Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዝንቅዶስቶቭስኪ የሞት ፍርዱን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ

ዶስቶቭስኪ የሞት ፍርዱን ተቀብሎ ቢሆን ኖሮ

ቀን:

ጊዜው 1849 የኅዳር ወር አሥራ ስድስተኛ ቀን ነው። እስረኞቹ በኃይለኛው ብርድ እየተንቀጠቀጡ፡ በማንኛውም ደቂቃ ከአፈሙዙ አፈትልኮ የሚወጣውን ጥይትና ሞታቸውን ይጠብቃሉ። በመሀል ግን አዲስ መልዕክት መጣ። እስረኞቹ ላይ ተላልፎ የነበረው የሞት ፍርድም ወደ አራት ዓመት ለሚቆይ ከባድ ሥራ መቀየሩን የሚነግር ብስራት ሆነ። እስረኞቹም በቀዝቃዛው ሳይቤሪያ የነበራቸውን አስከፊ የቆይታ ጊዜ አጠናቅቀው በ1854 ተለቀቁ። ለተጨማሪ አምስት ዓመታትም በሳይቤሪያ ክፍለ ጦር በወታደርነት አገለገሉ።

ከእስረኞቹ መሀል አንዱ ቅጣቱን በሙሉ ከጨረሰ በኋላ፡ የሩሲያ ብሎም የዓለም ሥነ ጽሑፍ ውድ ሀብት የሆኑትን ታላላቅ ልብ ወለዶች ጻፈ—Crime and Punishment፣ Brothers Karamazov፣ Notes from the Underground፣ The Idiot፣ The Gambler እና ሌሎችም…፡፡

በዚያች ታሪካዊ ቀን ፍዮዶር ሚካይሎቪች ዶስቶቭስኪ የሞት ፍርዱን ተቀብሎ ቢሆን፡ ሕይወቱን የሚያጣው አንድ ግለሰብ ብቻ ባልሆነ ነበር—ለሥነጽሑፍም ትልቅ ማጣት በሆነ ነበር፤ ሁላችንም እነዛን ውብ ልብወለዶች ማንበብ ባልቻልን ነበር። ከነጭራሹም ምን እንዳጣን እንኳን ባላወቅን ነበር። ይህ ቀን በዶስቶቭስኪ ሕይወት ውስጥ አንድ ተራ ቀን አልነበረም። ሞቶ የመነሳትን ያክል ነው። ከአንበሳ መንጋጋ ማምለጥ ያህል ነው። ሁሉም እስረኞች ሊሞቱ እንደሆነ እርግጠኞች ነበሩ። ጥይቱ አለመተኮሱን አትመልከቱ። በነዶስቶቭስኪ አእምሮ ጥይቱ ተተኩሷል። ሞተዋል። እና የምሕረት ዜናው ተአምር ነበር። ይህ ክስተት በዶስቶቭስኪ አስተሳሰብ፣ ሥነልቦና፣ እንዲያው በአጠቃላይ መላ ሰብእናው ላይ ዘላቂ አሻራ አሳርፏል። አንዳንድ ቅጽበቶች አሉ የዘለአለምን ያህል የሚረዝም ዱካ የሚተዉ።

- Advertisement -

እናም እነዛ የመከራ ጊዜያት፡ እንደው የመከራ ጊዜያት ብቻ ሆነው አልቀሩም—ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ሐሳቦቹን የቀየረበትና የሞረደበት ጭምር እንጂ! ወንጀልና ቅጣት በተሰኘው ልብወለዱ ላይ ያለው ዋና ገጸ ባህርይ ራስኮልኒኮቭም ለፈጸመው የነፍስ ማጥፋት ወንጀል፡ በሳይቤሪያ፡ በከባድ ሥራ እንዲያሳልፍ የተፈረደበትንም ፍርድ ዶስቶቭስኪ ከራሱ የሕይወት ልምድ ጨልፎ የጻፈው የራሱ የሕይወት አጋጣሚ ነው።

ታዲያ ስለ ራስኮልኒኮቭ ትንሽ ጨምረን ብናወራ ደስ ይለኛል። ምክንያቱም በከፊል ራስኮልኒኮቭ የዶስቶቭስኪ ነጸብራቅ ነው። በራስኮልኒኮቭ ውስጥ ዶስቶቭስኪን እንመለከታለን። ለምሳሌ ሁለቱም ከፍተኛ የማሰብ ብቃት አላቸው። ሁለቱም ወንጀል ፈጽመዋል። ሁለቱም የአእምሮ ሕመም አለባቸው። በአጭሩ ዶስቶቭስኪ የራሱን ሕይወት፣ ልምድ፣ ሰብእና ወሰደና ብዙ ሐሳብ ጨምሮ ልቦለዳዊ አደረገው። የራስኮልኒኮቭን ሕይወት አብረን እንይ፦

ራስኮልኒኮቭ ድሃ ተማሪ ነው። ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሳው ግን ተራ ማጣት አይደለም። ምክንያቱ ውስብስብ ነው። ይቺ ሊገድላት የተዘጋጀው አሮጊት “ክፉ” አራጣ አበዳሪ ናት። ምስኪን ወጣቶች ላይ ተጣብቃ የምትበዘብዝ መዥገር ናት። የሷ መሞት ለማኅበረሰቡ ጥቅም ነው።

ራስኮልኒኮቭ አንድ ፅኑ እምነት ነበረው፦ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሁለት ዓይነት ሰዎች አሉ―ተራና ልዩ። እነዚህ “ልዩ” ሰዎች ለማኅበረሰቡ እስከጠቀመ ድረስ ወንጀል የመፈፀም መብት አላቸው። ራስኮልኒኮቭ ይህንን “ልዩ” ሰውነት ለራሱ ሰጥቶ በማኅበረሰቡ “የተፈቀደለትን” ወንጀል ለመፈፀም ይወጣል።

ራስኮልኒኮቭ መጥረቢያ ታጥቆ ወደ አሮጊቷ ቤት ሄደና በአሰቃቂ ሁኔታ ገደላት። ምስኪን ሊዛቬታ በመጥፎ ጊዜ፣ በመጥፎ ቦታ ተገኘች። ሊዛቬታ የአሮጊቷ እህት ናት። በወንጀሉ ቦታ በድንገት ስለተገኘች ራስኮልኒኮቭ ሌላ ወንጀል ለመፈፀም ተገደደ። ሊዛቬታንም ገደላት።

ዶስቶቭስኪ እንዲህ ይላል፦ “ወንጀል በመፈፀም የምናጣው ትልቁ ነገር የራሳችንን ምርጥ ባህሪ ማውደሙ ነው። በጣም የሚያሳዝነው እውነት ሁላችንም ለማይረባ ነገር ስንል ክቡር እኛነታችንን ከድተናል”፡፡

ይህ በጣም መሠረታዊ፣ የሁላችንም እውነት ነው። ሁላችንም ወንጀል ፈጽመናል። በሁላችንም ውስጥ ክፋት አለ መጠኑና አይነቱ ይለያይ እንጂ። ከመካከላችን አንዳች እንኳን ንጹህ የለም። ሁላችንም በኃጢአት ጥላ ሥር ወድቀናል። ህሊናችንን ችላ ብለን ተላልፈናል። በወንጀልና ቅጣት ዶስቶቭስኪ ይህንን መራር እውነት ከአእምሮ እንዳይፋቅ አድርጎ በማይጠገብ ለዛ ይነግረናል።

እንደ ወንጀሉ ግዝፈትና ጥልቀት ህሊናችንም በዛው ልክ ይቆረቁረናል። ራስኮልኒኮቭ የፈፀመው ወንጀል ሳይታወቅ ለዘለአለም መኖር ይችል ነበር። የህሊናውን የውስጥ ጩኸት ግን መቋቋም አልቻለም። እረፍት የነሳው የራሱን ምርጥ ባህሪ በማውደሙ ነው። በመጨረሻም ወንጀሉን መፈፀሙን አምኖ እጅ የሰጠው ራሱ ነው። ዶስቶቭስኪን የምታደንቀው ይሄኔ ነው። የዶስቲቭስኪ ትኩረት የውጪው ግርግር አይደለም። ራስኮልኒኮቭ ወንጀሉን ከመፈጸሙ በፊትና በኋላ ያለውን አእምሯዊ ሁኔታ ይነግረናል። ዶስቶቭስኪ ስለ ወንጀለኛ ክትትል፣ መያዝ አለመያዙ ጉዳዩ አይደለም። ዶስቶቭስኪ የወንጀል ክትትል ልብወለድ ደራሲ አይደለም። የሥነልቦናዊ ልብወለድ ደራሲ ነው። የወንጀለኛውን ሥነልቦና አንጠርጥሮ በመመርመር እስከአሁን ድረስ ዋጋ ያላቸውን ቁምነገሮች ይነግረናል።

ዶስቶቭስኪ ዋጋ የሚሰጠው ለውስጡ ፍጭት ነው። ራስኮልኒኮቭ ጭንቅላት ውስጥ ተገኝቶ የሚያሳየንም ይህንኑ ግጭት ነው። ይህም ልብ ወለዶቹ ከፍተኛ ዋጋ እንዲኖራቸው አድርጓል። ምክንያቱም የጻፈው ስለ ሌላ ምንም ሳይሆን ስለ ሰው ነው። ስለ ሥነልቦናው። ከሱ በኋላ የተወለዱት እነ ሲግመን ፍሩይድ ከዶስቶቭስኪ ብዙ ኮርጀዋል።

ራስኮልኒኮቭ የፈፀመውን ወንጀል በማንኛውም ፍልስፍናዊ አጥር ሊከልል አይችልም። ምናልባት ማኅበረሰቡን ለተወሰነ ጊዜ ሊያታልል ይችላል። ከራሱ የህሊና ጩኸት ግን መደበቅ አይችልም። ዶስቶቭስኪ ታላቅ ደራሲ የሚያሰኘው ይህንን የሰው ልጅ ሥነልቡና ፈጣሪን በሚገዳደር ደረጃ በመረዳቱ ነው።

ሁሉም ሰው መጽሐፍ ለማንበብ ጊዜ ላይኖረው ይችላል። ዶስቶቭስኪን ለማንበብ የምትሆን ጥቂት ጊዜ መጥፋት የለበትም።

– ቴዎድሮስ ሸዋንግዛው በማኅበራዊ ገጹ እንደከተበው

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