Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግብርና ዘርፍ የመድን ዋስትና የተበታተነና ባለቤትነቱ የማይታወቅ እንደሆነ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግብርና ዘርፍ የመድን ዋስትናን የሚያስፈጽመው አካል ማን እንደሆነ በግልጽ ስለማይታወቅ፣ አሠራሩ ባለቤት አልባና የተበታተነ እንደሆነ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ በግብርና ዘርፍ የሚሰጠውን የመድን ዋስትና ለመምራት ሚኒስቴሩ የራሱ የሆነ የሕግ ማዕቀፍ ስለሌለው አርሶ አደሮች በየቦታው የተንጠባጠበ የመድን አገልግሎት እየተሰጣቸው ነው፡፡

ለአርሶ አደሮች የመድን ዋስትና ተቋማት ጥናትን መሠረት አድርገው አገልግሎት እንደማይሰጡ የገለጹት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ የመድን ዋስትና አሰጣጥ ሥርዓቱን ጠብቆ ተፈጻሚ ለማድረግ የግብርና ሚኒስቴር አዲስ አሠራር እንደሚዘረጋ አስረድተዋል፡፡

በእንስሳት፣ በሰብል፣ በአትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም በሌሎች ምርቶች ላይ ውድመት ሲደርስ ለአርሶ አደሮች የመድን ዋስትና አሰጣጡ ጤናማ ነው ወይ የሚለውን መለየት እንደሚያስፈልግ አክለው ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በግብርና ዘርፍ የመድን ዋስትና የሚሰጡት የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እንደሆኑ ገልጸው፣ ኩባንያዎቹ አርሶ አደሮች የመድን ዋስትና እንዲገቡ ሲያደርጉ ምን ዓይነት አሠራር መከተል እንዳለባቸው የሚያሳይ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም ብለዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ የሚሰጠውን የመድን ዋስትና በባለቤትነት የሚመራው ማነው የሚለው እንደማይታወቅ የገለጹት ሶፊያ (ዶ/ር)፣ ይህም በመሆኑ ዘርፉ በተበታተነ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ዘርፉን አስመልክቶ ኢንሹራንስ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም? የሚለውን በተመለከተ ምንም ዓይነት ውይይት አለመደረጉን ጠቁመው፣ የመድን ዋስትና አሰጣጡም በገንዘብ ሚኒስቴር፣ በባንኮች፣ እንዲሁም በግብርና ሚኒስቴር ነው የሚመራው የሚለው አጠያያቂ ሆኖ መቆየቱን አክለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ኢንሹራንስ ትግበራ ከሙከራ ባለፈ ትኩረት እንዳልተሰጠው፣ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሮች ሰብሎቻቸው በተባይ፣ በጎርፍ፣ በአየር ንብረትና በሌሎች አደጋዎች ሲወድሙ በሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ችግሮቻቸው እንዲፈታ የግብርና ሚኒስቴር ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የተለያዩ አሠራሮችን ለመተግበር ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስረድተዋል፡፡

በተለይ በርካታ ተቋማት የግብርና ዘርፉ በጣም ለአደጋ ተጋላጭ በመሆኑ የኢንሹራንስ መድን ዋስትና ለመስጠት ፍላጎት እንደማያሳዩ ገልጸው፣ ችግሩንም በመገንዘብና ዘርፉን በመደገፍ የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል፡፡

በግብርና ዘርፍ የመድን ዋስትና ለመስጠት የተለያዩ የግል ኩባንያዎችና ኤጀንሲዎች ሙከራ እንደሚያደርጉ ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ዘርፉም ባለቤት ኖሮት መመራት እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች