Saturday, May 18, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢሰማኮ የሠራተኞች የደመወዝ ግብር እንዲቀነስና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲወሰን ሊጠይቅ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር አድርጎት በነበረው ውይይት አስቸኳይ ምላሽ ይሻሉ ብሎ ያቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች እስካሁን ምላሽ እንዳላገኙ አስታወቀ። 

ኢሰማኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ረቡዕ ሚያዚያ 23 ቀን የሚከበረውን የሠራተኞች ቀን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ከበርካታ ወራቶች በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር የኢትዮጵያ ሠራተኞች ያሉባቸውን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ያለመ ውይይት ማድረጉን አስታውሷል። ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረው ወይይት ካቀረባቸው ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹ ምላሽ ያገኙ ቢሆንም የደመወዝ ገቢ ግብር እንዲቀነስ የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ወሳኝ የሚባሉ ጥያቄዎች ግን እስካሁን ምላሽ እንዳልተሰጣቸው አመልክቷል፡፡ 

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ውይይት ምላሽ እንዲያገኙ የተጠየቁትና አስካሁን ምላሽ ያልተሰጣቸው ጉዳዮችን በድጋሚ ለመንግሥት እንደሚያቀርብ በተለይም በሠራተኞች ደመወዝ ላይ የተጣለው የግብር ምጣኔ እንዲቀንስ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ኢሰማኮ በመግለጫው አስታውቋል፡፡ 

የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ በጉዳይ ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ በሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ያለው የዋጋ ንረት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለመቀነስ ከሚቻልባቸው ዕርምጃዎች መካከል አንዱ የደመወዝ ግብር ምጣኔው ላይ ማሻሻያ ማድረግ መሆኑን አመልክተው፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት በተደረገበት ወቅትም ይህ የመፍትሔ አማራጭ ተነስቶ እንደነበር ገልጸዋል።

አሁንም ቢሆን ኢሰማኮ እንዲመለስለት ከሚሻቸው ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይኸው የደመወዝ ግብር ማሻሻያ ጉዳይ በመሆኑ ጥያቄውን ዳግም ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርቡ አቶ ካሳሁን ገልጸዋል። ሌሎች ምላሽ ያላገኙና በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮችም አቶ ካሳሁን በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ 

ሠራተኞች አሁን እየተከፈላቸው ባለው የደመወዝ ክፍያ የኑሮ ውድነቱን በፍጹም መቋቋም ያልቻሉ በመሆኑ ከደመወዝ የገቢ ግብር እንዲቀነስ ላቀረብነው ጥያቄ መንግሥት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው የሚሹ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በጋራ ተደርጎ በነበረው ውይይት በጉዳዩ ላይ በተሰጠው አቅጣጫ መሠረት አስቸኳይ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወስድም በዛሬው የሜዴይ በዓል ላይ ደግሞ ጥያቄያቸውን ለማቅረብ እንዳስገደዳቸው አመልክተዋል፡፡ 

