Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከ400 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው  ባለቅርሱ ገዳም ካጋጠመው ችግር ለመወጣት የታደጉኝ ጥሪ አቀረበ

ከ400 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው  ባለቅርሱ ገዳም ካጋጠመው ችግር ለመወጣት የታደጉኝ ጥሪ አቀረበ

ቀን:

በሰሜን ጎጃም ሀገረ ስብከት ባህር ዳር ዙሪያ የሚገኘው የገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም፣ በተለያዩ ዘመናት የተወረሩበትን ይዞታዎች ለማስመለስ እየጣረ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡ ገዳሙ ‹‹የአባቶቼን ርስት አልሰጥም›› በሚል መሪ ቃል ሚያዝያ 15 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የአንድነት ገዳሙ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ዋና ሰብሳቢ ቀሲስ እንግዳ ወርቅ እንደተናገሩት፣ ገዳሙ በቀደመው ዘመን በደረሰበት መከራ የተነሳ ተዳክሞ በመቆየቱ የገዳሙ ይዞታ በአካባቢው አርሶ አደሮችና በሌሎች ጥቃቅን ነጋዴዎች እጅ ከገባ ዘመን ተቆጥሯል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድነት ገዳሙ ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን ተከትሎ በርካታ አባቶችና  እናቶች መነኮሳት ወደ ገዳሙ በመግባት በመልሶ ማቋቋም ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን የገዳሙ ይዞታ ለረዥም ዘመናት በሌሎች ግለሰቦች እጅ ተይዞ በመቆየቱ ምክንያት ለገዳሙ ልማትና ለመነኮሳቱ መጠለያ የሚሆን ቤት ለመሥራት አልተቻለም፡፡ እንደ ቀሲስ እንግዳወርቅ፣ አንድነት ገዳሙ የቦታውን ጥበት አስመልክቶ መፍትሔ እንዲሰጠው ለአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሲያቀርብ የነበረው ተደጋጋሚ ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል፡፡

የክልሉ ካቢኔም በገዳሙ ዙሪያ ሰፍረው የሚገኙት አርሶ አደሮች በሙሉ የቦታውንና የቤታቸውን ግምት ካሳ እየተከፈላቸው ቦታውን ለቀው ለገዳሙ እንዲያስረክቡ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

- Advertisement -

የአንድነት ገዳሙ በዚህ ውሳኔ የተደሰተ ቢሆንም፣ ከቦታው ለሚነሱት አርሶ አደሮች የካሳ ምትክ ግምት እንዲከፍል መወሰኑና ለዚህም ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ በማስፈለጉ ችግሩን ከአቅም በላይ አድርጎታል፡፡

በመሆኑም በገዳሙ ዙሪያ ተጠግተው ቤት መሥርተው እየኖሩ የሚገኙ ምዕመናንን ካሳ በመክፈል ለማስነሳትና ገዳሙን በቋሚነት ለማልማት የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ሚያዝያ 19 ቀን 2016 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስ የጅግጅጋና የሶማሌ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ   በበኩላቸው፣ ጥንታዊው ገዳም በእምነቱና በፀበሉ ብዙ  ተዓምራት የሚገለጡበትና በርካታ ሕሙማን እየተፈወሱ ይገኙበታል፡፡

ገዳሙ በተለያዩ ጊዜያት ለልዩ ልዩ ሕመሞች ፈውስ ፍለጋ የሚመጡ ምዕመናን ከበሽታቸው ከተፈወሱ በኋላ ‹‹የአቡነ ሐራን ደጅ አንርቅም፣ ከአፈራቸውም ተለይተን አንሄድም›› በማለት ሰፍረው የቆዩ ናቸው፡፡ በሰፈሩበት ቦታም ትዳር እየመሠረቱና እየተዋለዱ የገዳሙን ይዞታ ተሻምተዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ጊዜ ግን ገዳማውያኑ ተሰሚነት አጥተው እንጂ ርስቱን ለማስመለስ ዝም ያሉበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡
እንደ  ሊቀጳጳሱ፣ የአንድነት ገዳሙ የካሳ ግምት ተከፍሎ የገዳሙ ችግር በዘላቂነት እንዲቀረፍ፣ ገዳምያኑ በጸሎት ይተጉ ዘንድ ርስታቸውን መመለስ ይኖርበታል፡፡ ይህንንም ለማስቻል በመላው ዓለም የሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች፣ በጎ አድራጊ ግለሰቦችና ድርጀቶች በገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ በመሳተፍ እጃቸውን እንዲዘረጉ ሊቀ ጳጳሱ  ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የገዳመ ወንያት አቡነ ሐራ ድንግል አንድነት ገዳም በ1574 ዓ.ም. በፃድቁ በአቡነ ሐራ ድንግል መመሥረቱን የተናገሩት የገዳሙ አፈ መምህር አባ ገብረ ሥላሴ ናቸው፡፡
ገዳሙ ከባህር ዳር ከተማ ሰሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 17 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሰሜን ጎጃም ዞን ባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ‹‹ላጉና›› ቀበሌ አስተዳደር ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በገዳሙ ከ251 በላይ መናኒያንና ከ300 በላይ የአብነት ተማሪዎች የሚገኙበት ሲሆን፣ በተጨማሪም ከ30 ሺሕ እስከ 50 ሺሕ የሚደርሱ ፀበልተኞችን ተቀብሎ እያስተናገደ እንደሚገኝ አባ ገብረ ሥላሴ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