Saturday, May 18, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

አፈር አልሚ ኬሚካዊ ውህዶችን ከመግዛት የሚታደገው የኢትዮጵያ ኖራና ጥቅማ ጥቅሞቹ  በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤምሪተሰ) እና በባለሟል አጥናፉ (ዶ/ር)

መግቢያ

በአገር ቤት ቋንቋ ሳይንሳዊ ጽሑፍ ማበርከት፣ የሳይንስ ዘዴዎችንና ሳይንሳዊ ዕውቀትን ለብዙ የማኅበረሰቡ አባላት ማድረስ ይቻላል፡፡ በተጨማሪ የማኅበረሰቡን ሳይንሳዊ አስተሳሰብን፣ ብሎም ምክንያታዊነትን ያዳብራል የሚል እምነት አለን፡፡ ዕውቀትን በአገር ቤት ቋንቋ መገብየት፣ ግንዛቤውን ቀለል ተደራሽነቱን ሰፋ ያደርገዋል፡፡ የዚህች ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሳይንሳዊ አስተሳሰብን ማኸዘብ ብሎም ሳይንሳዊ ዕውቀትን በማኅበረሰቡ አባላት ውስጥ በውስን ደረጃም ቢሆን ማስረፅ ነው፡፡

አፈር አልሚ ኬሚካዊ ውህዶችን ከመግዛት የሚታደገው የኢትዮጵያ ኖራና ጥቅማ ጥቅሞቹ  በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤምሪተሰ) እና በባለሟል አጥናፉ (ዶ/ር) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

የድንጋይ ዓይነቶች አመሠራረት

 በዓለማችን ከአንድ መቶ በላይ አቶሞች (Atoms) ይገኛሉ፣ ከእነኝህም ውስጥ 92 ገደማ በተፈጥሮ የሚገኙ ሲሆን፣ ሌሎቹ በላቦራቶሪ ወስጥ የተዘጋጁ ናቸው፡፡ ከአንድ ዓይነት አቶሞች ብቻ የታነፁ ቁስ አካላት “ንጥረ ነገር” (Elements) በመባል ሲታወቁ፣ ቁጥራቸውም 118 ነው፡፡ ስለሆነም በዓለማችን ያሉ ቁስ አካላት ሁሉ የተገነቡት በእነኝህ ንጥረ ነገሮች ስብጥርና ውህደት ነው፡፡ በዓለማችን ላይ በተለያዩ ንጥረ ነገሮች በነጠላም ሆነ በውህደት የተመሠረቱ ወደ አራት መቶ የሚሆኑ የሚኒራል ዓይነቶች አሉ፣ በእነኝህ የተለያዩ ስብጥር የሚኒራል ጥርቅሞች ነው አለቶች የተገነቡት፡፡

በዓለም ላይ ሦስት የድንጋይ (አለት) ዓይነቶች አሉ፣ አነሱም “ግይ ድንጋይ/ቡልድ” (Igneous Rock)፣ “ጥቅጥቄ/ደለሌ” ድንጋይ (Sedimentary Rock) እና “ልውጤ” ድንጋይ (Metamorphic Rock) ናቸው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው በመሠረቱ አለት ዕምቅ/የተጠቀጠቀ የቅንጣት የሚኒራሎች (Minerals) ጥርቅም ነው፡፡

በከርሰ ምድር ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ያመቀ ቀልጦ የሚገኘው አለት ነው “ግይ ድንጋይ” በመባል የሚታወቀው፡፡ ያም ከከርስ ምድር ካለው “ገሞራ ህፅም” (Magma)፣ ወይም በእሳተ ገሞራ ይዘት ፈንድቶ ከሚወጣው “ገሞራ ትፍ” (Lava) ሊገኝ ይችላል፡፡ ይህ የቀለጠ አካል ከከርሰ ምድር ወጥቶ ቀስ በቀስ ሲቀዘቅዝ፣ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለው ግይ ድንጋይ በመባል የሚታወቀው የአለት ዓይነት ይሆናል፡፡ ገራናይት (Granite) የዚህ ዓይነት ድንጋይ ምሳሌ ነው፡፡

