Tuesday, May 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት አለ የተባለው የውስጥ ችግር በውጭ ኦዲተሮች ሊመረመር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የሚመረጠው ኦዲተር በአንድ ወር ውስጥ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውስጥ ታይተዋል የተባሉ ግድፈቶች በውጭ ኦዲተሮች ምርመራ እንዲደረግ የተወሰነውን ውሳኔ ለማስፈጸም ለምርመራው የሚመረጠው የውጭ ኦዲተር ውጤቱን በአንድ ወር አጠናቅቆ የሚያቀርብ መሆኑ ተጠቆመ፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በቦርድ አባላት ጭምር በቀረበ አቤቱታ መሠረት የታዩ ግድፈቶችን ለመመርመር ለውጭ ኦዲተሮች ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፣ የኦዲተር መረጣው በቀጣይ ሁለት ሳምንታት ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ አሉ የተባሉ ችግሮችን ለማስመርመር በንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ የተሰየመው አጣሪ ኮሚቴ የኦዲት ሥራውን የሚመረምሩ ኦዲተሮች በጨረታ እንዲመረጡ በመወሰኑ፣ በዚሁ መሠረት ለተጫራቾች ጥሪ ተላልፏል፡፡

ምራመራውን ለማካሄድ ለተጫራቾች የቀረበው ዝርዝር መረጃ እንደሚያመለክተው የዚህ የኦዲት ሥራ ተቀዳሚ ግብ የውጭ አገር ጉዞዎች፣ ግዢዎች፣ የአገር በቀልም ሆነ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሁለትዮሽ ትብብር ስምምነቶች፣ የንብረትና ሰው ሀብት ምልመላና ዕድገት አስተዳደር ትግበራዎችን ሕጋዊነት ማረጋገጥ ነው፡፡

የውጭ አገሮች ጉዞዎች ትግበራዎች ተቋማዊ ሕግጋትንና መመሪያዎችን የተከተሉ ስለመሆናቸው መመዘን፣ የግዥ ሥራ ትግበራዎችን በተቀመጡ የአሠራር ሥርዓቶች፣ ሕግጋትና ደንቦች መሥፈርትነት አግባብነታቸውን፣ ግልፅነታቸውንና አዋጭነታቸውን መገምገምን ጭምር የሚያጠቃልለው የምርመራ ሥራ፣ የሰው ሀብት ምልመላ፣ ዕድገትና ዝውውር ትግበራዎች አግባብነት ባላቸው ሕግጋት፣ ፓሊሲዎችና የአሠራር ሥርዓቶች መሥፈርት አንጻር እኩልነትን፣ ብቃትንና ተገዥነትን ማረጋገጥ መቻላቸውን ሁሉ የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባላት የውጭ አገሮች ጉዞዎች በጀትና ዕቅድ በማጽደቅና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ረገድ፣  የተሳትፎዋቸውን ደረጃ በመፈተሽ የውጭ ኦዲተሩ ሪፖርት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡

ከዚህም ሌላ በግለሰብ ደረጃ የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ አግባብነት ላላቸው ሕግጋት፣ የአሠራር ሥርዓቶች ደንብና መመሪያዎች አግባብነት ደረጃ ተገዥነታቸውንና በተቋሙ ትግበራዎች ሥራ ላይ ማዋላቸውን ማረጋገጥ፣ የምርመራው አካል እንደሚሆንም ተመላክቷል፡፡ በአገር በቀልና ዓለም አቀፍ ተቋማት በትብብር ስምምነቶች ወቅት የዳይሬክተሮች ቦርድን ዕውቅናና ድጋፍ እንዲሁም  ሥጋቶችና ጥርጣሬዎች ምጣኔ መመዘን፣ ለውጭ  አገሮች ጉዞ በጀት የተመደበላቸው ሥለመሆኑና አለመሆኑ መመርመር፣ ሥራውን የሚረከበው የውጭ ኦዲተር የመመርመር ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡

የግዥ አሠራርን በተመለከተም በተለይ የጨረታ ሥራ፣ አቅራቢዎችን አመራረጥና  የጨረታ አሸናፊዎችን ማዋዋል ሥራ ሒደትን መከለስ፣ የግዥ ሠነዶችን ትክክለኛነት፣ የተሟሉ መሆናቸውንና  ሕግጋትንና ድንጋጌዎችን የተከተሉ ሥለመሆናቸው መፈተሽ ሁሉ የሚያጠቃልል ሥራ የሚሠራ ይሆናል ተብሏል፡፡

ከሰው ኃይል ምልመላ፣ ዕድገትና ዝውውር ጋር በተያያዘ የተሰጡ ውሳኔዎች ግልጽነት፣ ዘላቂነትና  ተፈጻሚነታቸውን መፈተሽ፣ የአስተዳደር ሠነዶችን ትክክለኛነትና አግባብነት ባላቸው ድንጋጌዎችና አሠራር ሥርዓቶች መሠረት ሥለመፈጸማቸው መመርመር፣ መልካም አስተዳደርን ወይም አድሏዊና ሥነ ምግባራዊና ያልሆኑ ትግበራዎችን መፈተሽ ሁሉ የምርመራው አካል ይሆናል፡፡ የሰው ሀብት አስተዳደር ሥራ ትግበራዎችን ጤናማነት፣ ዘላቂነትና ተቋማዊ መርሆዎችን፣ የአሠራር ሥርዓቶችንና ድንጋጌዎችን የተከተሉ መሆናቸውን ኦዲተሩ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት፣ የኦዲተሩን ሥራ በተመለከተ የተሰናዳው ሰነድ ያመለክታል፡፡ ኦዲተሩ ምርመራ እንዲያካሂድበት በሰነዱ የተመለከተው ሌላው ጉዳይ ‹‹ማበረታቻዎች›› በሚል እንደ ተሽከርካሪዎች፣ የወርቅ ቀለበቶችና የመሳሰሉት ከአባላት ዕውቅና በመስጠት ሥም ለምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ የተሠጡበትን ሁኔታ ሕጋዊነት መፈተሽ የሚያጠቃልል ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ምርመራዎችን ለማካሄድም የትግብራ ዘዴው በሰነዱ የተመለከተ ሲሆን፣ የኦዲት ምርመራ ሥራው ጥልቅ የሠነድ ፍተሻ፣ ከሚመለከታቸው ሠራተኞች ቃለ-መጠይቆችን ማድረግንና የሒሳብ መዝገቦችን መመርመርን ባካተተ መልኩ የሚከናወን እንደሚሆንም ታውቋል፡፡

ኦዲተሮች የውጭ አገሮች ጉዞን፣ ግዥና የሰው-ኃብት አሥተዳደር ትግበራ ሁኔታዎችን እያንዳንዳቸውን ሳይንሳዊ የአሠራር ሥርዓቶችን ተከትሎ በእያንዳንዳቸው ላይ ዳሰሳ ማድረግ የሚያስችሉ በወጥነት የተዘጋጁ የግብረ መልስ መሥፈርቶችን እንደሚጠቀሙ ተጠቅሷል፡፡

እንዲህ ባሉትና በሌሎች ጉዳዮች የሚካሄደው የኦዲት ሥራ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ኦዲተሩ የኦዲት ግኝቶችን፣ ምልከታዎችንና የማሻሻያ ውሳኔ ሐሳቦች በየመልካቸው ተለይተው ዝርዝር ሪፖርቱን እንዲያቀርብ ኦዲተሮችን ለመምረጥ በተዘጋጀው የጨረታ ሰነድ ላይ በግልጽ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡

የምርመራ የጊዜ ሰሌዳን በተመለከተም በኦዲት ምርመራ ሥራው ትግበራ ሒደት ወቅት የአፈጻጸም ለውጦችን በቋሚነት ለአዲስ አበባ ንግድ ምክርቤትና የዘርፍ ማኅበራት ጽሕፈት ቤት ልዩ ኮሚቴ በየአሥር ቀናቱ የመግለጫ ጊዜያት ኖረውት በአንድ ወር ጊዜ ወስጥ ተጠናቅቆ የሚቀረብ እንደሚሆን ይኸው የጨረታ ሰነዱ ያመለክታል፡፡

የኦዲት ሥራው ምሥጢራዊነትን የጠበቀ እንዲሆንም በኦዲት ምርመራ ሥራው ሒደት ላይ የሚሰበሰብ መረጃ በጠቅላላ በከፍተኛ ሚስጥርነት የሚጠበቅና ለዚሁ የኦዲት ምርመራ ጥናት ፍጆታነት ብቻ የሚውል እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

ከኦዲት ሪፖርቱ የሚገኘው ውጤት ታይቶ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ የሚችሉበትን አቅጣጫም እንዳለ ያመለክታል፡፡ የኦዲት ሥራ ግብረ መልስ ግብ፣ የተቋማዊ ፖሊሲዎች፣ የአግባብነት ደረጃዎች፣ መመሪያዎችና ድንጋጌዎችን ተግባራዊነት የማረጋገጥ ዳሰሳዎችንና ጥልቅ ምዘናዎችን ማከናወን፣ ልዩ ልዩ ድንጋጌዎችን ተግባራዊነት የተመለከቱ  የኦዲትና ኢንስፔክሽን ምርመራዎችን ማከናወን እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን  ሥፍራዎች መለየትና እንደ አስፈላጊነቱ መተግበር፣ አፈጻጸምን በፖሊሲዎች፣ በአግባብነት ደረጃዎች፣ መመሪያዎችና በገለልተኝነት፣ ተመዛኝነትና ሙያዊ መርሆዎችን የተከተሉ ማድረግ፣ ከኦዲት ግኝቱ በኋላ ይወሰዳሉ ተብለው የሚጠበቁ ዕርምጃዎች ይሆናሉ፡፡

በኦዲት ግኝቱ ውጤት የመጨረሻ ግብ ይሆናሉ ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ  የሥነ ምግባር ጥሰቶችን ፈጽመው በተገኙ ግለሰቦች ላይ አስተዳደራዊ ዕርምጃዎችን መውሰድ የሚለው ተጠቅሷል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በምክር ቤቱ ታሪክ እስከዛሬ ሆኖ በሚያውቅ ደረጃ እንዲህ ያለው የኦዲት ምርመራ እንዲካሄድ የተደረገው፣ በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ሕግና ደንብን ያልተከተሉ ተግባራት ይከናወናሉ በሚል በቀረበ ጥያቄ ነው፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ጭምር በተለይ የውጭ ጉዞዎች ከደንብና ሥርዓት ውጪ መካሄዳቸውንና የውጭ ምንዛሪ ብክነት ታይቷል የሚሉ ቅሬታዎችን በማቅረብ ጉዳዩ እንዲመረመርላቸው በጠየቁት መሠረት፣ ከብዙ ንግግር በኋላ ጉዳዩ በገለልተኛ የውጭ ኦዲተር እንዲመረመር ቦርዱ በአብላጫ ድምፅ ሊወስን ችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በኢትዮጵያ ውስጥ በጠንካራነቱ ሲጠቀስ የቆየ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 15 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉት ይታመናል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች