Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት የሚያገኙበት መዋቅር ሊዘረጋ ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ግብርናን ብቻ ያማከለ ባንክ እንዲቋቋም ተጠይቋል

ግብርና ሚኒስቴር ከትንሽ እስከ ትልቅ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት በቀላሉ እንዲያገኙ ትላልቅ የፋይናንስ ተቋማት የተካተቱበት መዋቅር ሊዘረጋ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የፋይናንስ ተቋማት ለግብርና ዘርፉ እያደረጉ ያሉትን አስተዋጽኦ በተመለከተ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር ማክሰኞ ሚያዝያ 22 ቀን 2016 ዓ.ም. ውይይት ባደረገበት ወቅት ነው፡፡

በግብርና ሚኒስቴር አስፈጻሚነት ተግባራዊ በሚደረገው አዲሱ አሠራር ላይ ብሔራዊ ባንክ፣ ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የማይክሮ ፋይናንስና ንግድ ባንኮች የተካተቱበት መሆኑ ታውቋል፡፡

አርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት በቀላሉ አግኝተው የግብርና ዘርፉን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ ከፋይናንስ ተቋማቶች ጋር ውይይት ተደርጎ አዲስ አሠራር ለመዘርጋት ውሳኔ ላይ መደረሱን የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

የፋይናንስ ተቋማት ለማዳበሪያ ግዥ የብድር አቅርቦት የሚያቀርቡትን ያህል ለአርሶ አደሮች በቀጥታ ብድር እንዳልተመቻቸ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ አዲሱ አሠራር ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስረድተዋል፡፡

በቀጣይ የሚዘረጋው አዲሱ መዋቅር ተግባራዊ የሚሆነው ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ቀበሌ ድረስ ሲሆን፣ አሠራሩን በተመለከተ ከብሔራዊ ባንክ፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በድጋሚ ውይይት ተደርጎበት ወደ ሥራ የሚገባ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ተንቀሳቃሽ ንብረቱን አስይዞ ብድር እንዲያገኝ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ በአግባቡ ሊተገበር እንደሚገባ ጠቅሰው፣ በዝቅተኛ ደረጃ ለሚገኙ አርሶ አደሮች የሚሰጠው የብድር አቅርቦት በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር አስፈጻሚነት ተግባራዊ የሚደረገው አዲሱ መዋቅር መቼና እንዴት ተግባራዊ ይደረጋል የሚለው ለጊዜው እንደማይታወቅ የገለጹት ሚኒስትሩ፣ አሠራሩም ተግባራዊ ሲደረግ በርካታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል፡፡

አርሶ አደሮች ከባንኮች ከሚያገኙት ብድር ይልቅ ማይክሮ ፋይናንስ ከሆኑ ተቋማት የሚያገኙት ብድር የተሻለ እንደሆነ ገልጸው፣ ባንኮች ዘርፉን በመደገፍ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስታውቀዋል፡፡

በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮች ከባንኮች የብድር አቅርቦት ለማግኘት ቢፈልጉ እንኳን፣ የሚያሲዙት ዋስትና ወይ ተያዥ ነገር እንደሌላቸውና የባንኮች የኮላተራል መጠን ከፍ ስለሚል አርሶ አደሮች ብዙ ጊዜ ችግር ውስጥ እንደሚወድቁ የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ጌታቸው ድሪባ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሠረት በመንግሥት የሚደገፍ ግብርናን ያማከለ ባንክ ሊቋቋም እንደሚገባ የተናገሩት አማካሪው፣ በአሁኑ ወቅት ያሉ አብዛኛውን የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን የማይደግፉ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ባንኮችም ሆነ ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለአርሶ አደሮች ዝቅተኛ በሆነ የብድር መጠን አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎት እንደሌላቸው ገልጸው፣ ይኼም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አርሶ አደሮችን መጉዳቱን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ያሉ የማክሮ የፋይናንስ ተቋማት አሁን ባለው ሁኔታ የብድር አቅርቦት ለመስጠት እንደሚቸገሩና እነዚህም ተቋማቶች እስካሁን ከባንኮች የተሻለ ለአርሶ አደሮች የብድር አቅርቦት መስጠታቸው በራሱ የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡

ግብርናን እንደ አንድ ቢዝነስ በማየት ሚኒስቴሩ በራሱ የሚመራ አሠራርን ለመከተል አዲስ መዋቅር መዘርጋቱን ጠቅሰው፣ ይኼም አሠራር ላይ በርካታ የፋይናንስ ተቋማት መካተታቸው ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድገው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች