Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ለኪሳራ መዳረጉ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • መምህራን ከሕግ አግባብ ውጭ ንግድ ፈቃዱን እንደሚጠቀሙ ተጠቁሟል
  • ዩኒቨርሲቲው የዋና ኦዲተር ሠራተኞችን ሊደልል ሙከራ ማድረጉ ተነግሯል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ  ቤት የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝ ለኪሳራ መዳረጉን ባካሄደው የኦዲት ግኝት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዝና የውስጥ ገቢ ማመንጫ የሥራ አፈጻጸም ኢኮኖሚያዊ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ መሆኑን በተመለከተ፣ በ2014/15 በጀት ዓመት የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ከትናንት በስቲያ ሚያዝያ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ተወያይቷል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የተቋቋመው የገቢ ማመንጫ ኢንተርፕራይዙ፣ በዩኒቨርሲቲው ሥራ አመራር ቦርድ እየተመራ አለመሆኑን ቋሚ ኮሚቴው የገለጸ ሲሆን፣ ሲቋቋም ከተከፈለ ካፒታል በተጨማሪ ከዩኒቨርሲቲው በዓይነት የተሰጡት ንብረቶች ወደ ኢንተርፕራይዙ ካፒታል አለመካተታቸው ተመላክቷል፡፡

ኢንተርፕራይዙ ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ዓመታዊ ሒሳቡ እንደማይዘጋና የሒሳብ መግለጫውን ትክክለኛነት በዋና ኦዲተር ወይም ዋና ኦዲተር በሚሰይመው አካል ኦዲት እያደረገ እንደማያረጋግጥና አዳዲስ የንግድ ሥራዎችን ለመጀመር የአዋጭነት ጥናት እንደማያደርግ ተገልጿል።

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የገቢ ማስገኛ ድርጅቶች የሚተዳደሩበትን ሥርዓት ለመወሰን የወጣው መመርያ እንደሚገልጸው፣ የዩኒቨርሲቲው ተቀጣሪዎች በገቢ ማስገኛ ድርጅቶች ተቀጥረው ማገልገል እንደማይችሉ ይገልጻል ያሉት የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ  ቤት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ ግን ኢንተርፕራይዙ ባወጣው ንግድ ፈቃድ በመሥራት የገቢውን 15 በመቶ ለኢንተርፕራይዙ፣ 85 በመቶ ለራሳቸው ገቢ እያደረጉ መገኘታቸውንና ይህ ግን የሕግ መሠረት የሌለውና የሚቆጣጠረው ትምህርት ሚኒስቴር ሊያየው እንደሚገባ የፌዴራል ዋና ኦዲተሯ ገልጸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የኦዲት ክዋኔ ወቅት የዋና ኦዲተር መሥሪያ  ቤት ሠራተኞችን ለመደለል ሙከራ መደረጉንና በዚህም ምክንያት ሌሎች ኦዲተሮችን በመተካት ሥራው መከናወኑ ተመላክቷል።

በቋሚ ኮሚቴው እንዲሁም በዋና ኦዲተር ለተነሱ ጥያቄዎችና ማብራሪያ የሚሹ የኦዲት ግኝቶች ላይ የዩኒቨርሲቲው የሥራ ኃላፊዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል። የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት አያኖ በራሶ (ዶ/ር) የዋና ኦዲተር ሠራተኞችን ለመደለል ተሞክሯል በሚል ለተነሳው ግልጽ ማብራሪያ ባይሰጡም፣ ስለጉዳዩ እንደማያውቁ ገልጸው ‹‹የማውቀው ነገር የለም፣ ተፈጥሮ ከነበረ ግን በጣም ነው የማዝነው፤›› ብለዋል።

ኢንተርፕራይዙ የሒሳብ ሥርዓቱን ማዘመን ይኖርበታል በሚል የቀረበውን ሐሳብ እንደሚስማሙበትና በቀጣይም ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩበት አያኖ (ዶ/ር) ገልጸዋል። መጀመሪያ አካባቢ ዩኒቨርሲቲንና ኢንተርፕራይዝን አንድ አድርጎ መመልከት እንደነበር አስታውቀው፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን በኢንተርፕራይዙ ውስጥ የሚሠሩት በትርፍ ሰዓታቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የሕግ መሠረት የለውም በሚል የቀረበላቸውን ጥያቄ አስተባብለዋል። ‹‹በሙያቸው መምህራን ናቸው፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን አሸንፈው የሚያመጡት ገንዘብ ለእነሱም ለኢንተርፕራይዙም ይጠቅማል። ግን አካሄድ ላይ ሥርዓት ተዘርግቶለት መሆን አለበት የሚለውን እንቀበላለን። ሆኖም ግን ለኢንተርፕራይዙ ቋሚ ተቀጣሪ አይደሉም፤›› በማለት አስረድተዋል።

ምንም እንኳን ፕሬዚዳንቱ ይህን ቢሉም መምህራኖቹ በኢንተርፕራይዙ የሚሠሩት በትርፍ ጊዜያቸው ነው የሚለው መፈተሽ እንደሚኖርበት ዋና ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ገልጸዋል። እስካሁን ድረስ ለመምህራኖቹ 59,828,688 ብር መከፈሉንና ዩኒቨርሲቲው ግን በሦስት ዓመት ውስጥ ያተረፈው ትርፍ ሰባት ሚሊዮን ብቻ መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህ ሁኔታ የዩኒቨርሲቲዎችን ገቢ ማሳደግ እንደማይቻል ጠቁመዋል።

የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢንተርፕራይዙ የጣሳቸው የአሠራር ሥርዓቶች በቀላሉ ሊታለፉ የማይችሉ መሆናቸውን በመግለጽ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በትኩረት እንዲያየው ጠይቀዋል። የዩኒቨርስቲው አመራሮች ብልሹ አሠራሮችን በማረምና ተጠያቂነት በማስፈን ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት እንዳለባቸውም ሰብሳቢዋ አክለዋል፡፡

ዩኒቨርስቲው የድርጊት መርሐ ግብር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. እንዲሁም የማስተካከያ ዕርምት ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲያቀርብ የሺመቤት (ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች