዎች ጋር ማስተሳሰር እንዳለብን ደጋግመው የሚያሳስቡን። በሊበራሊዝም አስተሳሰብ ውስጥ ተቀርቅሮ ያለው የመብት ሐሳብ ከ18ኛው ክፍለ ዘመን የአብርሆት ፍልስፍና ውስጥ የሚመዘዝ መዘዝ ስላለው ነው። የዚያ ዘመን የመብት ሐሳብ ግለሰብን ማዕከል ላይ ስላስቀመጠ ብቻ ሳይሆን፣ ያንን ግለሰብ መብቱን ሊያሰላለት የሚፈልገው ከነጭነት፣ ከወንድነትና ከንብረት ባለቤትነት ጋር አያይዞ ስለሆነ ነው። ስለዚህ የግለሰብ መብት ሲባል በዚህ አስተሳሰብ ውስጥ የሚመጣው የዚያ ሰውዬ ንብረት ነው ማለት ነው። ምንም እንኳን የሊበራሊዝም ሐሳብ አቀንቃኞች ያንን ሰው ሁላችንንም በምሳሌነት እንደሚወክል ዓለም አቀፍ የሰውነት ሚዛን (Universal Human Right) ሊያደርጉት ቢሞክሩም። ለዚያም ነው በዚህ ዘመን የከተማ መብት ይከበር እንቅስቃሴ ውስጥ የመብት ጥያቄው መልሶ የባለሃብቱን መብት ለማፅናት ይሆንና፣ በሥርዓቱ በድህነታቸው ገለል የሚደረጉ ሰዎችን መብት እንዳናጤን የሚያደርገን። 

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ደግሞ ከነ ዴቪድ ሃርቪም ሐሳብ ተሻግረን መሄድ አለብን ብዬ አምናለሁ። ምንም እንኳን ዴቪድ የጥቁሮችን፣ የሴቶችንና የሌሎችንም ተገፊ ማኅበረሰቦችን ሕይወት በደንብ የመረመረና የብዙኃን መብትን ጉዳይ እነሱን ሁሉ አካቶ የሚያይ ቢሆንም፣ የአፍሪካ አገሮች ከእነዚያ ሐሳቦች ጋር እየተነጋገርን፣ የተለየ ትንታኔም ማካሄድ አለብን ብዬ አስባለሁ። ምክንያቱም የሊበራሊዝም የግለሰብ መብት ራሱን ዓለም አቀፍ የሰውነት መለኪያ ሲያደርግ ጥቁሮችን በተለይም አፍሪካውያንን ከሰውነት ተርታ አውጥቶ ነው የሚያስበው። ‘ታዲያ እኛን ምን አገባን? ድሮ ቅኝ አልተገዛን’ የሚሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይታወቃል። መልሱ ታዲያ ኢትዮጵያ ሳትወድ በግድ ከነጭ ዘረኛና ፆተኛ ሐሳብ ሥርጭትም ሆነ፣ ያንን ተንተርሶ ከተንሰራፋው የሊበራል ኢኮኖሚ ዓለም አቀፍ መዋቅር ጥላ ሥር ሾልካ ማምለጥ ስለማትችል ነው የሚል ነው የሚሆነው። ከውስጥ ሆና ትደራደራለች፣ ትፋለማለች እንጂ። እሱም ብልህና ጠያቂ ሕዝቦችና መሪዎች ካሏት። ለምሳሌ እንደ ማልኮልም ኤክስ ያሉት የነፃነት ታጋዮች ሰብዓዊ መብት ሲሉና፣ ድሆች ስላሏቸውም ንብረቶች ጭምር ሲታገሉ፣ አውሮፓ ተኮር የሆነውንና የግለሰብን ነፃነት ከነጭነትና ከጥቂቶች የንብረት ባለቤትነት ጋር የሚያያዘውን መብት መጥቀሳቸው አይደለም። ጥያቄዎቻቸው በዘረኝነት ከሰብዓዊነት ዓውድ ተገፍቶ የተጣለውን ሰውነታቸውን የማስመለስና በድህነትም ያፈሩትን ሀብት እንዲጠበቅላቸው የመታገል የእኩልነትና የማኅበራዊ ፍትሕ ጉዳይ ነው። 

ዛሬ ኢትዮጵያ የገባችበትን ዓለም አቀፍ ውጥንቅጥ የኋላ ታሪኩንም ሆነ፣ የአሁን ጣልቃ ገብነቶችን (በግድም በውድም) ስናስብ የሰውነትና የመብት እንዲሁም የነፃነት ጉዳዮች ወለል ብለው ይታዩናል። የሊበራሊዝም ፅንሰ ሐሳብ በፈረንሣይና በአሜሪካ አብዮቶች ውስጥ እየተተነተነ “ነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት” እየተባለ ሲለፈፍ፣ እነዚያው ነጮች ጥቁሮችን ባሪያ አድርገው በንብረትነት ይዘዋቸው ነበር። ሆኖም የሄይቲ ታሪክ በምሳሌነት እንደሚነግረን ባሪያ የተደረጉት ጥቁሮችም በአብዮት የሰውነት ነፃነትንና የነፃ ሕዝብ አገር የመመሥረት ተአምራቸውን አጣምረው በማሳየት የአውሮፓን “የነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነት” ፍልስፍናን ውስጣዊ ተቃርኖ አጋለጡ። ነፃነትን የሙጥኝ ብለው፣ አጥብቀው የተፋለሙ፣ በብዛት ቢገደሉም ወደ ነፃነታቸው በክብር መንደርደራቸው፣ አልፎም የሰውነት ነፃነትን መጎናፀፋቸው እንደማይቀርም ለዓለም አሳዩ። ጭቆናውና ትግሉ ባያቋርጥም፣ ለገዢዎች የዘወትር ጭንቀትን፣ ለተገዢዎችም ተስፋን ሰጡ። ይህንን ጉዳይ በጥልቀት ያብራሩ ከመገፋት ታሪክ ውስጥ የመጡ ብዙ ፈላስፎች አሉ። እነዚህ አሳቢዎች እያሉ ያሉት ‘የመብት ጥያቄ ብዙኃኑን የማካተት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ ሰው የመሆንና ያለመሆን ጥያቄ ተደርጎም መወሰድ አለበት’ ነው። የአፍሪካ የከተማ ችግር የሰውነት ነፃነት ጉዳይ ሆኖ መቅረብ ያለበት በሦስት ምክንያት መሆኑን ማሳየት የምፈልገው ለዚያ ነው።

1) በአገር ውስጥ ድሆችን ከመሬታቸውና ከሰፈራቸው ነቅሎ፣ ጠርጎና ሀብትን ነጥቆ፣ ሀብታምን በሥፍራው የመትከል አስተሳሰብ ምዕራብ ተኮርና ዘረኛ አስተሳሰብ በውስጡ የቀበረ ስለሆነ፣

2) ይህ ድሃ ጠረጋ የአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሀብቶችንም በሥፍራው የሚተካ በመሆኑ የሰፈር መበላለጥ ወይም የማኅበራዊ ፍትሐዊነትን ጥያቄ የዘረኝነት ችግር ያለበት ሆኖ እንዲቀጥል ስለሚያደርገው፣ በዚያም ዓለም አቀፉ የነጭ እንዲሁም የሌሎች የሰሜነኛው ዓለም (Global North) ክፍል ሀብታሞችን በላያችን ላይ እንዳነገሠ ስለሚያቆይብን፣

3) ካፒታሊዝምን ይዘን በመተንተንና የከተማን በቅራኔ መሞላት ልብ በማለት፣ ከተማን የመጪው ዘመን የነፃነት ትግል ቦታ አድርጎ መውሰዱ አስፈላጊ ስለሆነ፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉት አገሮች ከምዕራቡ ዓለም በተለየ ሁኔታ አብዛኛው ሕዝባቸው በግብርናና በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ በመሆናቸው፣ የገጠር-ከተማ የኢኮኖሚ ቁርኝትን የውይይታችን አካል እያደረግን መቀጠል ያስፈልጋል። ተያይዞም የልማት አረዳዳችን፣ እሴታችንና ምርጫችን እንዲሁም ተግባራችን ከተሜነትንና ገጠራዊ ሕይወትን አሰናስሎ መመልከት ይጠበቅበታል።

  1. መውጫ

በአዘቦት ብቻ ሳይሆን እንደ ኮቪድ ባሉትም ወቅቶች ከተማውን በመመገብ የሚታወቁት የገጠር ሕዝቦች (በተለይ ሴቶች) መሆናቸውን ደጋግመው አገራችን ያለችበትን ሁኔታ የሚተነትኑት ኢኮኖሚስት ዓለማየሁ ገዳ ያስረዳሉ። የሳቸውን ሐሳብ በመንተራስ መንግሥታት ምን ያህል ፖሊሲዎቻቸው እነዚህን የገጠሩን ክፍል ሰዎች በተለይም ሴቶችን ማዕከል ላይ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ሊን ኦሶሜ የተባሉ አሳቢ ይተነትናሉ። ጉዳዩ በብዙ ችግሮች ተተብትበውና ከመንግሥት ፖሊሲዎች ገሸሽ ተደርገው ባሉበት፣ ከተማው (ልማቱ ይምጣበትም ይምጣለትም) የቅድሚያ ትኩረት ሲሰጠው፣ የክልሎችንና የሕዝቦቻቸውን ህልውና አጠያያቂ እንደሚያደርገው እናያለን። የከተማ ልማት የተባለው አካሄድ ገጠሩን ጥሎ ከተማውን ለዚያውም ሃብታሙን አንጠልጥሎ ወደፊት መሄድ አይሆንለትም። ለጊዜው ቢመስለውም የነቀርሳን ሥር ነው የሚተክለው። በዚያ ላይ በገጠሩ ክፍልና በተለያዩ ከተሞች ላይ ጦርነት እየተካሄደ ሰላም ሳይመጣና ከወለጋ እስከ ትግራይና አማራ ክልል ድረስ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሕይወታቸው የተቃወሰባቸውን ሕዝቦቻችንን ሳናክምና ሳናቋቁም እንዴት ነው እንዲህ ባለ ፕሮጀክት ላይ ለመመሰጥ የበቃነው? እንዴትስ ነው የአዲስ አበባ ሰላም ተረጋግጦ ቱሪዝሟ የሚያብበውና ትርፍ እንዲያመጣ የሚጠበቀው? የትላይ ልፍሰስ እያለ የሚንቀዋለለው የዓለም አቀፍ ካፒታል ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፣ ከአካባቢያዊ ፖለቲካ ጋር ተያይዞ እንደመሆኑ ጦሱ ዓለም አቀፋዊ እንድምታም እንዳለው መገንዘብና መጠንቀቅስ አያሻንም?

ሁኔታዎቻችን በአገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ በመተሳሰራቸው “በዚህች ምድር መኖር፤ ሰው መሆን ምንድነው?” የሚለውን ጥያቄ ከዘር (Race) ጉዳይ ጋር አጋምደን ማየት እንዳለብን አሳይቶናል። ስለዚህም በከተማም ሆነ በገጠር ስንኖር ዘረኝነት ተጠናውቶት የሚመጣው ወረት በተለይ አሁን እየገባንበት ባለው የውጭ “ኢንቬስተሮችን” ወደ አገራችን በአካል ስቦ የማኖር ሁኔታ በልዩ አፅንኦት ልንመረምረው ይገባል። ከዚሁ ጋር ችግሩ አንድን አካባቢ ቆሻሻ ነው፣ የወንጀልና የወሲብ ንግድ መናኸሪያ ነው በሚል ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ከከተማው እየጠረጉ የማስወጣትና በኖሩበት ቦታቸውም ላይ ጥቂት ሀብታሞችን የመትከል ስለሆነ፣ የድህነትን (የመደብን)ና የሥርዓተ ፆታን፣ የአካል ጉዳተኝነትንና ሌሎችንም ጉዳዮች በደንብ ማጤንና በዚያው አግባብ የተንሰላሰለ መፍትሔ መስጠት አለብን። የብሔር ጥያቄ እየተንከባለለና እየተስፋፋ በመጣበት ሁኔታ፣ የፖለቲካ ጉልሃንንና ጥቂት ባለገንዘቦችን ብቻ በሚጠቅም መልኩ የብሔር ጉዳይና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚራገብበት መንገድ በመላ አገሪቱ በተለያዩ ምክንያቶች የሚፈናቀሉትን ሰዎች የበለጠ እያገፋፋ የባሰ ውጥረት ውስጥ ሊከታቸውና የግጭት መንስዔም ሊሆንባቸው ይችላል። ሁሉም ሕዝቦቻችን ሊተባበሩና የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ ጨቋኝ ከበርቴዎችን በኅብረት ሊፋለሙ እንጂ፣ ሊጋጩና ሊጋደሉ አይገባቸውም።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ezopaddis@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