Saturday, May 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሸዋሊድ አከባበር ጥንካሬዎች እንከኖችና መደረግ ያለበት

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች የበይነ መንግሥታዊው ኮሚቴ  ኅዳር 25 ቀን 2016 በቦትስዋና ባካሄደው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የሐረሪዎች ሸዋሊድ በዓልን ከማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች አንዱ ሆኖ እንዲመዘገብ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

ሸዋሊድ በሐረር ሙስሊም ማኅበረሰቦች መካከል ጥልቅ የሆነ የአንድነት፣ የደስታና የመንፈስ መነቃቃት ስሜትን ይፈጥራል። ይህ በዓል ከጂኦግራፊያዊ፣ ከቋንቋና ከባህላዊ ድንበሮች በላይ የሆነ፣ ጥልቅ የሆነ የባለቤትነት ስሜትና አብሮነትን ያጎለብታል።

ሸዋሊድ በሐረር ውስጥ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ከኢማም አህመድ ድል ጋር ተያይዞ የሚከበር በመሆኑም ጥንታዊ፣ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ባህሪያት እንዳሉት ይፈነጥቃል፡፡ 

የሸዋሊድ ፋይዳ ከመንፈሳዊው ዓለም በላይ የሚዘልቅ ሲሆን በበዓላቱ ወቅት የሸማቾች ወጪን በመጨመር፣ የእንግዳ ተቀባይነት አገልግሎትና በበጎ አድራጎት ልገሳ ጉልህ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎችን ይፈጥራል። በተጨማሪም፣ ሃይማኖታዊ ማንነትንና እሴቶችን ለማጠናከር፣ ማኅበረሰቦችን በጋራ ባህሎች ውስጥ አንድ ላይ የሚያስተሳስር ነው።

ስለዚህ ጉዳይ የሐረሪ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙሒዲን አህመድ እንደሚሉትም ሸዋሊድ የድል የሐረሪዎች የባህል በዓል ነው። ኢማም አህመድ ኢብራሂም የሽምብራ ኩሬን በረጀብ ወር ድል አድርገው በሸዋል ወር ደግሞ ድላቸውን ያከበሩበት ነው። ሕዝብ መረዳት ያለበት ይህ ነው። በዓሉም ወጣቶች  “አራ በልአራ” ብለው ይፎክራሉ። ከጀግንነት ጋር የተያያዘ ነው።

ከአቶ ሙሒዲን አህመድ ጋር በተደረገው ውይይት ሸዋሊድ እስካሁን የሐረሪዎች ሆኖ የኖረ ቢሆንም የኢማም አህመድ ድል ስለሆነ አገራዊ ብቻ ሳይሆን በይነ ብሔራዊ ጭምር  መሆን ያለበት ነው። በተለይ የኢማም አህመድ ድል ዕውን እንዲሆን ለታገሉና የእሳቸው አሻራ ለሚገኝባቸው (ኢትዮጵያ፣ ሶማሊያ፣ ጂቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ምሥራቅ ሱዳን) ሁሉ የኡማ በዓል ሆኖ መታየት ያለበት ነው። የመሰባሰቢያ ጃንጥላ ሊሆን ይገባል።

የዘንድሮው አከባበር እንዴት አለፈ?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሸዋሊድ አከባበርን ቢያንስ ላለፉት 33 ዓመታት ተከታትሏል፡፡ አዲስ አበባና ሐረር በሚከበሩት በዓላትም ለበርካታ ጊዜ እየተጋበዘ ተገኝቶ የበዓሉ ተካፋይ ሆኗል፡፡ ከሐረር ሌላ ባደገበት አካባቢ የሸዋል ፆም ስድስት ቀናት ከተፆመ በኋላ እንደፍች ቀን የሌለው ዶሮ፣ ያለው በግና ፍየል እየታረደ፣ የአብሽ መጠጥና ብርዝ እየተዘጋጀ፣ ጎረቤትና የቅርብ ዘመድ የሚጠራራበት ቡና እየተፈላ እየተጠጣ ይውል እንደነበር ያስታውሳል፡፡ በጎንደርም፣ በወሎም፣ በትግራይም፣ ተመሳሳይ የሆነ ልምድ እንደነበር ያውቃል፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በጉራጌና በስልጤ ከቤተሰቦቿ ርቃ ከባሏ ጋር የምትኖር ሴት ዳቦ ደፍታ ወላጆቿን ረጅምም ሆነ አጭር መንገድ ተጉዛ እንደምትጠይቅበትና ደስ ብሏት እንደምታሳልፍበት ተረድቷል፡፡ ለዛሬው ዓመት የደረሰው የሐረር ሸዋሊድ በዓል ዘንድሮ እንዴት ተከበረ? ምን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ነበሩት? ወደፊትስ ምን መከተል ያለበት አቅጣጫ ምንድነው?›› የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ያደርጋል፡፡ ይህ ግምገማዊ አስተያየት የጸሐፊው ብቻ መሆኑንም ለመግለጽ ይወዳል፡፡

 ሐረርን የማስዋብ ሕዝባዊ ዘመቻ

ሐረር ሸዋሊድን ለማክበር በምትዘጋጅበት ዋዜማ ከታዩት እንቅስቃሴዎች አንዱ ሐረርን የማስዋብ ኅብረተሰብ አቀፍ እንቅስቃሴ ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሐረር በሚገኝ ሕዝብና በአስተዳደሩ ወጭ የሚገፋ ባይመስልም የእዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እንዳየውና እንደተከታተው ሐረርን ገብተው በቀላሉ የማይወጡባት ከተማ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።  በእርግጥም ‹‹ረመዳን በመጣ ቁጥር ከለበጣ መኳኳልና የግብር ይውጣ ፅዳት ወደ መሠረታዊ ውበት ለማሸጋገር የተደረገው ጥረት ጥልቀት እያገኘ በመሄድ ላይ ያለ ይገኛል ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል። ጥረቱ ከቀጠለ በዓለም ውስጥ ከሚገኙት እንደ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ፣ አልጀሪያ፣ ሊቢያ፣ ሞሪታኒያ ጥንታዊ ከተሞች ጋር የተቀራረበ ውበት ይኖራታል የሚል ግምት ያሳድራል። እንዲያ ከሆነ፣ ይህ ትውልድ ‹‹ለሐረር መለወጥና የቱሪዝም ማዕከል መሆን መስዋዕትነት የከፈለ›› ተብሎ ስሙ እየተነሳ የሚኖር የታደለ ትውልድ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

ስለበዓሉ የባህል ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ መግለጫ

የ2016 ዓ.ም. ሸዋሊድ ለማድረግ የተደረገው ዝግጅት ምን እንደሚመስል ለማወቅ የባህል ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ ወደ አቶ ተወለዳ ዓብዶሽ ቢሮ ሄደን ነበር፡፡ መነሻቸው ‹‹ሐረር ውብ የቱሪስቶች መናኸሪያ እናደርጋለን›› የሚል ሲሆን፣ በዚህ ዝግጅት ከፕሬዚዳንቱ አቶ ኦርዲን በድሪና ከሐረሪ አፈ ጉባዔ አቶ ሙሒዲን ጀምሮ ሌሎች ቢሮዎችም ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው፣ ከዚህም በተጨማሪ የወረዳ አመራር፣ ወጣቶች፣ የሴቶች አፎቻዎች፣ ሽማግሌዎች፣ የንግዱ ኅብረተሰብ አባላት ለበዓሉ መሳካት የተጫወቱት ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ካለፉት ሦስት ዓመታት ከተገኘው ልምድ በመነሳት የተሻለ ዝግጅት፣ ደግሞም ቀልጣፋ እንዲሆን ታስቦ ዝግጅት መደረጉን ጠቅሰው፣ የጎዳና ትርዒት፣ የሙዚየሞችና የጥንታዊ ተጨባጭ ቅርሶች ጉብኝት እንደሚኖርበት አስረድተውናል። 

የበዓሉ አከባበር ጠንካራ ጎኖች 

በዓሉ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የተደረገ ሲሆን የመጀመሪያው እንቅስቃሴ የተጀመረው የፖሊስ የማርሽ ጓድ በከተማው ዋና ዋና መንገዶች እየተዘዋወረ ያሰማው የማርሽ ባንድ ሙዚቃ ነው፡፡ ሐረር የፖሊስ የማርሽ ባንድ ቀደም ሲል ከመሠረቱት አንዷ ስትሆን፣ በበዓሉ ዋዜማ የተደረገው እንቅስቃሴ የብሥራት ደወል በመሆን ልዩ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በሁለተኛው ቀን የጥንታዊ ጦር ልብስ የለበሱ ወጣቶች፣ የባህል ልብስ የለበሱ ልጃገረዶች፣ ከአው አው አቅበራና ከሹሉም አህመድ ተነስተው በሐረር አንደኛ መንገድ በመጓዝና በሐረሪ ጉባዔ በመሰባሰብ ሠልፉን ቅርፅ ካስያዙ በኋላ በሸንኮር ወረዳ አድርገው ከሦስት ኪሎ ሜትር ያላነሰ በመጓዝ ወደ ክልሉ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አደባባይ እጅግ ውብ በሆነ ሠልፍ አልፈዋል፡፡ በዚህ ዕለት በአደባባዩ ዙሪያ በነበሩ ድንኳኖች ልዩ ልዩ የባህል ዕቃዎች ለትርዕይትና ለሽያጭ የቀረቡ ሲሆን ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ጎብኝተዋቸዋል፡፡

የሐረሪ ባህላዊ ሙዚቃና ኖታ ዙሪያ የተጠና መጽሐፍ ምረቃ

በሐረሪ ባህላዊ የሙዚቃ ቅኝት ዙሪያ ተጠንቶ የተዘጋጀ መጽሐፍ በሁለተኛው የበዓል ቀን የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ተመርቋል፡፡ የሐረሪ ባህላዊ ሙዚቃ ኖታ ላይ ያተኮረው መጽሐፍም የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ከክልሉ ባህል ቅርስና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው። በዚህ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የተገኙት የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙሒየዲን አህመድ ሐረር በሙዚቃ ብቻ ሳይሆን የበርካታ የጥበብ ባለሙያዎች መፍለቂያ ጭምር መሆኗና የሐረሪ ባህላዊ ሙዚቃ ከዚህ ቀደም በሚፈለገው ደረጃ ማስተዋወቅ እንዳልተቻለ ጠቁመው፣ ከዚህ አንፃር የተዘጋጀው መጽሐፍ ይህን ችግር ሊቀርፍ የሚችልና ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት ለሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙሒየዲን አህመድ አስረክበዋል። የሐረሪ ብሔረሰብ ተዝቆ የማያልቅ ቱባ የሥልተ ምት እንዲሁም ማኅበራዊ ክንዋኔ ባለቤት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ መጽሐፉም ይህንን ሀብት በማጥናት ማስተዋወቅና መሰነድ ዓላማ ያደረገ ነው ተብሏል። አቶ ሠርፀ ፍሬስብሐት በበኩላቸው ሐረር የሁሉም ባህሎች መከወኛ መሆኗን ኅብራዊነት ባላቸው የጥበብ ሥራዎቿ ማረጋገጥ መቻላቸውን ገልጸዋል።

የሸዋሊድ የመጀመሪያ ምሽት ድባብ

በሸዋል ዒድ ሁለተኛ ቀን ምሽት በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣት ሴቶችና ወንዶች የሐረር አንደኛ መንገድን ሞልተው እየተመሙ ታይተዋል፡፡ አልፎ አልፎ የድሮ ትዝታው የተቀሰቀሰባቸው አዛውንቶችም በብዛት ይታያሉ። ‹‹ያኔ በልጅነታችን ተኳኩለን፣ እየሳቅንና እየተጎናተልን ስንሄድ ያምርብን ነበር። ብዙ ወጣት ወንዶች እኛን ለማነጋገር ሲፈልግ፣ እኛም እንዳላየን ስናልፍ እርስ በርስ እንጎሻሸም ነበር፤›› የሚሉ ይመስላሉ።  የምሽቱ ዝግጅት በዜማና በጭፈራ የተሞላ ስለነበር በጥቅሉ እጅግ ውብ ነበር ብሎ ማጠቃለል ይቻላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአው ሹሉም አህመድና በፈላና በር በድቢ የታጀበ የዚክር ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን በዚህ ዝግጅት በርካታ የሐረር ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

በበዓሉ ከቀረቡት ዝግጅቶች አንዱ የሙዚየሞች ጉብኝት ነው፡፡ በሐረር ውስጥ ከሚገኙት ሙዚየሞች ዋና ዋናዎቹ ተጎብኝተዋል፡፡ ሐረር የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የግል ሙዚየም ያላት ከተማ ስትሆን፣ እነዚህም ሙዚየሞች ከአምስት ያላነሱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም ተጨማሪ በጥንታዊ ቤቶች ውስጥ አነስተኛ ሙዚየም አከል የቅርስ ስብስብ ይገኛል፡፡