 በተቃራኒው ጠንካራ ያልሆነው “በርቴ” (Pumice) ወይም “ሁፌ” (ኦሮሚፋ) የግይ ድንጋይ ሌላ ምሳሌ ሲሆን፣ የዚህ ዓይነት ድንጋይ መሠረት የሳት ገሞራ ትፍ ነው፡፡ በርቴ ከገሞራ ትፍ ከውኃ ጋር ተቀላቅሎ፣ እንዲሁም አየር አምቆ በፍጥነት ሲቀዘቅዝ የሚገኝ የግይ ዓይነት ድንጋይ ስለሆነ፣ በመቀዝቀዝ ሒደት በውስጡ የነበረው አየር ሲወጣ፣ ድንጋዩ በየቦታው የተበሳሳ ይዘት ይኖረዋል፣ ክብደቱ በጣም ዝቅተኛ ይሆናል፣ በዚያም መንስዔ በውኃ ላይ ሊንሳፈፍ ይችላል፡፡

አፈር አልሚ ኬሚካዊ ውህዶችን ከመግዛት የሚታደገው የኢትዮጵያ ኖራና ጥቅማ ጥቅሞቹ  በሽብሩ ተድላ (ፕሮፌሰር ኤምሪተሰ) እና በባለሟል አጥናፉ (ዶ/ር) | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

 “ዝቅጤ ድንጋይ” ለመፍጠር በመጀመሪያ ዝቅጤው የሚከማቸው/የሚዘቅጠው የመሬት ገላ ላይ ባሉ የተመረጡ ዝቅጠት ከባቢዎች ውስጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ሐይቆችና ውቅያኖሶች የዝቅጠት ከባቢዎች ናቸው፡፡ ዝቅቴው/ደለሉ ከተለያዩ አካላት ሲሆን፣ እነሱም አፈር፣ ክርስታል፣ የዕፀዋትና የእንስሳት ቅሬት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በውኃና በነፋሳዊ ኃይል ተግዞ ከጊዜ ብዛት በአንዳንድ አካባቢ በደለል ይዘት ሊከማቹ ይችላሉ፡፡ የተለያየ ዝቅቴ፣ የዕፀዋትና የእንስሳት ቅሬት፣ ለምሳሌ ዛጎል (Shell) እንዲሁም አፈር ከመሬት ላይ በውኃና በነፋሳዊ ኃይል ታጥበው ተወስደው ዝቅተኛ ከፍታ ወደ አለው ገጸ ምድር ላይ ሲጠራቀሙ ነው መጤ ዝቅጤ/ደለል (Allochtonous Sediments) ተብለው የሚጠሩት፡፡

በሌላ መንገዶች ደግሞ ነባር ዝቅጤ/ደለል (Authochtonous Sediments) ሊፈጠር ይችላል፡፡ አንዱ መንገድ እንሳስትና ዕፀዋት ይኖሩበት የነበረ አካባቢ ውስጥ ሞተው ወይም ተሰባብረው እንደ ደለል ሊከማቹ ይችላሉ፡፡ ሌላው መንገድ ከውኃው ውስጥ በትነት ምክንያት ክርስታሎችን በማተል (Precipitate) ደለል ሊከማች ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በዚህ ሒደት ወደ ረባዳ ቦታ የሚከማቹት ቁስ አካላት፣ በነባሩ ላይ ሌላ የደለል ሽፋን ይመሠርታሉ፡፡ ስለሆነም በአንዳንድ አካባቢዎች በተለያዩ ዘመናት የተጠራቀሙ የደለል ሽፋኖች/ንብብራት ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

የኖራ ድንጋይ” (Limestone) አመሠራረት

ኖራ በመሠረቱ “ጥቅጥቄ/ደለሌ” ድንጋይ (Sedimentary Rock) ሲሆን፣ የድንጋዩ ዓይነትም በብዛት የካልሳይት ሚኒራሎች (CaCO3) አለው፡፡ እንደ ዶሎሚት (CaMg(CO3)2) ሚኒራል የኖራን ድንጋይ ሊቀላቀል ይችላል፡፡ ዶሎሚት የበዛው ድንጋይ፣ ዶሎ ድንጋይ (Dolostone) ይባላል:: ካልሳይት የካልሲየም፣ የካረቦንና የኦክስጅነ ውሁድ (CaCO3) ሲሆን፣ ዶሊሚት ደግሞ ስድሳ በመቶ (60 በመቶ) የካልሲየም፣ የካረቦንና የኦክስጅነ ውሁድ (CaCO3)፣ አርባ በመቶ (40 በመቶ) የማግኒዚየም የካረቦንና የኦክስጅን ውሁድ (MgCO3) ነው፡፡ ለገበያ የሚቀርበው የኖራ ዓይነት ከዘጠና በመቶ (90 በመቶ) በላይ የታነፀው በእነኝህ በሁለቱ ሚኒራሎች ነው፡፡

