Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ብሪክስ ኢትዮጵያ የበለጠ ጠንካራ ሆና የትኛውንም ዓይነት ጫና መቋቋም ያስችላታል›› ቪክቶሪያ ፓኖቫ፣ የሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና የባለሙያዎች ምክር ቤት ዋና ኃላፊ

ቪክቶሪያ ፓኖቫ (ዶ/ር) በሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና የባለሙያዎች ምክር ቤት ዋና ኃላፊና በሩሲያ ኤችኤስኢ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚተዳደረው የአገር አቀፍ የኢኮኖሚክስ ምርምር ዩኒቨርሲቲ ምክትል ዲን ሲሆኑ፣ በትምህርታቸውም ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በታሪክ የትምህርት ዘርፍ ያጠናቀቁ ናቸው። በሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና የባለሙያዎች ምክር ቤትን በሩሲያ መንግሥት ትዕዛዝ በአገሪቱ የውጭ ጉዳይና የገንዘብ ሚኒስቴር ትብብር የተቋቋመ በፖለቲካዊ፣ በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ ትብብሮችን በተመለከተ ሳይንሳዊ ሒደቶችን በመከተል ጥናቶችን በማካሄድ የባለሙያ ትንታኔዎችን እንዲያቀርብ ታስቦ የተመሠረተ መሆኑ ይነገራል፡፡ ከጅማሮው አንስቶ ቪክቶሪያ (ዶ/ር) በበላይነት ሲመሩት ቆይተዋል። በአገራቸው ብሔራዊ የብሪክስ ምርምር ኮሚቴም ዋና ዳይሬክተር ናቸው። የሩሲያ ስትራቴጂክ ስተዲስ ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አማካሪም ናቸው። በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በከፍተኛ የአመራር ደረጃዎችም ያገለገሉ ሲሆን ከጥናቶቻቸው መካከል የቡድን 8፣ የቡድን 7፣ የቡድን 20፣ እንዲሁም ብሪክስን የመሳሰሉ የአገሮች ጥምረት የሚተዳደሩባቸው አሠራሮችን በተመለከተ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችንና የኢንተርኔት አስተዳደርን፣ ቀጣይነት ስላላቸው ልማቶች፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ የመንግሥታት አስተዳደርን በተመለከተ ለኅትመት ያበቋቸው ጥናቶች ተጠቃሾች ናቸው። በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በግንቦት ወር መጨረሻ እንዲካሄድ ዕቅድ የተያዘለትን የብሪክስ ሲደመር ጉባዔ አስቀድሞ እየተደረጉ ባሉ ውይይቶች አካል በሆነ መድረክ ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተገኝተው ከፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት፣ ከውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት፣ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎችም የመንግሥት የጥናትና ምርምር ተቋማት ከተወከሉ ምሁራንና ባለሙያዎች ጋር ውይይትና ምክክር አድርገዋል። የብሪክስ ሲደመር የልሂቃንና ባለሙያዎች ምክር ቤት የተፅዕኖ አቅም መዳረሻ፣ በአባል አገሮች መካከል ስላለው የኃይል ሚዛን ሥርዓት፣ ጥምረቱን ለመቀላቀል ስለሚያስፈልጉ መሥፈርቶች፣ ኢትዮጵያ በብሪክስ ስላላት ሚና፣ ብሪክስን መቀላቀል ስለሚያስከትላቸው ጫናዎች፣ ብሪክስና የምዕራቡ ዓለም መስተጋብርና ሌሎችም በርካታ ሐሳቦችን አንስተዋል፡፡ ናርዶስ ዮሴፍ ከሩሲያ የብሪክስ የልሂቃንና ባለሙያዎች ምክር ቤት ዋና ኃላፊ ቪክቶሪያ ፓኖቫ (ዶ/ር) ጋር ያደረገችው ቆይታ እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

