Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርየከተማ ልማት እንዴት?

የከተማ ልማት እንዴት?

ቀን:

በአየለ ቸ.

የከተማ ልማት መሠረታዊነት

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ በተለይም በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ኢኮኖሚ መንኮታኮት ምክንያት ልማት በአጠቃላይ የኢኮኖሚ ልማት በተለይ እንዴት የሚለው ጥያቄ፣ በተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል አከራካሪ ጉዳይ ሆኖ ነበር። ጥያቄው ይበልጥ አከራካሪ የሆነው በ60ዎቹ ውስጥ ከሦስተኛው ዓለም አገሮች (በተለይም የአፍሪካ አገሮች) ነፃ መውጣት በኋላ አንዳንድ አዳዲስ የልማት ንድፈ ሐሳቦች ከወጡ በኋላ ነው። ዓለም በሁለት የርዕዮተ ዓለም ጎራ በመከፈሏና የእነዚህ ጎራዎች ፉክክር ከልማትም አልፎ ፖለቲካዊ በመሆኑና ከብዙ ጦርነቶችም ጋር የተያያዘ በመሆኑ፣ በሁለቱ ጎራ ውስጥ የሌሉት የልማት ንድፈ ሐሳቦች ይኼን ያህል ሳይታወቁ ወይም ሳይደመጡ ቀሩ። የቀዝቃዛው ጦርነት ማብቃትና ዓለም አነሰም በዛም በአንድ ርዕዮተ ዓለም ከተጠቃለለ በኋላ ግን በጣም ተደማጭነት ያገኙ አዳዲስ ንድፈ ሐሳቦች ብቅ አሉ።

- Advertisement -

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምም (UNDP) በእነዚህ ንድፈ ሐሳቦች ላይ ተመሥርቶ ልማት ሲባል ምን መሆን እንዳለበት፣ ዋና ዋና ገጾቹም ምን ምን እንደሆኑ ካስረዳ በኋላ በመላው ዓለም ያሉ አገሮችን የልማት ደረጃ በሰንጠረዥ በ1980ዎቹ ገደማ ማውጣት ጀመረ። የልማት ዓላማና መሰረቱ ሰዎች በተለይም ድሆችና የተገፉ (ለምሳሌ ሴቶች) መሆን እንዳለባቸው፣ ልማት ለሰዎች ደኅንነትና ብልፅግና ተብሎ የሚነደፍ መሆን እንዳለበት፣ ቅድሚያው የሰዎችን ደኅንነት ማረጋገጥና የኑሮ ደረጃቸውን ደረጃ በደረጃ ከፍ ማድረግ እንደሆነ አረጋገጠ። ስለዚህ ልማት ሲባል “ሀ” ብሎ የሚጀምረው የሰዎችን ደኅነንት በማስከበር፣ ሰዎች ከድህነትም ሆነ ከሌላ ጥቃት ነፃ ሆነው ዕፎይ ብለው በደስታ የሚኖሩበት መሆን እንዳለበት ከተረጋገጠ በጣም ቆየ። እነዚህ ሲዘረዘሩ ዴሞክራሲያዊ መብቶች (የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመሰብሰብ ነፃነቶች)፣ የሴቶች እኩልነትና መብት መከበር፣ የሕፃናት መብት መከበር፣ የትምህርት መዳረስ፣ የአካባቢ ጥበቃ፣ የሰዎች የመኖሪያ ቦታ  (ሃቢታት) መረጋገጥ፣ ወዘተ ናቸው። ከዚያም በላይ የሰዎችን መኖሪያ የማረጋገጥ ጉዳይ አንገብጋቢ በመሆኑ በ90ዎቹ ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢስታንቡል (ቱርክ) ውስጥ (UN Summit on Habitat) ተብሎ የሚታወቀው መሪዎችም የተገኙበት ታላቅ ስብሰባ ተደርጎ ሰዎች በከተማ ውስት የመኖር መብታቸውንና የኑሯቸው መሻሻል እንዴት መታየት እንዳለበት፣ እንዲሁም የከተማ ልማት ሲባል ምን ምን ሊያካትት እንደሚገባ ደነገገ። የኢሕአዴግ መንግሥትም ተገኝቶ የተስማማበት ነበር።