የኖራ ድንጋይ በብዛት የሚገኝ ከብዙ ዘመናት በፊት የባህር/ውቅያኖስ ውኃ በነበረ አካባቢ ሲሆን፣ ከባህር ውጭም ቢሆን መሬት ላይ ባሉ/በነበሩ ውኃማ አካባቢዎችም እንደ ምንጭ ወለድ ዓይነት መጠነ ውስን የኖራ ድንጋይ ይገኛል፡፡

 ዝቃጩ በብዛት የዛጎል ለበስና የሌሎች ባለአከርካሬ የባህር እንስሳት ቅሪት/አፅም፣ ከባህር ወለል በታች ተቀብሮ በተለያዩ ኬሚካዊና ፊዚካዊ ሒደቶች ተልም/ተለንቅጦ በውቅያኖስ ከላይ ያለው ውኃ ግፊት (Pressure) በክብደት ተፅዕኖ (Compression)፣ የታመቀ ሲሆን፣ ደረቆ የተቀበረው ዝቃጭ በዚህ መንገድ የኖራ ድንጋይ ይሆናል፡፡ ይኼ ድንጋይ በሥነ ምድራዊ እንቅስቃሴዎች ወደ የብስ ከፍታ ሲደረግ እኛ እንዳሁኑ እናገኘዋለን፡፡

 የተለያዩ ሕያው አካላት፣ በተለይ ዛጎል ለበስ የሆኑት ሕያው አካላት፣ “ካልስየምን” ከውኃ ውስጥ አጥለው አውጥተው/ምገው የራሳቸው ገላ መገንቢነት እንዲውል ያደርጋሉ፣ ስለሆነም ነው ህያውነታችው ሲቋጭ፣ በቅሬቶቻቸው ውስጥ ከፍተኛ የካልስየም ጥርቅም የሚገኘው፡፡ የ“ኖራ ድንጋይ” ይዘት ከ50 በመቶ በላይ “ካልሲየም ካርቦኔት” (Calcite-CaCO3) ሲሆን፣ እንዲሁም በሌሎች ኬሚካዊ ውሁዶች ሊታነፅ ይችላል፡፡ የኖራ ድንጋይ በዓለማችን ላይ በብዙ አካባቢዎች አንደሚገኝ ይታወቃል፣ በተለይ የኖራ ድንጋይ በበዛት የሚገኝም “ገሞጂማ ጠቀስ” (Sub-tropical) አካባቢ ነው፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰው ኖራ ድንጋይ የህያው ቅሬት ሆኖ፣ ከደለል ይዘት ወደ አለትነት የተቀየረ ቁስ አካል ሲሆን፣ በመሠረቱ የካረቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) እና የካልስየም (Ca) ውሁድ (CaCO3) ነው፡፡ ኖራ ድንጋይ በብዛት ቀለሙ ወደ ነጭነት/ግራጫነት ያደላ ነው፣ ቢጫ ቀመስ ሊሆንም ይችላል፡፡ ለምሳሌ በሚከተለው ኬሚካዊ ቀመር እንደሚታየው ማግኒዚየም (CaMg(CO3)2) ያካተተ ተዛማችነት ያለው የኖራ ድንጋይ ዓይነት አለ፡፡ ጠመኔ (Chalk) ከደቀቀ የህያው ቅሬት የሚገኝ ነው፡፡ ጠመኔ ቀለሙ ነጭ በቀላሉ የሚፈጭ አካል ሲሆን፣ ጠንካራውና በቀላል የማይፈጨውም ባልጩት (Crystalline Rock) የኖራ ድንጋይ አንዱ ዓይነት ነው፡፡

አንድን የድንጋይ የኖራ ድንጋይ መሆን አለመሆኑን ለመረዳት የሚያገለግል አንድ በተሞክሮ የተገኘ ዘዴ አለ፣ ያም የተበረዘ “ሀደሮክሎሪክ አሲድ” (Hydrochloric acid/ HCl)፣ ወይም የቆምጣጤ/አቸቶ/ቪኒጋር መሰል ፈሳሽ አለቱ ላይ ሲፈስበት፣ ከአለቱ ላይ አየር አዘል አረፋ መሰል ሲወጣ፣ ጋዝ (እንደ እንፋሎት መሰል) ቡል ቡል ሲል፣ አለቱ ካለሳይት (CaCO3) መኖሩን ያሳያል፡፡ ጋዙ (ቡል ቡሉ) የበዛ መሆኑ የኖራ ድንጋይ መሆኑ ይታወቃል፣ የሚወጣው ጋዝም ካራቦን ዳይኦክሳይድ (CO2) ነው፡፡

ኖራ ድንጋይበታሪክ

የሰው ልጆች በኖራ ድንጋይ መጠቀም ከጀመሩ ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ ከክርስቶስ ልደት አምስት ሺሕ ዓመት ገደማ በፊት የኖራ ድንጋይ ለከፍተኛ ሙቀት (ለእሳት) ተዳርጎ ከዚያም ከውኃ ጋር ሲቀላቀል፣ ባህርዩን ቀይሮ፣ በጣማ ጠንካራ ይሆናል፣ ዘመን እየጨመረ ሲሄድም ጥንካሬው እየጎላ መሄዱን ሰዎች ተገንዝበው ነበር፡፡

 እንዲሁም ከላይ በተጠቀሰው ዘመን፣ የኖራ ድንጋይ ለግንባታ ይውል እንደነበረ ማስረጃ “ይፍታህ ኤል” (Yiftah El) በሚባል፣ በዛሬይቱ እስራኤል፣ አካባቢ ተገኝቷል፡፡ ተግባሩ የተከናወነው ኖራን ለከፍተኛ ሙቀት በመዳረግ፣ ከዚያም በኋላ በመደቆስና ከውኃ ጋር በመቀላቀል ለግንባታ ተግባር (ለሕንፃ ግንባታ) በማዋል ነበር፡፡ ግዙፍ የግብፅ ፒራሚዶች በኖራ ድንጋይ ነበር የተገነቡት፣ ለምሳሌ ታላቁ “የጊዛ ፒራሚድ” (The Great Pyramid of Giza) የተገነባው በ2.3 ሚሊዮን የኖራ ድንጋይ ሲሆን፣ እያንዳንዱ የድንጋይ አካል አንድ ሜትር ኩቦ/ኪዩብ (ወርዱ፣ ቁመቱና ስፋቱ፣ አያንዳንዱ ገጽ አንድ ሜትር የሆነ)፣ ሆኖ ሦስት ሺሕ ኪሎ ግራም ገደማ የሚመዝን ነበር፡፡

ድንቅዬ የሆኑ ታሪካዊ ግንባታዎች ሲታነፁም የኖራ ድንጋይ ዋና ግብዓት ተደርጓል፣ ለምሳሌ የቻይናው ዝነኛውና ታሪካዊው ግድግዳ መሰል በሺ ኪሎ ሜትሮች የሚዘልቅ ግምብ (The Great Wall of China) ግንባታው በጠቅላላ አምስተ መቶ ዓመት ገደማ የፈጀው (ከክርስቶስ ልደት በፊት 771–221)፣ ጥንት ርዝመቱ 21,196 ኪሎ ሜትር የነበር፣ አሁን በነባር ቁመና ያለው ግንብ ርዝመት 8,850 ኪሎ ሜትር ብቻ የሆነው፣ ዋናው የግንባታ ግብዓት የኖራ ድንጋይ ነበር፡፡

የሮማን ግዛት ማክተሚያ አካባቢ፣ ሦስት መቶ አምሳ ጠቅላይ ግዛቶችን የሚያገናኙ፣ ሦስት መቶ ገደማ መንገዶች ሲታነፁ ዋናው ግብዓት የኖራ ድንጋይ ነበር፡፡

በዘመናችን ከአምስተ ሺሕ ቶን በላይ የኖራ ድንጋይ በየዓመቱ ለግንባታ፣ ለሲሚንቶ ፍብረካ፣ ለብረታ ብረት ኢንዱስተሪ ግብዓትነትና ለግብርና ግብዓት እናውላለን፡፡ ጠመኔ/ቾክ (40-60 በመቶ) ካልሳይት (CaCO3) ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች በጠመኔ መጠቀም የተጀመረው በ18ኛው ምዕተ ዓመት ገደማ እንደነበረ ይወሳል፡፡ ለዚህም እንደማስረጃነት የሚቀርበው “በኦክስፎርድ እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት” (Oxford English Dictionary) እንደጎርጎሪዎስ ዘመን አቆጣጠር በ1739 ዓ.ም. በጥቁር ሰሌዳ ላይ መጻፉ ተመዝግቧል፡፡ በአንፃሩ ይህ ተግባር በአሜሪካን በ19ኛው ምዕተ ዓመት መባቻ ላይ እንደተከናወነ ተሰንዷል፡፡

የኖራ ድንጋይጥቅማ ጥቅሞች

 ከላይ እንደተጠቀሰው የኖራ ድንጋይ በብዙ አካባቢዎች የሚገኝ ደለሌ አለት ነው፡፡ ኖራ ድንጋይ በፈርጀ ብዙ የኢንዱስተሪ ግብዓትነት እንዲሁም በግንባታ የጎላ ሚና አለው፡፡ ለሲሚንቶ ኢንዱስትሪ ዋናው ግብዓት፣ ከሰማንያ አሰከ ዘጠና በመቶ (80 እስከ 90 በመቶ) የኖራ ድንጋይ ነው፡፡ የተፈጨ “ኖራ ድንጋይ” (Limestone) በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስተሪ፣ ለጥርስ ሳሙና፣ ለቀለም፣ ለወረቀት፣ ለመስታወትና ፕላሲቲክ ፍብረካ ወዘተ. ግብዓት ሆኖ ያገለግላል፡፡ በብዙ የፍብረካ ሒደት ኖራ ድንጋይ የሚያገለግለው እንደ ቆሻሻ ማጣሪያነት ነው፡፡ ስለሆነም በብረታ ብረት ኢንዱስተሪ ለዝቃጭ ቆሻሻ አስወጋጅነት ተግባር ይውላል፣ ለውኃ ማጣራትም ያገለግላል፡፡ የኖራ ድንጋይ ለተለያዩ ግንባታዎችና ለቅርፃ ቅርፅ ሥራ ያገለግላል፡፡ ለመንገድ ምልክት፣ መከፋፈያ፣ ልዩ ልዩ ሥርዓትን አመላካች የሆኑ፣ በመንገድ ላይ የሚታዩ ምልክቶች መሠረታቸው የኖራ ድንጋይ ነው፡፡

ኖራ ድንጋይ ጋር ዝምድና ያለው “ጀሶ/ጅፕሰም” (Gypsum) ከካለሲየም፣ ድኝና ኦክስጅን ውኃ ቅልቅል (CaSO. 4· 2H2O) መሠረት ያለው ሲሆን፣ በዚህ ቁስ ለግንባታ ልስን ቡኪት፣ ለትምህርት ቤት ቾክ፣ እንዲሁም ለመኪና መንገድ ምልክቶች ማዘጋጀት ያገለግላል፡፡ የኖራ ድንጋይ “ከሲሊካ” (Silica) አሸዋ ጋርና “ከሶዲየም ካርቦኔት” (Na₂CO₃) ተቀላቅሎ ለከፍተኛ ሙቀት ሲዳረግ ብሎም ሲግል ይቀልጣል፣ ከዚያ ቀለም አልባ የሆነ መስታወት (Glass) ይሆናል፡፡

 ለግብርና ተግባር የሚውለው “የኖራ ድንጋይ” (Agricultural lime) የአፈር ምርታማነትን በማጎልበት ከፍተኛ ጥቅምን ያበረክታል፡፡ “የኖራ ድንጋይ” ተፈጭቶ የተለያየ መጠን ያለው ኮረት ሆኖ የግብርና ግብዓት ይሆናል፣ ስሙም የግብርና ኖራ (Agricultural lime) ወይም “አግሊን” (Agline) በመባል ይታወቃል፡፡ በተደጋጋሚ የሚታረስ መሬት አሲዳማ የሚሆነው፣ ዕፀዋት በዕድገት ሒደት አሲዳማነትን የሚገቱ ኬሚካዊ ውህዶች (Alkaline) ስለሚጠቀሙባቸውና በአፈር ውስጥ ያለው የእነኝህ ዓይነቶች ውህዶች መጠን ስለሚቀንስ ነው፡፡

ለግብርና ተግባር የሚውለው የኖራ ድንጋይ (Agricultural lime)፣ ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት የሆኑትን ካልሲየም (Calcium) እና ማግኒዚየም (Magnesium) አበርካች ነው፡፡ እንዲሁም አሲዳማ አፈር ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት የሆኑ ኬሚካዊ ውህዶችን ጠፍሮ/ቆልፎ ይዞ፣ ዕፀዋት ለዕድገታቸው ግብዓትነት አንዳይጠቀሙባቸው ይገታል፡፡

እነኝህን ለዕፀዋት ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን “ፎስፎረስ” (Phosphorous) “ናይትሮጅን” (Nitrogen) እና “ፖታሲየም” (Potassium) ከአሲዳማ አፈር አላቆ፣ ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት አንዲሆኑ፣ ዕፀዋት እነሱን በቀላሉ እንዲያገኙ፣ ያመቻቻል፡፡ ስለሆነም የኖራ ድንጋይ (Agricultural Lime) ለግብርና ተግባር አሉታዊ ሚናው የጎላ ነው፡፡

 ጠቅለል ተብሎ ሲታይ በአሲዳማ አፈር ተጠፍረው ተይዘው የነበሩ ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት የሚሆኑ ኬሚካዊ ውህዶችን ነፃ ያወጣቸዋል፣ ብሎም ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት እንዲሆኑ፣ ብሎም አካባቢውን ለዕፀዋት ዕድገት ያመቻቻል፡፡ አሲዳማ ማሳዎችን በማከም፣ የማሳውን ምርታማነት 50 በመቶ ለመጨመር ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የዝናብ ውኃም ሆነ በመስኖ የሚገኝ ውኃ በቀላሉ ከአፈር እንዲቀላቀል፣ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፣ ያም የአፈሩን ጠጣራነት የመቀነስ ብሎም የመፈረካከስ ባህሪን ያጎናፅፋል፡፡ እንዲሁም ውኃ ከአካባቢው እንዳይተንና የዕፀዋት ዕድገት እንዳይቀጭጭ ኖራ ይታደጋል፡፡

የኖራ አለት አንዱ ተፈጥሯዊና ጠቃማዊ ተግባሩ በከርሰ ምድር የሚገኝ ፈሳሽ (ውኃና የተፈጥሮ ነዳጅ/ዘይት)፣ በውስጡ እንዲሰርግና አንድ ቦታ እንዲቆይ ማድረግ ነው፡፡ ማለትም ብዙ የኖራ ድንጋዮች እንደ ፈሳሽ ማከማቻ ወይም ማቆያ (Reservoir) ሆኖ ያገለግላሉ፡፡ በተጨማሪ ኖራ ድንጋይ የተለያዩ ማዕድኖች በውስጡ ይገኛሉ፣ ለምሳሌ እርሳስ (Lead)፣ ደኝ አቀፍ ዚንክ (Zink Sulphide) በኖራ ድንጋይ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ኖራ ድንጋይበኢትዮጵያ

 በኢትዮጵያ “ማዕከለ-ዘመን” (Mesozoic) ከ252 አስከ 66 ሚሊዮን ዓመት በፊት የተመሠረቱ የኖራ ድንጋይ ክምችት አካባቢዎች አሉ፣ ዋናዎቹ፣ የኦጋዴን አካባቢ ካለው ትልቅ ዝብጥ (Basin)፣ የዓባይ ወንዝ ዝብጥና የመቐለ ዝብጥ ናቸው፡፡ በጣም በብዛት በኢትዮጵያ የሚገኘው የኖራ ድንጋይ ከዘመናት በፊት በውቅያኖስ ውኃ የተሸፈነ አካባቢ ስለነበረ ከጊዜ በኋላ በውቅያኖሱ ሞገድ ምልሰት (Marine Regression) የብስ በሆነ አካባቢ ነው የሚገኝ፡፡ ለምሳሌ በጣም ግዙፍ የኖራ ድንጋይ ክምችት የሚገኘው በኦጋዴን ዝብጥ ሲሆን፣ ያ አካባቢም ከ145 አስከ 200 ሚሊዮን ዘመን በፊት በህንድ ውቅያኖስ ውኃ ተሸፍኖ የነበረ አካባቢ ነው፡፡ በተመሳሳይ ኩነት በሥነ ምድራዊ ጊዜ በቅርብ ጊዜም በሰሜን አፋር ተከስቷል፡፡ ያም በሰሜን አፋር አካባቢ ያለው የኖራ ድንጋይ ክምችት ነው፡፡ ሰሜን አፋር ባለው የደናክል ዝብጥ ውስጥ ብዙ ዓይነት የዝቅቴ ድንጋዮች ይገኛሉ፡፡ የክምሩ ጥልቀትም ከሺ ሜትር በላይ ይልቃል፡፡ የድንጋዮቹ ዓይነቶች አብዛኞቹ ነባር ዝቅጤ ድንጋዮች (Authochtonous Sedimentary Rocks) ናቸው፡፡ ከክምሩ ውስጥ የኖራ ድንጋይ ክምችት ይገኛል፡፡

“በሩቅ ጠቀሳ” (Remote Sensing) የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ዓባይ ሸለቆ እንደ አካባቢው የሚለያይ ጥልቀት ያለው በባህር ቅሬት የተሞላ ሲሆን፣ በዚያን ዓይነት የባህር ቅሬት ስብስብ፣ እስከ አንድ ሺሕ ሜትር የሚዘልቅ ክምችት ውስጥ ነው የኖራ ድንጋይ የሚገኘው፡፡ በዓባይ ሸለቆ እንዲሁም በገባር ሸለቆዎች መጠነ ብዙ የኖራ ድንጋይ ይገኛል፣ ይህም የአገር ሀብት ብዙ ዜጎችን ከድህነት ሊታደግ ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት በዓባይ ሸለቆና ገባሮቹ (ሙገር ወዘተ) እና ሃሮ ገንዳና ዓለም ከተማ አካባቢ በብዛት ይገኛል፡፡ ከመካነሰላም ወደ መርጡለ ማርያም መሻገሪያም ሆነ ከጎሃፅዮን ወደ ደጀን ባለው የዓባይ ሸለቆ መሸጋገሪያ የኖራ ድንጋይ ስምንት በግልጥ ገደል ሆኖ ይታያል፡፡ ከዚህ ስብጥርና ግንኙነት ጋር በተያያዘ ጅፕሰም በኢትዮጵያ በዓባይ ሸለቆ በብዛት ይገኛል፣ እንዲሁም በኦጋዴን በብዛት ይገኛል፡፡

በአማካኝ በዓባይ ሸለቆ የሚገኘው የኖራ ደንጋይ ጥልቀት አምስት መቶ ሜትር ገደማ ነው፡፡ የዓባይ ገባር ወንዞች፣ ለምሳሌ ጅማና ሙገር ተመሳሳይ የኖራ ድንጋይ ክምችት ይገኝባቸዋል፡፡

 የአፈር አሲዳማነት በኢትዮጵያ ማሳዎች በብዙ አካባቢ እይተከሰተ ነው፣ ያም የማሳዎችን ምርታማነት በጣም ቀንሶታል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው አሲዳማ አፈር ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት የሆኑ ኬሚካዊ ውህዶችን ጠፍሮ/ቆልፎ ይዞ፣ ዕፀዋት ለዕድገታቸው ግብዓት አንዳይጠቀሙባቸው ይገታል፡፡ እንኝህን የዕፀዋት ዕድገት ግብዓቶች ከአሲዳማ አፈር አላቆ፣ ለዕፀዋት ዕድግት ግብዓት እንዲሆኑ በማስቻል፣ ኢትዮጵያን ከአፈር ማቅለዣ ኬሚካዊ ውህዶች ወጭ ሊታደግ ይችላል፡፡ ለአፈር ማቅለዣ የሚወጣው ሀብት ለሌሎች የልማት ተግባሮች ሊውል ይችላል፡፡

በኢትዮጵያ በብዙ አካባቢ አፈሩ ወደ አሲዳማነት የተቀየረባቸው ማሳዎች በግብርና ኖራ (Agricultural Lime) በማከም፣ የማሳዎችን ምርታማነት በጣም ለማሳደግ ይቻላል፡፡ በሒደት ኢትዮጵያ ከምግብ እህል ገዥነት ወደ ምግብ እህል ሻጭነት በቀላሉ ልትሸጋገር ትችላለች፡፡

መደምደሚያ

የጽሑፉ አንዱ ዓላማ ሳይንስና ቴክኖሎጂን ማስተናገድ ስለሆነ፣ የሳይንስ ዕውቀት፣ ቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ውስብስብነት ለመጠቆም ያህል፣ የሲሚንቶና የመስታወት ፍብረካን እንደምሳሌነት ብናወሳ እንደ ጥሩ ምሳሌ ያገለግላል የሚል ዕይታ አለን፡፡ ይህን ዓይነት ተግባር የሚከናወን ሚኒራሎች ተፈላጊውን መጠን ወስኖ በመቀላቀል ነው፡፡

ለምሳሌ “የፖርተላንድ ሲሚንቶ” (Portland Cement) ፍብረካ አራት ደረጃዎች አሉት፣ አንደኛው የኖራ ድንጋዩን መሰባበር ነው፡፡ ከዚያም በሁለተኛ ደረጃ የሲሚንቶ ግብዓት የሆኑ ጥሬ ዕቃዎች በተገቢው መጠን መደባለቅ ነው፡፡ ሦስተኛው የተደበላለቀውን ጥሬ ዕቃ ለከፍተኛ ሙቀት መዳረግ ነው፡፡ ከዚያም “ቅልጥ ድንጋዩ”/“ክሊንከር” (Clinker) በመባል የሚታወቀውን ከጥቂት ጀሶ ጋር (በአምስት በመቶ) መቀላቀል ነው፡፡

