Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊበቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፋሮ ፋውንዴሽን ቱሩፋቶች

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የፋሮ ፋውንዴሽን ቱሩፋቶች

ቀን:

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤናና በንፁህ መጠጥ ውኃ እየሠራ የሚገኘው ፋሮ ፋውንዴሽን ግብረ ሰናይ ድርጅት፣ ሚያዝያ 15 ቀን 2017 ዓ.ም. በኡንዱሉ ወረዳ ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ በፀሐይ ኃይል የሚሠሩ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ሲያስመርቅ፣ በአሶሳ ከተማ ደግሞ በ122 ሚሊዮን ብር ለሚያስገነባው ትምህርት ቤት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡

የፋሮ ፋውንዴሽን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ በጋሻው ተሾመ እንደተናገሩት፣ በክልሉ ኡንዱሉ ወረዳ፣ ሸጋ ደማዚን፣ አልሃመር ቀበሌዎችና ኡንዱሉ ከተማ የሚገኙና ከ15 ሺ በላይ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የውኃ ተቋማት ተገንብተዋል፡፡

በጸሐይ ኃይል እንዲሠሩ ተደርገው የተገነቡት የውኃ ተቋማት የአካባቢውን ኅብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር የሚቀርፉና በሰከንድ አራት ሊትር የማመንጨት አቅም ያላቸው ሲሆን፣ ለግንባታው ከ56 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንና ለቀጣዮቹ 20 ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጡ ታሳቢ ተደርገው የተገነቡ ናቸው፡፡

- Advertisement -

ከንፁህ መጠጥ ውኃ ግንባታ በተጨማሪም ለወረዳው አርሶ አደሮች ከሰባት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የግብዓት ማከማቻ መጋዘን መገንባቱንም ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ በጋሻው፣ በክልሉ በትምህርት ዘርፍ ያለውን ችግር ለማቃለል በተለይም የሴቶችን የትምህርት ተሳትፎ ለማሳደግ ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል፡፡ በአሰሶ ከተማ ከአንደኛ እስከ አሥረኛ ክፍል ትምህርት ቤት በመክፈትና በሆሞሻ ወረዳ ከዘጠነኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት በመገንባት ተማሪዎችን በዕውቀት በማነፅ ለውጤት እንዲበቁ በማድረግ በኩል ከፍ ያለ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ ነው፡፡

በአሶሳ ከተማ እየሰጠ የሚገኘውን የትምህርት አገልግሎት ለማስፋትና ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ ለማድረግ ከቅድመ አንደኛ እስከ 12ኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ለመገንባትም የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡

በ122 ሚሊዮን ብር የሚገነባውና በ17 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንደሚበቃ የሚጠበቀው ትምህርት ቤት፣ ከአንድ ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማስተማር እንደሚችልም አቶ በጋሻው ተናግረዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውኃና ኢነርጂ ሀብት ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጀርሞሳ ተገኝ እንደተናገሩት፣ ፋውንዴሽኑ ላለፉት ዓመታት በክልሉ በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በንፁህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ሥራዎች ላይ እየተሳተፈ ይገኛል፡፡

ክልሉ የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር በስፋት የሚስተዋልበት ነው፡፡ ይህንን ሥር የሰደደ ችግር ለመቅረፍ ድርጅቱ በኡንዱሉ ወረዳ ሥር በሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች በ56 ሚሊዮን ብር በጸሐይ ኃይል የሚሠሩና የማኅበረሰቡን የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር የሚቀርፉ የውኃ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡

ለመጪዎቹ ሃያ ዓመታት ለማኅበረሰቡ እንዲያገለግሉ ታቅደው የተሠሩትን እነኚህን የውኃ ተቋማት፣ ኅብረተሰቡ በተገቢው መልኩ ተንከባክቦ በመያዝ በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ዳይሬክተሩ አክለው ተናግረዋል፡፡

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ትምህርት ቢሮ፣ የትምህርት ፕሮግራም ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ በሽር አብዱራሂም በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የክልሉን የትምህርት ተሳትፎ ከማሳደግና የትምህርት መሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አንፃር ከመንግሥት ጋር በቅንጅት እየሠራ ነው፡፡

ድርጅቱ በክልሉ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ፣ በትምህርቱ ዘርፍ ጥራት ያለው ትምህርት በማቅረብ፣ ልጆችን ከታችኛው እርከን አንስቶ ችሎታቸውንና ተሰጥኦቸውን ተጠቅመው ለትልቅ ደረጃ እንዲበቁ በማድረግ ረገድ የጎላ ሚና ተጫውቷል፡፡

በሆሞሻ ወረዳ በከፈተው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የሚያስተምራቸውና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የወሰዱ ሴት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ የዩኒቨርሲቲ ማለፊያ ውጤት አስመዝግበዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ድርጅቱ ሊገነባው ያቀደው ትምህርት ቤትም ጥራት ያለውን ትምህርት ተደራሽ በማድረግ ብቁና ተወዳዳሪ ተማሪዎችን በማፍራት በኩል ከፍ ያለ አበርክቶ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚታመን አቶ በሽር ተናግረዋል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...