ከዚህም ሌላ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል የሚወስን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም የቀረበው ጥያቄም ምላሽ እንዳላገኘ ከአቶ ካሳሁን ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ቦርዱ እንዲቋቋም በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ የተደነገገ ቢሆንም የደመወዝ ቦርድ ማቋቋሚያ ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ባለመቻሉ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ተወስኖ ተግባራዊ እንዳይሆን እክል መፍጠሩን ተናግረዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር አድርገውት በነበረው ውይይት ይህ ጉዳይ በጥናት ለመመለስ እንዲቻል ታይቶ እንዲቀርብ በወቅቱ አቅጣጫ ተሰጥቶበት የነበረ ቢሆንም የተሰጠው አቅጣጫ አለመፈጸሙን ገልጸዋል። በመሆኑም ኢሰማኮ በዘንድሮው የሠራተኞች ቀን በዓል ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ ምላሽ እንዲያገኝ ዳግም ጥያቄ የሚቀርብበት ጉዳይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በሥራ ቦታ የሙያ ደኅንነትና ጤንነት መከላከልን አስመልክቶም የወጡ ሕጎች በአብዛኛው አሠሪዎች የማይከበሩ በመሆኑ በሠራተኛው ላይ ሞትና የአካል ጉዳትን እያስከተለ ስለሆነ የሥራ ቦታ የሙያ ደኅንነትና ጤንነትን አስመልክቶ የወጡ ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑም ኢሰማኮ ጠቅሷል፡፡ በማደራጀት ሥራው ላይ እንደተሰጠው አቅጣጫ ሁሉ በዚህም ዘርፍ ጥብቅ መመርያና ክትትል እንዲደረግበት እንጠይቃለን ብለዋል። በተጨማሪም ኢሰማኮ ከአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ምላሽ ይገባዋል ያለው ሌላው ነጥብ የሰላም ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹በጦርነት ዘላቂ መፍትሔ ስለማይመጣ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ግጭትና ጦርነት ቆሞ በውይይት ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ሁሉም ወገኖች ልዩነቶቻቸውን በድርድር እንዲፈቱ እንጠይቃለን፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

ሠራተኞችን የተመለከቱ ዋና ዋና ጥያቄዎች ላይ ለመነጋገር የውይይት በር በመከፈቱ ለሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድረስ በመቅረብ ጥያቄዎችን ማንሳታቸውን ያስታወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የውይይት በር መክፈት ብቻ ሳይሆን በውይይቱ ወቅት መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ሊተገበሩ እንደሚገባ አሳስበዋል። በተለይ ደመወዝ ተከፋይ ሠራተኛው በአገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነት መቋቋም ባለመቻሉ የደመወዝ ገቢ ግብር እንዲቀነስና በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ በተደነገገው መሠረት ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም የቀረቧቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአዎንታዊ መልኩ ተቀብለውት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የኑሮ ውድነትን በሚመለከት በጉዳዩ ላይ ዓይተው እንዲያቀርቡ  በውይይቱ ላይ ለተገኙት ለፍትሕ ሚኒስትሩ አቅጣጫ ሰጥተው እንደነበርም ጠቅሰዋል።

ለቀረቡ ጥያቄዎች ምላሽ መዘግየቱ ደግሞ በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተቀዛቅዞ የነበረው የዓለም ኢኮኖሚ ሳያገግም በራሺያና ዩክሬን መካከል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋጋን ንረቱን እንዲጨምር አድርጓል፡፡ ይህ ጦርነት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መናር ምክንያት የትራንስፖርት ክፍያ፣ የእህልና የሸቀጣ ሸቀጥ ዋጋ እንዲሁም  የመኖሪያ ቤት ኪራይ በእጥፍ ከመጨመሩም በላይ፣ በአገራችን በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት፣ ጦርነትና ድርቅ የዋጋ ንረቱንና የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው ስለመገኘቱም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ 

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በነበረ ውይይት ሌሎች ጉዳዮችንም ማንሳታቸውን በመግለጽ ምላሽ እንሰጣቸዋለን ከቀረቡ ጥያቄዎች መካከል ከ2013 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት ጀምሮ ተቋርጦ የነበረው የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አማካሪ ቦርድ ሥራ እንዲጀምር የሚለው አንዱ ነበር ብለዋል፡፡ የሠራተኛ በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት መጣስ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ የሜይዴይ በዓል በአደባባይ ማክበር መከልከልን፣ የውይይት ነበር የተዘጋብን መሆኑንና ሌሎች ጥያቄዎች ላይ ውይይት ተደርጎባቸው እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በተደረገውም ውይይት፣ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አማካሪ ቦርድ ሥራ እንዲጀምር በተደረገው ውይይት መሠረት የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ቦርዱ የ2016 የቦርዱን ዕቅድ በማዘጋጀት ሥራ ማስጀመሩ ከተሰጡ ምላሾች መካከል ተጠቃሽ ሆኗል፡፡ 

ከውይይቱ በኋላ ኢትዮጵያ የዓለም ሥራ ድርጅት አባል የሆነችበትን 1ዐዐኛ ዓመት ክብረ በዓል በሦስትዮሽ ትብብር መከበር መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በበዓሉ ላይም በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይ መንግሥት፣ አሠሪና ሠራተኛ የጋራ አቋም ማውጣታቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህ ድንጋጌ ያተኮረው የመደራጀትና የመደራደር ነፃነት እንዲከበር፣ የዝቅተኛ ደመወዝ ወለል መወሰኛ ሥርዓት መዘርጋት፣ የሥራ ቦታ ወሲባዊ ትንኮሳና ጥቃት እንዲቆም የቤት ሠራተኞች መብት እንዲከበር፣ የስደተኛ ሠራተኞች አስተዳደር ኮንቬንሽኖች የሚጸድቅበት ሁኔታ የሚያካትት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአሠሪዎች፣ በሠራተኞችና በመንግሥት መካከል ትብብርን በማጠናከር በተለያዩ ደረጃዎች ማኅበራዊ ምክክርን ማዳበር፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የሦስትዮሽ የአሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ቦርድን ማጠናከርና የክልል አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አማካሪ ቦርዶችን ማቋቋምና ሌሎችም አሠሪና ሠራተኛውን የሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ስለመደረሱ አመልክተዋል፡፡ 

በተጨማሪም የሠራተኛውን የመደራጀትና የመደራደር መብት ለማስከበር ያሉትን ተግዳሮቶች ለመፍታትና የመደራጀት ምጣኔን ለማሳደግ፣ አጠቃላይ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ለመፍታት የተሠሩ ሥራዎች ሁሉም ክልሎች በሚሳተፉበት በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ሰብሳቢነት በየስድስት ወር እየተገመገመ መሆኑንም አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ዙሪያ ያጋጠሙንን ችግሮች በሪፖርት መልክ እያቀረበ አቅጣጫ በማስቀመጥ አብረው እየሠሩ ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ከክልልና ከተማ አስተዳደሮች የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ጋርም በቅርበት እየሠሩ ቢሆንም አንዳንድ አሠሪዎችና በአንደንድ ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሠራተኛውን መብት ያለመቀበል ሁኔታዎች እያጋጠሙ መሆናቸው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ከክልል ቢሮዎች እየተነጋገርን ቢሆንም ችግሩን ለመፍታት ጊዜ እየወሰደባቸው ስለሆነ ሠራተኞቹ እየተንገላቱ በመሆኑ  በተጀመረው መሠረት የሦስትዮሹ ቅንጅት ተጠናክሮ  አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት አሳስበዋል፡፡ 

በሌላ በኩል የባለፈው ዓመት የሜይዴይ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ተደርጎባቸው የነበረውን የአደባባይ ክልከላ ተገቢ እንደልነበረ በየደረጃው ካሉ የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ባደረጉት ውይይት መግባባት ላይ መደረሱን ያመለከቱት ፕሬዚዳንቱ የዛሬው በዓል በአደባባይ የማይከበር ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

የዘንድሮው በዓሉ በአደባባይ የማይከበረው በመንግሥት ክልከላ ሳይሆን ኢሰማኮ የዘንድሮው በዓል ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው በተለያዩ የውይይት መድረኮች እንዲከበር በመወሰኑ ነው፡፡ 

ባለፈው ዓመት በአደባባይ በዓሉን ለማክበር የተገደዱት በሠራተኛው ዙሪያ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲሰጥ መንግሥት እንዲያነጋግራቸው ያደረጓቸው ሙከራዎች ሁሉ ተዘግተው ስለነበር የተዘጋባቸው በር እንዲከፈት ለማድረግ ሲሆን ይህም ውጤት መስገኘቱን አመልክተዋል፡፡ 

የዘንድሮን የሜዴይ በዓል አከባበር አስመልክቶ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ ደግሞ የዘንድሮው በዓል አሁንም አንገብጋቢ የሆነውን የሰላም ዕጦትና የኑሮ ውድነት መሠረት ያደረገ እንዲሆን ‹‹ለሰላምና ለኑሮ ውድነት መፍትሔ እንሻለን›› በሚል መሪ ቃል የሚከበር ይሆናል፡፡ 

በዚህ መሪ ቃል እንዲከበር የኢሰማኮ ማዕከላዊ ኮሚቴ ውሳኔ ሊደርስ የቻለበትን ምክንያት ሲያብራሩም ሠራተኛው መደራጀት፣ መደራደርና ጥራት ያለው ምርት ማምረት የሚችለው የተረጋጋና  ሠላሙ የተጠበቀ አካባቢ ሲኖር ብቻ ነው፣ የሚል እምነት ያላቸው በመሆኑ ገልጸዋል፡፡ ሠራተኛው ወጥቶ የሚገባው፣ ሠርቶ የሚኖረው ሠላም ሲኖር በመሆኑ፣ በተለይም በኢትዮጵያ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሠራተኞች ሕይታቸውን እያጡ በመሆኑ ከሚሠሩበት የሥራ አካባቢ ተወስደው በመታገታቸውና ከሚሠሩበትና ከሚኖሩበት አካባቢም በመፈናቀላቸው የሰላም ጉዳይ አጀንዳቸው ሊሆን መቻሉን አስታውቀዋል፡፡ የሰላም ዕጦት ሠራተኞ የሚሠሩባቸው ድርጅቶች በመውደማቸው ምክንያት የሥራ ዋስትናቸውን እያሳጣ በመሆኑ ጭምር ሰላም ይሰፍን ዘንድ ኢሰማኮ ያለውን አቋም ለማሳወቅ ነው የሰላም ዕጦት በሠራተኛው ላይ ያስከተለውን ችግር ለማጉላት እንደ ምሳሌ የጠቀሱት የሰሜኑን ጦርነት ሲሆን፣ ‹‹በትግራይ ክልልና በፌዴራል መንግሥት መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት በተከሰተው ጦርነት የክልሉ ሠራተኞች ላይ የሕይወት፣ የአካል፣ የኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጉዳቶች ደርሰውባቸዋል፤›› ብለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በተደረገው ሠላማዊ ድርድር ማኅበረሰቡ ከአስከፊ ጦርነት እፎይታ አግኝቶ በማገገም ላይ ባለበት አሁንም የሚሠሙ ችግሮች ወደዚያ አስከፊ መጠፋፋት እንዳይመጣ ትኩረትን የሚሹ ሆኖ እንዳገኙትም ጠቅሰዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ሁኔታ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሰላም ዕጦት ችግሮች ምክንያት ጥቂት የማይባሉ ቦታዎች ላይ የልማት ተቋማት ተረጋግተው መሥራት አለመቻላቸውንም አቶ ካሳሁን አመልክተዋል፡፡ 

መንግሥት በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ያሉትን ግጭቶችና ጦርነቶች በውይይት መፍትሔ እንዲያገኙ ሆደ ሰፊ በመሆን የአንበሳውን ድርሻ እንዲጫወት፣ በተለይም መንግሥትና ታጣቂ ኃይሎች ፊታቸውን ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ለውይይት እንዲያዞሩና ሰጥቶ የመቀበል መርህን ተከትለው ለአገራችን ዘላቂ ሰላም መፍትሔ እንዲያመጡ ለመጠየቅ ‹‹ለሠላም መፍትሔ እንሻለን›› የሚል መሪ ቃል ሊመረጥ ችሏል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ሠራተኞች በኑሮ ውድነቱ ምክንያት አንጻራዊ ሰላም በሰፈነባቸው አካባቢዎች ጭምር በቀን አንድ ጊዜ እንኳ መብላት የሚሳናቸውና አሰከፊ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙና ችግሩ ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ መንግሥት ለኑሮ ውድነቱ  አስቸኳይ  መፍትሔ እንዲሰጥ መሪ ቃሉ ሊመረጥ እንደቻለ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች