Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለተመዘገቡ የመድኃኒት ምርቶች ግብይት የሦስተኛ ወገን ስምምነት ሊቀር ነው

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስተዋልኩ ነው ያላቸውን፣ ከመድኃኒት ግብይት ጋር የተያያዙ አግባብነት የጎደላቸው አሠራሮችን ለመቅረፍ አዲስ የሦስትዮሽ ስምምነት መሥፈርቶችን እንደሚተገብር አመለከተ፡፡

በባለሥልጣኑ መረጃ መሠረት ከዚህ በኋላ የመድኃኒት አቅራቢ ወይም ድርጅት ሆኖ የሚቀርብ ሦስተኛ ወገን፣ በአምራቹ ወይም የምርት ባለቤትና የባለመብቱ አገር አስተዳደር ያስቀመጣቸውን ዝቅተኛ መሥፈርቶች ሊያሟሉ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡

በመድኃኒት ግብይት ውስጥ ሦስተኛ ወገን የሚያስፈልገው አምራቹ ወይም የምርት ባለቤትነት ባለመብቱ በአገር በቀል ወኪል አማካይነት ምርቶቹን በማስመዝገብና በማሠራጨት ላይ ያልተገኘ ከሆነ ብቻ መሆኑንም አስታውቋል፡፡

ለተመዘገቡ ምርቶች የሚቀርብ የሦስተኛ ወገን ስምምነት ተቀባይነት እንደማይኖረውም በዚሁ አዲስ የአሠራር መሥፈርቶች ውስጥ አካቷል፡፡  

በምግብና መድኃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር1112/2019 መሠረት የተጠቀሱ ምርቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር በቀል ወኪሎች ለማስመዝገብም ሆነ ለማሠራጨት የሚደረግ ስምምነት፣ ከአምራቹ በሕግ አግባብ በተፈረመ ስምምነት ሥልጣን ሊኖረው እንደሚገባም አስታውቋል፡፡ ከዚህም ሌላ በአዋጁ የተጠቀሱ ምርቶችን በኢትዮጵያ ውስጥ በአገር በቀል ወኪሎች ለማስመዝገብም ሆነ ለማሠራጨት የሚደረግ ስምምነት ከአምራቹ ወይም ከምርት ባለቤትነት ባለመብቱ ያለቀላቸቸውን ምርቶች ለመረከብ፣ ለማከማቸትና ለማጓጓዝ ኃላፊነቱ ሥልጣን ባለው ፈቃድ ሰጪ አካል ሕጋዊ ፈቃድ የተሰጠው ሊሆን እንደሚገባም አስታውቋል፡፡

የሦስተኛ ወገን ተቋሙ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኝና የምርት ሒደታቸው የተጠናቀቀላቸውን ምርቶች ለሌሎች አገሮች ለመላክ፣ ለማከማቸትና ለማጓጓዝ ኃላፊነት ያለበት ስለመሆኑ ከላኪው አገር ፈቃድ ሰጪ ባለሥልጣን የመጠቀሚያ ጊዜው ያላለፈበት ፈቃድ የተሰጠው ሊሆን ይገባዋልም ተብሏል፡፡

በአምራቹ ወይም በምርት ባለቤትነት ባለመብቱ የተፈረመበትና ቀንና ቁጥር የተሰጠው ቢያንስ በኢትዮጵያ ውስጥ በቀጥታ በአገር በቀል ወኪሎች አማካይነት ማመልከት ያልቻለበትንና ብቸኛ አቅራቢ ወይም የንግድ ተቋም ለመወከል ያስፈለገበትን ምክንያት የሚገልጽ ማረጋገጫ ደብዳቤ ሊያቀርብ እንደሚገባም ይኸው የአስተዳደሩ አዲሱ ድንጋጌ ያመለክታል፡፡

አዲሱ ድንጋጌ ሌላው ያከለው መሥፈርት የሦስተኛ ወገኑን የሥርጭት ትግበራና ሌሎች የፈቃድ አሰጣጥ ሁኔታዎች በፈቃድ ሰጪው ባለሥልጣን በቋሚነት ሊፈተሹና ቢያንስ ሁለት ተከታታይ በተቆጣጣሪው አካል የተከናወኑ የፍተሻ ሪፖርቶች ሊቀርቡ መቻል ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡

ሦስተኛ ወገን ከአምራች ወይም ከምርት ባለቤትነት ባለመብቱ ምርቱን ለገበያ ማቅረብ እንዲችል በተለይ ሦስተኛው ወገን በኢትዮጵያ ውስጥ አገር በቀል ወኪል መመደብ እንደሚችልና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የአምራቹን የምርት ባለቤትነት ባለመብቱ፣ የሦስተኛው ወገንና የአገር በቀል ወኪሉ ወይም አማካሪ ቢሮው የሦስትዮሽ ስምምነት ሊኖረው ይገባል ተብሏል።

ሦስተኛው ወገን የምርት አያያዙንና የማከማቸት ሥራውን ሕጋዊ መሥፈርቶችን ባሟላ መልኩ ስለማከናወኑ በኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለ ሥልጣን የምርመራ ቡድን ለመመርመር/ለመፈተሽ ፈቃደኛ ሆኖ መገኘት ይኖርበታልም ተብሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 24 ቀን 2024 ዓ.ም. ድረስ ሌተር ኦፍ ክሬዲት የተፈቀደላቸው አቅራቢዎች አስተዳደሩ ያስቀመጣቸውን መሥፈርቶች አሟልተው ከተገኙ በጊዜያዊነት የምርት አቅርቦታቸውን እንዲቀጥሉ የሚፈቅድላቸው ስለመሆኑም አሳውቋል፡፡ መሥፈርቶቹ አምራቹ የይፋዊ አቅራቢዎቹን ዝርዝር በተቋሙ ይፋዊ የኢሜይል አድራሻ መላክ፣ የአገር ውስጥ ወኪሉ ሌተር ኦፍ ክሬዲት የተፈቀደለት ስለመሆኑ ማስረጃውን ማቅረብና አምራቹ በነዚህ መሥፈርቶች ላይ ለሚከሰቱ ልዩነቶች መሟላት ተሳታፊነቱን የሚገልጽ የኃላፊነት ደብዳቤ ማስገባት በሚል ተጠቅሷል፡፡

አስተዳደሩ ወደዚህ ዕርምጃ የገባው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ አግባብነት በጎደለው መልኩ እየተከሰቱ ያሉ የአሠራር ችግሮች መኖራቸውን በማረጋገጡ ነው፡፡ አግባብነት በሌላቸው መልኩ ሲከናወኑ ነበር ካላቸው ተግባራት መካከል፣ ከተመሳሳይ መነሻ አገር በተመሳሳይ አምራች ለተመረቱ ተመሳሳይ ወይም የተለያዩ ምርቶች ከአንድ በላይ የንግድ ተቋማትን አቅራቢዎችን መወከል የሚለው አንዱ ነው፡፡ የተወሰኑ አመልካቾች የተፈቀደለት አቅራቢ የለም በማለት ከሦስተኛ አገር ላኪ ሆነው መገኘት፣ የተወሰኑ አገር በቀል ወኪሎች እንደ ዱባይ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካና የመሳሰሉት ባሉ ሦስተኛ አገሮች ራሳቸው ቢሮአቸውን እየከፈቱ ይህንኑ ቢሮዋቸውን አቅራቢ አድርገው ማቅረባቸውም ሌላ ችግር እንደነበር ገልጿል፡፡  

ከዚህም ሌላ ብዙኃኑ አቅራቢዎች፣ የንግድ ተቋማት ወይም ሦስተኛ ወገኖች በኢትዮጵያ ውስጥ ለተመዘገቡና ለሚገበያዩ ምርቶች፣ በሥርዓቱ ውስጥ የተካተቱ ሆነው መገኘታቸውና ተመሳሳይ ምርቶችን በተመሳሳይ ወቅት የሚያስገቡ አምራቾች፣ የንግድ ተቋማት ወይም ሦስተኛ ወገኖች መኖራቸው በመታወቁ ለአሠራሩ አዲስ መሥፈርት ለማውጣት መገደዱን ጠቅሷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች