Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ክልል ገበያን ለማረጋጋት የተቋቋሙ ማኅበራት ከሕግ ውጭ ታክስ እንዲከፍሉ መገደዳቸው ተነገረ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ገቢዎች ሚኒስቴር ክፍተቱ ከማኅበራቱ የመነጨ ነው ብሏል

በአማራ ክልል በደሴ ከተማ የሚገኙ 17 ገበያ ለማረጋጋት የሚውሉ መሠረታዊ ሸቀጦችን የሚያቀርቡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ በአዋጅ ከተሰጣቸው መብቶች በተቃራኒ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ መገደዳቸው ተገለጸ። 

በሌሎች የክልሉ ከተሞች የሚገኙ የኅብረት ሥራ ማኅበራትም ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ወደኋላ ተመልሰው የተጠራቀመ የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ በመገደዳቸው የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተነግሯል። 

ይህ የተነገረው ሐሙስ ሚያዚያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም. የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች ሚኒስቴር የተያዘውን በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረበበት ወቅት ነው። 

የምክር ቤቱ አባል ማኅተመ ኃይሌ (ዶ/ር) ለሚኒስቴሩ የበላይ ባለሥልጣናት፣ የአማራ ክልልን በጥቅሉና በተለይ ደግሞ ከደሴ ከተማ ጋር የተያያዙ ሁለት ጉዳዮችን በማንሳት ምላሽ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። 

እንደ ተወካይዋ ገለጻ በደሴ ከተማ የሚገኙ 17 የመሠረታዊ ኅብረት ሥራ ሸማቾች ማኅበራት በአዋጅ የተሰጣቸው መብት እየተጣሰባቸው የመዝጋት አደጋ ተጋርጦባቸው ይገኛሉ ብለዋል። 

ማኅተመ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ መሠረት ስለኅብረት ሥራ ማኅበራት የወጣው አዋጅ ቁጥር 985/2009 ላይ የተቀመጠው ድንጋጌ እንደሚገልጸው እነዚህ ማኅበራት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ናቸው። 

ከዚህ በተጨማሪም ድንጋጌው ስለኅብረት ሥራ ማኅበራት ያቀረበው ገለጻ እንዳስቀመጠው፣ ገበያ ለማረጋጋት አባላት በተናጠል ሊወጧቸው ለማይችሏቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን በተባባረ ጥረት መወጣት፣ መቋቋምና መፍታት እንዲችሉ፣ ሸማቾች በአነስተኛ ዋጋ ግብዓት ማግኘት እንዲችሉና የሥራ ዕድልም እንዲፈጥሩ መቋቋማቸውን ገልጸዋል። 

የምክር ቤት አባሏ ‹‹ከእነዚህ ጠቀሜታዎች ባለፈ እንደ መንግሥት ስንመለከተውም ግብዓቶችን ለሕዝብ ለማሠራጨት ያላቸውን ጠቀሜታ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ ማሠራጨትን በመሰሉ ግብዓቶች የማከፋፈል ሚና ይታያል፤›› ብለዋል። 

በደሴ ከተማ የሚገኙት 17 የሸማቾች ማኅበራት እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር እንዳቀርብላቸው ጠይቀውኛል ሲሉ እንደተናገሩት፣ አባላቱ መካተት ያልነበረባቸውን በሕግ ከከፋይነት ነፃ የተደረጉበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ እንዲከፍሉ መገደዳቸው፣ የአፈጻጸም ፍትሓዊነት እንዲሁም መልካም አስተዳደርን በሚያሰፍን መልኩ ሊደረግ ይገባዋል ማለታቸውን አሳውቀዋል።

ማኅበራቱ እንደ ክልልም ሆነ እንደ አገር ባደረጓቸው የልምድ ልውውጦች የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ሆነው ሳለ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመክፈል መገደዳቸው ተገልጿል። 

ማኅተመ (ዶ/ር) ማኅበራቱ የተገለጸውን የግብር ዓይነት እንዲከፍሉ መገደዳቸው እያሳደረባቸው ያለውን ተፅዕኖም አብራርተዋል። 

በመጀመሪያ የጠቀሱት ጉዳይም ክፍያው ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ እንዲንቀሳቀሱ እያደረጋቸውና ገበያ የማረጋጋት ሥራ እየሠሩ አለመሆናቸውን ነው። 

‹‹እንዲያውም ከእነሱ ይልቅ በየመንደሩ ያሉ የደረጃ ‹‹ለ›› እና የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች፣ ከማኅበራቱ በተሻለ ዝቅ ባለ ዋጋ ምርት ለሸማቾች እያቀረቡ በመሆኑ ከማኅበራቱ ለመግዛት የሚፈልግ ተጠቃሚ የለም፤›› ብለዋል።

በሌላ በኩል ማኅበራቱ በአካባቢው ካለ አርሶ አደር ምርት በደረሰኝ መግዛት እንዳይችል፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ ተመዝጋቢ በመሆናቸው ከሌላ የዚሁ ታክስ ከፋይ ከሆነ አካል ብቻ ለመግዛት የሚገደዱ በመሆኑ፣ የዚህ የግብይት ሥርዓት አካል በመሆናቸው ይህ የክፍያ ዋጋ ሲጨመር የሸማቾች አባላቱ ተጠቃሚ ሊሆኑ አለመቻላቸውም ተገልጿል። 

የሕዝብ ተወካይዋ ‹‹እንዳልኩት ማኅበራቱ ከደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ባነሰ ሁኔታ ላይ ነው ያሉት ስለዚህም ዓላማችንን ስተናል፤›› ብለዋል። 

ማኅበራቱ ከእነዚህ ጉዳዮች ባለፈም ባለአደራ ሆነው የሚሰበስቡት የዊዝሆልዲንግ ታክስ (withholding tax) አንዳንድ ነጋዴዎች አልሰጥም እንዳሏቸውና ካልሰጧቸውና ይህ አንድ ላይ ካልተደመረ በስተቀር ግብይት ማካሄድ እንደማይችሉና ለደሴ ከተማ ሕዝብም የሚጠበቅባቸውን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ አለመቻላቸው ተጠቅሷል። 

ማኅተመ (ዶ/ር) ‹‹በዚህ የተነሳ የህልውና አደጋ ውስጥ ገብተዋል›› ሲሉ ለምክር ቤቱ አባላትና ለሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ተወካዮች ተናግረዋል።

ስለኅብረት ሥራ ማኅበራት በሚል በሚጠራው አዋጅ መሠረት ሸማች ማኅበራቱ ችግር ሲያጋጥማቸው አባሉ በጠቅላላ ጉባዔ ተጠርቶ ይመክራል ይላል። 

ይሁንና በደሴ ያሉት እነዚህ የ17 ማኅበራት አመራሮች ይህንን እያደረግንም መቀጠል አልቻልንም ሲሉ አቤቱታቸውን ለተወካይዋ ማሰማታቸው ተነግሯል። 

ማኅተመ (ዶ/ር) ‹‹የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያው ባስከተላቸው ችግሮች ምክንያት ሁኔታውን መቋቋም ስላልቻልን እንዝጋ ወይ እስከማለት ደርሰዋል›› ብለው፣ ‹‹ይህ ብቸኛ ደሴ ከተማ ላይ ብቻ የሚፈጸመውን ነገር ሚኒስቴሩ እንዴት ያየዋል? ግብር በመክፈላቸው ኩራት ይሰማቸዋል ጥያቄው ግን የፍትሐዊነት ነው›› ሲሉ በሸማቾች ማኅበራት አባላቱ የቀረበላቸውን አቤቱታ አስተጋብተዋል። 

በሌላ በኩል በአማራ ክልል የሚገኙ ሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ወደኋላ ተቆጥሮና ከቅጣት ጋር ተጨምሮ እንዲከፍሉ ግዴታ ስለተደረገባቸው በተመሳሳይ የህልውና አደጋ ተጋርጦባቸዋል ተብሏል። 

ማኅተመ (ዶ/ር) ‹‹ግብር ይክፈሉ አስተዋፅኦ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ግብር ከደረሱበት ጊዜ አንስቶ እንዲከፍሉ ማድረግ የማይቻለው ለምንድነው ሲሉ ጠይቀዋል። 

ተወካይዋ የሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እያነሱ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ አቅማቸውን የሚገዳደርና እጃቸው ላይ የሌለውን ገንዘብ እንዲከፍሉ በሚጠይቅ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል። 

‹‹አንዳንዶች 20 እና 30 ሚሊዮን ብር እየተጠየቁ ነው፡፡ እጃቸው ላይ የሌለ ገንዘብ ነው። ይህ እንዴት ነው የሚታየው?›› ሲሉም ጠይቀዋል። 

የገቢዎች ሚኒስትሯ ወ/ሮ አይናለም ንጉሤ በሰጡት ምላሽ ገበያ ለማረጋጋት የሚውሉ መሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የተጨማሪ እሴት ታክስ የማስከፈል አሠራር በሚያስተዳደሩት መሥሪያ ቤት ተግባራዊ እንደማይደረግ ጠቅሰዋል። 

በደሴ የሚገኙ የሸማቾች ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጉዳይንም እንደሚያውቁትና ማኅበራቱን በስም ጭምር እንደሚያውቋቸውም ተናግረዋል። 

ይሁንና የሸማቾች የኅብረት ሥራ ማኅበራቱ ከሌሎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ክፍያ ፈጻሚ ምርት አቅራቢዎች ግዥ በመፈጸም፣ የሚመጣውን የታክስ ክፍያ የሚጠበቅባቸውን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወይም በኮምቦልቻ ከሚገኘው ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር የክፍያ ደረሰኝ እንዲኖር ማድረግ እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል። 

‹‹አንድ የኅብረት ሥራ ማኅበር ከአርሶ አደር ጋር ምርት መግዛቱን የሚያረጋግጥ የክፍያ ደረሰኝ ሊኖረው ይገባል፣ ሰነድ ከገቢዎች ሚኒስቴር ወይም ቅርንጫፉ ጋር ተነጋግሮ ማቅረብ መቻል አለበት›› ብለዋል። 

ከዚህ ባለፈ ሚኒስትሯ ማኅበራቱ የተጨማሪ እሴት ታክስን እነሱ ላይ ያለ ጫና አድርገው መውሰዳቸው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው ሲሉ ገልጸውታል። 

‹‹የተጨማሪ እሴት ታክስ አንድ ምርት ሲሸጥ የመንግሥትን ድርሻ 15 በመቶ ከሚገዛህ ሰው ላይ ተቀብለህ አምጣልኝ ማለት ነው እንጂ በነጋዴው ላይ የተቀመጠ ጫና አይደለም›› ሲሉ አብራርተዋል። 

የገቢዎች ሚኒስቴር ደኤታ ወ/ሮ መሠረት መስቀሌ በበኩላቸው፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይ የሚደረጉት በሕጉ መሠረት በዓመት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ግብይት የሚያከናወኑ የንግድ ተቋማት መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ይህንን የታክስ ዓይነት ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ ወደኋላ ተመልሰው እንዲከፍሉ ተደርገዋል የተባሉትን ሁለገብ የኅብረት ሥራ ማኅበራት በተመለከተ ‹‹ይህ በሕጉ ላይ ያለ ጉዳይ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። 

ሌላኛው ሚኒስቴር ደኤታ አቶ ተስፋዬ ቱሉ ደግሞ የኅብረት ሥራ ማኅበራቱን የተጨማሪ እሴት ታክስ ከፋይነት አስመልክቶ ‹‹ከፍትሓዊነት አንፃር ችግር አለ ከተባለ ወደ እኛ መጥተው ጉዳዩን ማየት ይቻላል፤›› ያሉ ሲሆን ‹‹ዊዝሆልዲንግ ታክስን በተመለከተ ኮምቦልቻ ቅርንጫፋችን አልያም ዋና መሥሪያ ቤታችን ይምጡና አብረን ለመፍትሔ እንሥራ›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች