Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየስፖርት ሚኒስትሩ ሪፖርትና  መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች

የስፖርት ሚኒስትሩ ሪፖርትና  መሬት ላይ ያሉ እውነታዎች

ቀን:

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የ2016 ዓ.ም. በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሚያዝያ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. አቅርቧል፡፡ ሚኒስቴሩ በተለይም በስፖርቱ ዘርፍ ባለፈው ዘጠኝ ወራት ውስጥ ‹‹አሳክቼዋለሁ›› ያላቸውን ማለትም ንቁ፣ ብቁ ተወዳዳሪና አሸናፊ ዜጋን ከመፍጠር፣ ከስፖርታዊ አደረጃጀት፣ ከስፖርት ማዘውተሪያ መሠረተ ልማት ግንባታና አስተዳደር፣ አኳያ፣ በስፖርት ሳይንስ ሕክምናና በፀረ አበረታች ቅመሞች ዙሪያ ሪፖርቱ በዝርዝር ከተመለከታቸው ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ሚኒስቴሩ በበጀት ዓመቱ ያከናወነውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ማቅረብ ተገቢ መሆኑ እንደተጠበቀ፣ ነገር ግን ደግሞ የሚቀርበው ሪፖርት መሬት ላይ ያለውን እውነታ የሚያመላክት መሆን ይኖርበታል ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዚሁ አሠራርና አካሄድ ጎን ለጎን ሪፖርቱ የሚቀርብለት አካል የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር የሚወስን፣ የሚከታተልና የሚቆጣጠር እንደመሆኑ፣ የሚቀርብለትን ሪፖርት መሠረት በማድረግ በየደረጃው በሚያዋቅራቸው ቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት የሪፖርቱን ትክክለኛነት ማረጋገጥ፣ መገምገምና ማገናዘብ የሚጠበቅበት ለመሆኑ ምስክር አያሻውም፡፡

ከዚህ አንፃር ሚኒስቴሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በስፖርት ዘርፉን ላይ አከናወንኩት ያለውን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ስንመለከት ሪፖርቱ በአብዛኛው መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር ተጣጥሞ የቀረበ እንዳልሆነ ለማየት ሌላው ቀርቶ ከማዘውተሪያ ጋር ብቻ ተያይዞ በየጊዜው የሚደመጡ ትችቶችን መመልከቱ በቂ ይሆናል፡፡

- Advertisement -

በዚህ ሪፖርት በአዲስ አበባ ስታዲየም ሊሠራ የተፈለገው ትራክ ጉዳይ፣ የዕቃ ግዥው ከተፈጸመ በኋላ ሥራውን ለመሥራት የተስማማው ግለሰብ ዕቃውን ከቀረፅ ነፃ ‹‹ላስገባ›› በማለቱ አለመግባባት በመፈጠሩ ምክንያት የዘገየበት ሁኔታ ማጋጠሙ ነው ለምክር ቤቱ ሲቀርብ የተደመጠው፡፡ በቅርቡ አንድ ታላቅ የኦሊምፒክ አትሌት ከማዘውተሪያ ጋር ተያይዞ ሲሰጥ የተደመጠው አስተያየት ‹‹ድንጋይ ላይ እየሠራን የወርቅ ሜዳሊያ እንድናመጣ ይፈለጋል፤›› ብሎ በአደባባይ የተናገረውን ልብ ይሏል፡፡

ሪፖርቱ ከትራክ ጋር ተያይዞ የቀረበበትን መንገድ በተለየ መልኩ መመልከት የሚያስፈልገው አንዱና መሠረታዊ ነገር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ዝግጅት በጀመሩበት ወቅት ላይ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ሪፖርቱ የቀረበበትን ሁኔታ አስገራሚ የሚያደርገው፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ቦታው በዝርዝር ሳይገለጽ ለ2219 የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ ሰነድ ማግኘት የቻሉበት ሁኔታ መጠቀሱ ልብ ይሏል፡፡

ከአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ ጋር ተያይዞ በመቋረጡ ምክንያት ለስታዲየሙ ምዕራፍ ሁለት ግንባታ ከተከፈለው ቅድሚያ ክፍያ 413 ሚሊዮን ብር ተቀናሽ ተደርጎ ተመላሽ መደረጉ መልካም ጎን ቢኖረውም፣ ከዚያ በመለስ ግን ለፓርላማው ሪፖርቱ ቀርቦ መታየት የነበረበት ጉዳይ የስታዲየሙ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ለምን ያህል ዓመት ታቅዶ ነው ዛሬ ለዚህ ተግዳሮት የበቃው? የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ የነባሩ አዲስ አበባ ስታዲየም ጉዳይም በሪፖርቱ ከተጠቀሱት አንዱ ነው፡፡

ሪፖርቱ ኅብረተሰቡ በሚኖርበት፣ በሚሠራበትና በሚማርበት አካባቢ ስፖርት ለሁሉም በሚል መርህ ማዘውተሪያ መዘጋጀቱን ያወሳል፡፡ ለመሆኑ በአዲስ አበባ ውስጥና አካባቢዋ የተሠሩ ኮንዶሚኒየሞች በውስጣቸው የሚኖረው የኅብረተሰብ ክፍል ስፖርቱን እንዲያዘወትር የሚያነሳሱ ምን ያህል ማዘውተሪያ ሥፍራዎች አሉ? የሚነሳ ጥያቄ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የሚታዩትን በውስን የስፖርት ዓይነቶች አሸናፊነት ብቻ ይዞ መቀጠል እንደማይቻል በሪፖርቱ ተካቷል እውነትነት ያለው ሪፖርት ነው፡፡ ታዲያ ችግሩን ለመቅረፍ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የታዳጊ ወጣቶች ፕሮግራም በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተመረጡ 11 የስፖርት ዓይነቶች 31,725 ታዳጊዎችን በመመልመል በየደረጃው በተከፈቱ 1,269 ጣቢያዎች ሥልጠና እንዲከታሉ ለማድረግ በዕቅድ ተይዞ፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 1,000 የሥልጠና ጣቢያዎች ተከፍተው 25,000 ታዳጊዎች ሥልጠና በመከታተል ላይ እንደሚገኙም በሪፖርቱ ተካቷል፡፡

እነዚህ ሁሉ ታዳጊ ወጣቶች በሥልጠና ላይ የሚገኙ ከሆነ፣ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሁሉም የስፖርት ዓይነት በተለይም የብዙዎችን ቀልብ በሚስቡት ሁለቱ ስፖርቶች ማለትም በእግር ኳሱም ሆነ በአትሌቲክሱ የታዳጊ ወጣቶች ክፍተት የዘወትር መነጋሪያ ሆኖ ሲነገር የሚደመጠው ለምንድነው? ሪፖርት አቅራቢውን ተቋም ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ አካላት ለነዚህ ሁሉ ታዳጊ ወጣቶች የሚበጀተው በጀት ግምት ውስጥ ገብቶ ክለቦችን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የስፖርት አመራሮች ታዳጊ ወጣቶቹን ከግምት ያስገባ አደረጃጀት እንዲኖራቸው የማይደረገው ለምንድነው?

ምክር ቤቱ በአገሪቱ ስፖርት የአደረጃጀት (መዋቅራዊ) ችግር እንዳለ በግልጽ እየታወቀ ዝም ብሎ የሚቀርብለትን ሪፖርት ብቻ አዳምጦ መለያየት ለምን ብሎ መጠየቅ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ከመሠረተ ልማት ግንባታ ጋር ተያይዞ በሪፖርቱ ከተካተቱት መካከል ከእውነቱ ጋር የሚጣረሱ ለመሆናቸው አንዳንዶቹን ወስደን ብንመለከት፣ ምንም እንኳ አንዳንዶቹ የስታንዳርድ (የጥራት) ችግር ቢኖርባቸውም በፌዴራል በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች ደረጃ 13 ስታዲየሞች ግንባታ በተለያየ ደረጃ የሚገኝ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ተደራሽነቱን ለማስፋትም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጭምር የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች እየተስፋፉ መሆኑን ያትታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ስታዲየሞች ባሉበት እንዴት ነው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አዳማ፣ ድሬዳዋና ሐዋሳ ከተሞች ላይ ብቻ ውድድሮቹን እያከናወነ የሚገኘው? ሊጉ አማራጮችን መመልከት ያልቻለውስ (አንደኛው ያውም የዩኒቨርሲቲ ስታዲየም መሆኑ ሳይዘነጋ) ለምንድንነው?

ሪፖርቱ ከፍ ሲልም የአፍሪካ ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የባህልና ስፖርት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የትምህርት ሚኒስቴር የበላይ ኃላፊዎች የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቁሞ የዝግጅት ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ አስፈላጊውን ዕቅድ በማርቀቅ ላይ እንደሚገኙም ተጠቅሷል፡፡ ዕቅዱን ዕውን ለማድረግ ደግሞ በሚቀጥሉት አራትና አምስት ዓመታት ውስጥ ከስድስት ያላነሱ ደረጃቸውን የጠበቁ ስታዲየሞች እንደሚያስፈልጉም እንደዚሁ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ የአዲስ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ በአገሪቱ ምን ያህል ስታዲየሞች ናቸው በግንባታ ላይ መሆናቸው የሚነገረው?

በሌላ በኩል ደግሞ ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንዳሉበትም ይጠቅሳል፡፡ ከተግዳሮቶቹ መካከል ከፌዴራል እስከ ክልል ታችኛው የመንግሥት መዋቅር ወጥና ተናባቢ የሆነ አደረጃት አለመኖር፣ ችግሩ በተለይም ለሚኒስቴሩ የፕሮግራም በጀት አነስተኛ መሆን፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የወሰን ማስከበር ሥራ ላይ እንቅፋት እየሆነ እንደሚገኝ ያትታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