የኮረሚ ጉብኝት

ኮረሚ ከጥንት የአርጎባዎች መንደሮች አንዱ ሲሆን ኮረሚ ከሐረር በስተ ደቡብ  አው ሐኪም ተብሎ በሚጠራው ተራራ በስተምሥራቅ፣ ከሐረር አሥር ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ይገኛል። ኮረሚ ጥንታዊ ምሽጎችና የነገሥታት መስጊዶች የሚገኙባት አካባቢ ስትሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ በ1520ዎቹ የነበሩት የአሚር ዑመረዲን መስጊድና ሌሎችም ጥንታዊ መስጊዶች ይገኙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እንደ አውሶፊ ያሉ ምሽጎች (ዛሬም በከፊል ወይም በተሟላ መልኩ የሚገኝ)፣ የየእመኾዳ መቃምና የፈራረሱ ጥንታዊ የምሽግ አካላት ይገኛሉ፡፡ ኮረሚ የሚገኘው ሕዝብ የአርጎባ ሕዝብ ሲሆን ይህም ሕዝብ በእርሻ፣ በዕደ ጥበብ፣ በሥነ ሕንፃ ሥራ ይታወቃል፡፡

በበዓሉ የታዩ እንከኖች

የዘንድሮን ሸዋሊድ ለማክበር ለአንድ ዓመት ያህል ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ በተደረገው ጥረትም ባለፉት መቶ ዓመታት ያልታየ ለውጥ ታይቷል፡፡ ይህም በእጅጉ የሚያስመሰግንና ይህን ለውጥ ያመጡትን ሁሉ በታሪክ ሲታወሱ እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው፡፡ ይህም ሆኖ በዓሉ የበለጠ ማራኪና የአገር ውስጥና የውጭ አገር ቱሪስቶችን ለመሳብና በዚህም ሰበብ ከፍተኛ የሆነ የውጭ አገር ምንዛሪ ለማግኘት ይቻል ዘንድ ተጠናክረው መቀጠል ያለባቸው ሥራዎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ ጸሐፊው ጥቂቱን እንደሚከተለው ለማቅረብ ይወዳል፡፡

በዓሉን የሐረርና የአካባቢው ሕዝብ እንዲሳተፍበት ማድረግ

እንደ ሸዋሊድ ያለ በዓል ሊደምቅ የሚችለው ሕዝብ የሚዘጋጀው በዓል የራሱና ለራሱ ጥቅም እንደሆነ ማሳወቅ፣ አሳውቆም ወደ አደባባይ እንዲመጣ በማድረግ በዓሉን እንዲያደንቅ፣ በዓሉን ለማየት ለሚመጡ እንግዶች የሚሸጡ ዕቃዎችን (ቁሳቁስ፣ አልባሳት፣ ምግቦች፣ ፍራፍሬዎች፣ ጌጣ ጌጦች) ይዘው እንዲመጡ መቀስቀስ፡፡ የዚህ በዓል አስተላላፊ ድልድዮች ሕፃናት ስለሆኑ ለእነሱ የሚሆኑ ነገሮችን በነፃና በቀላል ዋጋ የሚሸጡ ነገሮች ማቅረብ፣ ወላጆችም ልጆቻቸውን ወደ በዓሉ እንዲመጡ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ የሚኖሩ ሐረሪዎችና ቶሮንቶ ውስጥ ዓለም አቀፍ የሐረሪ ተወላጆች የባህልና የስፖርት ውድድርን ጥሩ ዝግጅት እንደነበራቸው መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

የምሽት ዝግጅቶችን ለዓይን እስኪይዝ አለማቆየት፣ የግንኙነት ገደብም ማበጀት

ምንም እንኳን ወጣት ወንዶችና ሴቶች እንዲተያዩና እንዲተጫጩ ማድረግ የበዓሉ አካል ቢሆንም የጊዜ ገደብ ማበጀትና ወጣት ሴቶች ለብቻ፣ ወጣት ወንዶች ደግሞ ለብቻ የሚጨፍሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ በሴቶች ጭፈራ ወንዶች ዘለው እንዳይገቡ መከልከል፣ ሴቶችም ወደ ወንዶች ጭፈራ እንዳይገቡ ማድረግ፣ በዚያ ዕለት ወጣት ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ከማንኛውም ሱስ የሚያስይዝ ወይም አዕምሮን የሚለውጥ ነገር እንዳይጠቀሙ መምከር ወዘተ. ያስፈልጋል፡፡

 የመፀዳጃ አገልግሎት

ምንም እንኳን በዚህ በዓል በስፋት ታይቷል ማለት ባይቻልም አልፎ አልፎ እጅግ የተዋቡትን የሐረር መንገዶችንና ግንቦችን በአዩኝ አላዩኝም የሚያቆሽሹ ሰዎች እንዳሉ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ተመልክቷል፡፡ ይህ ችግር የበዓሉ ተሳታፊ ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን ሊያድግ ይችላል፡፡ ስለዚህ ከወዲሁ መላ ሊበጅለት የሚገባ ሲሆን ኅብረተሰቡ ራሱም ወደ ነበረበት ችግር ተመልሶ እንዳይገባ አካባቢውን ተግቶ መጠበቅና የመፍትሔው አካል መሆን ይገባዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለፍሳሽ ቆሻሻ አገልግሎት ይውል ዘንድ ፈፋፊ ቢፒሲ ከአጥሮች ጋር በማጣበቅና የሽንት መቀበያ ማዘጋጀት ይቻል እንደሆነ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአማካይ ሥፍራዎች አራትና አምስት የመፀዳጃ ሥፍራዎች መሥራት ይቻል እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡    

የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች እንዲመጡ ግፊት ማድረግ

የዚህ በዓል አንዱ ዓላማ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኝዎች እንዲመጡና የኢኮኖሚ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጎብኝ እንዲመጡ ደግሞ በልዩ ልዩ መገናኛ ብዙኃን ዘዴዎች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በደብዳቤ፣ በበራሪ ወረቀቶች (ብሮሸሮች) በኢንባሲዎች ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ የባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮው የተጠናከረ የሕዝብ ግንኙነት ማዋቀር ይጠበቅበታል፡፡

 አቅጣጫ መጠቆሚያዎች

ሐረር እስከ አንድ ሺሕ ዓመት ያስቆጠሩ ታሪካዊ ሥፍራዎች ቢኖሯትም እነዚህን ቦታዎች ማወቅ የሚቻለው በመሪዎች (ጋይዶች) አማካይነት ነው፡፡ እርግጥ ነው በመሪዎች አገልግሎት ማግኘት በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ነው፡፡ ሆኖም በሁነኛ ቦታዎች የአቅጣጫ መጠቆሚያዎች ቢኖሩ በጣም ጠቃሚ ነው ብሎ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡

የዘንድሮው የሸዋሊድ በዓል አከባበር ካለፉት ሦስት ዓመታት በእጅጉ የተሻለ እንደነበረ አያጠያይቅም፡፡ እንዲያም ሆኖ ጠንካራ ጎኖቹን የበለጠ በማጠናከር የታዩ ውስንነቶችን በመፍታት፣ በሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ለሚካሄደው ዓለም አቀፍ የሐረሪዎች የስፖርትና የባህል ፌስቲቫል ከአሁኑ መዘጋጀት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለው፡፡

የሸዋሊድ በዓል ከማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል እንደ አንዱ ተቆጥሮ በዩኔስኮ መመዝገቡ ባህላዊ ፋይዳ ብቻ ሳይሆን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፋይዳው የላቀ እንደሆነ ባለሙያዎች ያምናሉ። ሸዋሊድ በዓል ወጣቱ ትውልድ ባህሉንና ባህላዊ እሴቶችን በመጠበቅ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ያስችለዋል። ይህ ስኬት የባህል ወጎችን የመጠበቅና የማክበርን አስፈላጊነት ያጎላል። ሐረር ባላት የባህል ቅርስ ምክንያት የሃላል ቱሪዝም ማዕከል ሆና እንድትገኝና የሃላል አማራጮች ለሚፈልጉ መንገደኞች ምቹ መዳረሻ ያደርጋታል።  በተጨማሪም የሐረርን ዕድገት ቀጣይነት ያለውና ነዋሪም ሆነ ጎብኝዎችን ያሳተፈ ሆኖ እንዲቀጥል ልዩ ባህላዊ ማንነቱን ጠብቆ ልማትን ማፋጠን ቁልፍ ሥራ ይሆናል። የማኅበረሰቡ ቅን አስተያየት የሐረርን የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚወስን ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ለተጨማሪ ድሎች በርትቶ መሥራትን ይጠይቃል። 

ከአዘጋጁ ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው bktesheat@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles