Tuesday, May 21, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሰላምና የኑሮ ውድነት ጥያቄው ምላሽ ይሻል!

የዘንድሮ የዓለም ሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲከበር፣ የአየር ንብረት ለውጥ በሥራ ከባቢ ደኅንነትና ጤና ላይ እያደረሰ ያለው ተፅዕኖ ትኩረት እንዲሰጠው ማሳሰቢያ መቅረቡ ይታወሳል፡፡ የቀኑ አከባበር መሪ ቃልም በዚህ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ነበር፡፡ በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ)፣ መንግሥት ለሰላምና ለኑሮ ውድነት ትኩረት እንዲሰጥ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል፡፡ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም. ታስቦ የዋለው ሜይ ዴይ ከምናነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጋር ቢገጣጠምም፣ ጥያቄው ግን ዘወትር በተለያዩ መድረኮችም ሆነ የመገናኛ ዘዴ የሚቀርብ ስለሆነ አፅንኦት መስጠት ተገቢ ነው፡፡ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳዬ ብሎ በዋነኝነት ከሚያነሳቸው ችግሮቹ መካከል ሰላምና የኑሮ ውድነት ግንባር ቀደሞቹ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት በእጅጉ የሚቆራኙ መሆናቸውም ሊዘነጋ አይገባም፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ዋስትና ያለው ሰላም ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም ሲባል ሁሉን አካታች የሆነ ሰላማዊ ንግግርና ድርድር መደረግ አለበት፡፡ ዋነኛ የሚባሉ ችግሮች አንድ በአንድ ተዘርዝረው በሰጥቶ መቀበል መርህ ምክክር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ችግሮች ዋነኛው ምክንያት የሰላም መጥፋት ነው፡፡ ሰላም ለማስፈን ቁርጠኝነት ካለ ብዙዎቹ ችግሮች በፍጥነት እንደሚወገዱ ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሸፍጠኝነት፣ ሴረኝነት፣ ቂመኝነት፣ ጉልበተኝነትና ወገንተኝነት ተወግደው ዘለቄታዊ ሰላም የሚያስገኙ ተግባራት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ብሔርን፣ እምነትን፣ የፖለቲካ አቋምን፣ ጥቅምንና ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ ሰበቦችን በመታከክ ሕዝብና አገርን ሰላም መንሳት መቆም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ከገባችበት አደገኛ የቀውስ አዙሪት ውስጥ እንድትወጣና ለሕዝብ ማሰብ ከተቻለ፣ ጦር ከመነቅነቅና ጠመንጃ ከመወልወል ባሻገር ያለውን ሰላማዊ መንገድ መያዝ አያቅትም፡፡

ከዚህ በፊት የነበሩና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተፈጠሩ ችግሮችን ለማስወገድ ቅደም ተከተል ያስፈልጋል፡፡ በረጅም፣ በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮችን መለየት ይገባል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት ከሚፈልጉ ጉዳዮች መካከል ሰላም፣ የምግብ ዋስትና፣ መጠለያ፣ የሥራ ፈጠራና የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡ መንግሥት ሌሎች ጊዜ የሚሰጡ ፕሮጀክቶቹን ገታ አድርጎ መሠረታዊና አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ቢያተኩር ከመካከለኛ ኑሮ ወደ ድህነት፣ ከድህነት ወደ ባሰው ፍፁም ድህነት ውስጥ እየተንደረደሩ እያሽቆለቆሉ ያሉ ወገኖችን መታደግ ይችላል፡፡ ለዚህ ዕውን መሆን ደግሞ በተለይ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ወጣት የሰው ኃይል ሊያሰማራ የሚያስችል አዋጭ ፖሊሲ መንደፍ ነው፡፡ የልማት ዕቅዱ በተጨባጭ የዜጎችን ሕይወት የሚለውጥ መሆን አለበት፡፡ የሕዝቡ ኑሮ ከዕለት ወደ ዕለት እየከበደ ሲሄድ አዋጭ አማራጮችን በባለሙያዎች ታግዞ ማየት ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ሰላም አግኝታ በአዋጭ ፖሊሲ የተደገፈ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ካልተፈጠረ በስተቀር፣ አሁን ባለው ሁኔታ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አንዲት ጋት መራመድ አይቻልም፡፡ በመላ አገሪቱ ሰዎችና ምርቶች በሚፈለገው ልክ ካልተዘዋወሩ የምርቶች አቅርቦት ይገታል፡፡ አቅርቦት ሲያንስ ደግሞ ፍላጎት በጣም ይጨምራል፡፡ በዚህ ላይ የግብይት ሥርዓቱ በወጉ ስለማይመራ ዜጎች ምክንያታዊ ላልሆነ የዋጋ ንረት እየተዳረጉ ድህነቱ እየተባባሰ ነው፡፡ መንግሥት በፕሮጀክቶቹ ሳቢያ ገበያው ውስጥ የሚረጨው ገንዘብ ሲበዛ ችግሩ ይጨምራል፡፡ በበርካታ ሥፍራዎች ሰላም ጠፍቶ የሰዎችና የምርቶች ዝውውር ሲገታ፣ ዜጎች የኑሮ ውድነቱን ሊቋቋሙት አይችሉም፡፡ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች መጠን ሲቀንስ የዋጋ ንረቱ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከባዱን የኑሮ ጫና መቋቋም የተሳናቸው ዜጎች ለከፍተኛ ችግር ከመጋለጣቸውም በተጨማሪ፣ የሰላም ዕጦት ታክሎበት ሕይወታቸው በምሬት እየተሞላ ነው፡፡ ከምንም ነገር በፊት ለሰላም መስፈንና ለኑሮ ውድነቱ መርገብ ቅድሚያ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ብቸኛዋ ቅኝ ያልተገዛች አገር በመሆኗ፣ ከበርካታ በልማትና በሥልጣኔ ከገሰገሱ አገሮች ተርታ መሠለፍ ነበረባት፡፡ ከእነ አሜሪካና አውሮፓውያን ጋር በእኩልነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን የመሠረተች አገር ናት፡፡ ዘመናዊውን ትምህርትና አገር በቀሉን ዕውቀት በመጠቀም የተፈጥሮ ፀጋዎቿን አልምታ በልማት መገስገስ የሚገባት ነበረች፡፡ እንኳንስ በድህነትና በምፅዋት ለማኝነት ስሟ ሊጠራ ቀርቶ፣ የአፍሪካና የዓለም ገበያዎችን በተትረፈረፉ ምርቶቿ ማጨናነቅ ነበረባት፡፡ ባለመታደል ግን በድርቅ፣ በረሃብ፣ በግጭትና በተለያዩ አሉታዊ ስያሜዎች ስሟ እየጎደፈ ነው፡፡ ብዙዎቹ ምሁራኖቿና የፖለቲካ ልሂቃኖቿ ተግባብተውና ተናበው አብረው ለመሥራት ካለመፈለጋቸውም በላይ፣ ጥቃቅን ልዩነቶችን በጨዋነት አስተናግደው ለአገር ግንባታ የድርሻቸውን ለማዋጣት ፈቃደኛ አይደሉም፡፡ አብዮትም ሆነ ለውጥ በመጣ ቁጥር ተባብሮ አገር ለማሳደግ ጥረት ከማድረግ ይልቅ፣ የሚቀድመው እርስ በርስ ለመፋጀት መጣደፍ ነው፡፡

መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ በሙሉ ይህንን የጨፈገገ ሁኔታ በመቀየር የሕዝባችንን የጠወለገ ተስፋ ያለምልሙ፡፡ ለዚህም ያኮረፉ ወገኖች ከትጥቅ ትግል ተላቀው ወደ ምክክሩ ሒደት የሚመጡበትን መደላድል ማመቻቸት፣ ለሐሳብ ነፃነት መከበር  ተግቶ መሥራት፣ አድሎአዊና ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ ማድረግ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብቶች ዋስትና መስጠት፣ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ቁርጠኝነትን ማሳየት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማስቻልና ኢሞራላዊ ድርጊቶችን በሙሉ ማስወገድ ይጠቅማል፡፡ ለሥልጣንና ለጥቅም ብቻ እያንጋጠጡ ምኅዳሩን አይረቤ ማድረግ የሚያባብሰው ቅራኔና ግጭት ብቻ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ከዚያ የተለመደ አረንቋ ውስጥ እንዳትወጣ ከማድረግ የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ ለአጠቃላዩ ሕዝብም ሆነ ሌሎች የአገር ጉዳይ ይመለከተናል ለሚሉ ወገኖች በሙሉ፣ ሰላም ለማስፈን በስክነት ከመነጋገር ውጪ አማራጭ የለም፡፡ ለሰላምና ለኑሮ ውድነት ጥያቄው ምላሽ የሚገኘው በዚህ መንገድ ብቻ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...