Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊለከፋ የጤና ዕክል የሚዳርገው የፅንስ ኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተት

ለከፋ የጤና ዕክል የሚዳርገው የፅንስ ኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተት

ቀን:

በቅድመ ወሊድ ወቅት የሚከሰት የኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውኃ መቋጠር ሕፃናት ከተወለዱ በኋላ ለከፍተኛ የጤና እክል የሚያጋልጥ ነው፡፡ ፅንሱን ለዚህ ጉዳት የሚዳረገው ደግሞ የምግብ ንጥረ ነገሮች በተለይም የፎሊክ ኢሲድ እጥረት ነው፡፡

ለከፋ የጤና ዕክል የሚዳርገው የፅንስ ኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተት | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የበሽታው ተጠቂ ሕፃናት የመንቀሳቀስ እክል፣ የስሜት ማጣት፣ የአዕምሮ ውስንነት፣ ሽንትና ሰገራ የመቆጣጠር ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ ለተጓዳኝ በሽታም ተጋላጭ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ከኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተት ጋር እንደሚወለዱም ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

- Advertisement -

አቶ ይማም ካሳሁን፣ በኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተት በሽታ ተጠቂ የሆነችው የሕፃን ፈሪሃን አባት ናቸው፡፡ የሦስት ዓመቷ ፈሪሃን፣ ከተወለደች ጀምሮ ዓይኖቿን መጨፈን አትችልም፣ በጭንቅላቷ የተለያዩ ቦታዎችም ዕባጭ አላት፡፡  

አቶ ይማም እንደሚናገሩት፣ ሕፃን ፈሪሃን እንደተወለደች ለሕክምና ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ወስደዋታል፡፡ በሽታዋ ‹የጭንቅላት ውኃ መቋጠር› እንደሆነም ተነግሯቸዋል፡፡

የበለጠ ሕክምና እንድታገኝ ዘውዲቱ ሆስፒታል ሪፈር ተጽፎላቸው፣ በሆስፒታሉ ካቲተር ተደርጎላታል፡፡ ሽንቷና ከጭንቅላቷ የሚወጣው ፈሳሽም በዚሁ መንገድ እንዲወገድ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ሕፃን ፈሪሃን እጅና እግሯን ማዘዝ አትችልም፡፡ ዓይኖቿም ማየት አይችሉም፡፡ በተጨማሪም የሜኒንጃይት ችግር ያለባት መሆኑን አባቷ ይናገራሉ፡፡

የኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውኃ መቋጠር ሕመም ያለባቸውን ሕፃናት የሚያሳድጉ እናቶች ደግሞ ፈተናቸው የበዛ ነው፡፡

ወ/ሮ ሙሉ ጌታነህ፣ የሕፃን አቤል እናት ናቸው፡፡ የአራት ዓመት ልጃቸው የኅብረሰረሰር ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውኃ መቋጠር በሽታ ተጠቂ ነው፡፡

ቆሞ መራመድ ስለማይቻል በሆዱ ተኝቶ የሚሳበው ሕፃን አቤል፣ በተወለደ በወሩ የነርቭ ችግር አለበት ተብሎ በዘውዲቱ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ተደርጎለታል፡፡ 

እንደ ወ/ሮ ሙሉ፣ ሽንትና ሰገራውንም መቆጣጠር አይችልም፡፡ በዚህም የተነሳ በቀን ሦስት ዳይፐር እየተጠቀመ ይገኛል፡፡ የጭንቅላት ውኃ መቋጠር ችግር ያለበት በመሆኑም በዘውዲቱ ሆስፒታል በየጊዜው ክትትል በማድረግ ላይ ነው፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከነርቭ ዘንግ ክፍተትና ከጭንቅላት ውኃ መቋጠር ጋር የሚወለዱ ሕፃናት ክፍል አስተባባሪ ነቢያት ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ የነርቭ ዘንግ ክፍተት ወይም የኅብረሰረሰር በትክክል አለማደግ የሚከሰተው በመጀመርያዎቹ የእርግዝና ሳምንታት ውስጥ ነው፡፡

አንዲት እናት ካረገዘች ጀምሮ በ28 ቀናት ውስጥ የነርቭ ዘንጉ መዘጋት አለበት፡፡ የፎሊክ አሲድ እጥረት በሚኖርበት ጊዜ የነርቭ ዘንጉ መዘጋት ከሚኖርበት ቀን ያልፍና ክፍት እንደሆነ ይቀራል፡፡ ይህም ኅብረሰረሰራቸው (ስፓይናል ኮርድ) ክፍት የሆነና እባጭ ያላቸው ሕፃናት እንዲወለዱ ያደርጋል፡፡ ሕፃናቱ በነርቭ ችግር ምክንያት እግሮቻቸው የመስነፍ፣ ሽንትና ሰገራቸውን ያለመቆጣጠርና የጭንቅላት ውኃ የመቋጠር እክል ይገጥማቸዋል፡፡

እንደ ነቢያት (ዶ/ር)፣ እነዚህ ሕፃናት በተወለዱ በ72 ሰዓታት ውስጥ ቀዶ ሕክምና ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ የጤና ችግር ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ሕክምና የሚደረግላቸው የነርቭ ህዋሶቻቸው የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ሲቀር እባጩ በመፈንዳትና ባክቴሪያ በመፍጠር የጭንቅላት ኢንፌክሽን (ሜኒንጃይትስ) ያስከትላል፡፡

የጭንቅላት መጠን በፍጥነት መጨመር ወይም  (ኃይድሮፋለሲስ) በእርግዝና ወቅት ወይም ልጆች ከተወለዱ በኋላ በኢንፌክሽን ሊፈጠር ይችላል፡፡

ለዚህ የጤና እክል እንደ መንስዔ የሚቀመጡት የፎሊክ አሲድ እጥረት፣ ሲጋራና ሌሎች አደንዛዥ ዕፆች መጠቀም፣ ከመጠን ያለፈ ውፍረትና እናትየው የምትወስዳቸው መድኃኒቶች ፎሊክ አሲድን የሚፃረሩ ከሆኑ ለምሳሌ የሚጥል ሕመም መድኃኒት የምትጠቀም ከሆነ፣ በሽታው የመከሰት ዕድሉ የሰፋ ይሆናል፡፡

በመሆኑም እነዚህን የጤና ችግሮች ለመቅረፍ በቅድመ እርግዝናና በእርግዝና ወቅት ጥንቃቄ የማድረግና የመከላከል ሥራዎች መሠራት ይኖርባቸዋል፡፡

ነቢያት (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ለመውለድ የሚያስችል የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴቶች በፎሊክ አሲድ የበለፀጉ ምግቦችን በመመገብ በፅንስ ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጤና እክል ለመከላከል ይችላሉ፡፡

አንዲት ለማርገዝ ያሰበች እናት እርግዝና ከመከሰቱ ከሁለትና ከሦስት ወራት አስቀድማ እንዲሁም ከእርግዝና ቀን ጀምሮ ለሦስት ወራት የፎሊክ አሲድ እንክብሎችን መውሰድ ይኖርባታል፡፡

የተሰባጠሩ ምግቦችን በመመገብ እንደ ነርቭ ዘንግ ክፍተትና የጭንቅላት ውኃ መቋጠር ያሉ በቅድመ ወሊድ ወቅት ሊከሰቱ የሚችሉና ለሕይወት አሥጊ የሆኑ የጤና እክሎችን ለመከላከልም ያስችላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...