Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየፋሲካን በዓል በግጭት ድባብ ውስጥ ሆነው የሚያሳልፉት የአማራ ክልል ከተሞች

የፋሲካን በዓል በግጭት ድባብ ውስጥ ሆነው የሚያሳልፉት የአማራ ክልል ከተሞች

ቀን:

በክርስትና እምነት አማኞች ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የፋሲካ በዓል የግጭት ድባብ ያጠላበት እንደሆነ፣ በአማራ ክልል የተወሰኑ ከተሞች ሪፖርተር ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ከተጀመረበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ሰላም የራቀው የአማራ ክልል፣ አሁንም በግጭት ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ በዚህ የግጭት ዓውድ ውስጥ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎችም በክርስትና እምነት አማኞች ዘንድ በስፋት የሚከበረውን የፋሲካ በዓል፣ በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆነው እንደተቀበሉት ተናግረዋል፡፡

በማኅበረሰቡ ዘንድ ያለው የሥነ ልቦና ጫና ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ፣ ‹‹በዓልን ከቤተሰብ ጋር የማሳለፍ ልምድ ቢኖርም የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በየብስ መጓዝ እንደማይቻል፣ ትንንሽ ከተሞችንም ቢሆን ለማቆራረጥ አዳጋች ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም በአየር ትራንስፖርት ለመጓዝ መገደዳቸውንና ለዚህ የሚሆን አቅም ያለው ደግሞ በጣም ጥቂት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ማኅበረሰቡ ሕይወትን በማቆየትና በዓልን በማክበር መካከል በመሆኑ እንደ ሌላው ጊዜ በዓል የማክበሩ ስሜት ሙሉ አለመሆኑን ገልጸው፣ በክልሉ ትልልቅ ከተሞች አንፃራዊ ሰላም ቢኖርም ወጣ ባሉ ገጠራማ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ ግን አስቸጋሪ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 

ሌላው የከተማዋ ነዋሪና የባጃጅ አሽከርካሪ እንደተናገሩት፣ ከዚህ ቀደም የበዓል ሰሞን የሰው እንቅስቃሴ ስለሚጨምር ሥራ እንደሚኖር፣ አሁን ግን እንደ በፊቱ የበዓል እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በሥራው ላይ መቀዛቀዝ መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ማኅበረሰቡ ያስቀመጠውን ገንዘብ እያወጣ እየተጠቀመ መሆኑንና ምንም ገንዘብ የሌላቸው ችግር ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ምንም እንኳን ባለፉት ሁለት ሳምንታት በከተማው ግጭት ባይኖርም፣ ከፍተኛ የሆነ ስርቆት ግን ነዋሪዎችን እንዳስመረረ አክለዋል፡፡

በክልሉ በተደጋጋሚ የሚከሰት ግጭት ከሚሰማባቸው አካባቢዎች አንዱ የላሊበላ ከተማ ነው፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የከተማዋ ነዋሪ፣ ‹‹ምንም ሊከሰት ይችላል የሚል ሥጋት በከተማው ነዋሪዎች ውስጥ አለ፤›› ብለዋል፡፡ በዚህም ምከንያት እንደሌላው ጊዜ ደስተኛ ሆነው በዓሉን እያከበሩ እንዳልሆነ ይገልጻሉ፡፡ 

‹‹ከዚህ በፊት ኮቪድ፣ በሰሜኑ ጦርነትና አሁን ባለው ግጭት በቱሪዝም ዘርፍ ተሰማርቶ ለሚኖረው አብዛኛው የላሊበላ ከተማ ነዋሪ በዓል ማክበር ቅንጦት ነው፤›› ያሉት ነዋሪው፣ ገንዘብ ኖሮት የሚገዛ ሰው ካለ የዋጋ ንረትም ሆነ የአቅርቦት እጥረት እንደሌለ ገልጸዋል፡፡ ከአሁኑ ጊዜ በከተማዋ የሚሰማ የተኩስ ድምፅ አለመኖሩን፣ የሰዓት እላፊ ገደብ መኖሩንና ነዋሪዎች በተፈቀደላቸው የሰዓት ገደብ ከተማ ውስጥ እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡

በዙሪያው ባሉ የገጠር አካባቢዎች ከሚሰማ ግጭት ባለፈ በላሊበላ ከተማ ውስጥ ምንም ዓይነት ግጭት የለም ያሉት ደግሞ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ እንደ ሌሎቹ የክልሉ ከተሞች ሁሉ እኚህ ግለሰብም ማንነታቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው ሁኔታ አንፃር በጎንደር ከተማ መረጋጋት ቢኖርም እንደ ምዕራብ አርማጭሆ፣ ደምቢያ፣ ወገራና ጣቁሳ ያሉ አካባቢዎች ግን አልፎ አልፎ ግጭት እንዳለ ገልጸዋል፡፡ ሆኖም ነዋሪዎች በዓሉን በኢኮኖሚና በሥነ ልቦና ጫና ውስጥ ለማሳለፍ መገደዳቸውን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...