ሪፖርተር– የብሪክስ ሲደመር የልሂቃንና ባለሙያዎች ምክር ቤት የሚያቀርባቸው ምክረ ሐሳቦች በብሪክስ አባል አገሮች መሪዎች ውሳኔ ላይ ምን ያህል ተፅዕኖ አላቸው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- ብሪክስ ከተቋቋመት ጊዜ አንስቶ የባለሙያዎች አስተዋጽኦ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ሆኖ ነው የቆየው። የተወሰነ የታሪክ ክፍል ለማንሳት ያህል በብሪክስ የባለሙያዎች ማኅበረሰብ እጅግ ትልቁ የሚባለው ዋነኛ ኩነት የሆነው የባለሙያዎች አካዳሚክ ፎረም፣ ለመጀመሪያ ጊዜ እ.ኤ.አ በ2008 ታኅሳስ ወር ላይ ነበር የተካሄደው፡፡ ማለትም እ.ኤ.አ. በ2009 የአገሮቹ መሪዎች ጉባዔ ሳይካሄድ በፊት አስቀድሞ ነበር የተደረገው። ከዚያም ደግሞ በደቡብ አፍሪካ እ.ኤ.አ. በ2013 በተደረገ ጉባዔ ተጠናቆ ለመሪዎች ውሳኔ የቀረበ ሰነድ ላይ ሁለት የተለያዩ ጉዳዮች፣ የአካዳሚክ ፎረም፣ እንዲሁም የኢኮኖሚና ፖለቲካ ልሂቃን ጉባዔ (BRICS Think Tank Council/BTTC) ላይ ውሳኔዎችን አሳልፎ ነበር። ስለዚህ የባለሙያዎች ማኅበረሰብና የንግድ ዘርፍ ማኅበረሰብ የየራሳቸው መንገድ ይዘው በአገሮቹ መሪዎች ተቀባይነት አግኝተው ቀጥተኛ ባልሆነው መንገድ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ እያሳደሩ ነው።

ሪፖርተር፡– እነዚህ ተፅዕኖዎችን መፍጠር የተቻለባቸውን ኩነቶች ምሳሌዎች መጥቀስ ይችላሉ?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡እንደ ማሳያ ልንቀንስ ከምንችላቸው ነገሮች መካከል ዋነኛው የብሪክስ ‹‹ኒው ዴቨሎፕመንት ባንክ›› የመመሥረት ሐሳብ የመጣው ከልሂቃን ባለሙያው ማኅበረሰብ ነው። ባንኩን የመመሥረት ዝግጅቶችም ሆኑ ውይይቶች በባለሙያዎቹ ከተካሄዱ በኋላ ነው፣ በመሪዎች ፀድቆ ባንኩ የተመሠረተው። የባንኩ ምሥረታ ሐሳብ በእኛ ምክር ቤት ለውይይት ከቀረበ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ነው ዕውን የተደረገው። ሌላኛው ደግሞ የብሪክስ ኔትወርክ ዩኒቨርሲቲ ነው። በእኛ በኩል እንዲሆን አጥብቀን የምንወደው ነገር የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲቀላቀሉትና ፕሮግራሞቻችንን በጥልቀት ለማስፋት አብረውን እንዲሠሩ ነው። ስለዚህ የብሪክስ ኔትዎርክ ዩኒቨርሲቲ አንደኛው የባለሙያዎች ምክር ቤት የሰብዓዊ ትብብሮችን ለማጠናቀር፣ በትምህርት አጀንዳዎች ላይ የጥራት ደረጃዎችንና አሠራሮችን በአባል አገሮች መካከል እርስ በርስ እንዲጋሩ በማድረግ በሰው ሀብት ልማት ላይ ከፍተኛ ጥራትና ተፈላጊውን ውጤት ለማስገኘት ወሳኝ ነው ብለን ያቀረብነው ሐሳብ ነበር። ይህም ያስገኘልን የባንኩን ሐሳብ ባቀረብንበት ተመሳሳይ ዓመት ለመሪዎች አቅርበን ተስማምተውበት ተግባራዊ የተደረገ ነው።

ሪፖርተር፡- በብሪክስ ሲደመር አባል አገሮች መካከል ያለው የኃይል ሚዛን ሥርዓት ምን ዓይነት ነው? በአሁን ወቅት በሥራ ላይ ያሉት ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የመሳሰሉት የሚጠቀሙበት አሠራርን በመከተል ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ለተወሰኑ በጣት ለሚቆጠሩ በኢኮኖሚ ኃያል ለሆኑ አገሮች ይሰጣል? ወይስ ሁሉም አባላት ተመሳሳይ መብት ነው የሚኖራቸው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- አንድ ዋነኛ መረዳት ያለብን ነገር ብሪክስ በመግባባት ላይ የተመሠረተ የመሪዎች ጥምረት ነው፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ጥምረቶች ላይ ደግሞ ስለኃይል ሚዛን ማውራት አንችልም። ድምፅን በድምፅ ስለመሻር ጉዳይም አንነጋገርም። የአገሮቹ ጥምረት እንቅስቃሴና ውሳኔ የሚያውጠነጥነው ማዕቀቦችን ስለመጣልና ጫና ስለማሳደር አይደለም፡፡ ይልቁንም የጋራ መግባባት ላይ ስለመድረስና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አንዱ አባል ከሌላው አባል ጋር ስምምነት ላይ መድረስ የሚችልባቸው ሁኔታዎችን ለመፍጠር ነው ዓላማው። ስለዚህም በሐሳብ ደረጃም እንኳን ቢሆን ድምፅን በድምፅ ስለመሻር ልናወራ አንችልም፡፡ ምክንያቱም በቅድሚያ ተቋማዊ መዋቅሩ ራሱ በዚህ ዓይነት መንገድ አልተቃኘም። ሲቀጥልም ተቋማዊው አሠራር የበለጠ ቢሮክራሲ ስለሚያበዛ እንደ ክለብ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፣ በአሁኑ ወቅትም ሆነ ምናልባትም ለቀጣይ መጪ ጊዜያትም ብንጓዝበት የተሻለ አማራጭ ነው ተብሎ የተወሰደው ይኼ ነው። የአቋማችን ዋነኛ መርህ አካታችነት ነው።

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ጊዜ 40 ያህል አገሮች የብሪክስ ሲደመር አባል ለመሆን እንዳመለከቱ እርስዎ ቀደም ሲል ተናግረዋል። አገሮችን አባል ለመሆን ብቁ የሚያስብሏቸው መሥፈርቶች ምንድናቸው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር) በአሁኑ ወቅት የአጋር አባልነት መሥፈርቶች ምን ምን ማካተት አለባቸው በሚለው ጉዳይ ላይ በሒደት ላይ ያሉ ውይይቶች አሉ። ባለፈው ዓመት ጥቅም ላይ ከዋሉ ዋነኛ መሥፈርቶች መካከል አንዱ አገሮቹ አምባገነናዊ ከሆነ አካሄድ ውጪ ገንቢ የሆነ ውይይት የማድረግ ፈቃደኝነታቸውና የፍላጎት ደረጃቸው ነበር። ምክንያቱም ብሪክስ አምባገነናዊነት ወይም አንድ ገዥ አለቃ ያላቸው ጥምረቶች ዓይነት መንገድ አይደለም የሚከተለው። ይህ እዚህ ተቀባይነት የለውም፡፡ ይህ ዓይነቱ መንገድ ከጥምረቱ መሠረታዊ ዓላማ በተቃራኒ ነው። ሁለተኛው ደግሞ አባል የሚሆነው አገር ለአባል አገሮቹ ዜጎች መልካም ነገሮችን ማድረግ ከመቻል አንፃር አስተዋፅኦ የሚያበረክት መሆን አለበት። ከዚህ ባለፈ ዝርዝር ማሟላት ያለባቸውን መሥፈርቶች በተመለከተ በግንቦት ወር በሞስኮ በሚካሄደው የአገሮቹ ጉባዔ ላይ እንሰማለን። ይህም በአባል አገሮች የጋራ ስምምነት የሚወሰንና በይፋ የሚገለጽ ነው፡፡ የባለሙያዎች ምክር ቤትም በዚህ ረገድ ለማገዝ ዝግጁ ሆኖ ነው የሚጠባበቀው።

ሪፖርተር፡- ሚያዝያ 16 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የሩሲያ የብሪክስ ባለሙያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ያካሄዱት የአካዴሚክ ፎረም ጉባዔ ዋና አጀንዳ ምን ነበር?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- እኛ ባለሙያዎች ምክር ቤት ከተሰጡን ኃላፊነቶች አንዱ የብሪክስን አጀንዳ ማስተዋወቅና ማስረዳት ነው። ለዚህም ነው በቻልነው መጠን አባል አገሮችን በአጀንዳ ውይይቶች ላይ ማሳተፍና ማንቀሳቀስ ወሳኝ ነው። ለምሳሌ አካዴሚክ ፎረምና ሲቪል ፎረም ብዙ ሰዎች ቢኖሩትም ለተሳትፎ የሚጠሩት ግን ውስን ናቸው፡፡ ያ ደግሞ በዋናው ጉባዔ የሚጠሩት የተወሰኑት የተመረጡት ባለሙያዎች አገራቸውን ወክለው እንደ አምባሳደር ቢያገለግሉም፣ በእያንዳንዱ አገር በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በስፋት ተቀባይነት ያለውን ዕሳቤ መረዳት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። ለዚህም ነው አጠቃላይ የልሂቃን ማኅበረሰቡን በብሪክስና በኢትዮጵያ ምን እየተካሄደ እንዳለ ማሳወቅና ወደ ውይይት ጠረጴዛው ማምጣት ወሳኝ ነው ያልነው፡፡ በአጠቃላይ ጉባዔው በብሪክስ ውስጥ የኢትዮጵያ ልሂቃን ባለሙያዎች የኢትዮጵያ አጀንዳ እንዴትና ወዴት እንዲሄድ እንደሚፈልጉ መረዳት፣ በቀጣይ ለመሪዎች የሚቀርቡ ውሳኔዎችና ምክረ ሐሳቦች ምን መምሰል እንዳለባቸው ለማጥናትና ለማወቅ ነው ዓላማው። ዋናው ሐሳብ ኢትዮጵያ ከብሪክስ ሲደመር ምን እንደምትፈልግ በጥልቀትና በየዘርፉ ለመረዳት ነበር።

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ለብሪክስ የምትጨምረው እሴት ምንድነው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መሥሪያ ቤት መገኛ ናት፡፡ ስለዚህ ሰፊውን የአፍሪካ ማኅበረሰብ ማግኘት የሚያስችል መግቢያ መንገድ አድርገን ልናያት እንችላለን። አሁን ደቡብ አፍሪካ፣ ግብፅና ኢትዮጵያ አባል አገሮች ሆነዋል፡፡ ይህ ደግሞ የአፍሪካ አኅጉር እንደ አጠቃላይም ሆነ አገሮች በየግላቸው እንዲጠበቅላቸው የሚፈልጓቸው ጥቅሞች፣ በብሪክስ አጀንዳ ውስጥ በሙሉ አቅም መካተታቸውን ለማረጋገጥ ያስችላል። ከዚህ በተጨማሪም የብሪክስ መሠረታዊ ዓላማ አገሮች እርስ በርስ በኢኮኖሚውም ዘርፍ መደጋገፍ የሚችሉበትን ዕድል መፍጠር ነው። ይህም ለኢትዮጵያ አዲስ የግንኙነት ትስስሮችን መፍጠር ወይም መመሥረት እንድትችል፣ በተለይ ደግሞ በራሷ አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ የዕድገት ዕቅድ ውስጥ ማካተት እንድትችል መንገድ የሚከፍትላት ይሆናል።

ሪፖርተር፡- የተለያዩ ዓለም አቀፍ ዘገባዎች በተደጋጋሚ አገሮች ብሪክስን ሲቀላቀሉ የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደረግባቸው ያሳያሉ። በእርስዎ አስተያየት ኢትዮጵያ ጥምረቱን በመቀላቀሏ ሊያጋጥሙኝ ይችላሉ ብላ መጠበቅ ያለባት ጫናዎች ምንድናቸው? ኢትዮጵያ እነዚህን ጫናዎች መቋቋም እንድትችል ብሪክስ ማከናወን የሚችላቸው ነገሮችስ አሉ ወይ?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- የምዕራቡ ዓለም ሌሎችን በራሱ ሐሳብ መምራት ይወዳል፡፡ በእንዲህ ዓይነት ኅብረቶች ላይም ተፃራሪ አስተሳሰብ አለው። ኢትዮጵያም ከተለመደው ዓለም አቀፍ አካሄድ ውጪ የሆነ ነገር ያስፈልጋታል፡፡ በእርግጥም ምዕራባውያን ብሪክስን አይፈልጉትም፣ ምክንያቱም አማራጮችን ያቀርባል። ይህም ማለት የብሪክስ መርህ የምዕራቡን የኃይል ሚዛን ለመገዳደርና ተመጣጣኝን ሌላ የኃይል ሚዛን መፍጠር ሳይሆን ለአገሮች አማራጭ መስጠት ነው። በአሳዛኝ ሁኔታ በኢትዮጵያ ላይ ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎችን በተመለከተ፣ በአንድ ሆነ በሌላ ጉዳዩ በተፅዕኖ መልክ ሊመጣ ይችላል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን። ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁን በጣም ጥሩ የሚባሉ አጋሮች አሏት፡፡ አሁን የበለጠ ጠንካራ ናት። በጥምረታችን ውስጥ አንድ ላይ መጓዝ እስከቀጠልን ድረስ፣ በአዎንታዊ መንገድ ተያይዘን መሄዳችን እስካላቋረጥን ድረስ እኛ ከእነሱ ጋር ጦርነት ላይ አይደለንም። አዎ የብሪክስ ሲደመር አገሮች አብረን ነን፡፡ ነገር ግን አብረን የሆንበት መንገድ አለ፡፡ ብሪክስ ኢትዮጵያ የበለጠ ጠንካራ ሆና የትኛውንም ዓይነት ጫና መቋቋም ያስችላታል።

ሪፖርተር፡- ብሪክስ አሁን ካሉት የመንግሥታት ኅብረትና ጉባዔዎች በምን ይለያል? 

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡ብሪክስ በአገሮች መካከል ፍትሐዊ የሆነ አስተዳደር እንዲኖር ቁልፍ ሚና ይጫወታል። ይህም ማለት ሁሉም አባል አገሮች በእኩልነት በውይይት የሚወስኑበት ስለሆነ ነው። ብዙዎች እንደሚያስቡት ብሪክስ የምዕራቡ ዓለም የፖለቲካ ሥርዓት ተቃዋሚ አይደለም። እርግጥ ነው ምዕራባዊ ያልሆነ ነው፡፡ ነገር ግን በመገዳደር ሳይሆን በትብብር ለመሥራት የተሰባሰቡ አገሮች ጥምረት ነው። በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የመንግሥታት አስተዳደር ሥርዓት አጀንዳ ውስጥ ያለ አገርን የኃይል ሚዛን ነክተንና ገፍተን ለማስነሳት የሚያስችል አብዮት የመፍጠር ምንም ዓይነት ፍላጎት የለንም። ነገር ግን ምዕራባውያን ስለእኛ ያላቸው ግንዛቤ ይህን ዕውቅና የሰጠ አይደለም። ጥምረታችን እያቀረባቸው ያላቸው ምክረ ሐሳቦች አሁን ያሉት የመንግሥታት ኅብረትና ጉባዔዎች መመለስ ያልቻሏቸውን ጥያቄዎች፣ መሙላት ያልቻሏቸውን ክፍተቶች ለማሟላት ነው። በምዕራቡ ዓለም እንደተለመደው አካሄድ የአንዳንድ አገር ፍላጎትና ዕቅድ በሥርዓቱ አቀንቃኞች ይሁንታና ተቀባይነት እስካላገኘ ድረስ የሚያግድና የሚከለክል ሕግ የለንም። መርሐችን የመተባበር እንጂ የመቧደንና ለአንዱ አገር አድልቶ ሌላውን የመግፋት አይደለም። ለሁሉም እኩል መፍትሔ መስጠት የሚያስችል መድረክ መፍጠር ነው ዋናው ዓላማ።