የከተማ ልማትን ጥያቄ ከዚህ አንፃር ነው መመልከት ያለብን። ስለሆነም በአሁኑ ጊዜ እንኳን የከተማ ልማትን የሚያህል ታላቅ የልማት ጥያቄን ይቅርና ዝቅተኛ ተብሎ የሚገመት ጉዳይም፣ ዓለም አቀፍ ድንጋጌ እንዳለውና ኢትዮጵያም የዚህ ድንጋጌ ፈራሚ እንደሆነች መገንዘብ ያስፈልጋል። የሃቢታት ጉባዔ (የኢስታንቡል) ራዕይ በቅጡ የታቀዱ፣ አግባብ ባለው አስተዳደር ሥር የሚኖሩና ቅልጥፍና የተሞላባቸው ከተሞችን መገንባት እነዚህም በቂ መኖሪያ ቤቶች፣ በቂ የከተማ መዋቅር ያሏቸው፣ ወዘተ መሠረታዊ የሆኑ ውኃ፣ መብራትና ንፅህና ያላቸው ከተሞች እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡

ከዚያም በላይ ሃቢታት የተባለው ይኼው የተመድ ድርጅት ዋናው አጀንዳው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የነደፈለት ሲሆን፣ ይኼውም ዘላቂ በሆነ ባካባቢ ጥበቃ የተካኑ ከተሞችና ኅብረተሰቦችን ማካበት ነው ይላል። እንግዲህ በከተማ ልማት ላይ ለመሰማራት የሚነሳ መንግሥት ሁሉ እነዚህን የተመድ ድንጋጌዎች በሚገባ ማወቅ አለበት። በተጨማሪ የአፍሪካ አንድነትም ይህንንን በሚመለከት ድንጋጌዎች አሉት (Pretoria Declaration on Economic, Social and Cultural Rights in Africa, 2004, ነጥብ 5 ይመልከቱ። Compendium of Key Human Rights Documents of the African Union, 399። ለተጨማሪ ንባብ የተመድን The International Covenant on Social and Economic Rights.) ይመልከቱ፡፡

ይሄን ካስቀመጥን በኋላ የብልፅግና መንግሥት  በአዲስ አበባ ስለሚያካሂደው  ደግሞ እናውጋ። ምንም እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የኢኮኖሚ መሠረታቸው ገጠሩ ነው ቢባልም፣ ከተሞች በልማት ላይ ያላችው ሚናም ከፍተኛ ነው። ከመንግሥት ገቢ አንፃር እንኳ ብናየው መንግሥት በጠቅላላው ከአገሩ ከሚሰበስበው ግብር የአዲስ አበባ ድርሻ እስከ 60 በመቶ እንደሆነ የታወቀ ነው። ያለ አዲስ አበባ ግብር ክፍያ የመንግሥት ገቢና ወጪ የማይታሰብ ነው። ይህ የሚያመለክተው መንግሥት የአዲስ አበባ ገቢው ከተቋረጠበት ምን ያህል ምስቅልቅል ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ነው። አዲስ አበባ ሲባል ደግሞ ግብር ከፋዩን በሙሉ የሚመለከት ስለሆነ፣ ይህ ግብር ከፋይ በጥንቃቄ መያዝ እንዳለበትም ያመለክታል። ከዚህም አንዱ ሕዝቡን አለማስኮረፍ ነው። “አኮረፈም አላኮረፈም ግብር መክፈሉ እንደሆን አይቀርም” ሊባል ይቻል ይሆናል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ግን አርቆ አስተዋይነት የጎደለው ነው እላለሁ።