እንዲሁም ለመስታወት ፍብረካ ዋናው መሠረቱ (70-75 በመቶ) “ሲሊካ” (SiO2) ሲሆን፣ “ሶዲየም ኦክሳይድ” (Na2O/14-16 በመቶ)፣ “ካልስየም ኦክሳይድ” (CaO/8-13 በመቶ) “አሉሚነም ኦክሳይድ” (Al2O3/1.5-2 በመቶ) እና “ማግኒዚየም ኦክሳይድ” (MgO/2-5 በመቶ) ቅልቅል ተደባልቆ ለሙቀት ሲዳረግ ነው መስታወት የሚፈበረክ፡፡ ሚኒራሎችን ለጥቅም ስናውል የተለያዩ ሚኒራሎችን (Minerals) በተለያዩ መጠኖች በመቀላቀል የሚፈልገውን ዓይነት መስታወት ለማግኘት ይቻላል፡፡ ይዘቱ የሚኒራሎች ስብስብ ስለሆነ፣ አንድ የተወሰነ መቅለጫ የሙቀት ልኬት የለውም፣ ሙቀቱ በጨመረ ቁጥር ውህዱ እየላላ ነው የሚሄድ፡፡ ለመስታወት ፍብረካ ግብዓት የሚሆኑት ሚኒራሎች ስብስብ እያንዳንዱ ከጠጣርነት ወደ ፈሳሽነት የሚቀየሩበት ሙቀት (Melting Pont) መጠን ይለያያል (በሴልስየስ/0C ሙቀት ሊኬት ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛው በቅደም ተከተል Na2O በ11320C፣ SiO2 በ17100C፣ Al2O3 በ20720C፣, CaO በ25720C፣ እና MgO በ28520C ነው ከጠጣርነት አሥር ወደ ፈሳሽነት የሚቀየሩት)፡፡ ስለሆነም በዚህ በልል ቁስ፣ ፈሳሽ ወይም ጠጣር ያለሆነ የተለያዩ ቅርፆች ያሏቸውን ቁሳቁስ መፈብረክ/ማበጀት ይቻላል፡፡

ከሰው ልጆች ዋና ዋና ፍላጎቶች ሁለቱ ምግብና መጠለያ ናቸው፡፡ ሁለቱንም ችግሮች በኖራ ድንጋይ ግብዓትነት መቅረፍ ይቻላል፣ በኖራ ድንጋይ ማሳን በማከም አሲዳማነትን አስወግዶ ምርትን ከፍ ለማድረግ፣ እንዲሁም የኖራ ድንጋይ ውጤት በሆነው በሲሚንቶ መጠለያም ለመገንባት ይቻላል፡፡ በሒደትም ሥራ ለመፍጠር፣ ብሎም የቴክኖሎጂ ሽግግርንም ለማስተናገድ ያስችላል፡፡

በኢትዮጵያ 3.5 ሚሊዮን ሔክታር አካባቢ የሰብል ማሳዎች አሲዳማ ሆነዋል፣ ስለሆነም ምርታማነታቸው በጣም ቀንሷል፡፡ ተፈላጊ ንጥረ ነገሮች ለዕፀዋት ዕድገት ግብዓት እንዲሆኑ በልዩ ዘዴ የተመረተ የኖራ ድንጋይ አሲዳማ አፈሮችን ማከም ይቻላል፡፡ ይህን በመተግበር የማሳዎች ምርታማነት እንዲጨመር ያደርጋል፡፡

 አፈርን በኖራ በማከም ኢትዮጵያ አፈር አልሚ ኬሚካዊ ውህዶች ከመግዛት ይታደጋል፣ አገር ቤት ያለ የሥራ ዕጦት ችግርንም በመጠኑ ሊፈታው ይችላል፡፡ በአፈር ማከሚያ ኖራ ማዘጋጀት የሥራ ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል፣ የሥራ ዕድል ለወጣቶች ይፈጠርላቸዋል፡፡ ስለሆነም፣ የማሳዎችን አሲዳማነት ማስወገድ፣ ሥራ ይፈጥራል፣ የውጭ ምንዛሪ ወጭንም ይቀንሳል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ሐፊዎቹ  ሽብሩ  ተድላ  (ፒኤችዲ)  የአዲስ  አበባ  ዩኒቨርሲቲ የሥነ ሕይወት (ባዮሎጂ) ኢመረተስ ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ባለሟል አጥናፉ (ዶ/ር) በተመሳሳይ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው፡፡ ሁለቱም በመስካቸው በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎቻቸውን አሳትመዋል፡፡ ጽሑፉ የጸሐፊዎቹን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  shibrut@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡ 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles