Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልየዘንባባ ሰንበት ወግ ከቀዳማዊ ምኒልክ ከተማ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ከተማ

የዘንባባ ሰንበት ወግ ከቀዳማዊ ምኒልክ ከተማ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ከተማ

ቀን:

ዛሬ (ዮም)፣ ክርስቲያኖች በተለይም ኦርቶዶክሳውያኑና ካቶሊካውያኑ በየአጥቢያቸው ተገኝተው የታደላቸውን የድል ምልክት የሆነውን ዘንባባ ይዘው የሚታዩበት፣ ከታላላቅ በዓሎቻቸው አንዱ የሆነውን የሆሳዕና በዓልን እያከበሩ የተገኙበት ነው፡፡ በዓሉ የዘንባባ ሰንበትም ይሰኛል፡፡

የዘንባባ ሰንበት ወግ ከቀዳማዊ ምኒልክ ከተማ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ከተማ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ልጆችና አዋቂዎች በበዓሉ መገለጫ ደምቀው

በዓሉን በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ክርስቲያኖች ሲያከብሩት መንስዔው እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በአህያ ውርንጫላ ላይ ሆኖ ሲገባ፣ ከሕፃን እስከ አዋቂ የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ‹‹ሆሳዕና የዳዊት ልጅ›› እያሉ የተቀበሉበትን የሚያስታውስ ነው፡፡

የቃሉ ምንጭ አራማይክ የሆነው ‹ሆሳዕና› መገኛ ትርጉሙ አድነን ማለት ነው፡፡ በዕብራይስጥም በግእዝም ተመሳሳይ ፍች አለው፡፡

- Advertisement -

የጎርጎርዮስ የዘመን ቀመር የሚከተሉ በዓሉን ባለፈው መጋቢት 15 ቀን 2016 ዓ.ም. ያከበሩት ሲሆን፤ ኢትዮጵያ በምትከተለው የራስዋ ቀመር (ኮፕቲክን ጨምሮ)፣ እንዲሁም የዩሊየስ የዘመን ቀመር የሚከተሉ የምሥራቅ ኦርቶዶክሶች እነ ሩሲያ ዛሬ ሚያዝያ 23 ቀን በማክበር ላይ ይገኛሉ፡፡

የዘንባባ ሰንበት ወግ ከቀዳማዊ ምኒልክ ከተማ ወደ ዳግማዊ ምኒልክ ከተማ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የዘንባባ ቀለበት

በቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት፣ ሆሳዕና እሑድ በሁለት ነገሮች ይታሰባል፡፡ ቀዳሚው በቅዳሴ ጊዜ ‹‹ያለ ሕማምና ያለ ደዌ፣ ያለ ድካምም ለከርሞም ያድርሰን ያድርሳችሁ›› እያሉ ካህናቱ ዘንባባ ሲያድሉበት፣ ሁለተኛው ካህናቱና ምዕመናኑ በቤተ ክርስቲያኑ ዙርያ የሚያደርጉት ዙረት ነው፡፡ ‹‹በታወቀችው በዓላችን መለከቱን ንፉ›› እያሉ የቅዱስ ያሬድ መዝሙር እየተዘመረ፣ በአራቱም ማዕዘኖች (ምሥራቅና ምዕራብ፣ ሰሜንና ደቡብ) ዕለቱን የሚጠቅሱ ከአራቱ ወንጌሎች (ማቴዎስና ማርቆስ ሉቃስና ዮሐንስ) እየተነበቡ ይከበራል፡፡

እንደ አስተምህሮው፣ ዕለቱ የሕማማት ሰሙን መክፈቻ ስለሆነና ሰሙነ ሕማማት (በተለይ እስከ ሐሙስ ያሉት) ከክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው 5500 ዓመት- ‹‹የዓመተ ፍዳ የዓመተ ኩነኔ›› መታሰቢያ በመሆኑ  ለሙታን የፍትሐት ጸሎት ስለማይፈጸምበት በሆሳዕና እሑድ፣ በሳምንቱ ውስጥ በሞት ለሚለዩት  አስቀድሞ ፍትሐት ይደረጋል፡፡

ከሆሳዕና በኋላ ከትንሣኤ በፊት ያሉት ቀኖች በተለይ በጾምና በስግደት የሚከበሩ ናቸው፡፡ በወይራ ቅጠል ጥብጠባ በማሳረጊያው ይደረጋል፡፡

በሆሳዕና በዓል ታላቅ ክብር የተሰጣት አህያ

በምሥራቁ ዓለም ትውፊት አህያ፣ የጦርነት እንስሳ ከሆነው ፈረስ በተለየ መልኩ የሰላም እንስሳ ሆና ትመሰላለች፡፡ ነገሥታቱም ሆኑ ሹማምንቱ በጦርነት ጊዜ የሚዘምቱት በፈረስ ላይ ተቀምጠው ነበር። ለዚህም ይመስላል በአማርኛው ብሂል ‹‹በፈረስ አንገት በጦር አንደበት›› የሚባለው፡፡

አህያ የሰላም ተምሳሌትነቷ አንዱ ማሳያ ንጉሥ በሰላም መምጣቱን ለማሳየት በአህያ ተቀምጦ መጓዙ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካሉት ትረካዎች አንዱ መሲሑ በአህያ ላይ እንደሚመጣ በዘካርያስ መነገሩ ነው፡፡ ይህ ትንቢት እግዚእ ኢየሱስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜ መፈጸሙም ተመልክቷል፡፡

የዘንባባ እሑድ – በወንጌል እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ኢየሩሳሌም በድል መግባቱን ያስታውሳል። ሕዝቡም የዘንባባ ዝንጣፊ እያውለበለቡ በመንገድ ላይ እያስቀመጡ ‹ሆሳዕና በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው› እያሉ ተቀብለውታል። 

ኢትዮጵያን የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት የሆሳዕና እሑድን በልዩ የአምልኮ ሥርዓቶች ያከብራሉ። ሰልፉ በዝማሬ የታጀበ ሲሆን አስደሳች ድባብ ይፈጥራል። የዘንባባ ቅርንጫፎች በኦርቶዶክስ ባህል ውስጥ  የድልና የዘላለም ሕይወት ምልክት መሆናቸው ተጠቅሷል።

 ከአክሱም የተቀዳ ጥበብ

ለኢትዮጵያ የክርስትና መሠረት፣ ለሁሉ ክርስቲያናዊ ትውፊት ምንጭ አክሱም ናት፡፡

በአክሱማውያን ወግ የዘንባባው እሑድ ማለትም ሆሳዕና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰቦችን የሚያገናኝ ባህላዊ ክስተት ጭምር ነው። ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ቅርሶች ዋነኛ አካል ነው። ምዕመናን ይህንን በዓል ለማክበር የሚጠብቁት በጾምና በጸሎት በመዘጋጀት ነው።

 በሰንበቱ ጠዋት ምዕመናን በመላው ኢትዮጵያም ሆነ በድዮስጶራ በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ይሰበሰባሉ። በካህናቱ የተባረከውን የዘንባባ ዝንጣፊዎች ይዘው በዑደታዊ  ሰልፍ ይሳተፋሉ። በምስጋና መዝሙርና የዘንባባ ዝንጣፊ በማውለብለብ የሚታጀበው ሰልፉ እግዚእ ኢየሱስ በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱን የሚያመለክት መሆኑን መምህራኑ ይናገራሉ፡፡

ሆሳዕና ባህላዊ ገጽታዎች የሚታዩበት ነው፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ምእመናኑ እየተገኙ የዘንባባ ዝንጣፊ ከመያዝ ባሻገር፣ ከአዋቂ እስከ ሕፃን በዘንባባው ቅጠል ለጣታቸው ቀለበት፣ ለእጃቸው እንደ አልቦ፣ ለራሳቸው እንደ አክሊል የሚጠለቅ አድርገው ያዘጋጃሉ፡፡ ምዕመናኑም የመስቀል ምልክት በመሥራት በቤታቸው ይሰቅሉታል፡፡

በሆሳዕና እሑድ ክርስቶስ ኢየሱስ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የገባበትን ሁነት በማስታወስ፣ በአንዳንድ ቤተክርስቲያኖች ተመሳሳይ ሥርዓት ይከናወናል፡፡ በኢትዮጵያ በመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን፣ በቀዳማዊ ምኒልክ ከተማ በአክሱም ጽዮን የበዓሉ አከባበር ለየት ያለ ነው፡፡ የአከባበሩ ትውፊት ለዳግማዊ ምኒልክ ከተማ ለአዲስ አበባም ተርፏል፡፡

በአዲስ አበባ ለመጀመሪያ ጊዜ ትርዒቱ የተካሄደው ከ118 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ‹የዘመን ታሪክ ትዝታዬ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት› በሚለው የትዝታ ድርሳናቸው እንደጻፉት፣ የሆሳዕና በዓል በአክሱም ሥርዓት ዓይነት ሆኖ እንጦጦ ላይ መከበር የተጀመረው በ1898 ዓ.ም. መጋቢት 30 በሆሳዕና ዕለት ነው፡፡

‹‹ከአክሱም የመጡ አንድ መምህር ከበዓሉ ቀን ቀደም ብለው ጀምረው የሥነ ሥርዓቱን አፈጻጸም ለደብሩ ካህናትና ለሕፃናት መዝሙር አስጠንተዋል፡፡ በበዓሉ ዕለት አንዲቱን የበቅሎ ግልገል በወርቅ ጥልፍ የተለጠፈ ባለመረሻት (የበቅሎ የማዕርግ ልብስ፣ በልዩ ልዩ ሐሮች ተጠልፎ የተዘጋጀ ወርቀ ዘቦ) ኮርቻ ተጭኖባት ድባብ ደብበውላትና አጅበዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን አመጡዋት፡፡ ዑደት ተደረገ፡፡

ከአክሱም የመጣው ያ የሆሳዕና በዓል ሥነ ሥርዓት ጃንሆይ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ መኳንንትም ሁሉ ባሉበት መከበሩ ተመዝግቧል፡፡

በኢትዮጵያ የሆሳዕና እሑድ ከሃይማኖታዊ አከባበር በተጨማሪ በተለያዩ ባህላዊ  ልማዶችና ወጎች ይከበራል። ቤተሰቦች ለልዩ ምግብ ይሰበሰባሉ፡፡ ልጆች ለበዓሉ ያማረ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ወቅቱ የደስታ ጊዜ ነውና፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...