Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበዓልን እንደ አክባሪው

በዓልን እንደ አክባሪው

ቀን:

በመጪው እሑድ ሚያዝያ 27 ቀን 2016 ዓ.ም. የሚከበረውን የትንሣኤ በዓል ‹‹ቤት ባፈራው›› ለመቀበል መዘጋጀታቸውን፣ በአንድ የግል መሥሪያ ቤት የሚሠሩ እናት ነግረውናል፡፡

‹‹የፋሲካ በዓል ዶሮ፣ ሽንኩርት፣ ቅቤን ጨምሮ ብዙ ግብዓት ስለሚፈልግ ከገቢ አንፃር ሊፈትን ይችላል፤›› ያሉን እናት፣ ሆኖም ማንኛውም ቤተሰብ ፋሲካን ሳያከብር ይውላል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡

በቋሚ ገበያ ቦታዎች ካልሆነ በስተቀር ለጊዜው የፋሲካ የምግብ ድምቀት የሆነው ዶሮ ገና አለመግባቱን፣ በዓሉ አንድና ሁለት ቀን ሲቀረው በየአካባቢው ጭምር በመኪና ይገባል የሚል ተስፋ እንዳላቸው የሚናገሩት እናት፣ የእሑድ ገበያ ለበዓሉ ተብሎ ሳምንቱን ሙሉ መደረጉ መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ሽንኩርት በአብዛኞቹ የእሑድ ገበያዎች 55 ብር፣ በአንዳንድ ቋሚ ገበያ ሥፍራዎች እስከ 60 ብር መሆኑን፣ ቅቤ 800 ብር፣ እንቁላል የፈረንጅ ዘጠኝ ብር፣ የሐበሻ 14 ብር፣ ዘይት የሱፍ አምስት ሊትር ከዚህ ቀደም ከነበረበት ከ750 ተነስቶ 1,150 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአትክልት በኩል ከዚህ ቀደም ከነበረው ዋጋ አሁን ላይ ቢቀንስም፣ አሁንም ቢሆን ውድ እንደሆነ አክለዋል፡፡

‹‹የፋሲካ በዓል የማይጎድልበት ነው›› የሚሉት እናት፣ ደሃ የሚባሉ እንኳን ለግማሽ ኪሎ ሥጋ አያንሱም ብለዋል፡፡ በፊትም ቢሆን የሚቸገሩ እንዳሉና አሁን ችግሩን ያጎላው ከጊዜ ወደ ጊዜ ኑሮ እየተወደደ መምጣቱ መሆኑን ነግረውናል፡፡ በቻሉት አቅም ሁሉ የፋሲካ በዓልን ቤታቸውን አድምቀው በደስታ እንደሚያሳልፉም አክለዋል፡፡

በአሽከርካሪነት የሚተዳደሩት ጎልማሳ ደግሞ ከፋሲካም በላይ የአገር ሰላም ያሳስበኛል ብለዋል፡፡ ‹‹መጀመርያ ጤና ሆኜ፣ አገር ሰላም ሆኖ ልጆቼን ማሳደግ እፈልጋለሁ›› የሚሉት ጎልማሳ፣ ‹‹አገር ሰላም ሳይሆን ለፋሲካ በዓል ቤቴ የቱንም ያህል ቢሞላ አያስደስተኝም›› ብለዋል፡፡

‹‹ልጆቼ የፋሲካ ሌሊት ተነስተው እንዲፈስኩ፣ ምንም እንዳይጎልባቸው ስል በዓሉን አከብራለሁ እንጂ፣ ለኔ የሚናፍቀኝና የሚያሳስብኝ የአገሬ ሰላም መሆን ነው፤›› ይላሉ፡፡

እንደ ድሮ በዓል መጣ ብለው የሚሯሯጡበት ጊዜ እንደሌላቸው፣ አሁን ላይ  ግዴታ መከበር አለበት ብለው እንደማያምኑ፣ ሰው ስለማያወራው እንጂ ብዙ ችግርን በቤቱ አፍኖ እንደተቀመጠ ያክላሉ፡፡

‹‹እየራበው አልራበኝም፣ እየጠማው አልጠማኝም፣ ሳይበላ በልቻለሁ የሚል፣ እያማረው እንዳላማረው ሆኖ የሚያሳልፍ በርካታ ቤተሰብ ባለበት፣ የእኔ ቤቴን ሞልቶ በዓልን ማሳለፍ ትርጉሙ አይታየኝም፤›› ሲሉም ያክላሉ፡፡

ዓመት በዓልን ተጨንቆ ማሳለፍ በሳቸው ቤት እንደቀረ፣ ምኞታቸው ሁሉ አገር ሰላም ሆና ማየት መሆኑን የነገሩን ጎልማሳ፣ በበዓልም ሆነ ከበዓል ውጭ  በየአካባቢው እየተቸገሩ ለመናገር የፈሩትን ሰዎች በማገዝ አቅም ያላቸው እንዲተባበሩ ጠይቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ግብይት በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ከዘመን መለወጫና ከገና በዓል ጋር ሲነፃፀር አንፃራዊ ቅናሽ መኖሩን ያነጋገርናቸው አንዳንድ ሸማቾች ተናግረዋል፡፡

በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎችም ተገዝተው ቢቀመጡ የማይበላሹ ሸቀጦችን ከወዲሁ እየገዙ መሆኑን ሪፖርተር ተመልክቷል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገበያውን ለማረጋጋት በየአካባቢው የተቋቋመው የእሑድ ገበያ ሸመታውን እንዳረጋጋላቸውም ተናግረዋል፡፡

ከከተማዋ ነዋሪዎችም ከእሑድ ገበያና ከግብርና ምርት የገበያ ማዕከላት ግብይት የሚፈጽሙ በርካታ ናቸው፡፡ በእነዚህ የገበያ ቦታዎች ከአትክልትና ፍራፍሬ በተጨማሪ ዘይት፣ እንቁላል፣ ቅቤና የመሳሰሉት ምርቶች በስፋት ቀርበዋል፡፡

ቅዳሜና እሑድ በነበረው በእሑድ ገበያ፣ ሽንኩርት ከ45 እስከ 60 ብር እንደነበር ሸማቾች ተናግረዋል፡፡ ስምንትና ዘጠኝ ብር ደግሞ የፈረንጅ ዕንቁላል ገበያ ነበር፡፡ በትናንትናው ዕለት በሾላ ገበያ በነበረው ግብይት አንድ ኪሎ ቅቤ ከ850 እስከ 900 ብር ሲሸጥ መዋሉን ተመልክተናል፡፡

የበሬ፣ የበግና የፍየል እንዲሁም የዶሮ ገበያ እኛ ገበያውን በቃኘንበት ከሚያዝያ 19 እስከ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ድረስ ገበያው እምብዛም ስላልቆመ በዘገበው ለማካተት አልቻልንም፡፡

መግለጫ የሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ በዓልን ከምግብ ፍጆታ ባለፈ በሰላም ማሳለፍ ዋናው ጉዳይ መሆኑን ጠቅሶ በዓሉ በሰላም እንዲከበርም ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ሕገወጥ ነጋዴዎች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱንም ገልጿል። የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ እንደተናገሩት፣ ኅብረተሰቡ ያለምንም ፀጥታ ችግር የፋሲካን በዓል በሰላም እንዲያከብር፣ ፀጥታው አስተማማኝ እንዲሆንና በዓሉ ፍፁም ሰላማዊ ሆኖ እንዲያልፍ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየተሠራ ነው።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ ምርትን በመጋዘን በማከማቸት ሰው ሠራሽ የዋጋ ንረት በሚፈጥሩ ነጋዴዎችም፣ ግብረ ኃይሉ ክትትል እያደረገ ሕጋዊ ዕርምጃ የሚወስድ ይሆናል።

በኅብረት ሥራ ማኅበራት በድጎማ የሚቀርቡ ምርቶች በተገቢውና በግልጽ አሠራር ለኅብረተሰቡ መቅረብ እንዳለባቸው የገለጹት ኃላፊዋ፣ በአምስቱም የከተማዋ የመውጫና የመግቢያ በሮች (ኬላዎች) ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት የሕገወጥ ምርት (ኮንትሮባንድ) ዝውውር እንዳይኖር ይሠራል ብለዋል።

እንደ ወ/ሮ ሊዲያ፣ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶች በገበያ ቦታዎች እንዳይሠራጩ መቆጣጠርና ኅብረተሰቡም ገንዘቦችን በጥንቃቄ እየለየ ግብይት መፈጸም አለበት፡፡

 የተለያዩ ባዕድ ነገሮችን እንደ  ቅቤና ማር  መሰል የምግብ ፍጆታዎች ጋር በመቀላቀል በሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንደሚገባ የገለጹት ኃላፊዋ፣ የኢኮኖሚ አሻጥርና ሰው ሠራሽ እጥረት ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ ሕገወጥ ደላሎችም ከሥራቸው መታቀብ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከገበያ ማዕከላት ውጪ የሚከናወኑ የቁም እንስሳ ንግድ የመዲናዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ እያስተጓጎሉና ሕገወጥ ዕርዶችም በዓልን ምክንያት በማድረግ የሚከናወኑ በመሆናቸው የደንብ ማስከበር ቢሮ ይህንን ተከታትሎ ማስተካከል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

በሁሉም የገበያ ማዕከላት ጤናማ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲኖር፣ ገበያውን ለማረጋጋት ተብለው በተቋቋሙ የእሑድ ገበያዎች በዓሉን ምክንያት በማድረግ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖርም ግብረ ኃይሉ መቆጣጠር ይኖሮበታል ብለዋል።

ከበዓሉ ዋዜማ ጀምሮ እስከ በዓሉ ፍጻሜ ኅብረተሰቡ በሰላም በዓሉን እንዲያከብር ቢሮው ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...