ሪፖርተር፡– ብሪክስ ወቀሳ የሚያቀርቡበት የምዕራብ አገሮችን መሠረታዊ መርሑን ካለማወቅ ነው የሚል ማብራሪያዎች ሲሰጥ ይደመጣል። ታዲያ የሚሠራቸውን ሥራዎች ውጤታማነትና በእርግጥ እርስዎ እንደሚሉት የሚያከናውናቸውን  ተግባራት ፍትሐዊ አካሄዶችን ከመከተል አንፃር መሆኑን ማነው አጥንቶ፣ ግምገማ አካሂዶ ማሳወቅ የሚችለው? አባል አገሮች ይህን በተመለከተ የደረሱበት ውሳኔ አለ?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- ከአራት ዓመታት በፊት የብሪክስ ጠቋሚ ሥርዓትን አስተዋውቀን ተግባራዊ ተደርጓል። በዚህ አሠራር መሠረት ራሳችንን መገምገም እንችላለን። የእኛ የልሂቃን ባለሙያዎች ምክር ቤት፣ እንዲሁም የአባል አገሮቻችን ልዑካን በአጠቃላይ ተሳታፊ ሊሆኑበት ይችላል። በሩሲያ ለምሳሌ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ የአገሪቱ ታላላቅ ሳይንቲስቶች ከመደበኛ ሥራዎቻቸው በተጨማሪ የምክር ቤቱ አባላት ናቸው፡፡ ስለዚህ በየሚሠሩባቸው ዘርፎች ትክክለኛ ግምገማ አካሂደው እውነተኛ ግኝቶቻቸውን የማቅረብ ኃላፊነቶች ተጥለውባቸው እየሠሩ ነው። እነዚህን የጠቀስኳቸውን አካሄዶችና ዋነኛ አሠራሩን በመከተል አጠቃላይ ግምገማ ማድረግ የሚያስችል መለኪያ መፍጠር ተችሏል። አሁን በዚህ ረገድ አስፈላጊውን መረጃ ለኢትዮጵያ ለማቅረብ የሚያስችለንን ትብብርና ድጋፍ እናገኛለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህን የግምገማ ሥርዓት መከተል አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ዋነኛ ውጤቱ የሚታየው፣ እኛ የብሪክስ አባል አገሮች አብዛኛውን ጊዜ በሌሎች ስንገመገም የቆየን መሆኑን ስንመለከት ነው።

ከእኛ ውጪ የሆነ ሌላ አካል ነው ለምዘና ብቁ የሚባሉት መለከያ መሥፈርቶች ምን እንደሆኑ የሚለየው፣ መሥፈርቶቹን የሚያስቀምጠው፣ የሚሰጡትን ደረጃዎች ሲወስንልን የቆየው። በእንዲህ ዓይነት አካሄድ አልፈን ተገምግመን ብዙውን ጊዜ ያን ያህል ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ሲያስቀምጡንም አይታይም። ይህን በተመለከተ በካናዳ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ በአሁን ወቅት ብሪክስ ላይ ምዘና እያካሄደ ነው። ስለራሳችን ማሰብና ራሳችንን መገምገም አስፈላጊ ሆኖ ሳለ፣ በሒደቱ እኛ ምን መሆን እንዳለብን ታሳቢ አድርገን ውጤቱንም ለዓለም እናቀርባለን። በምዘናችን ሚዛናዊ መሆን አለብን፣ እርስ በርሳችንም እውነተኛ መሆን አለብን። ነገር ግን ከውጭ ያለው አካል እኛን በመጥፎ ሁኔታ ለመሳል እንደሚሞክረው አይደለም። መረጃውን ራሳችን አስቀድመን ይፋ እናደርጋለን፡፡ በደንብ ጠንቅቀን የምናቀውን፣ የምንደግፈውንና ልንወያይበት የምንችለውን መረጃ እናሳውቃለን።

ሪፖርተር፡- የብሪክስ ሲደመር ጥምረት ኢኮኖሚን፣ ፖለቲካን፣ ደኅንነትን፣ ፖለቲካን ማዕከል ያደረገ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል። ጥምረቱ በኢኮኖሚ ኃያል የሚባሉትንም ገና ታዳጊ የሆኑ አገሮችንም በአባልነት ያካተተ እንደ መሆኑ፣ ለአገሮች አጋርነት በሥራ  ላይ እየዋለ ያለው የኢኮኖሚ ስትራቴጂ ምንድነው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ከተደረጉት አሠራሮች መካከል አንዱ የብሪክስ አገሮች ኢኮኖሚያዊ ጥምረት ስትራቴጂ ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ቀጣዩን ዓመት ታሳቢ አድርገን ነው የምንንቀሳቀሰው። ይህ ስትራቴጂ በየዓመቱ የተለያዩ አጀንዳዎችን ይዞ ነው ተግባራዊ የሚደረገው። በቀጣዩ ዓመት ተግባራዊ የሚደረገው ስትራቴጂ አዳዲስ ጥምረቱን የተቀላቀሉ አገሮችን ታሳቢ ተደርጎ በድጋሚ የሚከለስ፣ አዲስ ቅርፅ ወጥቶለት አዳዲስ ዕቅዶችን እንዲያካትት ተደርጎ የሚቀረፅ ነው የሚሆነው። ለዚህም ነው የልሂቃን ባለሙያዎች ምክር ቤቱ አባላት አሁን ቆም ብለው በዚህ አጀንዳ ላይ በጥልቀት መወያየትና ለቀጣዩ አምስት ዓመታት በአባል አገሮቹ መካከል የሚደረጉ ኢኮኖሚያዊ ትስስሮች ምን መምሰል እንዳለባቸው፣ እንዲሁም ብሪክስንም የተሻለ ከማድረግ አንፃር መካተት ያለባቸውን ነገሮች እንዲያሟላ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት።

ሪፖርተር፡- በመጪው ግንቦት ወር መጨረሻ ላይ ለመካሄድ ዕቅድ የተያዘለት የብሪክስ አካዴሚክ ፎረም ላይ ከሚነሱ አጀንዳዎች ዋነኛው የፋይናንስና የገንዘብ ሥርዓት ሪፎርም ጉዳይ እንደሆነ ይሰማል። በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት ውጤቶች ነው የሚጠበቁት?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡የአባል አገሮች የፋይናንስና የገንዘብ ሥርዓት ሪፎርም ጉዳይ በፎረሙ ከሚቀርቡት ዋነኛና በጣም ወሳኝ ጉዳዩች አንዱ ነው የሚሆነው። በዚህ ጉዳይ ላይ እንደ ብሪክስ ልሂቃን ባለሙያዎች ማኅበር መሪዎች በትክክለኛ መንገድ ላይ እንዲጓዙ ማገዝ ኃላፊነታችን ነው። እ.ኤ.አ. በ2023 በነበረው ጉባዔ በመሪዎች ከተላለፉ ውሳኔዎች አንዱ አገሮች የየግል የመገበያያ ገንዘቦችቻቸውን በመጠቀም፣ በብሪክስ ሲደመር አባል አገሮች መካከልም ሆነ ከሌሎች አገሮች ጋር በሚያደረጓቸው የንግድ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ያለ ምንም መሰናክልና ደኅንነቱ ተረጋግጦ ማካሄድ የሚችሉበት አሠራር መፍጠር የሚያስችሉ መንገዶችና ዝርዝር የአሠራር ዘዴ እንዲቀርብላቸው ነበር። የአባል አገሮች የልሂቃን ባለሙያዎች ምክር ቤት ያላቸውን አቅም አጣምረው ይህን መሬት ላይ እንዲወርድ ማድረግ የሚያስችል ሁኔታ መፍጠር መቻላቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ዋነኛ የሚጠበቅብንም ከልሂቁ ማኅበረሰብ የሚቀርቡ ጥናቶች ላይ ውይይት ማድረግና ለመሪዎቹ የሚቀርብ ዝርዝር የአፈጻጸም ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው።

ሪፖርተር፡- ብሪክስ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦች አማራጭ ዕቅድ አቅርቧል የሚሉ ሪፖርቶች አሉ። እውነት ነው? የቀረበው አማራጭ ምን ዓይነት ይዘት ነው ያለው?

ቪክቶሪያ (ዶ/ር)፡- ተገቢነት ያላቸው የልማት ግቦች የሚል ስያሜ ያለው ነው። የእነዚህ ግቦች ተቀዳሚ ነገር ቀጣይነት ያላቸው የልማት ግቦችን ለማሳካት የእኛ ማኅበረሰቦች በትክክል የሚያስፈልጓቸውን ጉዳዮች የሚያስቀድም ተግባራዊ መሆን የሚችል አማራጭ ሐሳብ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና አግኝቷል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ስምምነት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ የሚመስል ሁኔታ ላይ ነን። ቀደም ሲል የቀረቡ ዕቅዶችን ማሳካት እንዳንችል ሌሎች ጂኦ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል። ለምሳሌ ድህነትን ለማጥፋት፣ የምግብ ዋስትናን ለሁሉም ዜጎች ማረጋገጥ መቻል፣ እንዲሁም አጠቃላይ ትምህርት ለዜጎች ሁሉ የማዳረስን የመሳሰሉ ዕቅዶች በ2030 ሙሉ ለሙሉ ማሳካት አይደለም፣ ለማሳካት የምንቃረብበት ደረጃ ላይ እንኳን አይደለም። እንዲያውም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ሁኔታዎች እየተባባሱ የተጀመሩ ሥራዎች ወደኋላ እየተመለሱ እያየን ነው ያለነው። ስለዚህ እኛ እነዚህን ዕቅዶች ለማሳካት የምንሄድበት መንገድ ምን መምሰል አለበት ለሚለው አማራጭ የራሳችንን ራዕይ ነው ያቀረብነው። በእኛ የአማራጭ ሐሳብ ውስጥ ሁሉም ግቦች እኩል የትኩረት ደረጃ የሚሰጣቸው ሲሆን፣ ስለጉዳዩም በምንወያይበት ወቅትም የተመረጡ ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ የሁላችንም ፍላጎት ታሳቢ ተደርጎ የሚስተናገድበት አካሄድ ነው ያመጣነው።  

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...

‹‹ሐሳብ ማቅረብ ባልተገባ መንገድ የሚያስበይን ከሆነ እንደ አገር በአጠቃላይ የሳትነው ነገር አለ ብዬ እገምታለሁ›› ደስታ ጥላሁን፣ የኢሕአፓና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና...

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ‹‹እርስዎ ንጉሥ ነዎት ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትር?›› የሚል ጥያቄ እንዳቀረበች በሰፊው ሲወራ ሰንብቷል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያደረጉት የቅርቡ...