Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበኦሮሚያ በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ

በኦሮሚያ በተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ

ቀን:

በኦሮሚያ ክልል በ18 የተለያዩ ከተሞች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ። ሪፖርተር ያገኘው ሰነድ እንደሚያስረዳው የክልሉ ንግድ ቢሮ በቄለም ወለጋ፣ ሰሜን ሸዋ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ ኢሉባቦር፣ ቡኖ በደሌ፣ አርሲ፣ ቢሾፍቱ፣ ሸገር፣ ነቀምቴ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ጅማ፣ አምቦ፣ ፍቼ፣ ሞጆ፣ ሆለታ እንዲሁም ወሊሶ አካባቢዎች ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት እንዳጋጠመው በመግለጽ ለነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣንና ለኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መሥሪያ ቤቶች የነዳጅ አቅርቦት እጥረት እንዳጋጠመው አስታውቋል። 

ለሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ሰኞ ዕለት ሚያዝያ 21ቀን 2016 ዓ.ም. የተላከው ሰነድ በክልሉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ በተለያዩ ዞንና ከተማ አስተዳደሮች የነዳጅ (የቤንዚንና የናፍጣ) አቅርቦት እጥረት ስላጋጠመ አብዛኛው የነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጅ ባለመኖሩ የትራንስፖርት አገልግሎት ተጠቃሚ ማኅበረሰብ ከፍተኛ መጉላላት ማጋጠሙን፣ በተለያዩ የልማትና ፀጥታ ማስከበር ሥራዎች ላይም እንቅፋት ማስከተሉን የክልሉ መንግሥት ባደረገው ክትትል እንዲሁም ዞንና ከተማ መስተዳደሮች የችግሩን ግዝፈት በመግለጽ በደብዳቤ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ላላቸው ሁለቱ ተቋማት ማሳወቁን ያስረዳል። 

የአቅርቦት እጥረቱ ያጋጠማቸው ከተሞችን በዝርዝር በመጥቀስ ለችግሩ መፍትሔ እንዲሰጠውም ጠይቋል። 

- Advertisement -

በክልሉ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረትን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኦሮሚያ ከፍተኛ ባለሥልጣን ‹‹እጥረቱ በቢሾፍቱ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ በኦሮሚያ በሙሉ ማለት በሚቻል ሁኔታ የተፈጠረ ነው፣ ሁኔታው እኛንም አስደንግጦናል፤›› ብለዋል። 

እጥረቱ ያጋጠመው በተለይ ትልልቅና የክልሉን የነዳጅ ፍጆታ እንዲጨምር ያደረጉ የልማት ፕሮጀክቶች ማጠናቀቂያ በሆነበት አሁን ላይ መሆኑ ጉዳዩን አሳሳቢ እንዳደረገባቸው ገልጸዋል። 

ችግሩ እየተባባሰ የመጣ መሆኑን የገለጹት እኚህ የክልሉ ከፍተኛ አመራር የአቅርቦት ሁኔታው መንገጫገጭ ከጀመረ ወደ 20 ቀን ማሳለፉንና አሁን ግን ጫናው እጅግ ከፍ ማለቱን አሳውቀዋል። 

‹‹ቢሾፍቱ ከተማ የኮንፍረንስ፣ የቱሪስት፣ ብዙ ፋብሪካዎች የሚንቀሳቀሱበት፣ ሪዞርቶች በብዛት ያሉበት ከመሆኑ የሚመለከታቸውን  ሁለቱን የመንግሥት ተቋማት ችግር ገጥሞናል፣ እባካችሁ ቶሎ ፍጠኑልን እያልን ነው፤›› ብለለዋል። 

ቢሾፍቱ ከተማ ብቻ በየቀኑ አሥር የናፍጣና አምስት የነዳጅ ቦቴዎች እንደሚያስፈልጉት ከከተማው አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ነገር ግን ለአጠቃላይ ከተማው ነዳጅ የሚያቀርቡት ሁለት ነዳጅ ማደያዎች ብቻ መሆናቸው ታውቋል። 

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ኃላፊ አቶ ሔኖስ ወርቁ እጥረቱን በተመለከተ ከዚህ ቀደም ጥያቄ  እንደተነሳላቸው የገለጹ ሲሆን ችግሩ ግን በቢሾፍቱ ከተማ ብቻ የተወሰነ አይደለም ብለዋል። 

ምክትል ዋና ኃላፊው ለእጥረቱ መባባስ ከዚህ ቀደም ሲነሱ ነበር ያሏቸውን ሁለት ጉዳዮች ጠቅሰዋል። 

በቅድሚያ ከአምስት ወይ ከስድስት ወራት በፊት ጂቡቲ ሆራይዘን ዴፖ ላይ የተወሰነ የቃጠሎ አደጋ አጋጥሞ እንደነበር የገለጹ ሲሆን ከዚህም ጋር በተያያዘ የተወሰነ የፍሰት መጠም (flow rate) የመቀነስ አዝማሚያዎች አሉ፣ ማሽኖቹ ወደ ነዳጅ ቦቴ መኪናዎቹ የሚቀዱበት ፍጥነት የመቀነስ ነገር አለው፡፡ ይህም የራሱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ይኖራል ብለዋል። 

በሁለተኛ ደረጃ የቀረበው ምክንያት ደግሞ ‹‹ባለፈው ከክረምቱ ጋር በተያያዘ ብዙ መንገራገጮች ነበሩ። በዚያ ምክንያት ቦቴዎች እዚያው አካባቢ የመቆምና ሳይመጡ የመቆየት ሁኔታዎች ስለነበሩ እሱም የራሱ የሆነ ጫና ይኖረዋል፤›› ብለዋል። 

