Monday, May 20, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ግጭቶችን በሰጥቶ መቀበል መርህ ማስቆም ኢኮኖሚውን ይታደጋል!

ለፖለቲካ አለመረጋጋት መንስዔዎች ተብለው ከሚጠቀሱ ምክንያቶች መካከል ኢኮኖሚ አንዱ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ሲኖር ፖለቲካው የሚረጋጋ በመሆኑ በሥራ አጥነት፣ በኑሮ ጫና፣ በመሠረታዊ አቅርቦቶች እጥረትና በመሠረተ ልማት ችግሮች የሚቸገሩ ዜጎች ተስፋ ይለመልማል፡፡ ኢኮኖሚው ሲቀዛቀዝና የኑሮ ውድነት ከዜጎች አቅም በላይ ሲሆን ግን፣ ለግጭት መነሻ ሊሆን የሚችል አለመረጋጋት ይከሰታል፡፡ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ለኢኮኖሚ ዕድገት መዋል የሚገባው የሰው ኃይል፣ ሀብትና ጊዜ ሲባክን በስፋት እየታየ ነው፡፡ በበርካታ አካባቢዎች በሚካሄዱ ግጭቶችና ውጊያዎች ምክንያት ኢኮኖሚው እየተጎዳ ነው፡፡ ለአገር ልማትና ዕድገት መዋል የሚገባው በከፍተኛ ልፋት የሚገኝ ሀብት ለጦርነት ሲዳረግ የጤና፣ የትምህርት፣ የትራንስፖርትና የሌሎች መሠረተ ልማቶች ግንባታ እየተስተጓጎለ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የመንግሥት በጀት እየተጣበበ ማኅበራዊ አገልግሎቶች ይዳከማሉ፡፡ መንግሥትም ለሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያዳግተዋል፡፡

እንደሚታወቀው ኢኮኖሚው ሲዳከም ለግጭት ምክንያት የሚሆኑ ችግሮች ይበራከታሉ፡፡ ድህነት ሲባባስና የማደግ ዕድሎች ሲጨናገፉ ሰዎች ወደ ግጭት ያመራሉ፡፡ በማኅበረሰቦች ውስጥ በእኩልነት ፉክክር ለማደግ የሚያስችሉ አማራጮች ሲጠፉ፣ ሥራ አጥነት ሲስፋፋ፣ በቂ ምግብና መጠለያ ሳይኖር ሲቀርና ተስፋ አስቆራጭ ክስተቶች ሲበዙ ግጭት ውስጥ መግባት የተለመደ ሥራ ይሆናል፡፡ ከግጭት በመለስ ከኪስ አውላቂነት ጀምሮ እስከ ተደራጀ ዘረፋና ግድያ ድረስ የሚያስገቡ ወንጀሎች ይለመዳሉ፡፡ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሥፍራዎች የተካሄዱ ግጭቶችና ጦርነቶች ኢንቨስትመንቶችንና የንግድ ሥራዎችን አውከዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እንኳንስ ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር፣ ሥራ ላይ የነበሩ በርካታ ዜጎች ለሥራ አጥነት ተዳርገዋል፡፡ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በየመጠለያው ዕርዳታ ጠባቂ ከመሆን አልፈው፣ የከፋ ድህነት ውስጥ ሆነው ተስፋ እንዲቆርጡ ተገደዋል፡፡

በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል የነበረው ግጭት ቢገታም፣ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሄደ ያለው መጠነ ሰፊ ውጊያ ኢኮኖሚውን እያደቀቀው ነው፡፡ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት ካስገበረና በበርካታ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶላሮች የሚገመቱ ንብረቶችን ካወደመ በኋላ፣ ተስፋ ሰጪ የሰላም አየር በቅጡ ሳይነፍስ በራያና አካባቢው እንደገና ግጭት መቀስቀሱ ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ በቅርብ ርቀት ባለው የአማራ ክልል መጠነ ሰፊ ውጊያ እየተካሄደ መሆኑ፣ ችግሩን ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እያደረገው ነው፡፡ የሰላም ስምምነቱ ተስፋ ውስብስብ በሆኑ ችግሮች የተከበበ ቢሆንም፣ አሁንም ከጦርነት አዙሪት ውስጥ ሊያስወጡ የሚያስችሉ ዕድሎች አሉ፡፡ እነዚህን ዕድሎች በአግባቡ ለመጠቀም ግን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ስላለባቸው፣ በሥርዓት ተቀምጠው ለመነጋገር የሚያስችል ምኅዳር ይፍጠሩ፡፡

ያልተሟላ ሰላም ለአገር ህልውናም የማይበጅ ስለሆነ፣ በየቦታው የሚካሄዱ ውጊያዎች በመላ አገሪቱ ኢከኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ጫና ይፈጥራሉ፡፡ በዜጎች ሕይወትና አካል ላይ ከሚደርሱ ጉዳቶች በተጨማሪ መሠረተ ልማቶች ይወድማሉ፣ ከግጭት ውስጥ መውጣት አይቻልም የሚል ሥነ ልቦናዊ ፍራቻ ይፈጥራሉ፣ በየጊዜው መፈናቀል ሲበዛ ለኢንቨስትመንትና ለንግድ ሥራ መሰናክሎች ይበዛሉ፣ አርሶ አደሮች ተረጋግተው የእርሻ ሥራቸውን ስለማያከናውኑ የምርቶች አቅርቦት ችግር ይፈጠራል፣ ለአርሶ አደሮች የፋብሪካ ውጤቶችንና የግብርና ግብዓቶችን ለማቅረብ ይቸግራል፣ ዜጎች እንኳንስ ራቅ ያለ ሥፍራ ለመሄድ በአካባቢያቸው ለመንቀሳቀስ ያዳግታቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በጦርነት የፈረሱ መሠረተ ልማቶችን ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ያቅታል፣ ተፈናቃዮችን በቶሎ ወደ ቀዬአቸው መመለስ አይቻልም፣ ተጨማሪ ሥራዎችን መፍጠር አይታሰብም፣ እንዲሁም የኑሮ ውድነቱ የበለጠ እየጨመረ የዜጎች ሕይወት ይመሰቃቀላል፡፡

በግጭቶች ምክንያት ተፈናቅለው የዕርዳታ ያለህ እያሉ የሚጮኹ ወገኖችን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ሀብት ያስፈልጋል፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እ.ኤ.አ. በ2024 የእነዚህን ወገኖች ሰቆቃ ለመቅረፍ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ በተደጋጋሚ ቢያስታውቅም፣ በቅርቡ በኖርዌይ በተካሄደ የድጋፍ ማሰባሰብ ዘመቻ የተገኘው የሚፈለገውን ሩብ ያህል አልሞላም፡፡ የእነዚህን ወገኖች የምግብና ምግብ ነክ ፍላጎቶች ለማሳካት ዓለም አቀፉ ጥረት ፍሬ ካላፈራ፣ ከአገሪቱ በጀት ላይ ለሰብዓዊ ዕርዳታ ሲነሳ በአገሪቱ የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ ዕድገት ፍላጎት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፡፡ ለመንገድ፣ ለጤና፣ ለኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለትምህርትና ለሌሎች መሠረተ ልማቶች የሚውል ሀብት እየታጠፈ የዜጎች ሕይወት ለብርቱ ችግር ይጋለጣል፡፡ ግጭቶችን ማስቆም የሚያስችሉ በርካታ አማራጮች እያሉ፣ በችላ ባይነት ዝም ማለት መዘዙ ከባድ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት አመላካች አኃዞች በመንግሥትም ሆነ በሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት እየወጡ፣ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች እንደሚጠበቁ በስፋት ሲነገር ይደመጣል፡፡ አኃዞቹ የተለያዩ ቢሆንም ዕድገት የመኖሩ ተስፋ በአዎንታዊ ጎኑ ይወሰዳል፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም ቢኖራት ካላት ወጣት የሰው ኃይል፣ የመሬት ስፋት፣ የውኃ ሀብት፣ ተስማሚ የአየር ጠባዮችና ከሌሎች የተፈጥሮ ፀጋዎች አኳያ ከተጠቀሱት አኃዞች በላይም ማደግ እንደሚቻል ጥርጥር የለም፡፡ ይሁንና ሰላም ጠፍቶ ዙሪያውን ግጭት በበረከተባት ኢትዮጵያ ውስጥ፣ ከማደግ ይልቅ የህልውና ሥጋት ነው በስፋት የሚስተዋለው፡፡ ይህንን ሥጋት በዘለቄታዊ ሰላም በመግፈፍ ዕድገቱን ዕውን ለማድረግ ብርቱ ፈቃደኝነትና ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም በሰጥቶ መቀበል መርህ ግጭቶችን በማስቆም ኢኮኖሚውን መታደግ ይቻላል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...