ይህ በተራው የሚመራን አንድ አገር የብሔራዊ ልማት ዕቅድ ሲያወጣ የከተማው ልማትና የገጠሩ ልማት በአንድ በኩል፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአገራዊው ልማትና የከተማው ልማት እንዴት ሊያያዝ እንደሚችል ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፣ ወደ የሚለው ይወስደናል። አፍሪካ ውስጥ ያሉ መንግሥታት የአመለካከት እጥረት ስላላቸው ማንኛውንም ፖሊሲ ከማውጣታቸው በፊት በጉዳዩ ላይ ዕውቀቱ ያላቸውን ምሁራን ሴሚናር እያካሄዱና ሐሳብ ለማግነት ቢሞክሩ ይመከራል። ስለሆነም መንግሥት አዲስ አበባ ውስጥ ሊሠራ ያስበውን በጉዳዩ ዕውቀቱ ያላቸውን ምሁራን ቢያማክር ከብዙ ስህተቶች ሊድን ይችል ነበር።

በተመድ ሃቢታት ራዕይ እንደተገለጸው የከተማ ልማት በጠቅላላው በአንድ አገር ልማት ውስጥ ያለው ቦታ እጅግ ከፍተኛ ነው። የከተማ ልማት ከሁሉ አስቀድሞ ሰው ተኮር መሆን አለበት፡፡ የከተማውን ነዋሪና አገሪቱን የሚጠቅም መሆኑ የተረጋገጠ፣ እንዲሁም በከተማው ሕዝብ መደገፍ የሚገባው መሆን አለበት። ከአገሩ በጠቅላላ ወይም ከገጠሩ ልማት ጋር እንኳ ሳይያያዝ የከተማ ልማት ብቻውን እርስ በርሳቸው ተደጋጋፊ የሆኑ አያሌ ክስተቶችን የሚያካትት ነው። በከተማ ውስጥ ያለውን የኢንዱስትሪ ምርትና የሠራተኛውን ሁኔታ፣ እጅግ ግዙፍ የሆነውን መለስተኛ ንግድና ዕውቅና ያላገኘውን (Informal Sector) የሚባለውን ክፍል፣ የስቴት (መንግሥት) ግንባታን፣ ኪነ ጥበብን፣ የሲቪል ማኅበረሰቡን ግንባታ፣ የምሁራንን ሚና፣ ወዘተ ሁሉ የሚመለከት ነው። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የመብራትና የውኃ አቅርቦት፣ እንዲሁም የከተማ ንፅህና (Sewerage) ማረጋገጥ የከተማ ልማት ብቻ ሳይሆን የከተማ ህልውናን የሚመለከት ነው።

ከሁሉም በላይ ደግሞ የከተማ ልማት ሲባል ለአድስ አበባ ብቻ አይደለም። በመላው አገሪቱ ያሉትን ከተሞች ልማት የሚመለከት መሆን አለበት። ምክንያቱ ከገጠር ልማት ጋር የተቆራኘ ስለሆነ ነው። ከቻይና ተመክሮ እንማር ከተባለ ቻይናውያን በገጠር ከተሞች ሊኖር የሚገባው የኢኮኖሚ ልማት የገጠሩን ልማት እንዴት መልሶ እንደረዳ ድንቅ የሆነ ተመክሮ አላቸው። በገጠር ከተሞች ውስጥ ሊኖሩ ስለሚገባቸው የዘመናዊ ምርት እንቅስቃሴ (ከማጭድና መርፌ ምርት እስከሌላውም በገጠሩ ሕዝብ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶትን ማምረት ድረስ)፣ ብሎም ይህ እንቅስቃሴ መልሶ እንዴት የገጠር ልማቱን እንደሚያግዝና እንደሚያፋጥን ጠንቅቆ ማወቅን ይጠይቃል። በተለይም በአንድ በኩል ለአርሶ አደሩ ምርታማነት መጨመር ብሎም ገቢውን እንዲያሻሽል፣ በሌላ በኩልም ለአገሪቱ ገቢ የሚያስገኙ ምርቶች በሚመረቱባቸው አካባቢዎችም የምርት ቀጣይነት ለማረጋገጥ ዋስትና ሊሰጡ የሚችሉ አካባቢዎች ተለይተው ከከተማ ልማት ወይም በከተማ የሚመረቱ ምርቶች የእርሻ ልማቱን እንዴት ሊያግዙ እንደሚችሉ በቅጡ ተለይቶ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። በተመሳሳይ ትክክለኛ የአርብቶ አድሩ ልማት ስትራቴጂ ተነድፎ ተመሳሳይ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ የአርብቶ አደሩ አካባቢዎች ተለይተው ልዩ ፖሊሲ ሊወጣላቸው ያስፈልጋል (ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች በቀንድ ከብት ብዛት ሁለተኛ ስለሆነች አገሪቱ ይህንን ሀብት እንዴት ወደ ብሔራዊ ሀብት መቀየር እንደምትችል እስካሁን ትኩረት እንዳልተሰጠው መገንዘብ ያስፈልጋል። የአርብቶ አደሩ ልማት ጥያቄም ከከተማ ልማት ጋር ያለውን ቁርኝት በሚገባ መገንዘብ ያስፈልጋል)፡፡ አሁን ወደ አዲስ አበባ የከተማ ልማት ጥያቄ እንሂድ።