ቢሾፍቱን በተመለከተ የኢንዱስትሪ ከተማ ስለሆነ በልዩ ሁኔታ ሊስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ አለ ወይ? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላችው ጥያቄ አቶ ሔኖስ፣ ‹‹ቢሾፍቱ ብቻ ሳይሆን አፋር ሰመራ አካባቢ፣ ድሬዳዋም የመተላለፊያ መስመር እንደ መሆናቸው ብዙ መኪኖች ነዳጅ የሚቀዱት ከእነዚህ አካባቢዎች ነው። ስለዚህ በተቻለ መጠን ቅድሚያ ሰጥታችሁ የነዳጅ ድልድል ማካሄድ ያለባችሁ የሚል ምክረሃሳብ ነው የሰጠነው፤›› ብለዋል። 

ከዚህ ባለፈ በቢሾፍቱ ከተማ ውስጥ ነዳጅ እያቀረበ ከሚገኘው ኩባንያ ጋርም ለመነጋገር መሞከራቸውን ጠቅሰዋል። 

‹‹በተለይ ለትልልቅ ከተሞች ነዳጅ ከሚያቀርቡት ጋር ለመነጋገር እንሞክራለን። ነገር ግን አንዳንድ ኩባንያዎች ጉዳዩን ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከዘረጋው ፍትሐዊ የገበያ ድርሻ አሠራር ሒደት ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ። እንዲህ ዓይነት ነገሮች ገጥመውናል። ከዚህ ጋር የሚያያዝ ነገር የለውም ወደ አገር ውስጥ የሚገባው ነዳጅ መጠ አልቀነሰም፤›› ሲሉ ተናግረዋል። 

እንደ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ መረጃ በዓመት ከ4.4 ቢሊዮን ዶላር እስከ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለነዳጅ ግዥ ወጭ እየተደረገ ሲሆን በየቀኑ እስከ ዘጠኝ ሚሊዩን ሊትር የሚደርስ ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ እንዲገባ ይጫናል። 

በኦሮሚያ የተፈጠረው የነዳጅ እጥረት ከኮታ ድልድል ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ የተጠየቁት አቶ ሔኖስ ‹‹ኮታ ገበያውን ፍትሐዊ ለማድረግ የተደረገ ነገር እንጂ ተፈጠረ ከተባለው እጥረት ጋር ምንም የሚያይዝ ነገር የለውም፣ በአቅርቦት ደረጃም ሆነ ከጭነት አንፃር ምንም የቀነሰ ነገር የለም፤›› ብለዋል። 

እንደ ምክትል ዋና ኃላፊው ገለጻ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ነዳጅ ማደያ ኩባንያዎች የነዳጅ ገበያ ድርሻ (Market Share) ከዚህ በፊት በተለምዶ ያገኙ የነበረውን መጠን ባለበት ረግቶ እንዲቀጥል የሚፈልጉ በተለይ ገበያውን በብቸኝነት በመቆጣጠር (monopoly) በተወሰነ ደረጃ ይዘው የነበሩ ትልልቅ የሚባሉ የነዳጅ ኩባንያዎች ይህንን የኮታ ጉዳይ አንስተው ለማስጮህ ጥረት እያደረጉ ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። 

አቶ ሔኖስ ‹‹እኛ ከሥር ከመሠረቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሁሉም ነዳጅ አቅራቢ ኩባንያዎችም ባሉበት አጠቃላይ ውይይት ተደርጎ ገበያዊ ለሁሉም ፍትሐዊ መሆን አለበት፡፡ አዳዲስ አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ኩባንያዎች ስላሉ ይህንን አሠራር አበጅቶ በአግባቡ በፍትሐዊነት ማስተናገድ ያስፈልጋል በሚል ዕሳቤ ተግባራዊ ያደረግነው ነው እንጂ የትኛውም ቦታ ጋር ተፈጠረ ከሚባል እጥረት ጋር ኮታ የሚያገናኘው ነገር የለም፤›› ብለዋል። 

ይሁንና ምክትል ዋና ኃላፊው በቢሾፍቱና ሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፈጠረ ስለተባለው እጥረት የነዳጅ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ምላሽ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ጠቅሰዋል። 

የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ዋና ላፊ አቶ እስመለዓለም ምሕረቱ በበኩላቸው ጉዳዩ የሚመለከተው ድርጅቱንም ሆነ ኩባንያዎቹን የሚቆጣጠረው የባለሥልጣን መሥሪያ ቤት ነው ብለዋል። 

በኦሮሚያ ከተሞች የተፈጠረውን የነዳጅ እጥረት አስመልክቶም ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ መረጃው የለኝም ያሉ ሲሆን ‹‹እጥረት የለም፣ ከዴፖዎች እያወጣን፣ ነዳጅ እየሰጠን ነው ያለነው፣ እጥረት መኖሩን አላውቅም፤›› ብለዋል። 

የኦሮሚያ ክልል ንግድ ቢሮ እጥረቱን ለማስቆም እያደረገ ባለው ጥረት ከጅቡቲ ተጭኖ ከሚጓጓዘው በተጨማሪ  ከማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ 250 የነዳጅ ቦቴ ነዳጅ ከአዋሽ ተጭኖ እንዲሰራጭ ማዘዙን ሪፖርተር ከምንጮቹ መረዳት ችሏል። 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...