የአዲስ አበባ የከተማ ልማት ትኩረቱ ምን ምን ላይ መሆን አለበት

የአዲስ አበባ ልማት ሲባል ከእንጦጦ እስከ ቃሊቲ፣ ወይም ከጉለሌ እስከ ለገጣፎ ባለው ግዛት ብታ የሚወሰን አይደለም። አዲስ አበባ በብዙ ክሮች አካባቢዋ ካሉ ግዛቶች ጋር የተያያዘች ናት። እንዲያው ከውኃ አቅርቦት አንፃር ብቻ ብናየው አዲስ አበባ ብቻዋን ውኃ ከየትም ማግኘት አትችልም፣ በአካባቢዋ ካሉ ግዛቶች በስተቀር። እነዚህ አካባቢዎችም በተራቸው በአዲስ አበባ ላይ በተለያየ ንግድም ሆነ ምርት ተማምነው የሚኖሩ ናቸው። አሁን ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ብናደርግ ለከተማዋ ልማት ብቻ ሳይሆን፣ ለህልውናዋም ጭምር መሟላት ያለባቸው መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎች ሦስት ናቸው፡፡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፣ ውኃና ቆሻሻ ማስወገድ (Sewerage) ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ የከተማው ሕዝብ መሳ በመሳ በሚባል ኑሮው በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ ተማምኖ ያለ ነው። እንጀራ ለመጋገር እንኳ እንደ ድሮው በእንጨት መሆኑ ቀርቷል። በዚያ ላይ በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ የተመሠረቱ ግልጋሎቶች ቁጥራቸው እየጨመረ ነው። የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ኤሌክትሪክና ሲስተም መኖራቸው ወሳኝ ሆኗል። በአጭሩ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የማይጠይቅ እንቅስቃሴ አለ ለማለት አያስደፍርም። ስለሆነም የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከከተማዋ ሕይወት ጋር የተቆራኘ ነው ማለት ነው። የኤሌክትሪክ መቋረጥ ስንትና ስንት የንግድም ሆነ የልማት እንቅስቃሴ እንደሚገድብ የታወቀ ነው። ከዚህ ስንነሳ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ለከተማዋ ሕይወት ወሳኝ ነው። “መጀመሪያ የመቀመጫዬን” እንዳለችው ዝንጀሮ ስለከተማ ልማት ስናወራ ከመጀመሪያዎቹ ወሳኝ አቅርቦቶች አንደኛው የኤሌክትሪክ አቅርቦት ነው። የከተማ ልማት የሚጀምረው አንደኛ የኤሌክትሪክ አቅርቦትን በማረጋገጥ ነው። በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ የሚስተዋለው የኤሌክትሪክ አቅርቦትና አገልግሎቱ በአጭሩ እጅግ አድርጎ ኋላቀርና እጅግ አድርጎ የሚያሳዝን ነው። በየጊዜው የሚስተዋለው የአገልግሎት መቋረጥ፣ አገልግሎት ለማስቀጠል ተገልጋዮት የሚያዩት ፍዳ፣ በተለይም ለማስቀጠል የሚስተዋለው አሳዛኝ የጉቦ ባህል ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው የሚያሰኝ ነው። እኛ ሠፈር መብራት በየጊዜው  ከመቋረጡ የተነሳ መብራት ሲጠፋ መንደረተኛው “ኦ! መብራት ኃይሎች ሥራ ገብተዋል ማለት ነው!” እያለ የሐዘን ቀልድ ይቀልዳል። ስለአዲስ አበባ ልማት ስናወራ ከሁሉ አስቀድሞ ይህንን የመብራት አገልግሎት ማስተካከል፣ እንዳይቋረጥም እንደ ትራንስፎርመር የመሳሰሉ መሳሪያዎችን ለረጅም  ጊዜ እንዲያገልግሉ የሚያስፈልገውን መሣሪያ መለወጥ፣ ወይም አገልግሎቱን በማዘመን ትራንስፎርመሩን ማስቀረት ያስፈልጋል። የመብራት መቋረጥ እንዳይከሰት ማድረግ ይገባል። እዚህ ላይ ነው ቅድሚያ ለየትኛው የሚለው ጥያቄ የሚነሳው። እንዲህ ያለውን መሠረታዊ አገልግሎት ለኅብረተሰቡ ሳይቋረጥ እንዲደርስ ለማድረግ አስፈላጊውን በጀት መድቦ መሥራት ወይስ በ500 ቢሊዮን ብር ቤተ መንግስት መገንባት?

ሁለተኛው ለአዲስ አበባ የከተማ ልማት ወሳኙ ጉዳይ የውኃ አቅርቦት ነው። መቼም በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች የሚታየው የውኃ እጥረት አስፈሪ ደረጃ ላይ የደረሰ ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም። የወሰደውን በጀት ይውሰድ እንጂ ከሁሉ አስቀድሞ መረጋገጥ ያለበት የውኃ አቅርቦት ነው። አዲስ አበባ ውስጥ ታንከር የሌለው ቤተሰብ ውኃ ማጠራቀም አይችልም። ስለሆነም ውኃ ሲቋረጥ አያሌ ቤተሰቦች ይቸራሉ። አንዳንዴ ውኃ ከወራት በላይ የሚጠፋበት ጊዜ አለ። ያኔ ውኃ ፍለጋ ትርምስ ነው። እንዴት የአፍሪካ መዲና በምትባለዋ አዲስ አበባ ውስጥ ይሄ ሊከሰት ይችላል ይባል ይሆናል። ልክ እንደ ኤሌክትሪክ አገልግሎቱ የወሰደውን ያህል በጀት ይውሰድ እንጂ የቤተ መንግሥትና የፓርኮች ግንባታ እንኳ ቀርቶ የውኃ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ማረጋገጥ የከተማ ልማት ሀ ሁ ነው።

ሦስተኛው ለአዲስ አበባ ከተማ ልማት ቁልፍ ጥያቄ የሆነው ደግሞ ቆሻሻን የማስወገጃ ሥርዓትና መዋቅር መዘርጋት ነው። ቆሻሻ በሥርዓት የማስወገድ ተግባር ለአንድ ከተማ ሕይወት ቁልፍ ጥያቄ ነው። ልክ እንደ ውኃና ኤሌክትሪክ አቅርቦት የወሰደውን በጀት ይውሰድ እንጂ (አሁንም ከፓርኮችና ቤተ መንግሥት ግንባታ ይልቅ) ቆሻሻ የማስወገድ ተግባር በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ ነው። በተለይም እያደጉ በመሄድ ላይ ላሉ ከተሞች ጥያቄው አንገብጋቢ ነው። አዲስ አበባን በሚመለከት በፕላን የተቆረቆረች ባለመሆኗ ቆሻሻ የማስወገድ ሥርዓቱን መዘርጋት ከባድ ያደርገዋል። የከተማውን ሕዝብ ጤንነት መጠበቅ የሚያስፈልግ ከሆነና በንፅህናም ለመኖር ቆሻሻ የማስወገድ ተግባርና ሥርዓቱ ወሳኝ ነው። ከላይ ያነሳናቸው ሦስት ዋና ዋና ጥያቄዎች 99.9 በመቶ የሚሆነውን የከተማ ሕዝብ የሚመለከቱ ናቸው። የከተማ ልማት “ሀ” ብሎ የሚጀምረው እንዲህ ያሉ መሠረታዊ የልማት ጥያቄዎችን በመመለስ ነው።

በሕዝባችን አመለካከት ውስጥ በቅጡ አልሰረፀም እንጂ ሕዝብ ግብር የሚከፍልበት ምክንያት እንዲያው ጥንት የነበሩ መንግሥታት እንደሚያደርጉት “ለመገበር” አይደለም። በዘመናዊው መንግሥት አሠራር ሕዝብ ግብር የሚከፍለው እንዲያው በጭፍኑ ለመንግሥት ለመገበር ሳይሆን፣ ግብር ሰብሳቢው መንግሥት መልሶ ኅብረተሰቡን የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለመሥራት እንዲችል ነው። ህዝብ ግብር የሚከፍለው መሠረታዊ የልማት አውታሮችን ማለትም መንገዶችን፣ የኤሌክትሪክና የውኃ አቅርቦት፣ እንዲሁም የቆሻሻ ማስወገጃ ሥርዓት መንግሥት እንዲዘረጋ ነው። በእርግጥ የአገር መከላከያንና የፀጥታ አውታሮችን ማቋቋም፣ እንዲሁም ሌሎች መሠረታዊ ልማቶችን ማከናወንም አንዱ ነው።

የከተማ ልማት ያልሆነውስ ምንድነው?

“አዲስ አበባን እንደ ስሟ ማስዋብ” የሚለው መፈክር ከማስቀደም ጥያቄ (Prioritization) ጋር የተያያዘ ነው። በእርግጥ ቤተ መንግሥቶችንና ፓርኮችን መሥራት (ለዚያውም አስፈላጊነቱ በፓርላማ ተረጋግጦ ነው) የሚሆነው ቀደም ሲል ያነሳናቸው የመሠረታዊ ልማት ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ (ለዚያውም የትምህርት ሥርዓቱን እንደ ማሻሻል ያሉ መሠረታዊ ጥያቄዎችን አንገብጋቢነት ሳናነሳ) ነው። የውኃ አቅርቦት ደካማ በሆነበት ከተማ “አዲስ አበባን ማስዋብ” የሚለው የተባለውን ውበት አጥበን የምንጠጣው ወይም ጋግረን እንደ እንጀራ የምንበላው አይደለም። “አዲስ አበባን እንደ ዱባይ ማድረግ” የሚለው መፈክር ደግሞ አንድም ስለከተማ ልማት አለማወቅን፣ ሁለትም ስለዱባይ ራሱ አለማወቅን ያመለክታል። እስቲ መርካቶ አንድ በረሃብና በበሽታ ራሱን ችሎ መቆም አቅቶት መንገድ ላይ ተጋድሞ የሚለምነውን፣ ወይም ደግሞ ልጇን ማሳከሚያ አጥታ በልመና ተሰማርታ መከራዋን የምታየዋን እናት፣ ሲልም ልጆቿን ለማሳደግ መንገድ ላይ የባቄላ ቆሎ የምትሸጠዋን እናት “አዲስ አበባን አንደ ዱባይ ለማስዋብ” የአንተ ወይም የአንቺ ከዚህ ቦታ መነሳት አስፈላጊ ነው በሏቸው። እነዚህ ቀኑ የጨለመባቸው ድሆች ምን ብለው ሊመልሱ እንደሚችሉ ፖሊሲ አውጭዎች አስበውበታል፡፡ ለመሆኑ ኢትዮጵያና ኤሚሬትስ ምንና ምን ናቸው? ዱባይና አዲስ አበባስ ምንና ምን ናቸው? ማነው ዱባይ ውብ ናት ያለው? በዓለም ላይ ስንት ውብ ከተሞች እያሉ ምንድነው ዱባይ ዱባይ ማለት? እነ ሲንጋፖር፣ ኪጋሊ፣ ባንጋሎርና በርካታ የአውሮፓ ከተሞችና ሌሎችም የት ሄደው ነው ዱባይ ዱባይ የሚባለው?

አዲስ አበባ መሻሻል እንደሚያስፈልጋት ምንም ጥርጥር የለውም። ለነገሩ መሻሻል የማያስፈልገው ከተማ የለም። ዋናው ጉዳይ ግን አንደኛ ቅድሚያ ለምን ይሰጥ ነው። ሁለተኛ ዋናው ጉዳይ የከተማ ውበት ሳይሆን የከተማ ልማት ነው። አሁን እንደሚታየው በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ማለቅ አለበት ተብሎ መንገዶችና ሕንፃዎች እየተገነቡ ነው። ለዚህም ግንባታ መንገዱን ዘግተው ይዘዋል የተባሉ ቤቶች በቅጽበት እየፈረሱ ነው። ብዙዎች አማራጭ ቤት ወይም ሱቅ አልተሰጣቸውም። ብቻ “ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ” በመሰለ ፍጥነት ቤቶች እየፈረሱ ነው። አንዳንዶቹ የፈረሱት ቤቶች ከአዲስ አበባ ታሪክ ጋር የተያያዙ ስለዚህም የከተማዋ ቅርስ የነበሩ ናቸው። እንዲህ ያለው ዕርምጃ እኮ ሰፊ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ቅልጥፍናን፣ እንዲሁም ዕቅድ የማውጣትን ችሎታንም ይጠይቃሉ። የፈረሱ ሱቆች ምንም አማራጭ አልተሰጣቸውም፣ እየተመረጡ ተሰጥቶ ከሆነ አናውቅም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይፍረሱ ቢባል እንኳን አማራጭ የሆኑ ቤቶች በቅጡ መዘጋጀት አለባቸው። በአንዳንድ የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች አማራች ተብሎ የተሰጣቸው ሰዎች ቀርበው እንደተናገሩት አንዳንዱ ቤት በርና መስኮት፣ መብራትና ውኃም እንደሌለው ነው። እንግዲህ ይህ ምን ይባላል? “አዲሳባን ዱባይ ማድረግ!!”፡፡

እኔ ያሁበት ቤት ወላጆቼ የዛሬ 60 ዓመት መሀል አዲስ አበባ ውስጥ የሠሩት ሲሆን፣ በቀደም በአምስት ወራት ውስጥ እንደሚፈርስ በወረዳው ተነግሮናል። አማራጭ ይሰጣችኋል ተብለናል። አብዛኞቹ አማራጭ ቤቶች ከከተማ ውጭ ናቸው። ከመሀል ከተማ ተነስቶ ከከተማ ውጭ መኖር አሁን የአገሪቱ ጸጥታ አነጋጋሪ በሆነበት ወቅት አያሌ ጉዳዮችን ያስነሳል። የሚገርመው እኮ “አዲስ አበባን እንደ ዱባይ ለማስመሰል” የሚለው ሕልም እንዳለ ሆኖ ነገር ግን ችኮላው፣ ጥድፍያው ምንድነው? “ሮም እኮ በአንድ ቀን አልተገነባእም” ይባል የለ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...